የትምህርት ጥራት ጉዳይ ጥያቄ ከሆነ ሰነባብቷል:: ብዙዎችን እያነጋገረና መፍትሄንም እየፈለገ ዓመታትን ተሻግሯል:: ከመፍትሄዎቹ መካከል ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም ፈተናን ያካሄደበት ሥርዓት አንዱ ተደርጎ ተወስዷል:: ምክንያቱም ተማሪዎች ከትምህርት ቤታቸው ወጥተው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲፈተኑ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል:: ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮችን መቀየር መቻሉን የሚያሳዩ ውጤቶች እየወጡ ነው:: በዋናነት ከተማሪዎች ኩረጃ ጋር በተያያዘ የሚመጣውን የውጤት ግሽበት በእጅጉ ያሻሻለ ነው:: በዚያ ላይ ተማሪዎች በራሳቸው ሰርተው ምን ያህል ውጤት ማምጣት እንደሚችሉም ያመላከተ ነው::
የ2014 ዓ.ም ተፈታኞች ብዙ ነገሮች የተደራረቡባቸው እንደሆነ ይታወቃል:: ለአብነትም በጦርነቱ አካባቢ የነበሩ ተማሪዎች መማር ባለመቻላቸውና በሥነልቦና ታክመው ወደ ፈተና መግባት አለመቻላቸው በ2013 ዓ.ም የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም:: ስለዚህም በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ተሰጥቷቸው ዳግመኛ የሚፈተኑበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ነበር:: ስለዚህም የ2014 እና የ2013 ተፈታኞች በጋራ የሚፈተኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: በተመሳሳይ ኮቪድም ችግር እንደነበር ይታወሳል:: ያም ሆኖ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እንዲፈተኑ ተደርገዋል::
ይህ ደግሞ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ስብራት ለማከም በብዙ መልኩ ያስቻለ እንደሆነም ተነግሯል:: ማለትም ተፈታኞች ምንም እንኳን በችግሮች ውስጥ ቢያልፉም ጊዜ ወስደው እንዲዘጋጁ የተደረገበት መንገድ የሚያስመሰግን ነው:: ከሁሉም በላይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሲባል የተወሰደው እርምጃ አወንታዊ ምላሽ እንደሰጠም በአንዳንዶች ዘንድ ይነገራል:: በተለይም የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ስርቆትንና ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ በጎ ጅምሮች ታይተውበታል::
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈተናውን መውሰዳቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አጠቃላይ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁ በማድረግ ጉጉት እንዲያድርባቸውና ፈተናውን በራሳቸው አቅም እንዲሰሩት ያነሳሳ ነበር:: በተጨማሪም እውቀቱ ሳይኖረው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባን ተማሪ ቁጥርን ይቀንሳል::
ይህ የአፈታተን ሥርዓት ሌሎች እድሎችንም እንደሰጠም ይገለጻል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአግባቡ ከተመሩ፣ ከቆረጡና ጥረት ካደረጉ የትኛውንም ተልዕኮ መወጣት እንደሚችሉ ያሳየ ነበር:: ከዚህ ቀደም የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ ወድቆ መቆየቱን እና ለፖለቲካ ጥቅም ሲውል መስተዋሉን በአንድ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አንስተዋል:: ይህ ማለት ደግሞ አሁን የተወሰደው እርምጃ ወይም ፈተና እንዲሰጥበት የተደረገው አካሂድ የክልሎችን ብሎም የተማሪዎችን እንዲሁም የመምህራንን አቅም ያሳየ ነው::
በእኔ ክልል ይህንን ያህል አሳልፌያለሁ በሚል መኩራራትን የሚፈጥርም አይሆንም:: ምክንያቱም ውጤቱ ትንተና ሲደረግበት ከተወሰኑ ለያውም ከተማ አካባቢ ካሉት ውጪ ያሉ ክልሎች በመጠነኛ መልኩ ነው ልዩነት ያላቸው:: ውጤቱም የሚያኩራራ ሳይሆን ይልቁንም አንገት የሚያስደፋ ነው:: ስለዚህም እንደ ሀገር ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ያመላክታል::
የ2014 ዓ.ም ፈተና ከአለፈው በተሻለ ሁኔታ ተፈታኞችን ማስተናገድ የተቻለበትም እንደሆነ ተነስቷል:: ለዚህም ማሳያው በፈተና ጣቢያው ውስጥ የወለዱ ተፈታኞች መኖራቸው ነው:: እነዚህን ተፈታኞች ተፈታኝ በመሆናቸው ብቻ ቀጥሉ አልተባሉም:: በሰላም አርፈው በአንድ ወር ውስጥ በሚሰጥ ፈተና እንዲስተናገዱ እድሉ ተመቻችቶላቸዋል::
አዲሱና የመጀመሪያው የሪፎርም ሥራ ማለትም የፈተና አሰጣጡ ሁኔታ ውጤት ሲተነተን ማህበረሰቡን ከሁለት የከፈለ ሲሆን፤ አንዳንዶች ሲደነግጡና ልጆቻችንን የት ልናስገባቸው ነው ሲሉ ገሚሶቹ ደግሞ ጥሩ ተሰራ እንደውም ለትምህርት ጥራቱ ሁነኛ መፍትሄ ነው ሲሉ ይደመጣሉ:: በአጠቃለይ ግን የታየው ውጤት እንደሀገር የትምህርት ሥርዓቱ ያለበትን ፈተና ያመላከተ ነው::
ሚኒስትሩ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ የፈተና ውጤቱ በየደረጃው ሁሉም የተፈተነበት ነው:: በተለይም መምህራንና ትምህርት ቤቶች በደንብ የማስተማራቸው አቅም የተፈተሸበት ነው:: ምክንያቱም በአስተማሩትና በአሳወቁት ልክ ተማሪዎቻቸው ውጤት አስመዝግበዋል:: ለምሳሌ፡- በአጠቃላይ መደበኛ ተፈታኞች ትምህርት ቤቶች 2959 ሲሆኑ፤ ጥሩ ያስተማሩ ሰባት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል:: ከ50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት የተመዘገበባቸው ትምህርት ቤቶች ደግሞ 1798 (60.76 በመቶ) ማምጣት ችለዋል:: የማስተማርና እውቀት የማስጨበጥ ችግር ያለባቸው 1161 (39.24 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም::
ይህ የፈተና ውጤት አስተማሪ ነው:: ምክንያቱም ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም መምህራንና መንግሥት ያለባቸውን ክፍተቶች ለይተው ለቀጣይ እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸው ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ሀገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 3 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ናቸው:: ማለትም ከተመዘገቡ 985 ሺህ 354 ተማሪዎች ውስጥ 908 ሺህ 256 ፈተና ላይ የተቀመጡ ሲሆኑ፤ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች በመቀጣታቸው የተነሳ 896ሺህ 520 ተማሪዎች ፈተናውን እንዲወስዱ ሆነዋል:: በቁጥር መሰረት ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 29 ሺህ 909 ብቻ ናቸው ማለፍ የቻሉት::
የፈተና ውጤቱ ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የትምህርት ሥርዓት ትውልድ ገዳይ እንደነበረ ያሳየ ነው:: ተማሪዎች፤ መምህራን ፤ ትምህርት ቤቶችና ትምህርት አመራሮች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ያሳየ ነው:: ተማሪዎች በ12 ዓመታት ቆይታቸው የያዙት እውቀት እንብዛም እንዳልሆነም ተረጋግጦበታል:: ስለሆነም የዚህ ዓመት የፈተና ውጤት በእውነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለቀጣዩ ጊዜ መለኪያ ይሆናልም ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመግለጫቸው::
ብዙ ተማሪዎች ከፍ ያለ ውጤት አለማምጣታቸው ቢያሳዝንም በራሳቸው ሰርተው ያመጡት ውጤት ግን ያረካል:: ያሉበትን ደረጃ ያሳያቸዋልና ሊከፉበትም አይገባም:: ወላጆችም ቢሆኑ ሥራው ትክክል እንደሆነ ማመን አለባቸው:: ምክንያቱም ይህ አሰራር የትምህርት ጥራቱን ከማሳለጥ አኳያ የማይተካ ሚና አለው:: ትውልዱን በሥነምግባርና በውጤታማነት ለማፍራትም ሁነኛ መፍትሄ ነው:: እናም አሁንም በዚህ አይነት ሁኔታ ሥራዎች ይከናወናሉና ይህንን ታሳቢ አድርጎ መስራት ያስፈልጋል:: እንደ ሀገር ተማሪ ይውደቅ የሚል እሳቤ የለም:: የጠራና ያወቀ ተማሪ ይፈጠር እንጂ:: ስለዚህም በራሳቸው አቅም የሚሰሩ ተማሪዎችን ከማፍራት አኳያ ትምህርት ሚኒስቴር እያደረገ ያለውን ሥራ ሁሉም ሊደግፈው ይገባል:: ከጎኑ በመቆምም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
የወደቁት ምን ይሁኑ የሚለውን ለመቀየር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ውጤታቸው ከ50 በመቶ በታች የሆኑ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ባይችሉም አቅም ያላቸው ተማሪዎች እንዳይቀሩ በሚል የማብቃያ ትምህርት እንዲወስዱ እንደሚደረግ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የማብቂያ ትምህርቱ በየዩኒቨርሲቲው የሚሰጥ ሲሆን፤ ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል:: ስለዚህም ተማሪዎቹ በውጤታቸው ደረጃ መሰረት ተለይተው እንዲገቡ ይሆናሉ:: ይህ ማለት ግን የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል::
አካሂዱ በዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም ልክ የሚከናወን ሲሆን፤ እስከ 100 ሺህ ለሚደርሱ ከ50 በመቶ በታች ላመጡ ተማሪዎች እድል የሚሰጥ ነው:: የማብቂያ ትምህርቱን ከወሰዱ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣው ፈተና መሰረት የሚፈተሽ ይሆናል:: ከአለፉ ደግሞ ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል:: ይህንን ፈተና ሳያልፉ የቀሩት ደግሞ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በሚወጣላቸው የመቀበያ ነጥብ መሰረት ሌሎች ትምህርት ቤቶችን የሚቀላቀሉበት እድል ይፈጠራል::
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ይህ የፈተና አሰጣጥ እንደሀገር በብዙ መልኩ የተተነተነበት ነው:: ለአብነት በትምህርት ዘርፍ፣ በትምህርት አይነት፣ በክልሎችና በጾታ ተለይቶ ታይቷል:: በዚህም መሰረት በዘርፍ ደረጃ በማህበራዊ ሳይንስ ከታረመው ከ600 ውስጥ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 524 ሲሆን፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ 666 ነው:: ይህንን ውጤት ተመርኩዘን ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ ከ500 በላይ ያመጡት ተማሪዎች 10 ብቻ እንደሆኑ ማየት ተችሏል:: በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ ከ600 በላይ ያመጡ ተማሪዎች 263 ናቸው::
በማህበራዊ ሳይንስ ከ500 በላይ ያመጡትና በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 በላይ ያመጡት ተማሪዎች ለተማሪዎች አርኣያ መሆን የሚችሉ ናቸውና እውቅና እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በክልሎች ደረጃ የታየውን ልዩነትም ያነሳሉ:: ከክልሎች በከተሞች አካባቢ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል:: በተለይም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ የመጣው ውጤት በሁሉም ዘንድ ልምድ ሊቀሰምበት የሚገባው ነው::
የውጤቱ ትንተና መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ከክልል አንጻር ትግራይ ምንም ያልተፈተነበት ቢሆንም በትግራይ ክልል ስም የተያዙና ያለፉ ተማሪዎች ተቀምጧል:: የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይልቃል ወንድሜነህ እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል ስር ሆነው በድንበር አካባቢ የሚገኙ ትምህርትቤቶች ሲሆኑ፤ በእኛ ሲስተም ኮድ ውስጥ የተያዙት አሁንም በትግራይ ክልል ስለሆነ ስላልተቀየረ ነው በዚያ ክልል ስም እንዲወጡ የተደረገው:: ምክንያቱም እንደ ትግራይ ክልል ምንም ተማሪ አልተፈተነም:: ስለሆነም ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ያሉ ትምህርትቤቶች የተፈተኑ ተማሪዎች መሆናቸውን ነው ብለዋል::
ወደ ትምህርት አይነቶች ትንተና ሲገባ ደግሞ በመግለጫ ትንተናው እንደተቀመጠው፤ ሀገራዊ አማካኝ ውጤት 29 ነጥብ 25 ሲሆን፤ ከፍተኛው በኬሚስትሪ የመጣው ውጤት ነው:: ዝቅተኛው ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በሂሳብ ትምህርት የተመዘገበው ነው:: በጾታ ሲገባ ደግሞ ወንዶች የተሻለ አቅም እንደነበራቸው በፈተናው ታይቷል:: ስለዚህም በአጠቃላይ ይህ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት የሚኒስቴር መስሪያቤቱን ቅቡልነት መልሶ ለመገንባት እድል የፈጠረ መሆኑን ሚኒስትሩ ያስረዳሉ:: በትምህርት ሴክተሩ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ያበረታታልም ይላሉ::
በዚህ መልኩ መጓዝ ከተቻለ የማህበረሰቡ የዘወትር ጥያቄ የሆነው የትምህርት ጥራት ጉዳይ በጥቂት ዓመታት ይረጋገጣል::
በዚህ ፈተና ያየነው የማህበረሰቡ ምልከታ ዛሬም ከትምህርት ሚኒስቴር ጎን መሆኑን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ትናንት በፈተና ሂደቱ ሁሉም እንደተረባረበ ሁሉ ዛሬም በውጤቱ ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል:: በራስ መሥራትን ማስለመድም ይገባል:: ይህ ደግሞ በቀጣይ እንደ ሀገር ትምህርት ሚኒስቴር የሚሰራውን የሪፎርም ሥራ ለማገዝ ያስችላል:: በተለይም ሕዝቡ በሚያማርርባቸው የተደራጀ ሌብነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በትምህርት ሴክተሩ ሃሰተኛ ትምህርት ማስረጃ ማምጣትና መሰል ተግባራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እድል ይሰጣል:: ስለሆነም ተረባርቦ መስራቱ ላይ ሁሉም ትኩረት ሊያደርግ ገባል:: ምክንያቱም ሚኒስቴሩ የሚሰራው ትውልድን የማፍራትና የማነጽ ጉዳይ ላይ ነው:: ይህ ደግሞ በአንድ ወቅት ሥራ የሚመጣ አይደለም:: በአንድ አካል ብቻ የሚከወንም እንዲሁ ሊሆን አይችልም:: ብዙ ልፋት ይጠይቃል:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም ተደጋግፎ መስራት አለበት::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም