አዳማ ከተማን የኮንፈረንስና እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን የኮንፈረንስ እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ነው የተገለፀው።
የማዕከሉ ዲዛይን ተሰርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ዲዛይኑም የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህል እና እሴት በጠበቀ መልኩ የተሰራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ማዕከሉ መንግስትን እና የአካባቢውን ባለሀብቶች በማሳተፍ የሚሰራ መሆኑ ነው የተገለፀው።
ዲዛይኑ ተሰርቶ እንደተጠናቀቀም ከባለሀብቱ ጋር ወይይት ተደርጓል ያሉት ከንቲባው፥ የማዕከሉ ግንባታ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ግንባታው ከ3 እስክ 5 ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፥የዘንድሮውን አመት ለዝግጅት በመያዝ በቀጣይ ወደ ግንባታ ለመግባት በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።
ግንባታውን አጠናቆ ለመጨረስም 2 ቢሊየን ብር ስፈልጋል ያሉት ከንቲባው ፥ለግንባታው የሚያስፈልገው የ10 ሄክታር መሬት የማዘጋጀት ሂደቱም ተጀምሯል ብለዋል።
በሌላ በኩል በከተማዋ ከኢንቨስትመንት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ መቅረፍም፥ በዚህ አመት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ነው ከንቲባው የተናገሩት።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው ብዙ ጊዜ የከተማዋ አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጭ ላይ በቂ ዝግጅት ስለማይደረግ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ለበርካታ አመታት መቆየቱ እና ይህም የተለያየ ቅሬታ መፍጠሩንም ከንቲባው አንስተዋል ።
የተጠራቀሙ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የዘርፉን ውስንነቶች ለመቅረፍም የከተማዋን አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ለመስራት ከታሰበው የኮንፈረንስና የኮንቬንሽን ማዕከል አጋዥ የሆኑ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ለመስራት ፍቃድ የሚጠይቁ ባለሀብቶች በቅድሚያ የሚስተናገዱ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።