እየተባባሰ ለመጠው የግብርና ምርቶች ዋጋ መናር እና የኑሮ ውድነት የተለያዩ አባባሽ ምክንያቶች እንደ መንስኤ ይጠቀሳሉ። ለዚህም የግብርና ምርቶች ከአምራች አርሶ አደሩ እስከ ሸማቹ ያለው የግብይት ሰንሰለት እጅግ የተንዛዛ እና የተበላሸ መሆን በዋናነት ይጠቀሳል።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ መግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች ማከማቻ እና መሸጫ ማዕከላትን ለመገንባት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ሶስት የግብርና ምርቶች ማከማቻ ማዕከላት በመገንባት ላይ ያሉት ለሚ ኩራ ወረዳ 02 (አያት ሳይት)፣ ለሚ ኩራ ወረዳ 05 (ሰሚት ሳይት) ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 7 (ቤተል ሳይት) አካባቢዎች ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ግንባታ አስተባባሪ ኢንጂነር ጉርሜሳ ረታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የለሚ ኩራ ወረዳ 2 እና የኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 07 የግብርና ምርቶች ማከማቻ እና መሸጫ ማዕከላት ግንባታ ከተጀመረ ሁለት ወራት የሆነው ሲሆን፤ የፕሮጀክት ግንባታቸውም 20 በመቶ ደርሷል። በለሚ ኩራ ወረዳ አምስት ውስጥ የሚገነባው ማዕከል ግንባታ ከተጀመረ ግን ገና ሶስት ሳምንት ነው። ለማዕከላቱ ግንባታም 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
እንደ ኢንጂነር ጉርሜሳ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶቹ አስቸጋሪና ከባዱ የመሬት ውስጥ ግንባታ ስራ በሁለት ወር ውስጥ በስኬት ተጠናቆ ወደ ቀጣይ የግንባታ ምራዕራፍ ተሸጋግሯል። ከመሬት በላይ የሚሰሩ ስራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው። በቀን 16 ሰዓታት በመሥራት ፕሮጀክቱን ፈጥኖ ለማጠናቀቅም ጥረት እየተደረገ ነው።
ማዕከላቱ የምርቶች ማከማቻ፣ የጅምላና የችርቻሮ መሸጫዎች እንዲሁም የአስተዳደር ህንጻ ያላቸው ሲሆን፣ ህንጻዎቹ ከመሬት በላይ እስከ ሁለት ወለል ይኖራቸዋል። የማዕከላቱ የአስተዳደር ህንጻዎች ከመጀመሪያ ወለል በላይ ሁለት ወለሎች፣ ከመጀመሪያ ወለል በታች ደግሞ አንድ ወለል ይኖራቸዋል። የጅምላ እና የችርቻሮ መሸጫ ህንጻዎች ደግሞ ከመጀመሪያ ወለል በታች በመሬት ውስጥ አንድ ወለልና ከመጀመሪያው ወለል በላይ ደግሞ አንድ ወለል እንዲኖረው ተደርጎ ነው በመገንባት ላይ ያለው። የማከማቻ ህንጻ ደግሞ አንድ ወለል ይኖረዋል።
ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ማሟላት ያለባቸውን ቴክኖሎጂዎች ይገጠማሉ። ቴክኖሎጂው በሙቀት የሚበላሹ ምርቶችን ለማቆየት፣ በቅዝቃዜ መቆየት የማይችሉትን ምርቶች ደግሞ ለማሞቅ የሚያስችል ነው። በተጨማሪም የደህንነት ካሜራ ይገጠማል። ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያና ቆሸሻ ማስወገጃም ይኖራቸዋል።
የማዕከላቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ አርሶ አደሮችና የህብረት ስራ ዩኒየኖች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ በገበያ ማዕከላቱ ውስጥ ለሚገቡ አከፋፋዮች በማቅረብ ይገለገላሉ። የከተማዋ ህብረተሰብም እና ቸርቻሪዎች በማዕከላቱ ውስጥ የሚቀርቡትን ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ የእንስሳት ተዋጽኦዎች ለመገበያየት ያስችላቸዋል። እንዲህ ያሉ የማዕከል ውስጥ አገልግሎቶች የንግድ ሰንሰለትን በማሳጣር ያግዛሉ። የንግድ ሰንሰለቱ ሲያጥር በመሃል ያሉ በርካታ ቸርቻሪዎች በየደረጃው ትርፍ ለማግኘት የሚጨምሩትን ዋጋ ለመቀነስ ይረዳል። ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ ከማስቻሉም ባሻገር ሁሉንም ምርቶች በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የማዕከላቱ ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል ኢንጂነር ጉርሜሳ።
የገበያ ማእከላቱ ግብርና ውጤቶችን በወቅቱ በማቅረብ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ የከተማውን ነዋሪ ከኑሮ ውድነት ጫና መታደግ ከማስቻሉም ባሻገር አምራቹም ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማዕከላቱ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱን ዲዛይን እና ግንባታ ተቋራጩ ራሱ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ጉርሜሳ፤ ዲዛይን እየተደረገ የግንባታ ሥራው ከስር ከስር እየተፋጠነ መሆኑን አመልክተዋል። የፕሮጀክቱን ዲዛይን እና የግንባታ ሥራ እያከናወነ ያለው አንድ መስሪያ ቤት እንደሆነም ገልጸዋል። የፕሮጀክቱን የግንባታ ጥራት ለመቆጣጠር እና ፕሮጀክቱ የዋጋ ጭማሪ እንዳያመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
ኢንጂር ጉርሜሣ እንደገለጹት፤ የማዕከላቱ ግንባታ ለ1 ሺህ 500 ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል። ፕሮጀክቱ በአገር በቀል ድርጅት እየተሰራ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ነው። በስሩ ንዑስ ተቋጮችን ቀጥሮ እያሰራም ይገኛል። ከስሩ ያሉት ሰራተኞች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እና እውቀቶችን እየቀሰሙ ናቸው። ፕሮጀክት ለሀገር በቀል ድርጅት የተሰጠበት አንዱ ምክንያት የአገር በቀል ድርጅት አቅም ለማሳደግ እንዲሁም በፕሮጀክቱ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ ነው። የገበያ ማዕከላቱ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ለ30 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠርም የሥራ አጥነትን ችግር በመቅረፍ ሚና ይኖረዋል። ለፕሮጀክቱ ትልቁ ተግዳሮት የሲሚንቶ እጥረት ነው ያሉት ኢንጂነር ጉርሜሳ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ውስጥ ይስተዋሉ ከነበሩ ክፍተቶች አንዱ ሴቶችን የማያሳትፍ መሆኑ ነው የሚሉት ኢንጂነር ጉርሜሳ የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ላይ ችግሩን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል። በማዕከላቱ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ካሉት መካከል እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት ሶቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የማከማቻ እና መሸጫ ማዕከላቱን ኦሊድ ግሩፕ የተሰኘ ሀገር በቀል የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን የግንባታ ተቋራጩ የኮልፌ ሳይት ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፤ ተቋራጩ ሳይቱን ከተረከበበት ቀን አንስቶ ወዲያው ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎችን እና የሰው ሃይል በማምጣት ወደ ስራ መግባቱን ገብቷል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው የሚሉት ሙሉጌታ ዲዛይኑን እና የግንባታ ስራው ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑንም አብራርተዋል። ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በሁለት ፈረቃ በቀን 16 ሰዓታት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመላከቱት። ከዚህ ቀደም 16 ሰዓት የመስራት ልምድ የሌላቸው ንዑስ ተቋራጮች ጭምር በቀን 16 ሰዓት የመስራት ባህል እያዳበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የስራ ባህልን በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል። በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚሰሩ ወጣቶች የስራ ልምድ እየቀሰሙ እንዲሄዱ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
እየተገነቡ ያሉ የገበያ ማዕከላት የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማው ነዋሪ እንዲቀርብ ከማስቻሉም ባሻገር ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ያለው በመሆኑ ከዚህ ቀደም የግብርና ምርቶች መሸጫ አካባቢዎች ይታይ የነበረውን የንጽህና ጉድለት ችግሮች እንዳይኖሩ የሚያደርግ ነው። በፒያሳ አካባቢ በነበረው የአትክልት ተራ እንዲሁም በቅርብ ዓመታት ወደ ስራ የገበው ጋርመንት አካባቢ የሚገኘው የገበያ ማዕከሉ ውስጥ የሚስተዋለው አይነት የንጽህና ችግሮች እንዳይኖር በጥንቃቄ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ ፕሮጀክት ማነጀሩ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱን በመገንባት ሂደት ውስጥ የሲሚንቶ እጥረት ትልቁ ችግር ሆኗል። በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ፕሮጀክቱ እንዳይጓተት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ግንባታውን እያፋጠነው ይገኛል። ከአማራጮቹ አንዱ ከኤጀንሲዎች ሲሚንቶ በመግዛት ግንባታውን እያከናወነ ነው።
የክፍለ ከተማና የወረዳ አስተዳደር መዋቅሮችም ግንባታው እንዲፋጠን የጥበቃ ሃላፊነት በመወጣት፣ ኤሌክትሪክና ውሃ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ ከተቋራጩ ጋር እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ ነው ያሉት ማናጀሩ፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል። ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማመቻቸት ረገድ እያሳዩ ያለውን መልካም ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የአማካሪ ድርጅት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ በበኩላቸው ለፕሮጀከቱ በተገባው ውለታ መሰረት ሰርቶ ለማጠናቀቅ በእቅድ የተቀመጠ መርሃ ግብር በመቅረፅና እና ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በሁለት ፈረቃ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ከግንባታ ጥራት ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ክፍተት እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በፕሮጀክቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ዮሴፍ ሲሳይ አንዱ ነው። ዮሴፍ የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የስራ እድል በማጣቱ ከተማረበት ሙያ ጋር በማይገናኝ ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ተናግሯል። የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን ተከትሎ የተፈጠረውን ስራ እድል በመጠቀም በተማረበት የምህንድስና ዘርፍ ለመስራት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። በኮልፌ ማዕከል ውስጥ በምህንድስና ዳታ ሰብሳቢ ጀማሪ መሃንዲስ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።
በግንባታ ሳይቱ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ዳታ እየሰበሰበ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤቶች ኢንጂነሮች ያቀርባል። የጽህፈት ቤቱ ኢንጂነሮች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በነዚህ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የሚወሰን ነው። በሜጋ ፕሮጀክት ውስጥ መስራት ለኔ ትልቅ እድል ነው የሚለው ዮሴፍ በተለይም በተማረበት የሙያ ዘርፍ ስራ እድል በማግኘቱ በጣም ደስተኛ መሆኑንም ተናግሯል። እስካሁን ድረስ በርካታ እውቀት መቅሰም መቻሉንም ጠቁሟል።
በዚህ ሜጋ ፕሮጀክት ውስጥ የስራ እድል የተፈጠረለት ሌላኛው ወጣት ደምሴ ዋቤ ነው። ወጣት ደምሴ በፊት የጉልበት ሰራተኛ ሆኖ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ውስጥ ይሰራ ነበር። አሁን ደግሞ በኮልፌ ሳይት የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከል ግንባታ ውስጥ ጠራቢ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። ደምሴ እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ውስጥ በቀን 150 ብር እየተከፈለው ይሰራ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ 200 ብር እየተከፈለው ነው። ይህም ለሱ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ተናግሯል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም