ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ በተለይ ደግሞ በቀንድ ከብት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር እንደሆነች በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ኮሚሽን የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ በሀገሪቱ 70 ነጥብ 3 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 52 ሚሊዮን ፍየል፣ 43 ሚሊዮን በግና 8 ሚሊዮን ግመል እንዳሏት ይጠቁማል።
ከወተት ሀብት አኳያም 15 ሚሊዮን ላሞች፣ 6 ሚሊዮን ግመሎችና 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ፍየሎች በሀገሪቱ እንዳሉ ይኸው መረጃ የሚጠቁም ሲሆን የሀገሪቱ የወተት ሀብት የተመሰረተው በአብዛኛው በላሞች እንደሆነ ይናገራል።
ከዶሮ ሀብት አንፃር ደግሞ 57 ሚሊዮን በሀገሪቱ እንደሚገኙ መረጃው የሚጠቁም ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወይም 34 ከመቶ ያህሉ እንቁላል ጣይ ናቸው። እንዲሁም ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ የንብ መንጋ በሀገሪቱ እንደሚገኝም መረጃው ይጠቁማል።
የሀገሪቱ የእንስሳት ሀብት የትየለሌ ቢሆንም ታዲያ አሁንም ድረስ ይህን አንጡራ ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለም። በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ተሰማርተው ያሉ ሰዎችም ስራውን የሚያከናውኑት በእውቀት ላይ ተመስርተው እንዳልሆነ ይነገራል።
የግብርናው ዘርፍ በተለይ ደግሞ እንስሳትና ዶሮ እርባታ አዋጭና ምርታማ እንደሚያደርግ ቢታወቅም በሚገባው መጠንና ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተሰራበት አይደለም። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚሳዩት ከሆነ ደግሞ በእንስሳት ልማት ዘርፍ በዋናነት በዶሮ እርባታ ላይ የሚሰሩት ስራዎች 99 ነጥብ 2 ከመቶ ያህሉ በእውቀት ላይ ተመስርተው እንደማይሰሩ ያሳያሉ።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ 0 ነጥብ 8 ያህሉ ብቻ በዘመናዊ መልኩ እንደሚሰራበት ጥናቶቹ ይጠቁማሉ። ይህም ዘርፉ በእውቀት እንዲሰራ የማድረጉና የማዘመኑ ጥረት ደካማ መሆኑን ያመለክታል። ዘርፉን በማዘመን ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ አካላትም ውስን መሆናቸውን ጥናቶቹ ያሳያሉ።
ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት ለእንስሳት ሀብት ልማት በተለይ ደግሞ ለከተማ ግብርና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የጀመረው። በተለይ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በከተሞች አካባቢ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው አነስተኛ ቦታ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ አልምተው እንዲመገቡ ያሚያስችሉ የንቅናቄ ስራዎችን አስጀምረዋል።
በቅርቡ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር የንብ ማነብን፣ እንቁላል፣ ዶሮ ርባታ፣ ከብት ማደለብ፣ ወተትና አትክልትና ፍራፍሬ ማልማትን ያቀፈ ‹‹የሌማት ትሩፋት›› የተሰኘ ትልቅ ፕሮጀክት ይፋ አድርገው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተተገበረ ይገኛል።
በሌማት ትሩፋት እሳቤ በርካታ ወጣቶች በንብ ማነብን፣ እንቁላል፣ ዶሮ ርባታ፣ ከብት ማደለብ፣ ወተትና አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በስፋት ገብተው ይሰራሉ ተብሎ ይታሰባል። በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ገብቶ ውጤታማና ትርፋማ ለመሆን ደግሞ ወጣቶቹ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የእውቀትና ክህሎት ክፍተት ሊገጥማቸው ይችላል።
ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት በተለይ ደግሞ ወጣቶች በከተማ ግብርና፣ በወተት፣ በዶሮ ርባታ እና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ሲሰማሩ ሊገጥማቸው የሚችለውን የእውቀትና ክህሎት ክፍተት ሊደፍን የሚችል Skill Ethiopia ወይም ‹‹መስራትና ስራ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶችን ኢትዮጵያ ታፈራለች›› የሚል ፅንሰ ሃሳብ ያለው የስልጠና መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል።
ዶክተር አቡኑ አንዳርጌ የዚህ ስልጠና ፅንሰ ሀሳብ አመንጪና የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ስልጠናው በእንስሳት እርባታ ዙሪያ የሚያተኩር ሲሆን ስቲም ፓወር ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአምስት አመታት ተግባራዊ የሚሆንና ከ አስር ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
የስልጠናው ዋነኛ አላማም ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ የእንስሳት እርባታ እንዲያካሄዱ፣ የእንስሳት እርባታ ዘርፉን እንዲያዘምኑ፣ የምግብ ዋስትናን እንዲረጋገጡ፣ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ነው። ስልጠናው ከዚህ ባለፈ በዘልማድ የሚሰራውን የዶሮ እርባታ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ማድረግ፣ የመንግስት የልማት አቅጣጫዎችን መደገፍ ከውጪ የሚገባውን ምርት ማስቀረት እንዲሁም ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጪ ገበያ እንዲተርፍ የማድረግ አላማም አለው። የመንግስትን የልማት አቅጣጫን በተለይ ደግሞ ‹‹የሌማት ትሩፋት›› መርሃግበርን የሚደግፍ ዓላማንም ሰንቋል።
ከነዚሁ ዓላማዎች በመነሳት በአምስት አመታት ውስጥ ለ 10 ሺ ወጣቶች በከተማ ግብርና፣ በወተት፣ በዶሮ ርባታ እና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት እቅድ ተይዟል። በስልጠናው መርሃ ግብርም የሚታቀፉት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ወጣቶች ሲሆኑ በአስር ዙር አንድ ሺ ሰልጣኞች የሚስተናገዱ ይሆናል። በአምስት አመታት ውስጥ በነዚሁ ዘርፎች 10 ሺ ወጣቶች ስልጠናውን ያገኛሉ።
ስልጠናውን ለመከታተልም ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የስቴም ፓወር ዋና ቢሮ እና ቢሾፍቱ በሚገኘው የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ቢሮ በአካል በመገኘት ምዝገባ ማከናወን ይችላሉ።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ስልጠናው ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የስቲም ፓወር የስልጠና ማእከላት ውስጥ ይካሄዳል። ወጣቶቹ ስልጠናውን ከተከታተሉ በኋላ በዘርፉ በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። የራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲያመነጩም ያግዛቸዋል። ግዚያቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤት ለማምጣትም ይረዳቸዋል።
ከዚህ ባለፈ ስልጠናው ወጣቶች ብዙም ባልተነካው የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ እንዲገቡ ከማስቻሉም በላይ ሌሎች በዚሁ ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማትም እንዲነቃቁና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያደርጋል። ወጣቶች ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ አካል ጉዳተኞችንም ጭምር እንደፍላጎታቸው ስልጠናውን ተከታትለው ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ወጣቱ ይህን ስልጠና ወስዶ በዚህ ዘርፍ የራሱን ስራ መፍጠር ከቻለ ደግሞ ለሀገራዊ ሰላምና ደህንነት የሚኖረው አስተዋፅኦም ቀላል የሚባል አይደለም።
የስቴም ፓወር ኢትዮጵያ ሃላፊ ዶክተር ስሜነው ቀስቅስ በበኩላቸው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ከ 44 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከ60 በላይ የሚሆኑ የስልጠና ማእከላትን በመገንባት በዘመናዊ ቤተ ሙከራ የታገዘ ትምህርት እንዲሰጥ እያደረገም ይገኛል።
በተጨማሪም የስራ ፈጠራ ሙያ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በዘርፉ የሚያጋጥማቸውን የቢዝነስ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለማሳደግ የኢንትርንሺፕና የፋይናነስ ትምህርት ስልጠና ፕሮግራም እየሰጠ እንደሚገኝና አሁን ደግሞ ይህንኑ ልምዱንና ተሞክሮውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በእንስሳት ሃብት ልማት ዙሪያ ከትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር ስልጠና ለመስጠት ተስማምቷል።
በስምምነቱ መሰረት ድርጅቱ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ አስር ሺ የሚሆኑ ወጣቶችን በተለያዩ የእንስሳት ልማት ዘርፎችና ዙሮች በራሱ የስልጠና ማእከላት በነፃ በማሰልጠን ወደስራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል።
አብዛኛው የከተማ ግብርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑና በተለይ ደግሞ በእንስሳት ዘርፉ የሚሰራው ስራ ከሙያው ውጪ በሆነ ሰው ከመሆኑ አኳያ ይህን ለመለወጥ ድርጅቱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ እንዲሰራ ለወጣቶች በዘርፉ ላይ የክህሎት ስልጠና ለመስጠት ከትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ጋር ስምምነት አድርጓል።
ሃላፊው እንደ ሚሉት በአሁኑ ግዜ በርካታ ወጣቶች ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአመቱ ተመርቀው ይወጣሉ። ከዚህ አኳያ የስራ ፈላጊው ወጣት ቁጥርም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል።የዚያኑ ያህል ደግሞ በርካታ የግልም ሆኑ የመንግስት ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው መጠን የሰለጠነ የሰው ሀይል አላገኘንም ሲሉ ይደመጣል። በስራ ላይ የክህሎት ክፍተት እንዳለም ይነገራል።
ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት ድርጅቱ ከትረስት ኮንሰልቲንግ ጋር በመሆን የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የስራ ፈጠራ ክህሎትና የፋይናነስ አያያዝ ትምህርት ዙሪያ በአስር ዙር ለአንድ ሺ ወጣቶች ስልጠና ለመስጠት ተስማምቷል። በዚሁ ስልጠና ላይ ሙያዊ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚፈልጉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። ከዚህ አኳያ የስልጠናውን አቅም ማሳደግና ወጣቶች በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ክህሎት በማሳደግ የስራ እድል በራሳቸው ፈጥረው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል።
በስቴም ፓወር ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ አቤል ተፈራ እንደሚናገሩት ደርጅቱ ወጣቶች ቁጭ ብለው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ እድል ይሰጣል። ይህም ወጣቶቹ በልምምድ ውስጥ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል፤ ከተለመደው የስልጥና አሰጣጥ ሂደትም የተለየ ያደርገዋል። ከዚህ በዘለለ ወጣቶቹ ካገኙት ስልጠና በኋላ ያገኙት ስልጠና ወደመሬት እንዲወርድ በድርጅቱ በኩል የድጋፍና ክትትል ስራዎች ይሰራሉ።
ስልጠናው ከስደስት አስከ ዘጠኝ ቀናት የሚወስድ ቢሆንም ከስልጠናው በኋላ ወጣቶቹ ለሶስት ወራት ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል። ወጣቶቹ ወደ ስራ የሚገቡበትን መንገድም የማሳየትና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር ትስስር ፈጥረው የሚሰሩበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት ስራዎች ይሰራሉ።
በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር መሰረት በአምስት አመታት ውስጥ 10 ሺ የሚሆኑ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ወጣቶችን በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በማሳተፍ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ ውጥን የተያዘ ቢሆንም በቀጣይ ስልጠናው ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች የማስፋት እቅድ ተይዟል።
የምግብ ዋስትናን በሚመለከት የግብርናው ዘርፍ በተለይ የዶሮ እርባታ ዘርፍ በአነስተኛ ገንዘብና በትንሽ አውቀት ወደስራ ገብቶ ውጤታማና ትርፋማ መሆን የሚያስችል በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ ድርጅቱ ትኩረቱን አድርጎ በመስራት ለበርካታ ወጣቶች ተደራሽ የመሆን ፍላጎት አለው።
ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው ‘የሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብር ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን በእንስሳት፣ በዶሮ እና በማር ምርቶች በማትረፍረፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘውን ስኬት መድገም ነው።
የ’ሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ፤ በተለይ ስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ቅንጦት ሳይሆኑ ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማድረግ ነው።
የ”ሌማት ትሩፋት” መርሐ-ግብር የእንስሳት ተዋእፆ ምርት እምርታን ማረጋገጥ እና ከእምርታው ፍሬም የመቋደስ ግብ ከመሰነቁ አኳያ በዚሁ ዘርፍ ወጣቶች እንዲሰማሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚጋብዙ አውቀትና ክህሎትጨብጠው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት ስልጠናዎችን ለወጣቶቹ ማመቻቸት ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም