የትምህርት ጥራት ጉዳይ እንደሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ብዙዎችም ትችት ሲያቀርቡበት ይስተዋላል። ትችታቸው ደግሞ አንድ አካል ላይ ያረፈ አይደለም። ልዩ ልዩ ምክንያቶችን ያነሳሉ። አንዱ የማስተማር ብቃት አለመኖር ሲል ሌላው የግብዓት እጥረት ነው ይላል። አንዳንዱ መነሻው ላይ ያለመስራት ችግር እንደሆነ ሲያነሳ ሌላኛው ከፍተኛ ተቋማት ተመራቂዎችን በብቃት አስተምረው ስለማያወጧቸው እንደሆነ ይጠቁማል። ሁሉም በየፊናው እየተገፋፋም ዛሬ ድረስ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል። እናም ጉዳዩ በጥልቀት የሚመለከተው ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን በዘርፈ ብዙ ተግባር ለመፍታት የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አውጥቷል።
በየደረጃው ችግሮችን ለመፍታትም ሥራዎችን ጀምሯል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ጉዳይ አንዱ ነው። ቀጣሪዎችም ሆኑ ለልምምድ የሚወጡባቸው ተቋማት በብዙ ሲማረሩባቸው ነበር። እናም ብቃት ያለው ተመራቂ ለማውጣት ዋነኛ መፍትሄው ብቃታቸውን የሚያረጋግጥ የመውጫ ፈተና መስጠት የግድ መሆኑን እንደሀገር ታምኖበታል። ለመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመውጫ ፈተናውን ለመስጠት ምን አይነት ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ስንል በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሰይድ መሀመድን አነጋግረናል።
አዲስ ዘመን፡- የመውጪያ ፈተናው መሰጠት ለምን አስፈለገ ?ፋይዳውስ ምንድነው?
አቶ ሰይድ፡– የመውጫ ፈተና መስጠት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ምሩቃን ገበያው የሚፈልገውን አቅምና ብቃት ያሟሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፤ በሀገራዊ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፋዊ ገበያው ላይ በሁሉም የትምህርት መስክ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሩቃንን ማፍራት ስለሚያስፈልግ፤ ከሀገራዊ ኢኮኖሚው ጋር የሚዛመዱ ተማሪዎች ለማውጣት፣ ከቴክኖሎጂውና ከማህበረሰብ ፍላጎት አንጻር የሰለጠኑ እንዲሁም ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን አፍርተናል ወይ የሚለውን ለማየት ፤በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት የበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው።
ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው የተማሩትን ምን ያህል አውቀዋል የሚለውን ለማረጋገጥም መውጫ ፈተናው ትልቅ ፋይዳ አለው። ይህ ደግሞ የትምህርት ጥራቱን ማስጠበቂያ አንዱ መሳሪያ ነው። ስለዚህም ፋይዳው ብዙ ነው። ለምሳሌ የበቃ ተማሪ አለመፈራቱ ምሬቱን በሁሉም ደረጃ አበራክቷል። እናም በጥራትና በብቃት ተማሪዎችን የማፍራት ጉዳይ አንዱ ሆኖ ወደ ሥራ ተገብቶበታል።
በእርግጥ ይህ ሥራ አዲስ አይደለም። በአንዳንድ የትምህርት መስኮች ላይ ከዚህ በፊት ሲተገበር ቆይቷል። ብዙ ለውጥ ያመጣና ተማሪዎችን ከብቃት አንጻር ውጤታማ ያደረገም ነው። እናም የሚነሱ ክፍተቶችን ለማረም የመውጫ ፈተናው እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ታምኖበታል። ከዚህ በተጓዳኝ ተማሪው በየዓመቱ የተማረውን ትምህርት ምን ያህል አውቆት እንዳለፈ ራሱን የሚፈትሽበትና ብቁ መሆኑን የሚያረጋግጥበትም ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ባበቁት ተማሪ ልክ እውቅና የሚያገኙበት ሁኔታን ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናው ሁሉንም ትምህርቶች ያካተተ ነው ወይስ የተለየ ይዘት አለው?
አቶ ሰይድ፡– በግልም ሆነ በመንግስት የትምህርት ተቋም የሚማር ተማሪ ዲግሪውን የሚያገኘው ምዘናውን ሲያልፍ ብቻ ነው። እናም ፈተናው የተማሪዎችን እውቀት፣ አመለካከትና ክህሎትን በሚለካ መልኩ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ አንጻር ብቃትን ይለካሉ የተባሉ የትምህርት አይነቶች ( ኮርሶች) ተመርጠው ለፈተና ይቀርባሉ። የአፈታተን ዘዴው ደግሞ በበይነመረብ ሲሆን፤ መኮራረጅን ይቀንሳል ተብሎ የታሰበበት ነው። እንደየሁኔታው ማለትም እንደ የትምህርት አይነቱ የተግባር ፈተናም ይኖረዋል።
የመመረቂያ ጽሁፍ በተመለከተ በአንድ ጉዳይ ላይ ምን ያህል እውቀት እንደጨበጡ ለመለየት የሚያግዝ የምዘና ስርዓት ነው። ሁሉንም የተማርነውን በብቃት አያረጋግጥም። ስለዚህም በአሁኑ የፈተና አካሄድ ይህ አንድ መስፈርት ሆኖ ይቀጥላል እንጂ ዲግሪ የማግኛና አለማግኛ መስፈርት አይሆንም። በተመሳሳይ ለመመረቅም አያስችልም።
አዲስ ዘመን፡- የፈተና ዝግጅቱ ምን ይመስላል፤አሁን ያለበት ሁኔታስ ?
አቶ ሰይድ፡– በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በመሰረተ ልማትና መሰል ነገሮች ዙሪያም የመጀመሪያ ዙር እይታ ተደርጓል። በዚህም በየዓመቱ ከ150 እስከ 180 ሺህ በመጀመሪያ ዲግሪ የሚመረቁ ተማሪዎችን ምዘና ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለ ታይቷል። ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 146 ሺህ እንዲሁም ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 110 ሺህ በድምሩ 256 ሺ ተመራቂ ተማሪዎችን የመውጫ ፈተና ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ሰነድ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለፈተናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው። ለአብነት አራት የግል ከፍተኛ ተቋማትን ጨምሮ በአጠቃላይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በመውሰድ 33ሺህ የሚሆኑ ኮምፒውተሮች ዝግጁ ሆነዋል። ይህ ሲባል ደግሞ ሙሉ ግንኙነታቸው (ኮኔክሽናቸው) የተሟላና የመብራት መቆራረጥ እንዳይገጥማቸው ይደረጋል። እናም በአስር ዙር ፈተናው እንዲሰጥ ይደረግና የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ይሰራል።
በመንግስትና በግል ተቋማት ላይ የሚሰጡ ከ300 በላይ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉ። ሁሉንም ተማሪ በአንድ ጊዜ መፈተን አይጠበቅብንምና በየትምህርት መስኩ እየተደረገ እንዲፈተኑ ይሆናል። በአንድ ቀን ውስጥ 30 የትምህርት ክፍሎችን በመፈተንም በ10 ቀን ውስጥ 300ውን ማጠናቀቅ ይቻላል በሚል ተይዟል። በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የኮምፒውተር አቅርቦት እና የተፈታኞች ብዛት በመለየት የመውጫ ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገም ይገኛል።
በየዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች አጋዥ የትምህርት ሞጅሎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ፈተናውን ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው። ተማሪዎቻቸውን የሞዴል ፈተና እንዲሰጡም መመሪያው ያስገድዳልና ፈተናው እስኪደርስ ድረስ በዚህ መልኩ እንዲቀጥሉም እየተደረገ ነው። ያልተሟላ ነገር ካለ ደግሞ እንደ መንግስት ድጋፎች የሚደረጉ ይሆናል። በአጠቃላይ እስከ ግንቦት ወር ድረስ እንደትምህርት ሚኒስቴር ሁለት ተግባራትን ጎን ለጎን እየሰራ ነው። የመጀመሪያው ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችሉ ነገሮችን ማሟላት ሲሆን፤ ሁለተኛው በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ተማሪዎች ፈተናውን ሊሰሩበት የሚችሉበትን አቅም መፍጠር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናው የሙያ ብቃት ምዘና (ከሲኦሲ) ጋር ይመሳሰል ይሆን?
አቶ ሰይድ፡- በፈተና ይዘታቸው ተመሳሳይነት አላቸው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን አላማቸው የተለያየ ነው። የሙያ ብቃት ምዘና (ሲኦሲ) ፈተና ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ወደ ሥራ አለም ለመቀላቀል ሲባል የሚወሰድ ነው። ዝቅተኛ ብቃቱን አሟልቷል አላሟላም የሚለውን የሚመዝንም ነው። የመውጫ ፈተና ግን ከሥራው ጀምሮ የትምህርት ሴክተሩን ብቻ የሚያሳትፍ ነው። ዲግሪውን ጭምር የማግኘት ጉዳይ ነው። ብቁ ተማሪን የማፍራት እንጂ የመቀጠርን ጉዳይ አይመለከትም። ያለፉ ተማሪዎች እንደ ሲኦሲው ለመቀጠር ሳይሆን ለመመረቅ ብቻ የሚደርጉት ነው። ሥራ የመቀጠሩ ጉዳይ ከብቃት በኋላ የሚያዩት ሌላ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናው ዓመታትን በዩኒቨርሲቲ ቆይተው የመመረቃቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ስለሚያስገባ ብዙዎች በጥርጣሬ የሚያዩት ነው። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ሰይድ፡– ተማሪዎች ውጤታማ የሚሆኑትና የተሻለ አማራጭን ማግኘት የሚችሉት ብቁ ሲሆኑ ብቻ ነው። ዲግሪ ማግኘትና አለማግኘት አይደለም ግባቸው። በተማሩበት መስክ ተመርቀው ሲወጡ ምን ያህል እውቀት አላቸው? ክህሎታቸው የተሻለ እድልን ይሰጣቸዋል ወይ? የሚለው ነው ጥያቄው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ወሳኙ ነገር ፈተናውን መውሰድ ነው። ምክንያቱም ተማሪዎቹን ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ያሳያልና።
ፈተናው ዲግሪ ለመስጠትና ላለመስጠት ሳይሆን የሚሰጠው ብቁ የሆነ ዜጋ ለማፍራት ነው። የዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ መሆን ያለበት ዜጎችን በብቃትና በእውቀት ለሀገር ማበርከት ነው። ተማሪዎችን ማብቃትን እንደ ስራ አድርጎ የሚቆጥሩ ተቋሞች መሆን አለባቸው ። ስለሆነም ጉዳዩ ከዲግሪ መስጠትና አለመስጠት ጋር ተያይዞ ሊነሳ አይገባም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሲቀበሉ እናበቃችኋለን ብለው እንጂ ዲግሪ እንሰጣችኋለን አልያም ሥራ እናስቀጥራችኋለን ብለው አይደለም። እናም ሁሉም ትኩረት ሊያደርግ የሚገባው ተማሪው ብቃት ኖሮት ወደገበያው ገብቷል ወይ የሚለው ላይ ሊሆን ይገባል። ጭንቀቱም መሆን ያለበት ዲግሪ አገኛለሁ የሚለው ሳይሆን ምን ያህል ብቃት አለኝ የሚለው መሆን አለበት።
ብቃት ያለው ተማሪ ባለማፍራታችን እስከአሁን ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍላለች። መጠቀም ያለባትን ያህልም እንዳትጠቀም ሆናለች። ለአብነት አካውንቲንግ ተምሮ ተመርቆ ቢወጣም ወደ ሥራው አለም ሲቀላቀል ግን በአግባቡ የደመወዝ መቀበያ (ፔሮል) የማይሰራ ባለዲግሪ በርካታ ነው። ስለዚህም ተማሪውም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ማሰብ ያለበት እንዴት ብቁ ዜጋን ማፍራት ይቻላል የሚለው ላይ ነው። በተለይ ተመራቂው ብቁ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገሮች ላይ በመስራት የቀጣይ ራዕዩን ማሳካት አለበት። ብቁ ከሆነ ደግሞ ፈተናውን አንድ ጊዜ አይደለም ሺህ ጊዜ ቢፈተኑ እንደሚያልፈው ማመን ይጠበቅበታል። ቅጥሩም ሆነ ሌላው የግል ሥራው ፈተና እንደማይሆንበት ማሰብ አለበት። ምክንያቱም የተማረ ወድቆ አይወድቅም። በአንዱ ባይሳካለት በሌላው መሥራት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናው ለምን ያህል ጊዜ ይሰጣል፤ የወጪው ጉዳይ?
አቶ ሰይድ፡- ተመራቂዎች ፈተናውን የሚወሰዱት ላልተገደበ ጊዜ ነው። ዝግጁ በሆኑበት ወቅት ላይ ማሟላት ያለባቸውን ነገር አሟልተው መውሰድ ይችላሉ። ስለዚህም የተማሪው አቋማዊ ሁኔታ ብቻ ነው የሚወስነው። ይህ ሲባል ግን ልክ ትምህርቱን እንዳጠናቀቁ አይወስዱም ማለት አይደለም። ለመመረቅ ዝግጁ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን በመጨረሻው ዓመት ላይ የሁለተኛ ሴሚስተርን እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችንም ጭምር ባካተተ መልኩ ነው ፈተናው የሚሰጠው። ስለዚህ በመጀመሪያው ባይሳካላቸው ሁለተኛው ላይ የሚወስዱበት አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል።
የፈተና ወጪን በተመለከተ በመንግስት ዩኒቨርሲቲ ተምረው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ለመጀመሪያ ጊዜ ወጪያቸው የሚሸፍነው በመንግስት ይሆናል። በተደጋጋሚ ሲወስዱ ግን ወጪያቸውን ራሳቸው እንዲሸፍኑ መመሪያው ያዛል። ወጪው የሚወሰነው ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታውን ባማከለ መልኩ ነው። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ከመጀመሪያው ጀምሮ በራሳቸው ወጪ እየተማሩ ስለሆነ ለፈተና የሚሆነውን ወጪም ራሳቸው ይሸፍናሉ።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናን በተመለከተ መመሪያ መውጣቱ ይታወቃል። ምን ምን ነገሮችን ያካተተ ነው?
አቶ ሰይድ፡– መመሪያው ብዙ ነገሮች የተካተቱበት ነው። ከመውጫ ፈተና አስፈላጊነት ጀምሮ እስከ ተግባሪ ተቋማት ድርሻና ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ አስቀምጧል። ፈተናው እንዴት ይዘጋጃል፣ በእነማን፤ እንዴት ይሰጣል፤ ውጤቱ በእነማን ይለካል፤ እንዴት ይገለጻል፤ የፈተና ወጪ አሸፋፈን በምን መልኩ ይከናወናልና መሰል ነገሮችን አካቶ ይዟል። ያው በዝርዝር መመሪያዎች የሚጠናከርም ቢሆንም። ለዚህ ደግሞ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ናቸው። ምክንያቱም የመተግበሪያ ዝርዝር መመሪያ ስለሚያስፈልግ።
አዲስ ዘመን፡- በመመሪያው ላይ ሀገራዊ ዝቅተኛ የትምህርት ብቃት ብሎ ያስቀመጣቸው ነገሮች አሉ። እነዚህ ምንምን ናቸው?
አቶ ሰይድ፡– በርካታ ናቸው። በየትምህርት መስኩም ተቀምጠዋል። አለያየታቸው ደግሞ በደረጃ (ሌቭሎች) የሚቀመጥ ይሆናል። ስለዚህም የትምህርት አይነቶቹ ብዙ ስለሆኑ ይህ ይህ ነው ለማለት ያስቸግራል። በጥቅሉ ግን በደረጃ እንደሚለዩ ማወቅ ተገቢ ነው። ይህንን በደንብ ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል። ስለዚህም እርሱ ሲጸድቅ በዚያ መስፈርት መሰረት ተማሪዎች ዝቅተኛውን ብቃት አሟልተዋል አላሟሉም ተብሎ ይለያል።
አዲስ ዘመን፡- ፈተናውን ከብልሹ አሰራር ነጻ ለማድረግ ምን ታስቧል?
አቶ ሰይድ፡– የመጀመሪያው ፈተናውን በበይነመረብ ማድረግ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከሰው ንክኪ ነጻ ያደርገዋል። ከሰዎች ጋር ግንኙነት ከሌለው ደግሞ ተማሪዎች በራሳቸው አቅም ሰርተው ተገቢውን ውጤት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ተፈታኞች የራሳቸው የሚስጥር ቁጥር (ፓስወርድ) ጭምር ኖሯቸው ነው ወደፈተናው የሚገቡት። በዚህም ጎን ለጎን የሚቀመጡ የአንድ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ቢኖሩ እንኳን መኮራረጅ እንዳይችሉ ተደርጎ ነው የተሰራው።
አዲስ ዘመን፡- የመውጫ ፈተናው ስኬታማ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ሰይድ፡– ከተማሪዎች ስጀምር አንድ ተማሪ ዝቅተኛ የሚጠበቅብኝ ብቃት ምንድነው? የሚለውን በደንብ ማወቅ አለበት። ለዚህ ደግሞ መነሻ የሚሆነው ሰነድ ተዘጋጅቷል። ስለዚህም ሰነዱን በደንብ በማየት በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ይመዘናል ተብሎ የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ፤ እነርሱን አይቶ መዘጋጀትም ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ብቃታቸውን ለመለየት የሚያስችሉ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶችም) በመለየታቸው እነርሱን በሚገባ ማወቅና መዘጋጀት አለባቸው።
ትምህርት ተቋማትም በመመሪያው መሰረት ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል። በተለይ በስነልቦና ሳይጨናነቁ ራሳቸውን ዝግጁ የሚያደርጉበትን ስርዓት መፍጠር ላይ በደንብ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
አቶ ሰይድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015