በኢትዮጵያ የባለሀብቶችን ትኩረት ከሳቡ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች መካከል አንዷ መሆን የቻለችው የደብረ ብርሃን ሪጂኦፖሊታን ከተማ፣ የኢንቨስትመንት ስኬቷ ለሌሎች አካባቢዎችም አርዓያ መሆን የሚችል ነው። ከተማዋ የአያሌ ኢንቨስትመንት ተቋማት መገኛ ሆናለች።
ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፣ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት መሆኗ፣ ምቹ የአየር ንብረቷ እንዲሁም ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፎች ልማት የሚሆን እምቅ አቅም ያላት መሆኗ ደብረ ብርሃንን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ካስቻሏት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ለቀጣይ 50 ዓመታት የሚያገለግል መዋቅራዊ የከተማ ፕላን እየተዘጋጀላት ያለችው ከተማዋ፣ በቀጣይ ዓመታት የሚኖረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዋም እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
ከተማዋ አሁን ያለውን የኢንቨስትመንት አቅሟን በማሳደግ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እምብርት (Investment Hub) ለመሆን አልማ እየተጋች ነው። ይህን እቅዷን ለማሳካትም በአካባቢው እየተበራከተ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ማገዝና ማበርታት፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አቅሞችን በማስተዋወቅና ምቹ አሰራሮችን በመዘርጋት ተጨማሪ ባለሀብቶችን መሳብ፣ አዳዲስ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማገዝ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የንግድ፣ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ግብዓቶች መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህን ግብዓቶች ለማሟላት እገዛ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች ነው።
ከእነዚህ የኢንቨስትመንት አቅም ማሳደጊያ ግብዓቶች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር በማድረግ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰርና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ እንዲነቃቃ ለማድረግ አጋዥ ግብዓት ይሆናል የተባለለት ‹‹የደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖ›› ነው። ለ10 ቀናት የሚቆየው ኤክስፖው፣ ጥር ስድስት ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተከፍቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በኤክስፖው ላይ ከ250 በላይ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት እየተሳተፉ ሲሆን፤ በኢንቨስትመንት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች፣ የኪነ ጥበብ ትርኢቶችና የልምድ ልውውጥ መድረኮችም የኤክስፖው አካል ናቸው።
መቀዛቀዝና ውደመት የገጠመውን ምጣኔ ሀብት ማነቃቃት፤ ትርፍ አምራቾችና ለማንኛውም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምቹ ለሆኑት የሰሜን ሸዋ ዞን እና አጎራባች አካባቢዎች ከዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ ጋር የተሳሳረ የምጣኔ ሀብት ስርዓት መዘርጋት፤ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ተቋማት የጋራ የትስስር መድረክ መፍጠር፤ የኢንቨስትመንት ቅስቀሳ በማካሄድ የደብረ ብርሃን ሪጂዮፖሊታን ከተማን የኢንቨስትመንት እምብርትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ እንዲሁም የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አቅሞች እንዲያስተዋውቁ እድል መፍጠር ማስፈለጉ ኤክስፖውን ለማዘጋጀት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ኤክስፖው በደብረ ብርሃንና አካባቢው እየተበራከተ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ፣ በማገዝና በማበረታታት፤ አዋጭ በሆኑ ዘርፎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ አዳዲስ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች (Youth Entrepreneurs and Start-Ups) ከትልልቅ ኩባንያዎች ጋር ትስስር እንዲኖራቸው እድል በመፍጠር፤ የዓለም አቀፍ ንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ተቋማትን የትብብር ማዕቀፍና ትስስር በማጠናከር፤ የደብረ ብርሃንን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እምብርትነት በማሳደግ፤ ከዚህ ቀደም በኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ያተኮረ ኤክስፖ ተዘጋጅቶ የማያውቅ በመሆኑ በዘርፉ አዲስ ልምድ እንዲገኝ በማድረግ እንዲሁም ወረዳዎች፣ ከተሞችና ዞኖች የኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውን ለኢንቨስተሮች ማስተዋወቅ እንዲችሉ መድረክ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስት አቶ ደመቀ መኮንን ኤክስፖውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ኤክስፖው መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ጠቃሚ መድረክ ነው።
‹‹ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ቆይታ፣ በአሁኑ ወቅት ሰላምን ማፅናት እንደአንድ ቁልፍ አጀንዳ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች ነው። ሰላምን ከማፅናት በተጨማሪ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ባሉበት የመደገፍና በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ተግባራት የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። ›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱን ወደተሟላ ዘላቂ ልማት ለማሸጋገር እንደዚህ ዓይነት የፋይናንስና የኢንቨስትመንት መድረኮችን ማዘጋጀት ወቅታዊና ተገቢ ነው ብለዋል።
ኤክስፖው በእውቀት፣ በሀብት፣ በጉልበትና በጥበብ አቅም ያላቸው አካላት በጋራ የተሰለፉበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር ምጣኔ ሃብቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል። ኤክስፖው በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውን በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ጥረትን የሚደግፍ ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል።
‹‹ኤክስፖው የደብረ ብርሃንና አካባቢውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ንቅናቄ ነው›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ኹነቱን እንደመነሻ በመጠቀም መሰል የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በአማራ ክልልና በመላ ኢትዮጵያ ማስፋፋት እንደሚገባ አሳስበዋል። በደብረ ብርሃንና አካባቢው የኢንቨስትመንት መስፋፋቱን ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ከዚህ የበለጠ ለማሳካት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ደብረ ብርሃን በኢንቨስትመንት ምቹነትና መስህብነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዎንታዊነት ተጠቃሽ ከተማ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተማዋ እንደ ስሟ የኢንቨስትመንት ብርሃን እንድትሆን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ግብዓቶች ተመራጭና ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመው፣ ባለሀብቶች በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፣ ኤክስፖው አምራቾች ምርቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ ምርቶቻቸው ገበያ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ባለሀብቶችን ለመሳብ እና ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አበረታች ቢሆንም በክልሉ ከሚፈለገው አንፃር በምርት ላይ የሚገኙት ኢንዱስትሪዎች ቁጥራቸው ጥቂት እንደሆነም ጠቁመዋል። ‹‹በአማራ ክልል የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ኢንቨስተሮችን እየሳበ ቢሆንም በክልሉ በምርት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አሁንም ቁጥራቸው አነስተኛ ነው። ለኢንቨስትመንት በተሰጡት መሬቶች ላይ የታቀዱት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ስራ ካልገቡ የክልላችንንና የሀገራችንን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች መቅረፍ አንችልም ሲሉም አስገንዝበዋል። የኑሮ ውድነትን መቅረፍ የሚቻለው በዘላቂነት ምርታማትን በማሳደግ ነው። ምርታማነት የሚያድገው ደግሞ የተጀመሩ አምራች የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ መሆኑንም አመልክተው፣ ኢንቨስተሮች በተቻለ ፍጥነት ወደ ስራ እንደዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። ኢንቨስተሮች የጀመሩትን ስራ አጠናቀው ወደ ምርት እንዲገቡ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።
ዶክተር ይልቃል፣ ከጦርነት ድባብ በመውጣት ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በዚህ ረገድ የክልሉ መንግሥት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ መሰል የንግድና ኢንቨስትመንት ኹነቶች በሀገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ያስረዳሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ እንዲህ ዓይነት መድረኮች የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በየአካባቢው ያሉ እድሎችን ለማወቅ ያስችላቸዋል። በባለሀብቶች መካከል ትስስር ይፈጠራል። አንዱ አምራች ለሌላኛው የጥሬ እቃ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይልና የገበያ ምንጭ ይሆናል። መድረኮቹ የጥሬ እቃ አቅራቢ በሆኑ አርሶ አደሮች፣ በኢንዱስትሪዎችና በሸማቾች መካከልም የግብይት ትስስር ይፈጥራሉ።
በኤክስፖው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ድርጅቶችም ተሳትፏቸው እርስ በእርስ ለመተዋወቅና የገበያ ትስስራቸውን ለማስፋት እንደሚጠቅማቸው ይገልፃሉ። በ‹‹አምባሰል የንግድ ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የግብይት፣ የጥናትና ማስታወቂያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መዝገበቃል አየለ፣ በኤክስፖው ላይ መሳተፋቸው ድርጅታቸው የሚያቀርባቸውን ምርቶችና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማስተዋወቅና ለሽያጭ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ መሰል መድረኮች ምርት አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት እና ንግድን ለማነቃቃት ያግዛሉ። ‹‹በደብረ ብርሃኑ ኤክስፖ መሳተፍ በአካባቢው ያለውን አቅምና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ለመመልከት ይጠቅማል፤በአካባቢው ያሉትን ክፍተቶች ለመታዘብና በቀጣይ በንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ለመሰማራት ያለውን መልካም እድል ለማጤን ያስችላል›› ይላሉ። አቶ መዝገበቃል ከዚህ ቀደምም መሰል ኤክስፖዎች ላይ ተሳትፈው እንደሚያውቁ አስታውሰው፣ ተሳትፏቸው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እንዳስተዋወቃቸውና የሥራ ግንኙነታቸውን ለማስፋት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
የ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ›› የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርና የቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰጠኝ እንግዳው፣ ‹‹በላይነህ ክንዴ ግሩፕ›› በኤክስፖው ላይ ሲሳተፍ ምርቶቹንና አገልግሎቶቹን እያስተዋወቀና እየሸጠ እንደሆነ ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ የቅባት እህሎችን ጨምሮ ብዙ የግብርና ምርቶችን፣ በተለይም ሰሊጥና ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለተከታታይ 10 ዓመታት ተሸላሚ የሆነና የበርካታ ዓመታት ልምድ ያለው በመሆኑ በዚህ መድረክ ላይ መሳተፉ ከሌሎች ታላላቅ ተቋማት ጋር ለመተዋወቅና ልምዱን ተጠቅሞ ውጤታማ የሆነ የጋራ ስራ ለማከናወን መልካም አጋጣሚ ይፈጥርለታል።
ኤክስፖው ከሀገር በቀል ተቋማት በተጨማሪ የውጭ አምራቾችና የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች የተገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ አካባቢው ለመሳብ እድል የሚፈጥር እንደሆነ በመግለፅ፣ ኤክስፖው ለደብረ ብርሃንና አካባቢው ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያመጣ አቶ ሰጠኝ ይናገራሉ።
በ‹‹ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የሽያጭ መሃንዲስ የሆኑት አቶ ዘላለም ልይህ በበኩላቸው፣ የደብረ ብርሃኑ ኤክስፖው ‹‹ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ››ን ከዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት ጋር እያገናኘውና እያስተዋወቀው እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም የድርጅቱን የገበያ ትስስር ያሳድገዋል ይላሉ። ኤክስፖው ለተሳታፊ ድርጅቶች ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ ለደብረ ብርሃን ከተማ ስለሚኖረው ፋይዳ ሲናገሩ፣ ‹‹ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝና በርካታ ኢንዱስትሪዎች ያሉባት ከተማ በመሆኗ ኤክስፖው በከተማዋ መዘጋጀቱ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ያበረታታል። ከተማዋ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንድታገኝም ያስችላታል›› ይላሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015