ዓይኖቼ አያዩም ብርሃን የላቸው
በልጅነቴ ድሮ አጥቻቸው
ልቤን ተሰማው እንግዳ ነገር
ምርኩዝ ይዤ ነው የሚያውቀኝ ሀገር
ዓለም ታየቺኝ ባንቺ ውስጥ ሆና
በፍቅር ኩራዝ በላምባዲና እንዲል ቴዴ አፍሮ በሙዚቃው ለአይነ ስውራን የፍቅር፣ የእውቀት ላምባዲና የሆነው ትምህርት ቤት መከፈቱን ስንሰማ ወደዚያ ተጓዝን። ይህ የልጅነት ዓይኖቻቸውን ብርሃን ያደረገላቸው ትምህርት ቤት ሁለት ነገሮችን እንደሀገር የያዘ መሆኑን አውቀናል። የመጀመሪያው በየአቅጣጫው እንዳጣራነው የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት በሀገር ደረጃ በመዋዕለ ሕፃናት ደረጃ የለም። እናም የመጀመሪያው ሆኖ የመጀመሪያውን ተስፋ እየሰጣቸው ይገኛል።
እስከዛሬ ባለው ሁኔታ አይነ ስውራን ትምህርት የሚያገኙት እንደ እኩዮቻቸው በአራት ዓመት እድሜያቸው ገብተው አይደለም። ከፍ ካሉ በኋላ በአዳሪ ትምህርት ቤት አለያም በአንደኛ ደረጃ በአካቶ ትምህርት መልኩ ነው። ይህ ደግሞ በልጅነታቸው የሚያገኙትን እውቀት ሳያገኙ እንዲያልፉ ያስገድዳቸዋል።
በመዋዕለ ህጻናቱ ከመከፈት ብቻቸውን ሆነው በሚፈልጉት መልኩ እየተማሩም በመሆኑ ተስፋቸው እየለመለመላቸው ነው። በእርግጥ ትምህርት ቤቱ ለሁሉም ተደራሽ፤ ሁሉንም አይነ ስውራን ሕፃናትን የሚያስተናግድ አይደለም። ምክንያቱም ገና ጀማሪ፤ በቁሳቁስ ያልተሟላ ነው። በዚያ ላይ ተስፋን በሰነቁ እናቶች፣ በተቸገሩና ልጆቼን የት ላስገባና ላስተምራቸው ብለው በተንከራተቱና በተጨነቁ ወላጆች አማካኝነት የተመሰረተ ስለሆነ ከእነርሱ አልፎ ሌሎችን ለማስተናገድ አይቻለውም። ሆኖም አንድ ቀን ግን ለሁሉም አይነ ስውራን እንደሚደርስ ይታመናል። እንደሀገርም ለህጻናት አይነ ስውራን ዕውቀት የሚያስጎበኙ መዋዕለ ህጻናት እንዲበራከቱ በር ይከፍታል የሚል እምነት ያጭራል።
መስራቾቹ አምስት እናቶች ሲሆኑ፤ ከቦርድ አመራሮች ጋር ሲደመሩ ሰባት ናቸው። ነገር ግን እንደ ጅማሮ በጥሪ ሂደት ላይ ይገኛሉ። ከ37 በላይ ልጆችን በትምህርት ቤቱ ተቀብለው ያስተናግዳሉ።
የአመሰራረቱ መነሻ በበጎ አድራጎት ድርጅት ስም ነው። ቪዢን የአይነ ስውራን በጎ አድራጎት ድርጅት በሚል የተለያዩ ሥራዎችን ተቀራርበው በሚሰሩበት ጊዜ ይህ ሀሳብ በውስጣቸው አቃጨለ። የቤታቸው ጎዶሎ ደግሞ ይበልጥ ጠንክረው እንዲሰሩበት አደረጋቸው። በተለይም በልጆቻቸው ምክንያት በቤታቸው የሚቀመጡ እናቶች ብዙዎችን ያሳስባቸው ነበር። እናም አንድ ቀን ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ ልጆቻችን ለምን መማሪያ ያጣሉ፤ ለምንስ እኛ ከቤት ወጥተን ተጨማሪ መስራት አንችልም በሚል ተነሱ።
እርሳቸው በሙያቸው ኢንጅነር ቢሆኑም እንደልባቸው ሁለቱን አይነ ስውራን ልጆቻቸውን ትተው መስራት አይችሉም። በዚያ ላይ ለእነዚህ ልጆች በእድሜያቸው የሚማሩበት ትምህርት ቤት ቢፈልጉም የለም። እናም አቋም ይዘው ሥራውን ለመጀመር ብዙ ጓደኞቻቸውን ወደማማከሩ ገቡ። በቀላሉ ማድረግ ግን አልቻሉም። የሚያገኙትም ምላሽ እንደጠበቁት አልሆነላቸውም። ገሚሱ ባይሞክሩት እንደሚሻል ይነግሯቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ መንግስት ያልቻለውን እንዴት በእናንተ አቅም ትችሉታላችሁ የሚሉ ተስፋ አስቆራጭ ሃሳቦች አቅርበውላቸዋል። ጥቂቶች ደግሞ መልካም ነው ለእኛ ባይሆን ለልጅ ልጆቻችን ይደርሳል ይላል። ሆኖም ተስፋ ያልቆረጡት ወ/ሮ ትዕግስት ጉዟቸውን ወደፊት ቀጠሉ።
ልጆቻችን መውደቂያ ማግኘት አለባቸው፤ በእውቀት እንደሌሎች እኩዮቻቸው መጎልበት ይገባቸዋል ሲሉም ከድርጅት ሥራቸው በተጓዳኝ ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም የእያንዳንዱን ደጅ አንኳኩ። የተወሰኑት በራቸውን ከፈቱላቸውም። በዚህም ቪዥን የአይነ ስውራን ትምህርት ቤትን በ2014 ዓ.ም ኅዳር ላይ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ትምህርት ቤቱን በዳሬክተርነት እየመሩም ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
አንድ የትምህርት ተቋም ሲመሰረት ማሟላት የሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች አሉት። አንዱ የሥርዓተ ትምህርት ጉዳይ ሲሆን፤ ትምህርቱ እንደ ሀገር የተጀመረ ስላልሆነ የተሰጣቸውን እውቅና መሰረት አድርገው ማለትም ትምህርት ቢሮን የትምህርት ስርዓቱን በምን መልኩ እንደምናስኬደው ጠይቀን የተባለውን ለመተግበር ሞክረናል። ይህም የመጀመሪያ በመሆኑ በአዲስ መልኩ እስኪጀመርና አዲስ ካሪኩለም እስኪበጅለት ድረስ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ስነ ዘዴ ተጠቀሙ የሚል ነው። እናም በመደበኛ የትምህርት ስነ ዘዴ ጀምረው ከተለያዩ አካላት ተሞክሮዎችን በመውሰድ እያስተማሩ ይገኛሉ። በተለይ የውጭ ሀገራት ተሞክሮችን በአግባቡ ተጠቅመውበታል።
የማስተማር ስነ ዘዴያቸው እንደ መደበኛው የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት ነው። አይነ ስውር ናቸው ብለን ብሬል ትምህርት ላይ ብቻ አናተኩርም። ምክንያቱም ብሬን ማንበብና መጻፍ እውቀት አይደለም። ማንም ከተማረው ሊለምደውና ሊተገብረው የሚችል ነው። ስለሆነም ከዚያ ባሻገር ያሉ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ይደረጋል። ምክንያቱም ይህ ካልሆነ ከዚህ ሲወጡ በእጅጉ ይጎዳቸዋል። በአካቶ ትምህርት እንኳን መቀጠል አያስችላቸውም። የመምህራን ብቃት ጉዳይም እንዲሁ አንዱ መስፈርት ነውና በእነርሱ ትምህርት ቤት የተቀጠሩት አምስት መምህራን የልዩ ፍላጎት የትምህርት መስክ ተመራቂዎችን አድርገዋል። ደረጃቸውም ከዲፕሎማ እስከ ዲግሪ የደረሰ ነው።
‹‹ልጆቼ ሄራንና ሶልያና የማየት ችግር እንዳለባቸው የታወቀው ገና ዓመት ሳይሞላቸው ነው። እናም የት እንደማስገባቸው እያሰብኩ ቆየሁ። እንደእኔ የተጨነቁትንም ሳማክር ጭንቀታችን መፍትሄን ወለደ። ጠንካራ ሀሳቦችን ወደማመንጨቱ ገባንም። ልጆቻችንን በመጠቀም በሶሻል ሚዲያ እንቅስቃሴ ጀመርን። ለዚህ ደግሞ ዶንኪቲዩብ እጅግ በጣም አግዞናል። አንዳንድ በጎ አድራጊ ግለሰቦችን ከጎናችን እንደሆኑ ቃል ገቡልን። በእነርሱ ብርታትም ትምህርት ቤቱን ከፈትነው። ብዙ ርቀትም ተጓዝን›› የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ትምህርቱን ሲጀምሩ 31 ተማሪዎች ተቀብለው ማስተማር መጀመራቸውን ይናገራሉ። ሆኖም አሁን በመከታተል ላይ ያሉት 18ቱ ብቻ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቱ አንድ ቦታ ላይ ጀሞ አካባቢ ብቻ ነው። ከየአቅጣጫው የሚመጡ ልጆች ደግሞ ይህንን እድል መጠቀም አልቻሉም። በጣም ርቀት አለው። ይህም ቢሆን ቋሚ ገቢ ስለሌለን የአንድ ልጅ ወጪን በመሸፈንና የቤት ኪራያችንን በመሸፈን በጎ አድራጊ ግለሰቦች በመደገፋቸው ነው ዛሬ ላይ የቆምነው። እናም አሁንም የብዙዎች እገዛ ያስፈልገናልና ይዩን ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
የሕጻናት ህልም ገደብ አልባ ነው። ፍላጎታቸውም የተለያየ ነው። ይህንን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ በተለያየ መልኩ ማገዝ ያስፈልጋል። ለአብነት ከህክምና ተቋማት ጋር አብሮ መስራት። ትንሽ እገዛ ካገኙ ማየት የሚችሉና ተስፋቸውን መኖር የሚችሉ ልጆች ይኖራሉ። ህጻናቱ ለነገ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ የህክምናና የስነልቦና አማካሪም ያስፈልጋቸዋል።
ትምህርት ቤቱ ብዙ ህልምን ሰንቆ የተነሳ ነው። በመዋዕለ ሕፃናት አልፎ እስከ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የመክፈት ርዕይ አለው። ደረጃ በደረጃ መንግስት የሚያግዘው ከሆነ ለሁሉም አይነስውር ሕፃናት መድረስ ይፈልጋል። አሁንም የማህበረሰቡ ቤት እንደሆነ ነው የሚታሰበው። ምክንያቱም የቆመው በእነርሱ ስለሆነ። ጀማሪ በመሆኑ ገደበው እንጂ ሁሉን አሳታፊ ማድረግን ይሻል። ለዚህ ግን የሚመለከተው አካል ሁሉ ሊያግዘው ይገባል። የመጀመሪያው ከየቤት ኪራይ ነጻ የሚወጣበትን መንገድ የሚመለከተው አካል ሊፈታለት ይገባል። ከዚያ ደግሞ እንደ አይነ ስውርነታቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች ያስፈልጋቸዋልና በተቻለ መንገድ ለማሟላት ሁሉም መተጋገዝ አለበት።
ተቋሙ የመስራቾች ብቻ ሆኖ እንዳይቆይ በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ሊሰራበት ይገባል። ምክንያቱም መንግስት መጀመር የነበረበትን ተግባር ነው ግለሰቦች ዳዴ እንዲል ያደረጉት። እናም ማንም ሰው አይነስውር ልጅ ሊኖረው ይችላልና ለእድሜያቸው የሚመጥን ትምህርት ቤት እንዲኖራቸው መጀመሪያ መንግስት ከዚያም ግለሰቦች ተደጋግፈው ይህንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ ወይዘሮ ትዕግስት።
ትምህርት ቤቶች የወደፊቱን ሕይወት የምንቀይስበት፤ የመጀመሪያዎቹን ፊደላት የምንለይበት ተቋም ነው፤ አይነስውራን የሀገር ተስፋ እንዲሆኑ የምናደርግበትም ነው። ስለዚህም የመንግስት ተቋማት ማለትም ትምህርት ሚኒስቴርና ትምህርት ቢሮዎች ለዚህ ፈርቀዳጅ ትምህርት ቤት የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል። ለምሳሌ አስተማሪዎችን በማሰልጠን፣ መምህራንን በመመደብና የተለያዩ ለአይነ ስውራን የሚሆኑ ግብዓቶችን በመስጠት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ።
የመዋዕለ ሕፃናቱ መቋቋም ለእናቶች ልጆቻቸውን በእቅፉ ስላደረገላቸው ተጨማሪ ሥራ እንዲሰሩና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያዳብሩ አግዟቸዋል። በዚያ ላይ ልጆቻቸው እውቀትን ሸምተው በስነልቦና ጎልብተው ከቤት ሲደርሱ ደስተኛ እየሆኑላቸው ነው። ነገር ግን በአላቸው መጠነኛ ገንዘብ ብዙ ርቀት ቢጓዙም ቀጣይነቱ ያሳስባቸዋል። ዛሬ ተከፍቶ ነገ እንዳይዘጋ ስጋት አድሮባቸዋል።
ትምህርት ቤቱ እንደ ጀማሪነቱ መንግስት ማየት ካልቻለ በስተቀር ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው። ሕጻናት በመሆናቸው ልዩ እንክብካቤን ይሻሉ፤ ከዚያም ባሻገር ብሎ አይነ ስውርነት ሲጨመርበት ደግሞ ከዚህ በላይ ብዙ ድጋፍ ይፈልጋሉ። በትምህርት ብቻ ቢነሳ እንደማንኛውም ተማሪ ደብተርና እስኪርብቶ ተገዝቶላቸው በቃ ተማሩ የሚባልበት አይደለም። በቦታም ደረጃ እንደማንኛውም ተማሪ በጠባብ ክፍልና ግቢ ውስጥ የሚማሩ ሊሆኑ አይችሉም። እንደፈለጋቸው የሚንቀሳቀሱበትና አቅጣጫን የሚለዩበት ሰፊ ቦታና ክፍል ያስፈልጋቸዋል።
አይነስውራን ተማሪዎች በአንድ መምህር ክትትል የሚደረግላቸውና የሚማሩም አይደሉም። አይነስውርነት እየነኩ ማስተማርን ይጠይቃል። ስለዚህም የመምህር ተማሪ ጥምርታው ከዚህ የተለየ መሆን አለበት። እናም አምስት መምህራንን ቀጥሮ ማስተማሩ በራሱ ወጪውን ከፍ ያደርገዋል። ከዚያም በተጨማሪ አይነ ስውር ሆነው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችም አሉና እነርሱን ለማገዝ አልተቻለም። ተጨማሪ ቴራፒ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ለጊዜው እየተሰራ ያለው አይነ ስውርነታቸው ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ነው። እናም ይህንን ያማከለ ትምህርት ለመስጠት ልዩ ቴራፒ የሚሰጡ አካላት ቢደግፉት ይላሉ መስራቿና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ትዕግስት።
አሁን በአሉበት ደረጃ በቃል የሚማሩትን ትምህርት አጠናቀው ወደ ተግባር እየገቡ ነው። ነገር ግን በግብዓት አለመሟላት ምክንያት ይህንን ለማድረግ ያስቸግራል። ምንም ተግባር ውስጥ የሚያስገባቸው ቁሳቁስ የለም። እናም በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሆኑም ያስረዳሉ። ለምሳሌ፡- ስሌት፣ ስታይለስን የመሳሰሉ መጻፊያዎቹ እና የተለየ ወረቀት ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም ትምህርት ቢሮና ትምህርት ሚኒስቴር ቢያየንና ቢያግዘን ይላሉ ወይዘሮ ትዕግስት።
አይነስውር ተማሪዎች በስነልቦናም ከአሁኑ ጀምሮ መታገዝ አለባቸው። ምክንያቱም ከዚህ ሲወጡ የሚያጋጥማቸው ነገር የተለየ ነው። በተለይም እንደ ሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ብዙ ነገሮች መሰናክል ይሆንባቸዋል። እናም የቻለ ሁሉ ማገዝ ይኖርበታል። በተለይ መንግስት ከመምህራን ስልጠናና ቅጥር ጀምሮ በብዙ መንገድ ማገዝ ቢችል መልካም ነው ባይም ናቸው። እኛም ጅማሮው መልካም ነውና ቀጣይነቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራ ለሀገር የሚተርፍ ሃሳብ ነውና ይህንን ፋና ወጊ ትምህርት ቤት ማገዝ ከሁሉም አካላት ይጠበቃል የሚለው መልዕክታችን ነው። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም