ቀኑ ፀሃያማ ነበር። ደስ የሚል ጠዋት። እለቱ የአመቱ ቅዱስ ገብርኤል የሚነግስበት ቀን ስለነበር ህዝበ ክርስቲያኑ ያለውን ነጫጭ ልብስ ለባብሶ ታቦት ሳይወጣ ወደ ንግሱ ቦታ ለመድረስ ጠደፍ ጠደፍ ይላል። ታኅሣሥ 19 ቀን ጠዋት የልእልት እናት ባለቤቷን አቶ ሞገስን ወደ ስራ ሸኝተው ታቦት ሳይወጣ ለመድረስ እየተጣደፉ ወጡ።
የልዕልት እናት ወደ ደጅ ሲወጡ ልዕልትና ታላቅ እህቷ የጦፈ ጨዋታ ይዘው ነበር። ልዕልት ካየቻቸው አልቅሳ ከመንገድ ልታስቀራቸው እንደምትችል በማሰብ ከጨዋታ ሀሳብ ወጥታ ሳታያቸው በፊት በፍጥነት ማምለጥን ምርጫቸው አድርገዋል። የለበሱትን ነጠላ በደንብ ተከናንበው ቀስ ብለው ኮቴ ሳያሰሙ በር ከሌለው የሾህ አጥር ግቢ ወጥተው ወደ ቤተክርስቲያን አቀኑ።
በጥድፊያ የረገጡትን ደጀ ሰላም ተሳልመው “አብሳሪው ቅዱስ ገብርኤል ልጆቼን ጠብቀልኝ፤ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውርልኝ…..” በማለት በመቀነታቸው የያዙትን የስለት ብር አውጥተው ሙዳየ ምፅዋት ውስጥ ጨመሩ። ከዛም በእልልታ ታጅቦ ከመቅደሱ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን እየዞረ ያለውን ታቦት በእልልታና በጭብጨባ አጅበው ቤተክርስቲያኑን መዞር ጀመሩ።
በሆታ የደመቀው የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል ላይ ሆነውም ግን ግማሽ ልባቸው ቤት ወደተዋቸው ልጆቻቸው ማሰብ አላቆሙም። ሀሳባቸውን መስብሰብ ቢሞክሩም አሁንም አሁንም ልጆቻቸው ወደ አይነ ህሊናቸው እየመጡ ሀሳባቸውን ሲሰርቋቸው “አባቴ ገብርኤል የልጆቼን ነገር አደራ…….” በማለት ደግሞ ወደ ዝማሬው መለስ አሉ። የእናት ሆድ ነውና ልባቸው ግን አላርፈ አላቸው። ጭንቅ ጭንቅ እያለም ልባቸው እረፍት ነሳቸው። ጸሀዩ ይሆን እያሉም ምክንያት መደርደራቸውን ግን አላቋረጡም።
ታናሿ ልእልት
አቶ ሞገስ ግርማ ለእናት ለአባታቸው ብቸኛ ልጅ ናቸው። በብቸኝነት ማደጋቸው ይሁን ሌላ ለልጆች ያላቸው ፍቅር ለየት ያለ ነው። ለወግ ማእረግ በቅተው ባገቡ በመጀመሪያው አመት ነበር ቆንጆ ሴት ልጅ ለመታቀፍ የበቁት። የመጀመሪያ ልጃቸውን ዓለም አሳየችኝ ሲሉ አለሜ ይሏታል። አለሜ ከተወለደች በኋላ ግን የልጅ ፍቅር ይሁን ጉጉታቸው… ልጅ ሳይወልዱ ሰባት አመታትን ይቆያሉ። “ እኔ አንድ ልጅ፤ ልጄ ደግሞ ብቸኛ ሆና ልትቀር ይሆን?” እያሉ በሚያወጡ በሚያወርዱበት ጊዜ ነበር የባለቤታቸው ማህፀን ዳግም ለምልሞ ልጅ ሊያሳቅፋቸው መሆኑን የሰሙት።
ደስታቸው ወሰን ያጣው አቶ ሞገስ የልዕልትን መወለድ ከበኩር ልጃቸው መምጣት በላይ ጓጉተው ይጠባበቁ ጀመር። ያኔ ነው ሁለተኛይቱ ሴት ልጅ ትንሿ ልዕልት የተወለደችው። በጣም የምታምር የምታሳሳ እንደስሟ ልዕልት የመሰለች ልጅን ወልደው ሳሙ። ደስታ በቤታቸው ገባ። ሁሌ ሳቅ ጨዋታ ሆነ። ቀን ቀንን እየወለደ ልዕልት አፈ ስትፈታ ጣፋጭ አንደበቷ የሚናፈቅ ጠረኗ ከልክ በላይ የሚናፍቅ ፤ ድክ ድክ ስትል ያያት ተመልካች አይን ሁሉ እሷን ከመከተል ውጭ ምንም አማራጭ የማትሰጥ ቆንጅዬ ልጅ ሆነች።
ይችን የሳር ቅጠሉ አይን ማረፊያ ልጅ በአንድ ክፉ ቀን በክፉ ሰው አይን ገባች። ልቡ ክፋት የሞላው ህፃንን በሀጢያት አይን የሚመለከት ርካሽ ሀሳብን ውስጡ ሞልቶ ይችን ለዓይን የምታሳሳ ህጻን ተጠጋት። አላፊ አግዳሚው ወዳጇ የሆነው ይች ልጅ ሰዎች ጉዳት ያደርሱብኛል ብላ ለማሰብ ሳትችል በፈገግታ ተጠጋችው። እንኳን ፈገግ ብላ እንዲሁም ልብ የሚሰረቅ የሆነ ምትሃት ያላት ወብ ህፃንን ጉንጯን አገላብጦ ሳማትና አብራት ከምትጫወተው ታላቅ እህቷ ነጥሎ ጣፋጭ ከረሜላ እንደሚገዛላት ነግሮ እጇን ይዞ ወደ ክፋት ማስፈፀሚያው ቦታ ሄደ።
አትጉደይ የተባለች የልእልት ቀን
የሶስት ዓመቷ ህፃን ልዕልት በድንገት ቀርቦ ስሟት እጇን ይዞ ከረሜላ ሊገዛላት የሚሄደው ሰው ስር ድክድክ እያለች በደስታ እየተፍለቀለቀች አንዴ ቀና ብላ እያየችው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሀሳቧ ስለሚገዛላት ብስኩትና ከረሜላ ብዛት እያሰላሰለች ከሰፈራቸው ራቅ ወዳለው ሱቅ ጉዟቸውን ቀጠሉ።
የሰላሳ አንድ ዓመቱ ግለሰብ ያሰበውን እኩይ ድርጊት ለመፈፀም የሱቁ ርቀትና የልእልት የትንንሽ እግሮች እርምጃ ያገደው ይመስል ከስሩ ቀስ ብላ ድክ ድክ የምትለውን ህፃን አንሰቶ ታቀፋት። ከዛም ከሩጫ ባልተናነሰ ፍጥነት ወደ ሱቁ ገሰገሰ። በሱቁ ደርሶ በፍጥነት ብስኩትና ከረሜላ ገዝቶ መልሱን እንኳን ሳይቀበል ወደ ሰዋራ ሰፍራ ፈትለክ አለ።
ባለ ሱቁም መልስ ሳይቀበለው የሮጠውን ግለሰብ ከተል ሲል በፍጥነት ወደ አንድ መታጠፊያ ሲገባ ተመለከተው። ሁኔታው ጥርጣሬ ስለፈጠረበት መለስ ብሎ ሱቁን በመዝጋት ተከተለው።
አቶ ሙላት ይርጋ ደስየ የተባለው ለልዕልት ከረሜላና ብስኩት የገዛው ግለሰብ በወልዲያ ልዩ ቦታው “አደንጉር” ከተባለው ስፍራ አዳዲስ ከተሰሩ ቤቶች ውስጥ እጇን ይዞ ገባ። እለቱ የገብርኤል ንግስ በዓል ስለነበረ በእለቱ ታቦት አስገብቶ የመጣው ህዝበ ክርስቲያን ዝክር በተደገሰበት ቤት መሽጎ ድጉሱን ይቋደሳል። አቶ ሙላት ዙሪያ ገባውን ሰው አለመኖሩን አይቶ አዲስ ከተሰራና ሰው መኖር ካልጀመረበት ቤት አስገብቶ መሬት ላይ ያስተኛታል።
ያ ብስኩትና ከረሜላ የገዛላት ደግ ሰው የፈለገው ነገር ስላልገባት ከታች ሆና በሷ አይን ከፊቷ የቆመውን ረጅም ሰው ትመለከታለች። ከቆመበት በርከክ ብሎ እንዳታለቅስ አፏን አፍኖ ህፃን ልእልትን ሊደፍር ሲል ባለሱቁና እሱ ያስከተላቸው ሰዎች ይደርሱበታል።
ባለሱቁ የሰውዬው ሁኔታ አላምር ሲለውና ልእልትን ከወላጆቿ እቅፍ ውጭ አይቷት ስለማያውቅ ሱቁን ዘግቶ በሩጫ ሰውየው ወደ ታጠፈበት አቅጣጫ ሲያቀና ነበር በመንገድ ያገኙት። ሰዎች ስለጉዳዩ ጠይቀው ዱላም ድንጋይም ይዘው ይከተሉታል።
ያኔ ነው እንግዲህ ህፃን ልእልት በክፉ አይኑ ከተመለከታት አውሬ ሊያድኗት የቻሉት። ልክ ሰዎቹ ቦታው ሲደርሱ እገሬ አውጪኝ ብሎ የተፈተለከው አቶ ሙላት በአንድ ያበረው ህዝብ በድንጋይ ውርወራና በቅዝምዝም ዱላ ጀርባውን እየደለቀ መሬት ላይ ይጥለዋል።
ከመሬት ላይ አንስተውም እየዳፉ ይዘው ለህግ አካል ያስረክባል። ፖሊሰም ተጠርጣሪው አቶ ሙላት ይርጋ ደስየን ይዞ ወደ ጣቢያ ይወስደዋል።
እናት ከሄደችበት መልስ
ሰላም አውለኝ ብላ ከልጆቿ ተደብቃ በማለዳ ደጀ ሰላም ረግጣ ታቦት አንግሳ “ደሞ ለከርሞው በሰላም አድርሰኝ” ብላ ነበር ከቤተክርስቲያን የወጣችው። ወደ ልጆቿ ልቧ የተንጠለጠለውን እናት ከቤተክርስቲያን ስትመለስ ያገኟት አንደ ወዳጇ “አፈር ስሆን…..እንደው በገብርኤል ይዤሻለሁ….አንድ ሲኒ ቡና በቁምሽ ጠጥተሽ ትሄጃለሽ” ብለው ወደ ቤታቸው ይወስዷታል። ቡናው ምሳው ሲባል ሳይታወቃቸው ጀንበር ታዘቀዝቃለች። ከዛም በፍጥነት ከሩጫ ባልተናነሰ እርምጃ ሜዳ ላይ ጥላ ወደ ዋለቻቸው ልጆቿ ገሰገሰች።
ለወትሮው ጎረቤቶቿ ልጆቿን አብልተው ሲደክማቸው አስተኝተው ይጠብቋት ነበር። ዛሬ ግን ሰፈሩ ጭር ብሏል። ልቧ መታ ወደ ቤቷ ስትጠጋ ማንም የለም። በድንጋጤ የምትይዘው የምትጨብጠው አጣች። ወደየ ጎረቤቱ ቤት ብትሮጥም አንድም የሰው ዘር ልታይ አልቻለችም። ግራ ገባት የምትይዘው የምትጨብጠው ጠፋ።
ድንገት ከማዶ አንድ የጎረቤት ልጅ እየሮጠ ወደሷ ሲመጣ ተመለከተች። ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ የሚለው ልጅ በተቆራረጠ አንደበት የሆነውን ሁሉ ነገራት። ጎረቤቶቿም ገሚሱ ሰውየውን ይዘው ወደ ህግ ቦታ ገሚሱ ደግሞ ልጅቷን ይዘው ሆስፒታል መሄዳቸውን ሰማች።
የሰማችውን ማመን ተሳናት። እንደ መጮህም እንደ ማበድም ቃጣት “ምነው አባቴ ገብርኤል፤ ነገሬህ ነግሬህ አሳልፈህ ሰጠህኝ” እያለች ልጇ አለች ወደ ተባለችበት ሆስፒታል ገሰገሰች። ሆስፒታል እንደደረሰች ልጇ ደህና መሆኗን ተመለከተች። ፈጣሪዋ ከለሎ ልጇን ከጉዳት ስለጠበቀላት አመሰገነች “የነገሩህን የማትረሳ ቸኩዬ አፌን አበላሸሁ በማለት” ይቅርታን ተማፅና ማን ደፍሮ የአይናን ማረፊያ ሊተናኮል እንዳሰበ ለመመልከት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አቀናች።
የፖሊስ ምርመራ
ዕድሜው ሰላሳ አንድ ዓመት ሲሆን ግለሰቡ ከእሱ ጋር ተቃራኒ ፆታ ያላትን የሶስት ዓመት ህፃን ልዕልት ሞገስን ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 11 ከ30 ሰዓት አካባቢ ከታላቅ እህቷ ጋር እየተጫወተች እንዳለ ቤተሰብ መስሎ በመጠጋት ጎንጯን አዟዙሮ በመሳም በወልዲያ ልዩ ቦታው “አደንጉር” ከተባለው ስፍራ አዳዲስ ከተሰሩ ቤቶች ውስጥ እጇን ይዞ ሰው ከማይኖርበት ቤት አስገብቶ ሊደፍር ሲል ሰዎች ደርሰው እጅ ከፍንጅ የያዙት ግለሰብ ላይ ፖሊስ ምርመራውን ይጀምራል።
ህፃኗንም ከወደቀችበት አንስቶ ወደ ወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይወስዳታል። በሆስፒታሉም ምርመራ ተደርጎላት ክብረ ንፅህናዋ ያለና በግራ በኩል የብልት ቆዳ መላጥ የደረሰባት መሆኑን በህክምና መረጃ ይረጋገጣል።
ፖሊስም የሰነድ ማስረጃዎችን፤ የአይን ምስክሮችንና የተከሳሽን ቃል በመቀበል ለአቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ ይመሰርታል። ክስ የቀረበበት ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን ክዶ ቢከራከርም ዓቃቤ ህግ ባቀረባቸው የሰው ምስክሮችና የህክምና ማስረጃ ጥፋተኝነቱ ሊረጋገጥ ችሏል።
ውሳኔ
አቃቤ ህግም ፖሊስ አጠናክሮ የላከለትን መረጃና ማስረጃ ተመልክቶ በከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መሰርቶበታል።
በወልዲያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀን ቀጥሯል። በቀነ ቀጠሮውም ተከሳሽ መከላከያ እንዲያቀርብ የተጠየቀ ቢሆንም ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለቱ የወልድያ ከተማ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ ተከሳሽን ያስተምራል ሌላውን ማህበረሰብ ያስጠነቅቃል ያለውን ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚሁ መሰረት የወልዲያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሶስት አመቷን ህፃን ልዕልት ሞገስን የመድፈር ሙከራ ያደረገው አቶ ሙላት ይርጋ ላይ የ16 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት አሳልፏል። መረጃውን ያገኘነው ከወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን ድረገፅ ላይ ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም