በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍናና የአንትሮፖሎጂ ምሑሩ ፕሮፌሰር ምንዳርያለው ዘውዴ በመለስ ዜናዊ አመራር ወቅት ከተባረሩ 40 ምሑራን መካከል አንዱ ናቸው። በአንድ ወቅት ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳነሱት የመባረራቸው መንስኤ ምክንያት የለሽ ነው። ለዚህም ማሳያ ያደረጉት የተባረሩበትን ደብዳቤ ጭብጥ ሲሆን፤ ቃል በቃል ባላስታውሰውም እንዲህ ይላል ሲሉ ጭብጡን ያስቀምጣሉ።
‹‹ ሀገርዎን በከፍተኛ ብቃትና ትጋት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማገልገልዎ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ከፍተኛ አክብሮት አለው። ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መንግሥት በወሰነው መሰረት ዩኒቨርሲቲውን እንዲያስተዳድር የሰየምነው ቦርድ የእርስዎን ውል ላለማደስ ወስኗል›› ይላል። ምስጋና ችሮ፣ እውቀትና እምቅ አቅም እንዳለ አምኖ ልታስተምር አትችልም ማለት ዩኒቨርሲቲው እንዲተገብረው የሚፈለገው ሌላ ተልዕኮ አለ ማለት ነው።
ምሑር ደግሞ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚል፣ በምርምር አገርን ከፍ ለማድረግ የሚጥርና ሁልጊዜ መልካም ዜጋን ለመፍጠር የሚችል ነው። እናም አዲስ ተልዕኮውን አላስፈጽምም ስለሚል በአንድ ብጣሽ ወረቀት እሳቸውን ጨምሮ 40 የዩኒቨርስቲ መምህራን ተመርጠው እንዲባረሩ ሆነዋል ይላሉ የነበረውን ሁነት ሲያስታውሱ።
ይቀጥሉና በጣም የሚገርመው በብቃታቸው ካመነና ካመሰገነ በኋላ በአባሪ ወረቀት የተጻፈውን ደብዳቤ ጭብጥ ያነሳሉ። ‹‹በእጅዎ የሚገኘውን ማንኛውንም ንብረት በ24 ሰዓት ውስጥ አስረክበው በአስቸኳይ ግቢውን ለቀው ይውጡ›› ማለቱም እጅግ የሚያሳዝንና ለሀገር በለፋ ምሑሩን ያሳቀቁበት ተግባራቸው መሆኑን ያብራራሉ። ነገር ግን ምሑር መቼም በሀገሩ ተስፋ የሚቆርጥ እንዳልሆነም በተግባር ማረጋገጣቸውን ያወሳሉ። ምክንያቱም እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የተባረሩ ሰዎች ቁጭ ብለው በተሠራባቸው ሴራ አልቆዘሙም። ይበልጥ የሚጎሉበትንና ለሀገራቸው የሚያበረክቱበትን ሥራ መርጠው ወደ መተግበሩ ገቡ እንጂ።
ለምሳሌ፡- ፕሮፌሰር ምንዳርያለውን የብዙ ሀገራት የሥራ ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም በሀገራቸውም አንቱታን ያተረፉ መምህር ቢሆኑም ሀገራቸውን ትተው ባህር ማዶ አልተጓዙም እንደውም ወደ ትውልድ ቀያቸው ሄደው ግብርና ሥራ ላይ ተሠማሩ እንጂ። ይህ ደግሞ ፕሮፌሰሩን አርሶ አደር አሰኝቷቸው የብዙዎች መነጋገሪያ አድርጓቸው ቆይቷል። በዚህ ሳያበቁም አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር የመጽሐፍ ሥራቸውን ቀጥለዋል። ከመባረራቸው በፊትም ሆነ በኋላ 25 የተለያዩ መጽሐፍትን ጽፈዋል። አብዛኞቹን መጽሐፍት የጻፉት ከዩኒቨርስቲ ከተባረሩ በኋላ ከግብርና ሥራቸው ጎን ለጎን ነው።
እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ የመባረራቸው ምክንያት ሞጋች ምሑራን እንዲኖሩ የመንግሥት አለመፈለግ ነው። ፍራቻው ብዙ የባከነ ትውልድ እንዲፈጠርና መንግሥትና ምሑሩ እንዳይናበብ አድርጓል። ከዚያም በላይ ዛሬ ድረስ የዘለቀ መገፋፋቶች እንዲኖሩ ምክንያት መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ። ግን ይህ ነገር በዶክተር ዓቢይ አሕመድ አመራር በመጠኑ የተፈታ ይመስላል ባይም ናቸው። በምክንያትነት የሚያነሱትም እርሳቸው ከተሾሙ ብዙ ሳይቆዩ የተባረሩትን ምሑራን ሰብስበው ‹‹እኛ ነን ይቅርታ መጠየቅ ያለብን›› በማለት በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀዋል። ከዚያም አልፈው ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ሁኔታ አመቻችተዋል። ይህ ደግሞ በእጅጉ የመንግሥትንና የምሑራንን ቅርርብ የሚያጠናክር ነው።
‹‹ሰው የባርነት ምቾትን ከመረጠ ለውሻ አሟሟት መፈረሙ የተረጋገጠ ነገር ነው። በባርነት ምቾት የኖረ ኑሮው ያሳማ ነው ሞቱም የውሻ። ተንገላቶ ያለው ደግሞ ኑሮው የጀግና ሲሆን፤ ሞቱ የሰማዕት ነው።›› የሚሉት ፕሮፌሰር ምንዳርያለው፤ የሰው ልጅ የተፈጠረው እንዲያስብ ነው። ነገር ግን ማሰብን በሆዱ ተክቶ ከኖረ ሁሉን ነገር ይሸጣል። ፈጣሪውን ጨምሮ።
ምሑር ደግሞ ይህንን አያደርግም የተፈጠረበትን ዓላማ ያስታውሳል። ስለዚህም ምሑራን በምንም ተዓምር ነጻነታቸውን ለማንም አሳልፈው መስጠት የለባቸውም። ታግለው እስከሚያሸንፉ ድረስ ሀገራቸውን በማቆም ተግባር ላይ መሥራት አለባቸው። አንድ ጊዜ ነጻነትህን ለአምባገነን ከሰጠህ መልሶ ለማግኘት ከእርሱ መበደር ግድ ነው። ስለዚህ ነጻነትን ከአምባገነን ከመበደር መታቀብ የሁሉም ምሑር ግዴታ መሆን እንዳለበትም ይመክራሉ።
እስከመጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል ነውና በስተመጨረሻ በዶክተር ዓቢይ አሕመድ ይህ ነገር ተፈቶላቸው ዛሬ የጥንቱ የሥራ ቦታቸው ላይ የሚገኙት በርካታ ናቸው። አሁንም የምሁራን ድርሻ በዚህ ልክ መታየት ይኖርበታል የሚባለው ለዚህ ነው። ምሑር ከሌለ በዕውቀት የበለጸገ ትውልድ አይኖርም፤ በስነምግባር የተኮተኮተ ዜጋ አይፈጠርም። አገር ወዳድ ትውልድም ማፍራት የማይታሰብ ነው። እየታሰበ ያለው አገርን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት መካከል ማሰለፍም ሕልም ይሆናል።
ምሑር የሌለበት ዩኒቨርሲቲ ተጠያቂነት አይኖርበትም፤ ሙስናና ብልሹ አሠራሩ እንደልብ ይንሰራፋል። በቀደሙት ጊዜያት የታየውም ይህ ነው። ሞጋቾች በመባረራቸው የተነሳ በዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር ውስጥ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ብር መዘረፉን ዋናው የኦዲተር መሥሪያ ቤት ለተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ነበር። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውጤታማ የአገር ግንባታ ሥራ እንዲከናወን ምሑራንን ማበረታትና ወደ ሥራ ማስገባት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በተለይም እንደመንግሥት ይህ ሊታሰብበት ይገባል።
በእርግጥ መንግሥት አሁን ላይ ይህ ጉዳይ የገባው ይመስላል። ለዚህም ማሳያው በምሑራንና መንግሥት መካከል ያለውን መገፋፋት ለመቀነስ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አንዱ ማሳያ ነው። በመንግሥትና በምሑራን መካከል ጥብቅ ግንኙነት እንዲኖርም መንግሥት የተለያዩ መድረኮችን እየፈጠረ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እየጠየቀ ይገኛል። ሰሞኑን በብሔራዊ ደረጃ በዩኒቨርሲቲዎች ለውይይት የቀረበው ‹‹ለአገር ግንባታ የምሑራን ሚና›› የሚለው ሰነድ ለዚህ አንዱ አብነት ነው።
በመድረኩ ላይ ያገኘናቸው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዲን የሆኑት ዶክተር ኃይለሚካኤል ሙሌ እንደነዚህ አይነት የውይይት መድረኮች እጅግ አስፈላጊና የሚደገፉ እንደሆኑ ያነሳሉ። ውይይቱ በምሑራንና መንግሥት መካከል ያለውን መገፋፋትም እንደሚያጠበው ያምናሉ። እስከዛሬ በነበሩት ሁኔታዎች ሁለቱ አካላት እርስ በእርስ ሲኳነኑ ነበር። ሲገፋፉና ለሀገር ማበርከት ያለባቸውን ሳያበረክቱ ቀርተዋል። አሁን ግን ጅማሮዎቹ እጅግ ያስደስታሉ። ቀጣይነቱ ግን አጠያያቂ ነው። ምክንያቱም መንግሥትና ምሑራኑ ተቀራርበው ሠሩ የሚባለው የምሑሩ ሥራ ከመደርደሪያ ወርዶ መሬት ላይ ደርሶ የማኅበረሰቡን ችግር ሲፈታ ነው።
ምሑራን ሀሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ለሀገር ግንባታ ሥራ ሲውል ነው። እናም መንግሥት በውይይቱ ልክ ቀርቦ ሥራዎችን ወደተግባር የሚቀየርበትን መንገድ መዘርጋት እንዳለበት ያነሳሉ። ቀጥለውም ምሑራን በምርምር ሥራዎቻቸው ብዙ ነገሮችን መለወጥ ይችላሉና ያንን በማድረጉ ዙሪያ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው ይላሉ።
ምሑራን በሙያም፣ በፖለቲካውም ፤በማኅበራዊውም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ የዳበረ እውቀት አላቸው። በዚህም ሀገርን ልጥቀም ብለው ከተነሱ የሚያግዳቸው አካል አይኖርም። መንግሥትን ጭምር ማሸነፍ የሚችል ኃይል ባለቤት ናቸው። እናም መጠቀሙ ላይ መትጋት አለባቸው። ከምንም በላይ ግን መንግሥት ነገሩን ተረድቶ በመናበብ ቢሠራ የበለጠ ሀገርን በመገንባቱ ዙሪያ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል ይላሉ።
ምሑራን ለሀገር መረጋጋት ግድ አስፈላጊ ናቸው። መፍትሔ አመንጪ ብቻ ሳይሆኑ መፍትሔ አውራጅና ማኅበረሰቡን አሳማኝ ናቸው። ምክንያቱም ሕዝብ ይሰማቸዋል፤ ተማሪዎቻቸው ደግሞ ይቀበሏቸዋል። ከዚያም አለፍ ብሎ በአካባቢያቸው ሰዎችን ማሳመን በሚችሉት ልክ መጓዝ ይችላሉ። እናም ይህንን ሁሉ ተቀባይነታቸውን ከብሔርም ሆነ ከፖለቲካው ነጻ አድርገው ሙያቸው ላይ ብቻ ተንተርሰው ለአገር ማበርከት ያለባቸውን ማበርከት አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ።
እውነተኛ ምሁር አይዋሽም፣አድርባይና ወላዋይም አይደለም ስለዚህም ሀገር ችግር ውስጥ በሆነችበት ጊዜ የመፍትሔ ሀሳብ በማመንጨት ሕዝብን ይታደጋልና ዛሬ ላይ ያለን ምሑራን ይህንን ማድረግ ይጠበቅብናል የሚሉት ዶክተር ኃይለሚካኤል፤ ምሑራን ለሀገራችን አሳቢ ነን ብለው ካመኑ የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምርምሮችን በማቅረብ፤ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተሻሉ ሀሳቦችን ለማኅበረሰቡና ለመንግሥት ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ታግሎ ማታገል የእነርሱ ድርሻ መሆኑን አምነው በእውቀት ሌሎችን ማሻገር ይገባቸዋል። በትምህርት የሚገነቡት አዕምሮ፣ በባህሪ የሚያንጹት ትውልድ አመለካከቱን የሚቀይሩት ሀገር ተረካቢ ትውልድ ይዘው የሚጓዙ በመሆኑ ትክክለኛ መስመርን ተከትለው ለሀገራቸው ውለታ መዋል ይኖርባቸዋል። ሀገር ስትፈርስ አብሮ መፍረስ አለና ከአሁኑ ጀምሮ መገፋፋቱን ማቆም አለባቸውም መልዕክታቸው ነው።
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለውይይት የቀረበውን ሰነድ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙም በዶክተሩ ሀሳብ ይስማማሉ። የሀገር ግንባታ ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው አይደለም። እንደውም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ምሑራን እንደሆኑ ያነሳሉ።
የሥርዓተ መንግሥት ግንባታ በምሑራን ሥራ የሚረጋገጥ ነው። ምክንያቱም ምሑራን በተሠማሩባቸው መስኮች ብዙ ለሀገር ግንባታ የሚጠቅሙ ምርምሮችን ይሠራሉ። መልካም ውጤቶችን ያሳያሉ፣ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ሀገራቸውን ይበልጥ መጥቀም የሚችሉም ናቸው። በተለይም ዕውቀታቸውን በመጠቀም የሀገራቸውን ኢኮኖሚ የተቃና እንዲሆን፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥሉ እንዲሁም የዜጎች ደህንነትና የሀገር አንድነት እንዲከበር በማድረግ በኩል ትልቅ ኃይል አላቸው። እናም በዚህ ጉዳይ ላይ አበክረው ሊሠሩ ይገባል።
የሀገር ግንባታ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ያከናወኑ በርካታ አገራት የስኬታቸው መሠረት ምሑራን ናቸው። እነርሱ በተሠማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሲያደርጉ ሀገራቸውም በዚያው ልክ አድጋለች። የእኛም የሀገር ግንባታ ሥራ የተደራጀ የምሑራንን ሚና ይሻል። በመሆኑም ምሑራን ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው መሥራትን ይበልጥ ሊላመዱ ይገባል። ምክንያቱም ከለውጡ በኋላ ሀገር የሚገነባው በእውቀት እና በሀሳብ ነው የሚለው ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከምሑራን ጋር ያሉ ናቸው።
ስለዚህ መንግሥት እንደመንግሥት የእነርሱን ሀሳብ ተቀብሎ ለመተግበር ቁርጠኛ ነው። እየተገበረም እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ለአብነት ዘላቂ መፍትሔዎችን በምርምር አምጥቶ የሚቀጥለው ትውልድ በዚያ ችግር ውስጥ እንዳያልፍ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች መበራከታቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምርና የችግር መፍቻ ማዕከላት እንዲሆኑ ለማድረግ ነጻነታቸውን ማወጅ የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትመች፤ ዜጎቿ የሚኮሩባትና ታሪኮቿ የተጠበቁላት ማድረግ ላይ እጅግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። በተጨማሪም ጊዜው የቴክኖሎጂ በመሆኑ ሰውን ከቴክኖሎጂው ጋር በማዋሐድ መሥራት ይጠበቅባቸዋልና እነዚህና መሰል ነገሮች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጠንካራ ግንኙነትን ፈጥሮ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
አቶ መለሰ በእርግጥ ይላሉ፤ በእርግጥ በአገር ግንባታ ጉዳይ ላይ በርካታ ችግሮች አሉብን። እነዚህን ችግሮች ነቅሶ ለማውጣትና የመፍትሔ ሃሳቦችን ወደተግባር ለመቀየር ደግሞ የምክክር መድረኮች አስፈላጊ ናቸው። በተለይም ከምሑራን ጋር መወያየት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እናም እንደመንግሥት ይህ እቅድ ወርዶ ለውይይት ቀርቧል። ከውይይቱ በኋላ ደግሞ መልካም ሥራዎች እንደሚኖሩም ይታመናል።
አሁን አገር የምሑራንን ተሳትፎ በእጅጉ ትፈልጋለች። ምክንያቱም የተለያዩ ችግሮችን ስታሳልፍ ቆይታለች። እናም ይህንን የሚያክም አካልን ትሻለች። ይህንን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ሙያ ያለው በእውቀቱ መሥራት የሚችለው ምሑር ነው። ስለሆነም አገርን ለመፈወስ ምሑሩ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ይላሉ።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠናም ያላቸው ምልከታ ልክ እንደአቶ መለሠ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ምሑራን የዳር ተመልካች ነበሩ። እንዳይሠሩም ይደረጋሉ። በዚህም ስር የሰደደ ቅሬታ ውስጥ ሆነው ዘልቀዋል። ይህ ግን ሊሆን አይገባም ነበር። ምክንያቱም ምሑሩን አግልሎ የሚገነባ ሀገር የለምና።
አይደለም እንደሀገር እንደ ተፈጥሮም ብዙ ነገራችን ሁለት ነገሮችን የያዘ ነው። ለወንድ ሴት ፤ ለጨለማ ብርሃን፤ ለእጅ ቀኝና ግራ እየተባለ ይዘረዘራል። ይህ ግን ሥራው ቢለያይም ተፈጥሮነቱን መቀየር አይችልም። በፖለቲካና በርዕዮተ ዓለም ምልከታችን ቢለያይም በሀገር ጉዳይ ግን የማንቀይራቸው በርካታ ነገሮች አሉ የሚሉት ዶክተር ብርሃነመስቀል፤ ሌላ ሀገርም ሀብትም ስለሌለን በሥራችን፣ በምርምራችን መውጣት አለብን። ይህ ሲሆን ደግሞ የሚሠራውን ሰው ጉልበት በመስበር፣ አቅም በማሳጣት ሳይሆን እርሱን በመደገፍ መሆን አለበት።
ትናንት በመንግሥትም ሆነ እንደሀገር በርካታ ችግሮች ነበሩ። ምሑር ደግሞ አስተማሪ ነውና ስህተቱን ማሳየት ይገባዋል። የመፍትሔ መንገዱንም ማመላከት ግዴታው ነው። ስለዚህም ጥቂቶች በጩኸታቸው አደንቁረውን አገራችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ ዛሬ በግንባታው ላይ የተቻለንን ማበርከት ይገባናል። ቀጣይ ብዙ ተባብረን የምንፈታቸው ችግሮች አሉ። ስለሆነም ጣት በመቀሳሰር ሳይሆን በመተሳሰብ ለስኬቱ መትጋት ይገባናል ሲሉም ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015