ሰሞኑን የወጣ አንድ የሙዚቃ ቪዲዮ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል። የሙዚቃ ክሊፑ “እናትዋ ጎንደር” ይላል። በዩቲዩብም በአጭር ጊዜ ብዙ ተመልካችና አድናቆት አግኝቷል። ሙዚቃውም ይሁን የሙዚቃው ቪዲዮ ላይ ያሉትን ቴክኒካዊ ጉዳዮች ለባለሙያዎች ወደ ጎን ትተን የተዘፈነለትን አካባቢ ቱባ ባህል ሳይበረዝ ሳይደለዝ ትክክለኛውን ገጽታ በማቅረብ ረገድ የተዋጣለት ነው ማለት ይቻላል።
በእርግጥ ከዚህ የሙዚቃ ክሊፕ በፊትም በተለያዩ ጊዜዎች በበርካታ አካባቢዎች ተመሳሳይ የባህል ሙዚቃ ቪዲዮዎች በብዙ ቋንቋዎች ተሰርተው አድናቆትን አትርፈዋል። አንድ ኢትዮጵያን ቀርቶ ማንን እንደሚገልጽ ግራ የገባው የሙዚቃ ክሊፕ ለመስራት ዱባይ ባህር ዳርቻ ድረስ ብዙ ወጪ አድርገው የሚሄዱ አርቲስቶች ባሉበት በዚህ ዘመን ገጠር ድረስ ሄደው ትክክለኛውን ባህል ለማሳየት የሚጥሩ እንዲህ አይነት ባለሙያዎች ሊደነቁና ሊበረታቱ ይገባል።
የዛሬው ትዝብቴ ዘመናዊ ሙዚቃን በዘመናዊ ክሊፕ አቀረብን እያሉ እርቃናቸውን በሚባል ደረጃ እየጨፈሩ ሌትና ቀን የሚያደነቁሩን ላይ አይደለም። እነሱ አንዴ ከጥበብም ከኢትዮጵያዊ ባህልና እሴትም የተጣሉ ናቸውና ንቆ መተው እንጂ መወያያ እንዲሆኑ መፍቀድ አይገባም። ይልቁንም የሆነን ባህል ለማስተዋወቅ በሚል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚሰሩ የባህል ሙዚቃ ክሊፖች ላይ ትኩረት ማድረጉ የተሻለ ጥቅም አለው።
አንዳንድ ክሊፖች የተለያዩ አካባቢዎችን ባህል ለማንፀባረቅ በሚል ቢሠሩም ስህተት እንደሚበዛባቸው ማስተዋል ይቻላል። በዚህ ረገድ በተለይ በአልባሳትና ውዝዋዜ መወከል ካለባቸው አካባቢ ባህል ውጪ እንደሚሠሩ ትችት የሚቀርብባቸው ጥቂት አይደሉም። ለዚህም የሙዚቃውን ክሊፕ የሚያሰሩ አርቲስቶች ወይም ፕሮዲውሰሮች ተወዛዋዦችን በአነስተኛ ገንዘብ መቅጠር የተዋጣላቸው ክሊፖች እንዳይሠሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ይነሳል። ትክክለኛውን ባህላዊ ውዝዋዜ የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች አለመኖራቸውም ጠንካራ ሥራ እንዳይቀርብ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው። ከተለመደው ወጣ ያለና ማራኪ አቀረራብ ያላቸው ክሊፖች በብዛት አለመታየታቸው ሌላኛው ችግር ሲሆን፣ ክሊፖች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የሚታይባቸው ለፈጠራም የታደሉ አለመሆናቸው ይታያል።
ብዙዎቹ ተወዛዋዦች ከውዝዋዜ ድረ ገጾች እያዩ ነው የሚማሩት። ከተለያዩ አገሮች የሚመለከቷቸውን ስልቶች ከባህላዊ ውዝዋዜ ጋር ደባልቀው ያቀርባሉ።ባህላዊ ውዝዋዜ ደግሞ ያለ ምንም ተጨማሪ ስልት ነው መቅረብ ያለበት።
የባህላዊ ዘፈን ክሊፖች ሲሰሩ ወደተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱ በመመልከት የአካባቢውን ባህላዊ ውዝዋዜ በደንብ አጢኖ ማዘጋጀት ቢገባም ይህን ማድረግ በማይፈልጉና አዲስ አበባ ላይ ብቻ ተቀምጠው የተለያዩ አካባቢዎችን ባህል ለማሳየት በሚጥሩ ግለሰቦች ከባህል የሚጻረሩ ውዝዋዜዎች እየታዩ ነው።
ዘፈን ያለ ምክንያት አይዘፈንም፣ በየአካባቢው ስሜትን ለመግለጽ ወይም ለበዓላት የሚዘፈኑ ዘፈኖች የየራሳቸው አጨዋወት እንዳላቸው መታወቅ አለበት። ዛሬ ዛሬ የትኛው አለባበስና መጊያጊያጫ የቱን ብሔረሰብ እንደሚወክል ሳይታወቅ ክሊፕ ሲሠራ ይታያል።በየብሔረሰቡ ያሉ ቁሳቁሶችና አኗኗሩ መልዕክት ቢኖራቸውም ይህን ተረድተው በክሊፕ የሚያካትቷቸው ጥቂቶች ናቸው።
ከአነስተኛ ቁሳቁሶች አንስቶ የአንድ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ ግብዓቶች ተሟልተው ክሊፖች መሠራት ቢኖርባቸውም የሚያሠራው ሰው በትንሽ ወጪ ለመጨረስ ሲል እንዲካተቱ ጥረት አያደርግም።ከእውቀት ማነስ በተጨማሪ ለክሊፕ የሚወጣው በጀት አነስተኛ መሆን ችግሩን ያጎላዋል።
ውዝዋዜ ፈጽሞ መነሻውን መልቀቅ እንደሌለበትና ከምንም ዘዬ ጋር መቀየጥ እንደማይገባው የዘርፉ ባለሙያዎች በአጽንኦት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። ውዝዋዜ ከሰውነት እንቅስቃሴ ባሻገር መልዕክት ማስተላለፊያ ነው።በክሊፖች ውዝዋዜ አንዳች ስሜት በሚሰጥና መልዕክት በሚያስተላልፍ መልኩ መሰናዳት ያስፈልጋል። ባህል ለማሳየትና ለክሊፑ ትርጉም ለመስጠት አስፈላጊው ወጪ ተመድቦ በጥንቃቄ ሊሰራ ይገባል።ተወዛዋዦችና ኬሮግራፈሮች የሚከፈላቸውን አስበው ድምፃውያን የፈለጉት ዓይነት ውዝዋዜ ቢያቀርቡ እንጀራ ስለሆነ ላይፈረድባቸው ይችላል። ነገር ግን ዘመናዊነት በሚል ከባህል ጋር የሚቀየጡ ውዝዋዜዎችና አልባሳት ከባለሙያዎች ተቃውሞ የሚገጥማቸው በዚህ ምክንያት ነው።
ለገበያ ሲባል ብቻ አካባቢን የማይወክሉ ሥራዎች ከሚሠሩ፣ በባለቤትነት የሚያሠሩ ድምፃውያን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ክሊፖች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በአንዳንድ ግለሰቦች አለባበስ ላይ ጭምር መታየቱን እዚህ ጋር ማስታወስ ያስፈልጋል። ባህል እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነት ከባህልና ሚኒስቴር አንስቶ የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት በመሆኑ ክሊፖች ሲሰሩ በጥናት ሊመረኮዙ ይገባል።
ክሊፖች ከተሠሩ በኋላ የሚነገርለት አካባቢ ተወላጆች ወይም ትክክለኛውን ባህል የሚያወቁ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። አልባሳቱና ውዝዋዜው ባህሉን እንደማይገልጹ የሚተቹበትም አጋጣሚም ጥቂት አይደለም።በቸልተኝነትና የእውቀት ማነስ የሚሠሩ ስህተቶች ቢኖሩም ትክክለኛው ሥፍራ ሄዶ ለመሥራት የሚያስችል አቅም ማጣትም ለዚህ አንድ መንስኤ ነው።
ባህላዊ ክሊፖች ዘመናዊነትን ማሳየት ቢፈልጉ በዘፈቀደ ማደበላለቅ ሳይሆን ትክክለኛውን ባህላዊ ውዝዋዜ አቅርቦ ዘመናዊ የሚባለውን ለብቻው ማሳየት ይችላሉ። አቅም ያላቸውና የአንድ አካባቢን የዕለት ከዕለት ሕይወት በቅርብ ተከታትለው በክሊፖች ያካተቱ ባለሙያዎች ተደማጭነትና ተቀባይነት የሚያገኙበት ሚስጥርም ይህ ነው።
ክሊፖች ለዕይታ ከመብቃታቸው አስቀድሞ መገምገምና መታረም አለመቻላቸው ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ክሊፖቹ ለቀጣይ ትውልድ ባህል የሚያተላልፉና ለዓለም የሚያስተዋውቁ ከመሆናቸው አንፃር ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። ‹‹ለምሳሌ በአማራ ክልል የጎጃም፣ ሰቆጣ፣ አገው፣ ጎንደር፣ ምንጃር፣ ከሚሴና ወሎ እየተባለ የተለያየ ጭፈራ አለ።አማራ ስለተባለ ብቻ አንድ ዓይነት አይሆንም።መጠነኛም ቢሆን ልዩነት ያላቸው እንቅስቃሴዎች ተነጣጥለው መቅረብ አለባቸው።
በክሊፖች ከውዝዋዜ በተጨማሪ የተለያዩ አካባቢዎችን አኗኗር የሚያሳዩ ክንውኖች ማካተት አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል።ለምሳሌ ስለ አፋር የተዘፈነ ክሊፕ ሲሠራ ግመልን የመሰሉ እንስሳት ወይም በአካባቢ ያለውን ልዩ አኗኗርና የሉሲን ቅሪተ አካል ማሳየት ይቻላል።ከተቻለ የአካባቢውን ተወላጆች ማሳተፍ ክሊፖቹን ከማሳመሩ በላይ ለቀጣይ ሥራዎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
ውዝዋዜን በትክክል ማሳየት የሰውነት እንቅስቃሴው የሚያስተላልፈውን መልዕክት ሳያዛባ ያደርሳል።የኩናማ ምት ለማስደንገጥና የጎጃም እንቅጥቅጥ ፍርኃትን ለማንፀባረቅ እንዲሁም ሌሎች ውዝዋዜዎችም መስመራቸውን ሳይለቁ ሲሠሩ ትርጉም ይሰጣሉ። በተያያዥ የትኛውም ዘፈን የሚያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ለውዝዋዜው መሠረት መሆን አለበት።ስለ አገር፣ ፍቅር፣ ግብርና ወይም ሌላ ጽንሰ ሐሳብ ሲነሳ ክሊፑ ግጥሙን በሚገልጽ ውዝዋዜ መታጀብ አለበት።፡
በእርግጥ በሚዘፈንለት አካባቢ የሚቀረፁ ክሊፖች ተወዳጅ የመሆን ዕድላቸው ቢሰፋም ሁልጊዜ ላይሳካ ይችላል።ክሊፖቹ በማንኛውም ቦታ ቢሠሩ በጥናት ላይ የተመረኮዙና ትክክለኛውን ባህል የሚያንፀባርቁ መሆን እንደሚገባቸው ግን ባለሙያዎች የሚያምኑበት ጉዳይ ነው። በክሊፖች ዝግጅት ድምፃውያን፣ ኬሮግራፈሮች፣ ተወዛዋዦች እንዲሁም አዘጋጆች ኃላፊነት አለባቸው። የክሊፑ ግብዓቶች ባጠቃላይ የአንድ አካባቢን ትክክለኛ ባህል የሚያሳዩ መሆን አለባቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015