በኢትዮጵያ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ዋነኛ ችግር መሆኑ ይገለፃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 36 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረትና መቀንጨር ችግር ውስጥ እንደሚገኙ እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ መንግሥትና በተባበሩት መንግሥታት የህፃናት አድን ድርጅት የተሰራው ጥናት ያመለክታል፡፡
‹‹ዘ ኮስት ኦፍ ሀንገር ኢን አፍሪካ›› በሚል በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ድጋፍ በ12 የአፍሪካ ሀገራት በቅርቡ የተሰራው ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት አምራች ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ በመምጣቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መጥቷል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረትም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ህፃናት መካከል ሁለቱ ወይም ከዛ በላይ የሚሆኑት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ይቀነጭራሉ፡ ፡ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ከቀነጨሩ ህፃናት መካከል ደግሞ 81 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም፡፡
በተመሳሳይም በሰባት የአፍሪካ ሀገራት በቅርቡ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ 44 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በሚከሰቱ በሽታዎች ሆስፒታል ሲገቡ ከፍተኛ የሕክምና ወጪ ይደረግባቸዋል፡፡ ይህም 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ከሚሆነው የሀገሪቱ ዓመታዊ ገቢ ውስጥ 16 ከመቶ የሚሆነውን እንደሚያሳጣ ነው የተመለከተው፡፡ ህፃናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት የአእምሮ አድገት ውስንነት ስለሚያጋጥማቸውም 16 ከመቶ የሚሆኑት ትምህርታቸውን ይደግማሉ፡፡
በኢትዮጵያ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግር ውስጥ ያሉ ህፃናትን ለመደገፍ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም በተለይም ስፓይሮሊና / spirulina/ የተሰኘውን አልሚ ምግብ በሀገር ውስጥ በማምረት ችግሩ ያለባቸው ህፃናት እንዲጠቀሙ ማድረግ አንዱ አዋጭ መንገድ እየሆነ መጥቷል። አልሚ ምግቡን ከውጪ ለማስመጣት ቀደም ሲል ሲወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስቀራል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ይህን ችግር መፍታትን ታሳቢ ያደረገ ፕሮግራም ‹‹በጥሩ ዘር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ›› በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ከሶስት ዓመት በፊት ተጀምሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በዓለም ደረጃ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ ለተቋቋመው ተቋም በማመልከት
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተቋሙ አባል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ዋነኛ አላማውም በጋምቤላ ከተማ የስፓይሮሊና አልሚ ምግብ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በማቋቋምና በሁለቱ ሀገራት ምርቱን በማከፋፈል የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግርን ለመፍታት ነው። ይህም ተቀባይነት አግኝቶ ከተቋሙ ጋር ስምምነት በማድረግና በመፈራረም በኢትዮጵያ አልሚ ምግቡን ማምረት ተጀምሯል፡፡
ድርጅቱ ምርምር በሚያካሄድበት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መኖሪያ ግቢ የሙከራ ምርቱን ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡ አልሚ ምግቡ በተለይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግርን ከመፍታት አኳያና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ሊኖረው በሚችለው ጉዳይ ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅና ከምርምር ማዕከሉ ኃላፊ ከአቶ ዮሃንስ ማሞ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል። ስፓይሮሊና /spirulina/ ምንድን ነው?
ስፓይሮሊና /spirulina/ ለምግብነት ከሚውሉ አልጌዎች የሚዘጋጅ አልሚ ምግብ ነው፡፡ አልሚ ምግቡ ለምግብነት የሚውሉ የአልጌ ዝርያዎችን ሞቅ ባለና የአሲድ መጠኑ ዝቅተኛ በሆነ ውሃ በተሞሉ ገንዳዎች ውስጥ በማሳደግና በመሰብሰብ ይዘጋጃል፡፡
ስፓይሮሊና ከሌሎች የአልጌ ዝርያዎች በተሻለ በርካታ የምግብ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ በመሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት ጭምር ‹‹ ቀጣዩ ምርጥ ምግብ›› ወይም ‹‹best food of the future›› እየተባለ ለመጠራት በቅቷል፡፡ ምግቡ በአይረንና በፕሮቲን የበለፀገ በመሆኑ በተለይ ለህፃናትና ለነፍሰ ጡር ሴቶች ጥቅም ላይ ይውላል። ከ65 እስከ 71 በመቶ የሚጠጋ የተሟላ ፕሮቲን አስፈላጊ ከሆኑ የአሚኖ አሲድ ጋር በተመጣጠነ መልኩ የያዘ መሆኑም ከሌሎች የተመጣጠኑ የምግብ አይነቶች የተሻለ ያደርገዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ አልሚ ምግቡ ምን ይላሉ? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1974 ባካሄደው ዓለም አቀፍ የምግብ ኮንፍረንስ ስፓይሮሊና የተሰኘውን አልሚ ምግብ የወደፊቱ ምርጥ ምግብ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤም አባል ሀገራት፣ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ የበይነ መንግሥታት ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ዘርፎች የአልሚ ምግቡን ምርትና ጥቅም እንዲያበረታቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅትም የሀገራት መንግሥታትና የበይነ መንግሥታት ድርጅቶች ስፓይሮሊና በተለይ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ያለውን ጥቅም ዳግም ሊገመግሙትና ሊያዩት እንደሚገባ አስታውቋል። በተጨማሪም ድርጅቱ ስፓይሮሊናን ለማምረት የሚያጋጥሙ ቴክኒካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይም የዓለም ጤና ድርጅት አልሚ ምግቡ በፕሮቲንና በአይረን የበለፀገ መሆኑንና በተለይ ለህፃናት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና ምንም አይነት የጤና ጉዳት የሚያስከትል አለመሆኑን አረጋግጧል፡፡
አልሚ ምግቡ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው? ስፓይሮሊና የተሰኘው አልሚ ምግብ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በዓለም ጤና ድርጅት ተረጋግጧል፡፡ በተለይም ሰውነት የሚፈልጋቸውንና ለጤንነት ተስማሚ የሆኑ የፕሮቲን፣ ቫይታሚንና ሚነራል ንጥረ ነገሮችን በመያዙ በሽታ የመከላከል አቅምን በመገንባት ሰውነት እንዲታደስና የጤነኝነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ሰውነትን በማጠንከርም በሽታ የመከላከል አቅምን ያሳድጋል። በውስጡ ምንም አይነት ኬሚካል የሌለውና መቶ በመቶ ተፈጥሯዊ ምግብ በመሆኑ ማንኛውም ሰው በየትኛውም ጊዜ ራሱን ከበሽታዎች ለመከላከል፣ ለአጠቃላይ ጤንነት አልያም ለጥንካሬ ሊገለገልበት ይችላል፡፡
በተጨማሪም አልሚ ምግቡ በተለይም የኤች አይ ቪ ታማሚዎች ሲዲ 4 እንዲጨምር በማድረግ በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ያሳድጋል፡፡ የራይቦኒዩክሊክ አሲድ እንዲጨምር በማድረግ አእምሮ ተጨማሪ ጉልበት እንዲያገኝም ያስችላል፡፡ ለጤናማና የተስተካከለ የዓይን እይታ፣ ጡንቻን ለማዳበርና ለሌሎችም ያለው ጥቅም የጎላ ነው፡፡
ስፓይሮሊና ለሰውነት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ባለባቸው ሀገራት በማምረት ሂደት ለወጣቶችና ሴቶች የስራ አድል ለመፍጠር ያስችላል። በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በተለይ በህፃናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ይረዳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የመጀመሪያ ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ያለውን የምገባ ፕሮግራም ለመደገፍም ያስችላል፡፡
የአልሚ ምግቡ አዘገጃጀትና አጠቃቀም
ስፓይሮሊና በዱቄት፣ በእንክብል አልያም በእሽግ መልክ በገንቢ ወይም በበሽታ ተከላካይ ምግብነት ለተጠቃሚዎች ሊቀርብ ይችላል፡፡ የሰፓይሮሊናን ዱቄት በአነስተኛ መጠን በበሰሉ ምግቦች ውስጥ ወይም ለብ ባለ ውሃ ውስጥ በመጨመር መጠቀም ይቻላል፡፡ ወይም ደግሞ በእንክብል መልከ የሚዘጋጀውን ስፓይሮሊና በቀን ሁለት መውሰድ ይቻላል፡፡
የስፓይሮሊና አወሳሰድ መጠን እንደ ግለሰቡ ፍላጎትና እንደ እድሜ ደረጃ ይለያያል። ይሁንና የስፓይሮሊና አጠቃቀም መመሪያ እንደሚያሳየው አምስት ዓመት የሞላቸው ህፃናት በቀን ከ1 እስከ 2 ግራም፣ ከ5 ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናት በቀን ከ2 እስከ 3 ግራም እንዲሁም አዋቂዎች በቀን ከ 3 እስከ 5 ግራም እንዲወስዱ ይመከራል፡፡
በኢትዮጵያ የአልሚ ምግቡ ፕሮግራም የሚካሄድባቸው ቦታዎች
ጥሩ ዘር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት በታዳጊ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አልሚ ምግቡን የማምረትና የማከፋፈሉን ስራ የሚያከናውን ሲሆን በአፋር ክልል በዞን 1፣2፣4 እና 5፣ በጋምቤላ ኑዌርና አኙዋክ ዞን፣ በቤንሻንጉል አሶሳ ከተማና መተከል ዞን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የልደታና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞችን ያካትታል፡፡ ፕሮግራሙ የሚካሄድባቸው ሶስቱ ታዳጊ ክልሎች ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ የያዙ ሲሆን 17 የገጠር ቀጠናዎችን፣ አምስት ከተሞችንና ሶስት ዩኒቨርስቲዎችን (ሰመራ፣ጋምቤላና አሶሳን) ያጠቃልላል፡፡
አልሚ ምግቡን በኢትዮጵያ ለማምረት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ስፓይሮሊናን የማምረቱን ስራ በኢትዮጵያ ለመጀመር ያጋጠመው ተግዳሮት ከሀገሪቱ አካባቢ ጋር ተስማሚ ሊሆኑ የሚችሉና ሊያድጉ የሚችሉ ለምግብነት የሚውሉ አልጌዎችን ማግኘት ነበር። ሆኖም በደቡብ አፍሪካ፣ሩዋንዳ፣ጋና ላይ ከሚሰራ የእስራኤል ድርጅት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ተስማሚ የሚሆኑ የአልጌ ዝርያዎችን በማስመጣት ማምረት ተጀምሯል፡፡ በመንግሥት በኩል የታዩ ቢሮክራሲዎችም ምርቱን በቶሎ ለማስጀመር ተጨማሪ ተግዳሮት ነበሩ፡፡
ከመመረቱ በፊትም የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በዚህም የምርቱን ጠቀሜታና ፍላጎት አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒትና ጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርቱ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን አረጋግጠዋል። ምርቱ ለተጠቃሚዎች መቼ ይደርሳል?
በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የስፓይሮሊና ማምረቻ ኢንዱስትሪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርቱን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለማምረት የሚያግዙ ቁሳቁስም በአብዛኛው የመጡት ከውጭ ሀገር ነው፡፡ ከውጪ የመጡ ባለሙያዎችም ለአምስት ዓመታት የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን እያሰለጠኑ ይቆያሉ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያን ሙሉ ስራውን ያከናውናሉ፡፡
ይሁንና የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ይቀጥላል፡፡ በቀጣይም አልሚ ምግቡን በቀላሉ ማዘጋጀት ስለሚቻል ለህብረተሰቡ የአልጌውን ዘር በመስጠትና ስልጠናዎች በማመቻቸት በራሳቸው አምርተው እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011
በ
አስናቀ ፀጋዬ