ሀገሮች በመዲናዎቻቸው ለተለያዩ ጉባኤዎች የሚመጥኑ አዳራሾችን፣ ከእነሱ ጋር የሚራመዱ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሟላት አዳራሾቹንና ሌሎች መሰረተ ልማቶቹን ለጉባኤ ወይም ለንግድ ትርኢት ማስተናገጃነት እያወሉ ይገኛሉ:: እነዚህ መሰረተ ልማቶች ከዚህም የላቀ ፋይዳ እያበረከቱ ይገኛሉ፤ ሀገሮች በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ::
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ባለጸጋ፣ የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ እና የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለስሟ የሚመጥኑ እና ከታሪኳ ጋር የሚስተካከሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የንግድ ትርዒት ማሳያ መሰረተ ልማቶችን፣ የመዝናኛ አማራጮችን እንዲሁም የነዋሪዎችን የዕለተ ዕለት እንቅስቃሴ የሚያዘምኑና ታሪክን ሰንደው ለትውልድ የሚያስተላልፉ ፕሮጀክቶችን በሚመጥናት ልክ አልገነባችም የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘርባት ቆይታለች:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከተማዋ ይህን ታሪኳን ለመቀየር በከፍተኛ ርብርብ ውስጥ ትገኛለች::
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ስሟንና ዝናዋን የሚመጥኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ:: በመዲናዋ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ከሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ሲኤምሲ አካባቢ እየተገነበ የሚገኘው የአዲስ አፍሪካ የንግድ ትርዒትና ኮንቬንሽን ማዕከል አንዱ ነው:: ግንባታው የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ሲሆን ግንባታውን በ2012 ለማጠናቀቅ ታቅዶም ነበር ወደ ግንባታ የተገባው::
የማዕከሉ ፋይዳዎች ምንድን ናቸው? በአሁኑ ወቅት የማዕከሉ ግንባታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ግንባታው ለምን ተጓተተ? ግንባታውን ለማፋጠን ምን እየተሰራ ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል አክሲዮን ማህበር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አባተ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል::
የማዕከሉ ፋይዳዎች
የማዕከሉ ፋይዳ በጣም ሰፊ ነው:: ፋይዳዎቹን ከፋፍሎ ማየት ያስፈልጋል:: ከትልቁ ፋይዳ ለመጀመር ሀገራዊ ፋይዳውን እናንሳ:: ሀገራዊ ፋይዳው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደታች የማለት ሁኔታዎች ቢኖሩበትም፤ እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ ነው:: ይህ ኢኮኖሚ እንደዚህ አይነት መሰረተ ልማት ይፈልጋል:: ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስተዋወቅ፣ የእነሱን መረጃ ለመስጠት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ፣ የማርኬቲንግ ስራ ለመስራት፣ በውጭ ሀገራት ያሉትን እና ሀገር ውስጥ ያሉትን የንግድ ተዋናዮችን ለማገናኘት እንዲህ አይነት ማዕከል ያስፈልጋል::
ሁለተኛው ፋይዳው ይህ ስራ በሚሰራበት ጊዜ የስብሰባ አዳራሾች አሉ:: ሀገሪቱ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ነች:: የህዝብ ብዛቷም ከ110 ሚሊየን በላይ ነው:: ብዙ አይነት ስብሰባዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳሉ:: ስለዚህ የስብሰባ አደራሾች ያስፈልጋሉ::
እስካሁን ድረስ እንዲህ አይነት የስብሰባ ማዕከል በሀገሪቱ ውስጥ የለም:: በሀገሪቱ ውስጥ ግን እንዲህ አይነት የስብሰባ ማዕከል ፍላጎት አለ:: ፋይናንስ ተቋማት እና የአክሲዮን ማህበሮች ዓመታዊ ስብሰባዎች ሲያደርጉ ሰፊ እና ዘመናዊ የመሰብሰቢያ ቦታ እጥረት እንዳለባቸው እየታየ ነው:: ዩኒቨርሲቲዎች ዓመታዊ የምርምር ጉባኤዎችን ማካሄድ ቢፈልጉ የስብሰባ ማዕከል ያስፈልጋል:: ይህ ማዕከል ተጠናቆ ስራ ሲጀምር በስብሰባዎች በሚገኘው ገቢ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል:: ቱሪዝሙ እንዲያድግም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፤ የስራ እድልም ይፈጥራል:: ከታክስና ከሌሎች ምንጮችም ገቢዎችን ማግኘት ይቻላል:: በአጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ ሀገራዊ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው::
ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ፋይዳ ቀጥሎ ኢንቨስት ላደረጉ ሰዎች ከፍተኛ ፋይዳ አለው:: ይህ ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ዘርፍ እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎች እና ሼር ሆልደሮች ከኢንቨስትመንታቸው ከፍተኛ ትርፍ ያገኛሉ::
በስብሰባም ሆነ በንግድ ትርዒቶች በሚደረጉ ተሳትፎዎች ለቀጣናዊ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት በቀጥታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ የሆነ ተቋም ነው:: የማዕከሉ አካባቢም የተለያዩ አገልግሎቶች ይሟሉለታል:: የእሳት ማጥፋት አገልግሎት፣ የህክምና አገልግሎት፣ ከጸጥታ ጋር የተገናኘ ስራ ይሰራበታል:: ከማህበራዊ ጉዳይ እና ከጉምሩክ፣ እንዲሁም ከኢሚግሬሽን እና የዜግነት ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ስራዎችም ይሰሩበታል:: ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳዎች ጋር የተገናኙ ስራዎችም ይሰራበታል:: እነዚህ ስራዎች ሁሉ ሲሰሩ የሚያስገኙት ጥቅም አለ:: ያለ ጥቅም የሚሰራ ስራ የለም::
የማዕከሉ ግንባታ በምን ደረጃ ይገኛል?
አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና አግዚቢሽን ማዕከል ግንባታው የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው፤ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የተቀደውም በ2012 ዓ.ም ነበር:: የማዕከሉ ግንባታ ሶስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከሚካሄዱ የግንባታ ስራዎች መካከል ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለት ሁለገብ የንግድ ትርዒት አዳራሾች ግንባታ፣ ኮሜሪሻል ህንጻ፣ ኮንኩርስ ህንጻ የተሰኘ ሌላ ህንጻ እንዲሁም የድልድይ ላይ ሬስቶራንት ይጠቀሳሉ::
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 70 ከመቶ ተጠናቋል:: በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተካተተው የኮሜርሻል ህንጻ ግንባታ ተጠናቋል:: በአጭር ሳምንታት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል::
የአዳራሾች ግንባታም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል:: ይህ ፕሮጀክት በ2012 ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ፤ 2014 ላይ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ነበር:: በተለያዩ ምክንያቶች በ2014ም ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ አሁን ደግሞ በ2016 ኅዳር ወይም ታኅሳሣሥ ወር ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ርክክብ ለማድረግ እየተሰራ ነው::
ሁለተኛው ምዕራፍ አምስት ሺ ሰው የሚይዝ መሰብሰቢያ አዳራሽ እና ሌሎች መሰብሰቢያ አዳራሾችን አካቷል:: ይህንንም በ2014 ለማጠናቀቅ ነበር የታቀደው:: የመጨረሻው ምዕራፍ ወይም ሶስተኛ ምዕራፍ የሚባለው ትልቅ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የያዘ ባለኮከብ ሆቴል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በ2016 ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡
ፕሮጀክቱን በተያዘው እቅድ መሰረት ለምን ማስኬድ አልተቻለም?
ፕሮጀክቱ በተለይም የመጀመሪያው ምዕራፍ በተያዘለት እቅድ መሰረት ሊሄድ ያልቻለበት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ:: አንዳንዶቹ ምክንያቶች ከአቅም በላይ የሆኑ ናቸው:: የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ፕሮጀክቱ እንዲጓተት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል:: የስራ ተቋራጩ የቻይና ኩባንያ በመሆኑ በቻይና የኮቪድ ፕሮቶኮል ስትራክቸራል የሆኑ ምርቶች የሚያመርተው ፋብሪካ አጭር ለማይባል ጊዜ ተዘግቶ ነበር:: በኢትዮጵያም በኮቪድ 19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ መዘጋጋት ባይኖርም የሰራተኛ ቁጥር መቀነስ የመሳሰሉ እርምጃዎች ተወስደዋል:: ሁለቱ ነገሮች ሲዳመሩ ግንባታውን አጓተውታል::
ፕሮጀክቱ እንደ ተጀመረ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከውጭ ገንዘብ አንጻር ያለው የመግዛት አቅም በ15 በመቶ ቀንሶ ነበር:: ይህ ደግሞ ዋጋ ጭማሪን አምጥቷል:: ዋጋ ጨምሩ አንጨምርም የሚል ክርክር ጊዜ ወስዷል:: ይህ ሁለተኛው ምክንያት ነው:: ሶስተኛው ምክንያት ከግንባታ እቃ ጋር ይያያዛል:: በ2011 አካባቢ ላይ በተለይም በሀገሪቱ የብረት እጥረት አጋጥሟል:: ይህን ብረት ከውጭ ሀገር ማስገባት የግድ ነበር:: ብረት ከውጭ ማስመጣት የራሱ ሂደት አለው:: ፍቃድ መጠየቅ፣ ገበያውን ማፈላለግ፣ እቃውን መግዛት፣ ማጓጓዝ እና ሀገር ውስጥ ማስገባቱ አጭር የማይባል ጊዜ ፈጅቷል::
በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የዋጋ መናር ለፕሮጀክቱ መጓተት የራሱን ሚና የተጫወተ አራተኛው ምክንያት ነው:: በሀገሪቱ የዕቃ ዋጋ በሰዓታት ውስጥ እየጨመረ ይገኛል:: የስራ ተቋራጩ ይህንን ሰበብ በማድረግ ፕሮጀክቱን አጓቷል:: የስራ ተቋራጩ አንዴ ዋጋ መናሩን፣ አንዴ የዋጋ ጭማሪ መኖርን፣ አንዴ እቃው ጠፍቷል የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ፕሮጀክቱ እንዲጓተት አድርጓል::
ከተጠቀሱት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ተደማምረው እና አንዱ ምክንያት ሌላውን እያጠናከረ በመጀመሪያ በተያዘው እቅድ መሰረት ፕሮጀክቱን በ2012 መጨረስ አልተቻለም:: ከዚያ በኋላ በ2014 ለማጠናቀቅ የእቅድ ማሻሻያ የተደረገ ቢሆንም በ2014 ማጠናቀቅ አልተቻለም::
ከተዘረዘሩ ምክንያቶች በተጨማሪ የግንባታ ስራ በተፈጥሮው በታቀደው መሰረት የሚጠናቀቅ አይደለም:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት አብዛኛዎቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘው እቅድ መሰረት ሲጠናቀቁ አናይም:: ይህን የመጓተት ባህሪ የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዕትና ኮንቬንሽን ማዕከል ፕሮጀክትም ወርሷል::
በ2016 ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለ ጥረት ምን ይመስላል?
ፕሮጀክቱን በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው:: ከተደረጉት ጥረቶች መካከል ከስራ ተቋራጩ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር አማካኝነት ከቻይና ኤምባሲ ከሚመለከታቸው ስራ ክፍሎች እንዲሁም ከተቋራጩ ጋር ያለሰለሰ ውይይት በማድረግ አሁን ኩባንያው ባህሪውን አስተካክሏል::
ከዚህ ባሻገር ኮቪድ 19 ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በቻይናም ሆነ በኢትዮጵያ በመሻሻላቸው የነበሩት የፕሮቶኮል አፈጻጸሞች ላይም መሻሻል ታይቷል:: በዚህ ምክንያት ለግንባታው የሚያስፈልገው ስትራክቸር የሚባል ግብዓት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ የግንባታ ቦታ ላይ ደርሷል:: ትንሽ ነው የሚቀረው:: ግንባታውን ማጠናቀቂያ የፊኒሽንግ እቃዎች ሳይቀሩ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል:: ብዙዎቹም ግንባታው ቦታ ላይ ይገኛሉ::
መንግስት በተለይም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ክትትል እያደረጉ ነው:: አመራሩ በክትትሉም ሆነ በሱፐርቪዥኑ እያገዘ ነው:: አሁን የተሻለ ሁኔታ እና የተሻለ የግንባታ አፈጻጸም ነው ያለው:: የሲሚንቶ እና የሌሎች የቁሳቁስ ችግሮችም ተፈተዋል:: ሲሚንቶ ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር ለመፍታት ለማዕከሉ ቅድሚያ እንዲሰጥ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እና እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል::
ችግሮችን ለይቶ በማውጣት እንደገና ከልሰን ተፈራርመን የተጠየቀውን ቀንና ጊዜ ጨምረን በ2016 ለማጠናቀቅ፤ ከተቻለ ደግሞ ከ2016 በፊት 2015 ማብቂያ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው:: ክትትሉ ከመቼውም ጊዜ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል:: ከኮመርሻል ህንጻ የተወሰነው ህንጻ ተጠናቆ ሰሞኑን ስራ ይጀምራል:: የኤግዚቢሽን አዳራሾቹ ስቲል ስትራክቸር የሚባለውን የመበየድ፣ እንዲሁም የግድግዳ ስራዎች ተጀምረዋል፤ ጣራዎቹም ለብሰዋል:: በ2016 ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እውን ለመሆን ተቃርቧል::
የማዕከሉ የአክሲዮን ባለቤቶች እና የአክሲዮን ሽያጭ
ማዕከሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 987 ባለአክሲዮኖች አሉት:: ትልቆቹ ከሚባሉት የአክሲዮን ባለቤቶች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስድስት የልማት ተቋማቱ አማካኝነት ከፍተኛ የአክስዮን ባለቤት ነው:: የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት፣ የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ አዋሽ ኢንሹራንስ፣ አቢሲንያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ድርጅት፣ ጸሃይ ኢንሹራንስ ደርባ እና ሌሎችም ባንኮችና ኢንሹራንሶች ባለአክሲዮን ናቸው::
የተለያዩ ግለሰቦችም የማዕከሉ ባለአክሲዮኖች ናቸው:: ውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ከባለአክሲዮኖች መካከል ይጠቀሳሉ:: ከዲያስፖራዎች መካከልም በማህበር ተደራጅተው አክሲዮን የገዙትን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: በመካከለኛው ምስራቅ፣ ካናዳ፣ እና አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦችም ባለአክሲዮን ናቸው::
በኢትዮጵያ ውስጥ ስመጥር የሆኑ የታወቁ ተቋማትም በቅርቡ ባለአክሲዮን ይሆናሉ:: ባለአክሲዮን ለመሆን በቅድሚያ መጠናቀቅ ያለባቸውን ነገሮችን ለማጠናቀቅ እየሰሩ ይገኛሉ:: በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንባታው መፋጠኑ፣ የማስተዋወቅ ስራዎች በመሰራታቸው እና በሌሎች ምክንያች እንዲሁም የመንግስት ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ በመቀጠሉ፤ ተጠናክሮ ከመቀጠሉ ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በወር ከሁለት እስከ አራት ጊዜ እየመጡ እየጎበኙ ያሉበት ሁኔታ ማእከሉ የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብ አድርገውታል:: የጎደለው እንዲሞላ መመሪያ እየሰጡ ነው:: ፋይናንስ የማሰባሰብ ስራ ወይም የአክሲዮን ሽያጩ አሁን ችግር አይደለም:: ከማንኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጭ እየተካሄደ ነው::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም