የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ክብር ማህተም እና ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟ ጎልቶ እንዲወጣ ካደረጉት አንዱ ከመሆኑም ባሻገር የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው። ይህ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ኩራት የሆነው የአድዋ ድል በየዓመቱ የካቲት 23 በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከበራል። በአሉ ሲከበር ሁሌም የዚያ ታሪክ ባለውለታዎች ይታሰባሉ፤ ይህ ትውልድ ደግሞ የአድዋን አይነት ታሪክ እንዲደግም መልእክትም ሲተላለፍበት ኖሯል።
አድዋን ለማሰብ የሚያስችሉ መንገዶችን አደባባዮችን በመሰየም ታሪኩን ለማስታወስና ለመዘከር ሲሰራም ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ ግን የአድዋ ገድል ታላቅ መሆኑን በመጥቀስ ይህን የሚመጥን ታሪኩን የሚዘክር ተግባር አልተከናወነም በሚል ትችት ሲሰነዘር ነው የኖረው።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የመጣው መንግስት ይህን ጥያቄ በመገንዘብ ታሪኩን ይመጥናል ያለውን ግዙፍ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ስፍራ ፒያሳ /አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ/ ላይ ካስጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። ፐሮጀክቱ አድዋ ዜሮ ፕሮጀክት በመባል ይታወቃል። ላለፉት ዓመታት ግንባታው እየተካሄደ ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ የተለያዩ ግንባታዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ሁሉም ግንባታዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ተወካይ ኢንጂነር ፈለቀ ወ/ዮሃንስ ለፋና ብሮድካስት እንደገለፁት፤ አራት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት ይህ የአድዋ ዜሮ ፕሮጀክት ሶስት ነጥብ ሶስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው። ፕሮጀክቱ 11 ህንጻዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ 11ዱ ህንጻዎች የተለያየ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ናቸው። ህንጻዎቹ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ከመሆናቸው በተጨማሪ፤ እርስ በእርስ ተሰናስለው የተሰሩ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውና በአድዋ ስም የተሰየመው አድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ግንባታ የተጀመረው በ2012 ሲሆን፣ በ2016 ለማጠናቀቅ ታቅዷል።
ፕሮጀክቱ የአድዋ ታሪክ እንዲዳሰስ እና እንዲታይ አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው እየተገለጸ ነው። በውስጡ የአድዋ ታሪክን የሚያስታውሱ የተለያዩ እውነቶች ይዘከሩበታል። ይህም ኢትዮጵያዊያን ስለ ታሪካቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማስቻሉ ባሻገር ሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞች ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ነጻነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የበለጠ እንዲገነዘቡ ይረዳል።
አድዋ ላይብረሪ፣ አድዋ ሙዚየም፣ የአድዋ የድል በዓል ማክበሪያ ስፍራ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱት ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ፋውንቴኖች፣ ብዙ ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቢሮዎች፣ ጂምናዚየም፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የህጻናት ማጫወቻ፣ አውቶቢስ ማቆሚያ፣ ታክሲ ማቆሚያ፣ የአድዋ ድልን የሚገልጹ አድዋ ተራራዎችን የሚገልጹ የተለያዩ የቅርጻ ቅርጽ ስራዎችን፣ በወቅቱ ለክተት አዋጅ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ነጋሪቶችን ያካተተ እጅግ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ማዘጋጃ ቤቱን ከአድዋ ሙዚየም ጋር የሚያገናኘው ድልድይም የዚሁ አካል ነው።
አድዋን ከሚዘክረው የሙዚየም ክፍል በተጨማሪ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች፣ የኢትዮጵያዊያን የጦር መሳሪያዎች፣ ጦርና ጋሻ በግንባታው ላይ ከሚገለጡት መካከል ናቸው። በህንጻው ላይ የአድዋ ታሪክ እንዲዳሰስ ተደርጎ በግንባታው ላይ እንዲታይ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ኢንጂነሩ የሚያብራሩት።
የፕሮጀክቱ አብዛኛው ክፍል ከመሬት በታች የሚገኝ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ፈለቀ፤ የህንጻው ቁመቱ ብዙም ረጅም አለመሆኑን አንስተዋል። ፕሮጀክቱ አድዋ ዜሮ የተባለበትን ምክንያት ሲያስረዱ ቦታው ለብዙ ነገር እንደ መነሻ ስለሚቆጠር ዜሮ ፕሮጀክት የሚል ስያሜ መሰጠቱን ጠቁመዋል። በአንድ በኩል ቦታው ለአዲስ አበባም ሆነ ለኢትዮጵያ እምብርት ወይም ማዕከላዊ ቦታም ስለሆነ የአዲስ አበባም ሆነ የክልሎች ርቀት መነሻ ከዚህ ቦታ ነው የሚለካው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን አድዋን ያሰቡበት፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲነሱ ጥሪ የተደረገበት፣ አሸንፈው የተመለሱበት ስለሆነ አድዋ ዜሮ የሚል ስያሜ መሰጠቱን ያነሳሉ።
‘’ይህ ዘመን ተሻጋሪ የግንባታ አሻራ አዲስ አበባ የእንቅስቃሴዎች ማእከል መሆኗን ከማመላከቱ በሻገር፤ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሁሉም አቅጣጫ ተሰባስበው ለድል የተነሱበትና ድል ያስመዘገቡበት ታላቅ ማስታወሻ ነው’’ ሲሉ ኢንጂነር ፈለቀ ይጠቁማሉ።
አድዋ የመላ ኢትዮጵያዊያን የትብብር ውጤት ነው። ትብብር ስለነበር ዘመናዊ መሳሪያዎችን የታጠቀውን የጣሊያንን ጦር ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ሳይዙ በጦርና በጋሻ ማሸነፍ ችለዋል። ማሸነፍ የቻሉት ደግሞ መዋጋት ያለበት በመዋጋቱ፣ ማዋጋት ያለበት ደግሞ በአግባቡ በማዋጋቱ፣ ስንቅ ማቃበል ያለበት ስንቅ በማቃበሉ ነው። በማለት በትብብር የትኛውንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል የታየበት መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ፤ ለአድዋ የተደረገው ጥሪ ጭምር በፕሮጀክቱ እንዲካተት ጥረት ተደርጓል። በጦርነቱ ጥቅም ላይ የዋለው የብልሃት፣ የእውቀት፣ የትብብር ተምሳሌት የሆኑት በፕሮጀክቱ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ በአድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው እና ለሉዓላዊነታቸው ያሳዩት አይነት ትብብር ተግባራዊ እየተደረገበት መሆኑን የጠቆሙት እንጂነሩ፤ የተለያዩ ሙያ ያላቸው ሰዎች በፕሮጀክቱ ላይ ተሳትፈዋል። ሁሉም በእውቀቱና በሙያው አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል። የታሪክ ባለሙያዎች፣ የአርክቴክቶች ማህበር ተሳትፏል፣ የአርበኞች ጀግኖች ማህበር ተሳትፏል፣ እንዲሁም የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ዛሬም ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ናት። ከችግሮቿ ለመሻገር የሁሉንም ዜጋ ትብብር ትሻለች። ሁሉም በሙያው፣ በእውቀቱ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ለሀገሩ መስራት አለበት። በአድዋ ወቅት የነበረውን አይነት ትብብር እና ህብረት የሚፈልጉ በርካታ ችግሮችን ድል መንሳት ያስፈልጋል።
አብዛኞቹ ህንጻዎች እርስ በርሳቸው የተገናኙ ሲሆን አድዋ ሙዚየምን ከማዘጋጃ ቤት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ግንባታም መጠናቀቁን ተናግረዋል። ድልድዩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሉትም አንስተዋል።
እንደ ኢንጂነር ፈለቀ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱን ግንባታ ጃንግ ሱ የተባለ የቻይና ተቋራጭ እየገነበ ሲሆን፤ የማማከር ስራውን እየሰራ ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ነው። ፕሮጀክቱ ላይ ዘመኑ የደረሰበት አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እና ሀሳቦች ተግባራዊ የተደረገበት እንደመሆኑ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች እየተሳተፉ ያሉበት እንደመሆኑ የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን ተስፋ የተጣለበት ነው።
እንደ ኢንጂነር ፈለቀ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ውብ መልኮች መካከል አንዷ በሆነችው ፒያሳ ላይ የሚገነባ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ከአድዋ የአድዋ ታሪክን ከመዘከር በተጨማሪ የአዲስ አበባ እምብርት የሆነችው ፒያሳ ኪነ ህንጻ፣ ጥበብ እና ታሪክ በሚያሳይ መልኩ እየተሰራ ነው። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባን በተለይም የፒያሳን ውበት በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል።
ፕሮጀክቱ ካካተታቸው አምስት ወለሎች አንዱ ዜሮ ወለል የሚባል ሲሆን ይህ ወለል የአድዋን በዓል የማክበሪያ ቦታ ነው። ኢንጂነሩ እንደሚሉት የአድዋ በዓል ማክበሪያ ቦታ ግንባታው እየተፋጠነ ነው። የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩለት ነው። በቦታው የዘንድሮውን የአድዋ በዓል ለማክበር ርብርብ እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅት የበዓሉ ማክበሪያ ቦታ የውሃ ስርገት የመከላከያ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ይገኛል። የውሃ ስርገት የመከላከያ ሥራው እንደተጠናቀቀ ግራናይት የማንጠፍ ሥራ ይሠራል። ለዚህ የሚሆኑ ቁሶች ከውጭ ሀገራት እየመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁሶች እንደደረሱ የአድዋ በዓል ማጠናቀቂያ ሥራው እንደሚፋጠን ጠቁመዋል። አድዋ ድል ማክበሪያ ስር አድዋ ሙዚየም ይገኛል። የዚህ ሙዚየም የማጠናቀቂያ ሥራዎችም በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
እንደ ኢንጂነሩ ማብራሪያ፤ በፕሮጀክቱ ውስጥ ከተካተቱት መካከል የመኪና ማቆሚያ አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅትም የመኪና ማቆሚያ ቦታው የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩለት ነው። ቀለም የመቀባት እና ሜካኒካል እና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ስራዎች እየተሰሩለት ነው። ፓርኪንጉ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እየተሠራ ይገኛል። ፓርኪንጉ የራሱ የሆነ የእሳት መከላከያ እና የፓርክንግ ማነጅመንት ስርዓት አለው። መኪኖች ሲገቢ እና ሲወጡ የራሱ የሆነ የቲኬቲንግ እና የሰርቬላንስ ስርዓት እንዲሁም የአየር እንቅስቃሴን የሚቆጣጠሩ ሜካኒካል ስራዎች ጭምር እንዲኖረው ተደርጎ እየተሠራ ያለ ፕሮጀክት ነው። በአጠቃላይ መኪና ማቆሚያው እጅግ ዘመናዊ ሲሆን ዘመኑ የደረሰበትን የመኪና ማቆሚያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያካትት ተደርጓል።
ይህ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ በከተማዋ ውስጥ የሚስተዋለውን የመኪና ማቆሚያ ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል። የመኪና ባለቤቶች መኪናቸውን በመንገድ ዳር በማቆም ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት እንዳይሆኑ መፍትሄ የሚሰጥ ነው። በአጠቃላይ ለከተማው ገጽታ ትልቅ ፋይዳ አለው። በከተማው ያለውን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጥ ባሻገር ለደንበኞች ንብረት ደህንነት መጠበቅ፤ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠርና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ግዙፍ የመዲናችን ፕሮጀክት ነው።
በመኪና ማቆሚያው የሚቀሩ የፓርኪንግ ጋይደንስ ሲስተሞች/ የመኪና ማቆሚያ ስርአቶች/ የመግጠም ሥራ ሲሆን ቲኬቲንግ እና ሌሎች ሲስተሞችን የማጠናቀቂያ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ አብዛኛው የመዋቅር (structure) ግንባታ ሥራው መጠናቀቅን ተከትሎ የማጠቃለያ ስራዎች (Finishing works) የሆኑት የአሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የተለያዩ የወለል ንጣፍ ሥራዎች (ሴራሚክ ስራ)፣ የጅብሰም እና ሌሎች መሰል የማጠቃለያ ተግባራት በህንጻው ውስጣዊ ክፍሎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
አክለውም አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለአገልግሎት ለማብቃት የማጠቃለያ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች እየተፋጠኑ ሲሆን፣ የፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀም ደረጃም ከ77 ከመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
ቀሪውን ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት እንጂነሩ፤ ተቋራጩ ግንባታውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እያደረገ ነው። ከተማ አስተዳደሩ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአሁን ወቅት እየተደረገ ባለው ክትትል ፕሮጀክቱ በቀጣይ ዓመት ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም