ሰላም ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? በጣም ቆንጆ ነበር እንዳላችሁኝ እርግጠኛ ነኝ፤ምክንያቱም ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የገና በዓል የተከበረበት ነው። ልጆች በዓል እንዴት ነበር? እኔጋ በጣም ቆንጆ ነበር። በአል ሲመጣ እንኳን አደረሳችሁ መባባል ባህላችን ነውና እንኳን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት የገና በዓል ላይ ያተኮረ ፅሁፍ ነው። ልጆች የገና በዓል በሁለት መንገድ ይከበራል። አንደኛው ከእምነት አንፃር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከባህል አንፃር ነው። በመጀመሪያ ከእምነት አንፃር እንመልከት፤ የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በልን የልደት በዓል ወይም የውልደት በዓል በማለት ይጠሩታል። ይህ በዓል የእየሱስ ክርስቶስን በከብቶች በረት መወለድ የሚዘክሩበት ነው።
በንጉስ አውግስቶስ ቄሳር ዘመን ንጉሱ ሰው ሁሉ እንዲቆጠር ባዘዙ ጊዜ፤ ሰው ሁሉ ለመቆጠር ወደየትውልድ ቦታው መሄድ ጀመረ። ዮሴፍ እና የእየሱስ ክርስቶስ እናት ማርያምም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ቤቴልሄም ጉዞ አደረጉ። በቤቴልሄም ሳሉም ማርያም የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤ በቦታው ብዙ እንግዳ ነበርና የምታርፍበት ቦታ አልነበረም በመሆኑም ማደሪያ ስላልነበራቸው በከብቶች በረት ውስጥ ልጇን እየሱስ ክርስቶስን ወለደችው።
በዚያን ሌሊት ከብት ሲጠብቁ የነበሩ እረኞች ህፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በከብቶች በረት ውስጥ ተኝቶ ባዩት ጊዜ እጅግ ተደሰቱ። ደስታቸውንም “በሰማይ ለእግዚያብሄር ክብር ሆነ በምድርም ለሰው ልጆች በጎ ፍቃድ ሆነ” በማለት ገለፁ። እንግዲህ ልጆች ይህ የገና በዓል ከእምነት አንፃር የሚከበርበት ምክኒያት ነው።
ሌላኛው ደግሞ ከባህል አንፃር የሚከበርበት ነው።በኢትዮጵያ የገና በዓል ሲከበር ዘመድ አዝማድ እየተገናኘ እንኳን አደረሰህ? እንደምን ከረምክ ?ልጆች፤ አዝመራው፤ እህሉ ፤ጤንነት እንዴት ነው? የሚባባልበት በዓል ነው። በዓል ሲቃረብ ለበዓሉ የሚሆን ጠላ ይጠመቃል፣ በዋዜማው ድፎ ዳቦ ይጋገራል ከዚያም ሲል ደግሞ ጠጅ ይጣላል።
ልጆች መቼስ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ “፣ “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለው። እንደዚህ የሚባለው ለምን እንደሆን ታውቃላችሁ? በገና በዓል ሁሉም ሰው እኩል የመደሰት መብት ይሰጠዋል። በዓሉን አስመልክቶ የሚደረግ ‹‹የገና ጨዋታ›› በመባል የሚታወቅ ባህልዊ ጨዋታ በወንዶች መካከል ይካሄዳል። በዚህ ጨዋታ ላይ ማንም ከማንም ልዩነት ሳይደረግበት እኩል ይሳተፋል። በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እረኞችም ሆኑ አለቆቻቸው የገና በዓል ቀን እኩል በጨዋታው ይሳተፋሉ፤ በዚያን ቀን አዛዥና ታዛዥ አለቃና ሰራተኛ የሚባል ነገር የለም ። በፍቅርና በነፃነት አበረው በዓሉን ያከብራሉ።
የገና ጨዋታ የገና በዓልን መድረስን ተናፋቂ ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ ዋናውና የበዓሉም ድምቀት ነው። ልጆች የገና ጨዋታ መቼ እንደተጀመረ የሚገልፅ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም ከክርስቶስ ልደት በፊት እረኞች በተለይ በበጋው ወቅት ከብት እየጠበቁ መስክ ላይ የጫወቱ እንደነበር ይነገራል። ታዲያ ልጆች የገና ጨዋታን ለመጫወት ሩር እየተባለ የሚጠራ ድቡልቡል ያስፈልጋል። ክብደቷ እስከ አምስት መቶ ግራም የሚመዝን ከእንጨት፤ ከጠፍር አሁን አሁን ደግሞ ከፕላስቲክ ይዘጋጃል። ድቡልቡል መጫወቻ ወይም ሩሩን ለመምታትና ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ለማስቆጠር ልክ እንደማንኪያ ቅርፅ ያለው ከአንድ ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው የገና ዱላ ያስፈልጋል።
እንግዲህ ልጆች የገና ጨዋታ ላይ ተንኮል የለም፤ ሁሉም በፍቅር ከልብ ይጫወታል፤ ማንም አውቆ ሌላን ሰው አይጎዳም። ይህ የገና ጨዋታ የሚደረገው ኢትዮጵያ ብቻ ውስጥ ነው፤ ይህም የሚያሳየው ሀገራችን ምን ያህል የሚያምር የራሷ የሆነ ባህል እና የባህል ማድመቂያ የሆኑ ጨዋታዎች እንዳሏት ነው። እናንተም እነዚህን ባህሎችና የበዓል ጨዋታዎች ማወቅ አለባችሁ፤ ጎበዝ ልጆች የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋና ወግ ጠንቅቀው ያውቃሉ እናንተ ደግሞ ጎበዞች ስለሆናችሁ ቤተሰቦቻችሁን ስለሀገራችሁ ባህል ጠይቃችሁ ማወቅ ይኖርባቹሃል።
ልጆችዬ ብዙ ጊዜ የገና በዓል ሲመጣ አብዛኞቻችን የምናስታውሰው የገና ዛፍ ማዘጋጀትና በተለያዩ ጌጣጌጦች ማሳመር ነው፤ ነገር ግን ይህ የኛ ባህል አይደለም። ይህ ባህል የፈረንጆች ባህል ነው በዚያ ላይ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ ያመዝናል፤ ምክኒያቱም የገና ዛፍ ለማዘጋጀት የግድ ዛፍ መቁረጥ አለብን የህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የእፅዋት ጭፍጨፋን ያስከትላል።
ልጆች ትምህርት ቤት ስለእፅዋት ስትማሩ የእፅዋት መመናመን የሚያስከትለውን የአየር መዛባት ትማራላችሁ፤ በትምህርታችሁ ታዲያ የደን መመናመን ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጨመርን እንደሚያሥከትል መምህራኖቻችሁ ያስተማሯችሁን ታስታውሳላችሁ ብዬ አስባለው። ስለዚሀ ለገና በዓል ብለን ዛፍ መቁረጥ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል አውቀን ይህንን ባህል በራሳችን ሃገርኛ ባህል መተካት አለብን ማለት ነው።
እናንተም ለገና ብላችሁ ጥድ ዛፍ መቁረጥ የለባችሁም ከዚያ ይልቅ በጣም ደስ የሚለውን የገና ጨዋታ ከእድሜ እኩዮቻችሁ ጋር በመጫወት ማክበር ትችላላችሁ። በሚቀጥለው አመት እንደዚህ ባለ መልኩ እንደምታከብሩ ተስፋ አደርጋለሁ። በሉ ልጆች የዛሬ ፅሁፌን እዚህ ላይ ላብቃ ፤ሳምንት በሌላ ፅሁፍ እስክንገናኝ መልካም የበዓል ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015