ግብርና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ መተዳደሪያም ይኸው ግብርና ነው። ነገር ግን የኢኮኖሚ አውራነቱን ያህል ሕዝቡ ጠግቦ እንዲያድር አላስቻለም። አገሪቱም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ምርት እያገኘች አይደለም። ለዚህም ገበሬው አሁንም ድረስ ከኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ አለመላቀቁ፣ በቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራር አለመደገፉ እንደዋና ምክንያት ይጠቀሳል።
ከዚህ በተጓዳኝ ለአፈር ተስማሚና ምርታማነትን የሚጨምሩ ማዳበሪያዎችን ጥቅም ላይ አለመዋል የዘርፉ ሌላኛው ማነቆ ሆኗል። በተለይ ከውጪ አገር የሚገቡ ማዳበሪያዎች የኬሚካል ይዘታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ በአፈር ለምነትና በምርት ላይ አሉታዊ ጉዳት ሲያደርሱ ይሰተዋላል። ገበሬውም ሌላ አማራጭ የለውምና እነዚሁ ማዳበሪያዎች በተደጋጋሚ ይጠቀማል።
ለአፈር ተስማሚና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ማዳበሪያዎችን ማግኘት የገበሬው አንዱ ችግር ሆኖ ሳለ ይህንኑ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ የምርምር ስራዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲሰሩም ቆይተዋል። ነገር ግን ችግሩን ከስር መሰረቱ የፈቱ የምርምር ስራዎች አሉ ለማለት አያስደፍርም። በተለይ ደግሞ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መላ ያበጁ በአፈር ማዳበሪያ ላይ የተሰሩ ስራዎች አሉ ማለት አይቻልም፤ ቢኖሩም በተግባር ችግር ሲፈቱ አልታዩም። ከዚሁ ችግር በመነሳት ግን ተስፋ ሰጪና በቀጣይ ተግባራዊ ቢሆን ችግሩን በዘለቄታው ሊፈታ የሚችል የአፈር ማዳበሪያ ላይ ያተኮረ የቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራ በወጣቶች እውን ሆኗል።
ወጣት ጊዮናዊት ገብሩ የግሪን ኢትዮጵያ መስራችና ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ናት። ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ2020 በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ስቴም ፓወር ከተሰኘና ወጣቶችን በተለያየ መልኩ በስራ ለማብቃት እየሰራ ከሚገኝ ድርጅት ጋር በጀማሪ የቢዝነስ አሰልጣኝነት እየሰራች ትገኛለች።
ወጣት ጊዮናዊት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እንደወጣች ከሌሎች የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቿ ጋር በመሆን ምን እንስራ ስትል አሰበች። እርሷና ጓደኞቿ ይህን ሀሳብ ሲያወጡና ሲያወርዱ አንድ ችግር ፈቺ ስራን እንደሚሰሩና ይህም ግብርና ላይ እንደሚያርፍ እርግጠኛ ነበሩ። ስድስት ሆነው በግብርናው ዘርፍ ምን አይነት ችግር እንዳለ በሚዳስሱብት ግዜ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም የሜካናይዜሽንና የቴክኖሎጂ እጥረቶች ዋነኛ ማነቆ መሆናቸውን አረጋገጡ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ለግብርና ስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እጥረት በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ችግሮች እንዳሉም አወቁ።
ጓደኛሞቹ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ሁሉንም ችግሮች ከተመለከቱ በኋላ የትኛው በእነርሱ አቅም፣ እውቀት፣ ጥሬ እቃና ሀብት ሊፈታ ይችላል የሚለውን አስበውና ችግሩን አይተው የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ለመስራት ወሰኑ። በመቀጠል በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ውስጥ ገብተው የቢዝነስ ሃሳባቸውን ማበልፀግ ቻሉ። ከዛም ጂ አይ ዜድ ያወጣው የግብርና ስር (ቢዝነስ) ሃሳብ ውድድር ላይ ገብተው ሃሳባቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችላቸውን እውቀት ቀሰሙ። በዛው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ፕሮጀክታቸውን ይፋ አደረጉ።
በመቀጠል ወጣት ጊዮናዊትና ጓደኞቿ ይህን ሂደት አልፈው የተፈጥሮ ማዳበሪያን ሊያመርቱ የሚችሉ የተለያዩ ማሽኖችን በማየትና በሀገር ውስጥ አሻሽለው ለመስራት ሁሉም በተማሩበት የኬሚስትሪና ቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት መስክ ያላቸውን እውቀት አዋጥተዋል። ወጣት ጊዮናዊትም ማሽኖቹን ዲዛይን ለማድረግ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ እውቀቷን ተጠቅማለች ።
ወጣት ጊዮናዊትና ጓደኞቿ ዲዛይን ያደረጉት ማሽን ‹‹ቬዝል›› የሚሰኝ ሲሆን ማሽኑ ከየቤቱ የሚወጡ ተፈጥሯዊ (ከኬሚካል የፀዱ) ቆሻሻዎች ተሰብስበው የመፍጨትና መርጦ የማውጣት ስራ ያከናውናል። በመጨረሻም በባክቴሪያና ሌሎች ንጥረ ነገሮች የበለፀገ ራሱ አፈር የመሰለ የአፈር ማዳበሪያ ምርት ይዞ ይወጣል። ይህ ምርት ነው እንግዲህ የአፈር ማዳበሪያ ሆኖ የሚያገለግለው።
በአሁኑ ወቅት ከስድስቱ ወጣቶች ጊዮናዊትና ሁለት ጓደኞቿ ብቻ ሆነው የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ከግብ ለማድረስ እየሰሩ ሲሆን የመጀመሪያውን የአፈር ማዳበሪያ ምርት በቴክኖሎጂ ለማውጣት ችለዋል። የአፈር ማዳበሪያው ከሌሎች መሰል አምራቾች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆንም በአፈር ጤንነት ላይ ያተኮሩና በስፋት ሊመረቱ የሚችሉ ተፈጥሯዊ የአፈር ማዳበሪያ ማምረት ችለዋል።
ጓደኛሞቹ የመጀመሪያውን የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ምርት እ.ኤ.አ በጥር ወር 2021 አምርተው ያወጡ ሲሆን በሳይንስ ባለሙያዎች በላብራቶሪ ተፈትሾ የተሻለ መሆኑ ተረጋግጧል። እነርሱ ምርቱን በሚያመርቱበት ቦታ ላይ ተሞክሮም ውጤታማነቱ በሳይንስ ባለሙያዎችና በዚህ ላይ በሚሰሩ የግል ኩባንያዎች ይሁንታን አግኝቷል። ይሁንና አንድ ማዳበሪያ ለሁሉም የአፈር አይነት እንደማይሆን በመረዳት እንደአፈሩና እፀዋቱ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያ ምርቶችን እያሻሻሉ በማምረት ላይ ይገኛሉ።
ይሁንና ማዳበሪያውን በስፋት አምርቶ አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ቦታ፣ ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ወጣት ጊዮናዊትና ጓደኞቿ እርዳታ የማሰባሰብ ስራ ጀምረዋል። ለተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ የግል ተቋማት ስለስራቸው በማሳወቅ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እየጠየቁ ሲሆን በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች ተቋማት ጋርም የጋራ ግንኙነት የመፍጠርና ምርቱ በስፋት ተመርቶ ወደአርሶ አደሩ የሚደርስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሰሩም ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም ምርቱ የመጨረሻ ማረጋገጫ ወደ ኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት መላኩን ይናገራሉ።
እነ ጊዮናዊት ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምርት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ካገኙ በኋላ ምርቱን በስፋት አምርቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሃሳብ አላቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአፈር ጤንነትና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አንገብጋቢ እየሆነ በመምጣቱ ድርጅታቸውን ወደ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በመቀየር ምርታቸውን በሜካናይዝ ግብርና ውስጥ ላሉ ባለሀብቶች የመሸጥና ለአርሶ አደሩ ደግሞ በነፃ የማቅረብ ውጥንም ይዘዋል።
ስራው ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚጠይቅ የትኛው ሊያዋጣ እንደሚችልም በጥልቅ እያሰቡበት ነው። አርሶ አደሩ በአፈር ማዳበሪያ ግብአት እርዳታ ማግኘት ስላለበት የተሻለ አካሄድን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ድጋፍ አግኝተው በስፋት የአፈር ማዳበሪያውን በማምረት አርሶ አደሩን እንዲሞክረው ማድረግ የቀጣይ ስራቸው ይሆናል።
ድጋፉን ለማሰባሰብም በግብርናው ዘርፍ ያሉ የተለያዩ ባለሀብቶች ጋር በመሄድ ምርቱን የማስተዋወቅና ለዚህም ድጋፍ እንዲያደርጉ የመጠየቅ ስራዎችን እያከናወኑ ሲሆን በአገር ውስጥና በውጪ ባሉ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አሸንፎ ገቢ የማግኘት ስራዎችንም እየሰሩ ነው። ፕሮጀክቱን ገና ‹‹ሀ›› ብለው ሲጀምሩ ከጂ አይ ዜድ 5 ሺ ዩሮ ድጋፍ ያገኙ ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ማሽን ዲዛይን ከማድረግ ጀምሮ እስከ ምርት ድረስ ባለው ሂደት ተጠቅመውበታል።
‹‹የእኛ የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ሌሎች ከሚያመርቱት በብዙ ይለያል›› የምትለው ወጣት ጊዮናዊት አንድ ማዳበሪያ ለሁሉም ገበሬ ይሆናል ብለን አናምንም፤ ከዚህ አኳያ እኛ የምናመርተው እንደአፈሩ አይነት በመሆኑ ከሌሎች እንለያለን ትላለች።
የአንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ አፈር ጥሩ ይሆናል። የሌላው ደግሞ ጥሩ ላይሆን ይችላል። ጥሩ የሆነው ብዙ ማዳበሪያ ሲጠቀም አፈሩ ከመጠን በላይ ዳብሮ መሬቱ ይቃጠላል። ወይም ደግሞ ማውጣት ያልነበረበትን ወጪ ለማዳበሪያ ግዢ ያወጣል። ሌላው ደግሞ ማዳበሪያ አምጥቶ ሲሞክር በአፈር ውስጥና በማደበሪያው ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ተመጣጣኝ ሳይሆን ቀርቶ ላይሰራለት ይችላል።
ከዚህ አንፃር እነ ጊዮናዊት የእያንዳንዱን አርሶ አደር አፈር በቅድሚያ በውስጡ ምን እንዳለውና ምን እንደሚጎደለው በማጥናት የማላመድ (custum made) ስራ ይሰራሉ። ገበሬው ምን አይነት እፀዋት እንደሚተክል፣ አፈሩ ምን እንደሚጎድለውና እፀዋቱ ምን አይነት ንጥረ ነገር እንደሚፈልጉ በማጥናትና ሳይንሳዊ መንገዱን በተከተለ መልኩ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ያዘጋጃሉ። ይህም ምርቱ ለእያንዳንዱ ተጠቃሚ የተሻለና ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል።
በሌላ በኩል ለእፀዋት እድገት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች NPK (nitrogen, phosphorus and potassium) በሚያጥሩ ግዜ መመለስ ስለሚኖርባቸውና ማዳበሪያው በነዚህ ንጥረ ነገሮች በበለፀገ ቁጥር ይበልጥ ተመራጭ ይሆናል። እነርሱም ማዳበሪያቸው የተሻለ ተፈጥሯዊና ከፍተኛ NPK ይዘት ያለው ሆኖ እንዲመረት ዋነኛ ዓላማቸው ነው። የአፈርን ጤንነት በመጠበቅ ኬሚካል ሳይጠቀሙ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ብቻ ወደ ተፈጥሯዊ ግብርና መግባትም ነው የእነርሱ ውጥን።
በግብርናው ዘርፍ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳለ የምትናገረው ወጣት ጊዮናዊት፤ ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ትገልፃለች። ከዚህ አንፃር የማዳበሪያ እጥረት በመኖሩና አገራዊ ችግር በመሆኑ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ እርሷና ጓደኞቿ እንደተነሱም ትናገራለች። በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም አፈር በቀጣዮቹ ሃምሳ ዓመታት ብቻ ሊቆይ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣውን ጥናት ታሳቢ በማድረግ መሬት ሳይጎዳ ምርትን በዘላቂነት በመጨመር የመጠቀም አካሄድ እንደሚከተሉም ነው የምትገልጸው።
‹‹የግሪን ኢትዮጵያ ዋነኛ ግብ ተፈጥሯዊ ግብርናን ማስተዋወቅ ነው›› የምትለው ወጣት ጊዮናዊት፤ ይህ የሚሆነው ግን መሬታችን ሳንጎዳና ግብርናን ዘለቄታዊ በማድረግ መሆኑን ትገልፃለች። ገበሬው በግብርና ዘላቂ እንዲሆን ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ሊቀርብለት እንደሚገባ ትጠቁማለች። ተፈጥሯዊ ግብርናን እንዲከተል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም ትጠቅሳለች። እኛም የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደየአፈሩ ሁኔታ አምርቶ በመሞከር ግብርናውን ዘላቂ ለማድረግ ስራ ጀምረናል ትላለች።
ይህን ተፈጥሯዊ ግብርና ከተፈጥረሯዊ የአፈር ማዳበሪያ ጋር አጣምሮ በስፋት ለማስተዋወቅና ለአካባቢ ተስማሚ በሆኑ ስራዎች ዙሪያ ለሚሰሩ የተሻሉ እድሎች ቢኖሩና ሁኔታዎች ቢመቻቹ አካባቢን በተሻለ ሁኔታ መጠበቅ እንደሚቻል ነው የምትናገረው። በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደመሆኑ አካባቢና ግብርና ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በማህበራዊና አካባቢያዊ ቢዝነስ ላይ ለሚሰሩ ሰዎች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ትጠቁማለች።
ግብርናው የአገሪቱ ትልቁ ክፍለ ኢኮኖሚ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ጊዮናዊት፤ ወጣቱ በስፋት በዚህ ዘርፍ ላይ ተሳትፎ ስራ መፍጠርና በተለይ ደግሞ በዘርፉ ችግር ፈቺ የፈጣራ ስራዎችን መስራት እንዳለበት ትገልፃለች። ግብርናና አካባቢ ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን መፍታት ካልተቻለ ቴክኖሎጂ ብቻውን ጥቅም እንደሌለውም ነው የምታክለው። ከዚህ አንፃር መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ከተቻለ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ባይ ናት ።
በመሆኑም ሁሉም ወጣት በግብርናው ዘርፍ ለመግባት ወደኋላ የሚያፈገፍግ መሆን እንደሌለበትና በዘርፉ መስራት ከቻለ ከራሱ አልፎ ሀገሩንም ሊጠቅም እንደሚችል ወጣት ጊዮናዊት መልእክቷን ታስተላልፋለች። በአካባቢ ጉዳይ ላይም ትኩረት አድርገው ቢሰሩ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያለውን ችግር መቅረፍ እንደሚችሉም ትገልፃለች።
የግብርናው ዘርፍ ገና ብዙ አልተሰራበትም። ዘርፉን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግም ይገባል። የሀገሪቱ ትልቁ ኢኮኖሚ እንደመሆኑ ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል ። እነ ወጣት ጊዮናዊት በግብርናው ዘርፍ ገብተው የጀመሩት ስራ ዘርፉን ለማሻሻል እንደ አንድ ጥረት የሚታይ እንደመሆኑ ሌሎች ወጣቶችም የእነርሱን አርአያ በመከተል በግብርናው ዘርፍ የሚታየውን ችግር ፈቺ ከራሳቸው አልፎ ሀገርንም ጭምር የሚጠቅም ሃሳብና ስራ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም