አርሂቡ ኮምቦልቻ»
የኮምቦልቻ ሪጆ ፖሊታን ከተማ ተፈጥሮ ያደላት፣ በሰንሰላታማ ተራሮች የተከበበች፣ ቦርከና ወንዝን የመሰለ ብዙ የተዜመለት፣ ብዙ የተነገረለት ስመ ጥር ወንዝ ከነግርማ ሞገሱ በክረምት እየተገማሸረ፤ በበጋ እየተስረገረገ የሚያቋርጣት፤ የአየር ንብረቷ ተስማሚና ከአራቱም ማዕዘናት የሚመጡ እንግዶቿን ለማስተናገድ ፈገግታ የማይለያት የስራ፤ የኢንዱተስትሪ እና የንግድ ከተማ ናት፡፡
ነዋሪዎቿ አቃፊና እንግዳ ተቀባይ፤ ‹‹አርሂቡ›› ካፋቸው የማይነጥሉ፤ ያላቸውን ያለስስት የሚያካፍሉ እንግዳ ተቀባዮች፣ መከባበርና መዋደድን በተግባር ያስመሰከሩላት የሁሉም ከተማ ናት፡፡
ታዲያ ይህች ‹‹አሪሂቡ›› ብላ አድንግዶቿን በምትቀበለው ከተማ በጦርነት ውስጥ ቆይታች፡፡ ታዲያ ከዕለታት በአንዱ ቀን በጦርነት ቁዘማ ውስጥ የነበረችውን ኮምቦልቻ ከተማ ለማነቃቃት በማሰብ በተዘጋጀው የሩጫ እና የማነቃቂያ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ወደ ከተማዋ አመራሁ፡፡ በማለዳው ‹‹አርሂቡ ኮምቦልቻ›› የፍቅር ሩጫ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት የሰውነት ማሟሟቂያ ከሚያሰሩ ወጣቶች ከአንዱ ጋር አስተዋወቀችኝ፡፡
ኤፍሬም- ኮምቦልቻ
ኤፍሬም ይትባረክ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንን ደግሞ በሚሊኒየም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን ኮምቦልቻ ከተማ በሚገኝ ኢንዱትሪያል ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶ ሞቲቭ ቴክኖሎጂ /Auto motive Technology/ ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን እንዲሁ ኮምቦልቻ ከተማ በሚገኘው ወሎ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ፓወር ስትሪም ነው የተመረቀው፡፡
ኤፍሬምና ስፖርት ቁርኝታቸው የላቀ ነው፡፡ ‹‹ስፖርት የጀመርኩት ልጅ እያለሁ አክሽን ፊልሞችን በጣም አይ ነበር እና ፍላጎቴ ጨመረ፤ በአጋጣሚም በምኖርበት አካባቢ ብላክ ስታር ሾቶካን ጃፓን ካራቴ ክለብ በሚባል ተቋም ውስጥ ኢንስትራክተር ሰንሴ ኡስማን አህመድ ያሰለጥን ነበር እዛ ክለብ ውስጥ ተመዝግቤ ሥልጠና ጀመርኩ፡፡ በሥልጠና ወቅት በፋይናንስ እና በማቴሪያል ቤተሰቦቼ ይደግፉኝ ነበር፡፡ በአሰልጣኜ ሰንሴ ኡስማን አህመድ አማካኝነት በርካታ ውድድሮችን በመሳተፍ ከተማዬን፣ ዞኔን፣ ክልሌን በመወከል እስከ መላው ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያን አምጥቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውጤቶች ጀርባ የአሰልጣኜ ሶንሴ ኡስማን አህመድ አስተዋፅዖ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር›› ሲል የስፖርት ጅማሮ እና ጉዞውን በማስታወስ በአጋጣሚው ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ ይላል፡፡
ኤፍሬም ከዚህም በተጨማሪ በቦክስ የስፖርት ዘርፍ በከተማና ዞን የተዘጋጁ ውድድር ላይ በመሳተፍ የብር ሜዳሊያ አምጥቷል፡፡ በሰልጣኝነት ሰባት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ወደ ‹‹ብለድ ካራቴና ኤሮቢክስ›› ክለብን ለመክፈት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ጀመረ፡፡ የስፖርት ክለቡን ለመክፈት እጅግ በጣም ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ከነዚህም መካከል የቦታ ችግር ነበር፤ ይህንን ችግር ለማቃለል ሁለት አመት ወስዶበታል፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ በርበሬ ወንዝ ቀበሌ 05 ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ቦታ ማግኘት ቻለ፡፡ ቦታውን ካገኘ በኋላ ግንባታውን በግል ወጪ መገንባት እንዳለበት ተነገረው፡፡ ይህ ደግሞ ሁለተኛው ፈተና ነበር፡፡ ይህንን ችግር ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር እንዲሁም ከአንዳንድ መልካም ሰዎች ጋር በመሆን ብለድ ካራቴ ክለብን ለመክፈት በቃ፡፡
ስፖርት የትም ለማንም
ስፖርት እና ጤና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የሚለው ኤፍሬም፤ ስፖርት ማለት ተላላፊም ተላላፊ ያልሆኑትንም በሽታዎች ያለምንም መድኃኒት ማዳን የሚችል ትልቅ ኃይል ያለው ነገር ነው፡፡ ስፖርት ስኳር፣ አስም፣ ደም ግፊት፣ የደም መርጋት እንዲሁም የወገብ ህመም እና የጭንቅላት በሽታን ያለምንም መድኃኒት ማዳን ወይንም መከላከል የሚችል ትልቅ ኃይል ነው፡፡
‹‹ሱሰኛ ማለት እንደኔ አመለካከት ረጅም ዓመታት ተፈርዶበት እንደታሰረ ሰው ነው የምቆጥረው›› የሚለው ወጣት ኤፍሬም፤ ይሄ የታሰረ ሰው ቤተሰቦቹን፣ ጓደኞቹን መርዳት መጠየቅ ቢፈልግ ወይንም ልጆቹን ተከታትሎ አስተምሮ ለትልቅ ማዕረግ ማብቃት ቢፈልግ ይህንን ለማድረግ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስለታሰረ ሱሰኛም ሙሉ አካል እያለው መስራት፣ የቤተሰቦቹን እና የማህበረሰብን ሕይወት መቀየር የማይችል ሰው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሱስ እጅግ በጣም የሚጠላ እና የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡ ከሱስ የፀዳ ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችን የምንፈጥርበት ትልቅ ተቋም ነው፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግም ኤፍሬም በሱስ የተጠመዱ የኮምቦልቻ ወጣቶችን ለመታደግ እየሰራ መሆኑን ይናገራል፡፡ ያለውን ክህሎት በመጠቀም ወጣቶች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከማዋል እንዲቆጠቡ የቅስቀሳ ስራ ጭምር በመስራት በርካቶችን ከሱስ ማላቀቁን ይናገራል፡፡
ኮከቡ አሰልጣኝ
ስፖርት ክለባችን እስካሁን የመጣሁበትበት መንገድ እንደ ስፖርት ክለብ ከተማችንን፣ ዞናችንን እና ክልላችንን በመወከል በርካታ ሜዳሊያዎችን እና ዋንጫዎችን አምጥተናል የሚለው ይህ ወጣት፤ እኔም እንደ አሰልጣኝ የአማራ ክልል በካራቴ ዘርፍ ኮከብ የፕሮጀክት አሰልጣኝ መሆን ችያለሁ ይላል፡፡ በዚህ ወደፊት ኢትዮጵያ በመወከል የወርቅ ሜዳሊያ ለማምጣት ሃሳብ እንዳለውም ኤፍሬም ይገልጻል፡፡
ኤፍሬም እና ጥበብ
ኤፍሬምና ጥበብ ነብስያቸው በእጅጉ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ስፖርትም ጥበብ ነው፡፡ ግን ደግሞ በስፖርት ውስጥም ሌላ ጥበብ አለ የሚል እምነት አለው፡፡ ታዲያ ኤፍሬም ከዕለታት በአንዱ ቀን ከስፖርት በተጨማሪ በፊልም ዓለም ራሱን ለመፈተን ወሰነ፡፡ ‹‹ፊልም ለመስራት ያነሳሳኝ ነገር አንድ የሕይወት ፍልስፍና አለኝ ያም ሁሉም ነገር ይቻላል (i can do it every thing) የሚለውን መርህ ስለማምንበት ነው›› ይላል፡፡ ሰው የሰራው ነገር ለእኔ አይከብደኝም ጊዜ ሊወስድብኝ ይችል ይሆናል እንጂ የሚል እምነት አለው፡፡
ገና በልጅነቱ ፅሁፎችን ይፅፍ ስለነበር የሆነ ጊዜ ላይ በቴሌቭዥን፣ በሬድዮ እና በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች ላይ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ እና እዚሁ በቅርብ በደሴ ከተማ ስለ ህሕፃናት ስርቆት በስፋት ይዘገብ ነበር፡፡ እናም ድሮ ከፃፋቸው በመነሳትና አሁናዊ ሁኔታዎችን በማጣመር እንዲሁም ከሰውኛ ሕይወት ጋር በማዋሀድ ይህንን ሃሳብ ለምን ወደ ፊልም አልቀይረውም በማለት ፊልም ለመስራት ወሰነ፡፡
አይረቴው ኤፍሬም ፊልሙን ለመስራት ሲነሳ በጣም ብዙ ፈተናዎች ነበሩበት፡፡ አንደኛው እንደዚህ ዓይነት ስራ ከዚህ በፊት በኮምቦልቻ ከተማ ላይ አልተሰራም፡፡ ስለዚህ ባለሙያዎችን ለማግኘት እንዲሁም ለቀረፃ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን ለማግኘት ከብዶትም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለቀረፃ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን እና ባለሙያዎችን ከአዲስ አበባ እና ከደሴ በመምጣት ፊልሙን መስራት ጀመርን ይላል፡፡
በቀረፃ ወቅት በጣም ብዙ ሰዎች ይቀልዱባቸው ነበር፡፡ እርሱ ግን ዓላማ የማቻለውን እንደሚቻል ማሳየት ስለነበር እልህ በተሞላበት ስሜት ፊልሙን በርካታ ገንዘብ በማውጣት መስራት ጀመረ፡፡
ፊልም ቀረፃ ላይ
በቀረፃ ወቅት በርካታ ችግሮች ገጥመውናል የሚለው ወጣት ኤፍሬም፤ ከገንዘብ እና ቁሳቁስ ችግር ባሻገር ስራው ሌት ተቀን መስራትን ይጠይቅ ነበር። እነዚህን ችግሮችን በመቋቋም በኮምቦልቻ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹ንፍታሌም›› የተሰኘውን የአማርኛ ፊልም ሰርቶ አስመረቀ፡፡
በፊልሙም፤ ስፖርት ለማህበረሰቡ እና ለአገር ግንባታ አስፈላጊ እንደሆነ፣ የቤተሰብ ፍቅርን፣ የአገር ፍቅርን እንዲሁም መረዳዳትና መተጋገዝን፣ የህፃናትን እንክብካቤና ክትትል፣ ማህበረሰቡ ወንጀልን በጋራ መከላከል እንዳለበት የሚያስረዱ ጭብጦችን የያዘና ተገቢውን መልዕክት ለማስተለላፍ የተሞከረበት ስለመሆኑም ይናገራል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት
ማህበራዊ ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ‹‹ብለድ ካራቴና ኤሮቢክስ ክለብ›› በኮምቦልቻ ከተማዋ ታዋቂ ሆኗል፡፡ በበርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ይሳተፋል፤ አሁንም በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ከተማ ማፅዳት፣ የችግኝ ተከላ፣ ለአቅመ ደካሞች የገንዘብ ድጋፍ፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የአልባሳት ልገሳ፣ የደም ልገሳ፣ እንዲሁም ያለክፍያ በኮንዶሚኒየሞች ላይ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ በቋሚነት ማሠራት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ)፣ ሳኒታይዘር እና የገንዘብ ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበርና ለዚህም ብዙ ምስጋና እደተቸራቸው ይናገራል፡፡
የቸገረን ነገር
በዚህ ወቅት ኤፍሬምን የገጠመው ችግር የማሰልጠኛ ቦታ ነው፡፡ ብለድ ካራቴና ኤሮቢክስ ክለብ ከ 80 በላይ ህፃናትን ከ 60 በላይ ወጣቶችን እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት የሆኑ ከ180-200 የሚደርሱ ሰልጣኞችን አቅፎ የያዘ ትልቅ ክለብ ቢሆንም የማሰልጠኛ ቦታ ችግር አለበት። ለሥልጠና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ችግር ሌላኛው ፈተና ነው። ‹‹ይሁንና እነዚህ ማቴሪያሎች ቢሟሉልን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተማችንን፣ ክልላችንን እንዲሁም አገራችንን ማስጠራትና ማኩራት እንችላለን›› ይላል – ወጣት ኤፍሬም።
ረጅሙ ህልም
ወደፊት ማሳካት ከሚፈልገው ነገሮች መካከል የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በካራቴ ስፖርት ዘርፍ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ እና ለከተማዋ ማህበረሰባችን ኩራት ለወጣቶች ደግሞ ተስፋ መሆን ነው። ከሱስ የፀዳ ብሩህ አዕምሮ ከከልል አልፎ በአገር ደረጃ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ወጣቶችን ማፍራት ዋነኛ ህልሙ መሆኑን በመናገር ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015