እነዛ ሁለት ዓመታት ለእርሷ የጭንቅ ግዚያት ነበሩ። ሁለት ዓመታት በብርቱ ተፍትናለች። በህይወትና በሞት መካከልም ነበረች። የጦርነትን አስከፊ ገፅታ በቅርበት ተመልክታለች። ጦርነት ያመጣውን ጣጣም ቀምሳለች። በዚሁ ጦርነት ጦስ ተርባለች፣ ተጠምታለች፣ ታርዛለች። በጦርነት ምክንያት ካሳላፈችው መከራና ፍዳ አንፃር ዛሬ ላይ ሆና እነዛን ግዜያት ስታስባቸው እውነት አይመስላትም። ያ የመረበሽና የድንጋጤ ስሜት አሁንም አለቀቃትም። አሁን የተገኘው ሰላም ግን ቀስ በቀስ ወደቀድሞው ሁኔታዋ እየመለሳት የመጣ ይመስላል። ውስጧም ተረጋግቶ የወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ታይቷታል።
ወጣት ቅሳነት ዳኘው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ናት። የዛሬን አያድርገውና ከጦርነቱ በፊት እንደማንኛውም የመቀሌ ወጣት ስራ ነበራት። በአክሱም ሆቴል በመስተንግዶ ሰራተኝነት ተቀጥራ ራሷን ታስተዳድር ነበር። ነገር ግን በሕወሓትና በመንግስት በኩል በተፈጠረው ጦርነት ከስራዋ ተፈናቅላለች። ባለፉት ሁለት ዓመታትም ያለ ስራ ቆይታለች። በዚህ ጦርነት ምክንያት በሁለቱ ዓመታት እንደልብ መንቀሳቀስ፣ መብላት፣ መጠጣትና መልበስ አልቻለችም።
ጦርነቱ መቀሌ አቅራቢያም እደመደረጉ አስከፊነቱን በቅርበት አይታለች። የምትበላውን እስከማጣትም ደርሳለች። በተለይ ደግሞ ልጅ ያላቸው፣ የመንግስት ሰራተኞችና ተቀጥረው የሚሰሩ ገንዘብ ለማግኘት ስለሚቸገሩ የሚበሉትን ለመግዛት እንኳን ሲቸገሩ ተመልክታለች። እርዳታም ቢሆን ከስንት አንዴ የሚመጣና በቂ ባለመሆኑ እርሷም ሆኑ ሌሎችም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነበሩ። ከዚህ አንፃር የነበረው ሁኔታ ፈታኝ ነበር።
ከዚህ ሁሉ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ መንግስትና ሕወሓት ወደሰላም መምጣታቸው በእጅጉ እንዳስደሰታት ትገልፃለች። ሁለቱ ኃይሎች ይህን የሰላም ስምምነት ቀደም ብለው ቢያደርጉ መልካም ቢሆንም አሁንም ግን እንዳልረፈደ ትናገራለች። ይህ የደስታ ስሜት እርሷ ጋር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የትግራይ ወጣቶችም ዘንድ ያለ መሆኑንም ትጠቁማለች።
ይህንኑ የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሁሉም ነገሮች ቀስ በቀስ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ቅሳነት፤ በሂደት በትግራይ ምድር ሰላም ሙሉ በሙሉ የሚሰፍንበት እድል ሰፊ መሆኑንም ትገልፃለች። የጠፋው ነገር እንዳለ ሆኖ አሁን የመጣው ሰላም መሬት ላይ እንዲወርድና ተግባራዊ እንዲሆን መንግስትም ሆነ የሕወሓት ኃይሎች ለህዝቡ ሲባል የግል ፍላጎታቸውን ትተው ከውስጣቸው በመነጨ ስሜት ታርቀው ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ትጠቁማለች።
የትግራይ ወጣት በጦርነቱ ምክንያት ብዙ ነገሮችን እንዳጣ የምትናገረው ወጣት ቅሳነት፤ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንዳለባቸውና ወጣቱም ቢሆን ወደ ስራ እንዲመለስ ለዚህም መንግስትም ሆነ ሕወሓት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ትናገራለች። በተለይ መንግስት የፈረሱ መሰረተ ልማቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት ትላለች። በመንግስት በኩል ለመሰረተ ልማት ግንባታ የተመደበው በጀት በአፋጣኝ ስራ ላይ መዋል እንዳለበትም ትገልፃለች። ሕወሓትም ቢሆን ይህን በማስፈፀም ሂደት የድርሻውን ሊወጣና ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባም ትጠቅሳለች።
ወጣቱም ጦርነት አስፈላጊ እንዳልሆነ ትምህርት በመውሰዱ ከዚህ በኋላ ወደመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ትምህርትና ስራ መመለስ እንዳለበትና ለሰላሙ መረጋገጥም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበት መልእክቷን ታስተላልፋለች። ከጦርነት ይልቅ ሰላምን በመምረጥ አሁን የመጣውን የሰላም እድል መጠቀም እንዳለበትም ትመክራለች።
አሁን ላይ በትግራይ ምድር የሚነፍሰውን የሰላም አየር እያጣጣመች እንደምትገኝም ወጣት ቅሳነት ገልፃ፤ እርሷን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶች በጦርነቱ ምክንያት የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል ይህ ደግሞ ጠንካራ ወጣት ለመፍጠር ትንሽ ግዜ የሚፈጅ ይሆናልⵆ ወጣቱ ከደረሰበት የስነ ልቦና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዲያገግም ትልቅ የስነ ልቦና ግንባታ ስራ መስራት እንደሚጠይቅም ትገልፃለች።
ከሁለት ዓመት በፊት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የተመረቀችው ወጣት ለምለም ገብረም ስራ እየፈለገች ሳለ ነበር ጦርነቱ የተቀሰቀሰው። በጦርነቱ ምክንያት ልክ እንደ ወጣት ቅሳነት በበርካታ ፍዳና መከራ ውስጥ አልፋለች። የጦርነትን መጥፎ ገፅታንም አይታለች። ጦርነቱ ከቤተሰቧ ጋር እንድትለያይም አድርጓታል። ለእርሷ ያለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ነበሩ።
በመንግስትና ሕወሓት በኩል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ግን ዛሬ ላይ አዲስ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምራለች። በተማርችበት የአካውንቲንግ ሞያ ስራ ለመስራትና ራሷን ለመቻልም ተስፋ አሳድራለች። በዚሁ ሁሉ ውጣውረድ ውስጥ አልፋ ሁሉ ነገር ሰላም ሲሆን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷታል። ይህ ሰላም እንደዚሁ እንዲቀጥልም ምኞቷ ነው። አዎ! ሰላሙ እሷን ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የትግራይ ወጣት አስደስቷል።
‹‹የአሁኑ ግዜ ከባለፈው በእጅጉ የተለየ›› ነው የምትለው ወጣት ለምለም አሁን ላይ በይነ መረብ (ኢንተርኔት)፣ ስልክ፣ መብራት እንደተስተካከለ ከሁሉ በላይ ደግሞ በተፈጠረው ሰላም ለሁለት ዓመታት የተጠፋፋ ቤተሰብ እንደተገናኙ ትገልፃለች። ባንኩም ቢሆን የሚቀረው ነገር ቢኖርም በቀጣይ ይሰተካከላል የሚል ግምት እንዳላት ትጠቅሳለች። አሁን የተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ትልቅ ተስፋ ይዞ የመጣ መሆኑንም ትጠቁማለች።
የሰላም ስምምነቱ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ሁለቱ አካላት አሁንም ቀርበው ሊነጋገሩና ሊወያዩ ይገባል ትላለች ወጣት ለምለም። በሰላም ተግበራዊነቱ ሂደት አንዳንድ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳን ሁለቱም ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳየትና በችግሮቻቸው ዙሪያ ቀርበው መነጋገር እንደሚኖርባቸውም ትጠቁማለች። በተለይ ደግሞ ሰላሙ የተሟላ እንዲሆን አሁንም የቀሩ ነገሮች ሊስተካከሉ እንደሚገቡም ትናገራለች።
ለዚህም መንግስት በተለይ በባንክ በኩል የሚታየውን ችግር በቶሎ መቅረፍ እንዳለበት ታሳስባለች። በጦርነቱ ምክንያት አብዛኛው ወጣት ከስራውና ከትምህርቱ ተፈናቅሎ እንደቆየም ተናግራ፤ አሁን ግን በክልሉ ሰላም በመረጋገጡ ተማሪው ወደትምህርቱ ሰራተኛው ደግሞ ወደስራው በመመለስ ለሰላሙ መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት ትገልፃለች። አብዛኛው ወጣት በጦርነቱ ምክንያት የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰበት እንደመሆኑ ተሀድሶ ገብቶ ወደነበረበት ሁኔታ የመመለስ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግም ትጠቁማለች። ለዚህም መንግስት ትልቅ እገዛ ማድረግ እንደሚኖርበት ትጠቅሳለች።
ወጣቱም ቢሆን ፊቱን ወደ ስራና ልማት በማዞር ለሰላሙ መረጋገጥ የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት ገልፃ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ከመንግስት ጎን በመቆምና ተቀራርቦ በመስራት ብሎም መንግስትን በማገዝ የድርሻውን ይወጣ ትላለች። መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕወሓትም ለሰላሙ መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ታክላለች። ለዚህ ደግሞ ከመንግስትም ሆነ ከሕወሓት በኩል ወጣቱን ቀርቦ ማነጋገር እንደሚያስፈልግም ነው ወጣት ለምለም መልእክቷን የምታስተላልፈው።
ወጣት አብርሃም ስሜ የትግራይ ተወላጅና ሙዚቀኛ ነው። በሙዚቃ ስራው በጦርነቱ ወቅት ስለሰላም አብዝቶ ሲሰብክ ቆይቷል። በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርቦ ስለሰላም ተናግሯል። ልክ እንደ ወጣት ቅሳነትና ለምለም የጦርነትን አስከፊ ገፅታ ቀርቦ የታዘበ ባይሆንም የጦርነት ወላፈኑ እዚሁ አዲስ አበባ ሆኖ ገርፎታል። ምክንያቱም ጦርነቱ እዛው ትግራይ ያሉትን ዘመዶቹን አቆራርጦታል። በቤተሰብና በዘመድ አዝማድ ናፍቆት ተቃጥሏል። ዘመዶቹን መቼ ይሆን የማገኛቸው በሚል ከነገ ዛሬ ተብሰልስሏል።
ምንም እንኳን የሰላም ስምምነቱ ከተደረገ ወዲህ በቀጥታ ወደ ትግራይ ሄዶ ቤተሰቦቹንና ዘመዶቹን ባያገኝም ወላጆቹን በስልክ አግኝቶ የናፍቆቱን ጥም ቆርጧል። ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ጓደኞቹ ጋር ተገናኝቶም አውግቷል፤ ተጫውቷል። ለእርሱም የሰላም በረከቱ ደርሶታል።
ወጣት አብርሃም በመንግስትና በሕወሓት በኩል በተደረገው የሰላም ስምምነት እጅግ ደስተኛ መሆኑን ይገልፃል። በሰላሙ ጉዳይ ከዚህ በፊት እርሱም በሙዚቃ አማካኝነት ሲዘፍንበት የቆየ እንደነበርም ያስታውሳል። ጦርነቱ ባይከሰት ለሁሉም መልካም የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ ሰላም መምጣቱ እንዳስደሰተውም ይናገራል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለቱም በኩል ትልቅ ጉዳት ደርሷል። ከጉዳቱ በኋላ ቢዘገይም ሰላም መምጣቱ እርሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የትግራይ ተወላጅ ወጣቶችንም እንዳስደሰተም ነው የሚገልፀው። እዚህ አዲስ አበባና በውጪ አገራት ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በላይ በጦርነት ውስጥ ያለፈው የትግራይ ህዝብ ሰላም መምጣቱ በእጅጉ ሊያስደስተው እንደሚችል ያለውን ግምት ያስቀምጣል።
የሰላም ስምምነቱን የፈፀሙት መንግስትና ሕወሓትም ከልብ ይበቃናል ብለው ድሮ የነበረውን የአንድነት መንፈስ እንዲመለሱና ህዝቡ ሰላሙን እንዲያጣጥም በማድረጋቸው አሁንም ለዚሁ ሰላም ከልብ እንዲሰሩ ምኞቱን ይገልፃል። ሁለቱ አካላት ይህን የሰላም ስምምነት ቀደም ብለው ቢያደርጉት ጥሩ የነበረ ቢሆንም ከዚህ በላይ ተጨማሪ የሰው ህይወት ሳይጠፋና ተደራራቢ ችግር ሳይፈጠር ተኩስ አቁመው መነጋገራቸውና የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው በራሱ ትልቅ ነገር መሆኑን ያስረዳል።
ለሰላም ስምምነቱ ተግበራዊነቱ ታዲያ ሁለቱም አካላት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ሊሰሩ እንደሚገባ ወጣት አብርሃም ይናገራል። መንግስት እንደ መንግስት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም ይጠቁማል። የትግራይ ክልል አንዱ የኢትዮጵያ አካል እንደመሆኑ ለክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው የሚገልፀው። በተለይ ደግሞ ህዝቡ ከደረሰበት ጉዳት በቶሎ እንዲያገግምና የተሻለ ነገር እንዲያገኝ አስፈላጊ የሚባሉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ባፋጣኝ ወደነበሩበት ሊመልስ እንደሚገባ ያመለክታል።
ህዝቡ በፋይናንስ፣ በኢኮኖሚ፣ በልማት፣ በማህበራዊና በስነልቦና ጠንካራ እንዲሆን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እደሚገባውም ያስረዳል። በተመሳሳይ ሕወሓትም የፌደራሉን መንግስት በማገዝ በተለይ ደግሞ ለህዝቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርስ በመርዳት ህዝቡን ሊክስ እንደሚገባም ይጠቁማል። በዋናነት የሰላም ዋጋው ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ተረድተው አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ከመንግስት ወደ ትግራይ ህዝብ እንዲደርስ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ነው የሚናገረው።
‹‹በዚህ የሁለት ዓመት ጦርነት የትግራይ ወጣት ብዙ ነገር አይቷል›› የሚለው ወጣት አብርሃም ከዚህ አንፃር የሰላም ዋጋ የገባው ይመስለኛል ይላል። ይህ ትውልድ የሰላምን ዋጋ ሳያውቅ ቀርቶ ዋጋ እንደከፈለም ይገልፃል። አሁን ላይ ግን የትግራይ ወጣት የሰላም ዋጋ ከምንም በላይ ከፍ ያለ መሆኑን እንደተረዳ እርግጠኛ ነኝ። በይበልጥ ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ ሳይሆን እዛው ትግራይ ያለው ወጣት የጦርነትን አስከፊነት በሚገባ የተመለከተና ከጦርነት ይልቅ ሰላምን ምርጫው የሚያደርግ እንደሚመስለውም ይጠቁማል። ከዚህ አንፃር ወጣቶቹ አሁን ላይ የመጣው ሰላም እንዲጠበቅና ዘላቂ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም መልእክቱን ያስተላልፋል። መንግስትንም ሊያግዙ እንደሚገባ ይመክራል።
ከሁሉ በላይ በዚህ ጦርነት ወላጆችና ህፃናት የተጎዱ በመሆናቸው ወጣቶች ይህ ገብቷቸው ለሰላሙ መረጋገጥ አጋዥ ሊሆኑ እንደሚገባቸውም ነው ወጣት አብርሃም የሚጠቁመው። ለዚህም የትግራይ ወጣት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የማገዝና ከትግራይ ወጣት ጎን የመቆም ድርሻ እንዳለባቸው ይጠቅሳል።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት የትግራይ ህዝብ ህይወቱን ገብሯል። አካሉ ጎሏል። ተርቧል፤ ተጠምቷል፤ ታርዟል። በርካታ ግፍና መከራም አይቷል። የዚህ ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ደግሞ ወጣቱ እንደመሆኑ በዚህ ሁሉ መከራና ፍዳ ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ በህይወት ያለው የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንደሚረዳ ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንፃር የትግራይ ወጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር በመተባበርና እጅ ለእጅ በመያያዝ ፊቱን ወደ ትምህርት፣ ስራና ልማት ያዞራል ተብሎ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም