የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መንገዶችን ለመገንባት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከሚያስገነባቸው አስር አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከልም የባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ መንገዱ 120 ነጥብ 65 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውና በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባ መንገድ ነው፡፡ መነሻውን ከአዲስ አበባ በ437 ኪ.ሜ ላይ ከሚገኘው ባሌ ሮቤ ከተማ ያደረገው ይህ መንገድ ጊንር- ራይቱ-ኢሚ መገንጠያ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡
መንገዱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አበርክቶ እጅግ የጎላ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ነዋሪነታቸውን በባሌ ሮቤ ከተማ ያደረጉት አቶ ግርማ አባሴና ባሌ ትልቅና ሰፊ አገር መሆኗን በመግለጽ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡ ባሌ ከምግብ እህል በተጨማሪ በማዕድን ሃብቷ የታወቀች ብትሆንም በመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ሳትታወቅ መቅረቷንና የማዕድን ሃብቷንም አውጥታ መጠቀም እንዳልቻለች በቁጭት ይናገራሉ፡፡
አሁን ጅማሮውን ያደረገው የባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ መንገድ፤ የኦሮሚያ ክልልንና የሱማሌ ክልልን በማስተሳሰር ለአካባቢው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ፡፡ ለአብነትም ከዚህ ቀደም ገበያ ተነፍገው የቆዩ ምርቶችን በተለይም የቀንድ ከብቶችንና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ለገበያ ማቅረብ ያስችላል፡፡ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ገበያ የሚወጡ በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ማዕድናት ስለመኖራቸው ያነሱት አቶ ግርማ፤ አካባቢው ሲለማና መንገዱ ሲሠራ እነዚህን ማዕድናት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አገሪቷ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ትችላለች ይላሉ፡፡
የመንገዱ መገንባት እጅግ መሰረታዊና አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ ለባሌ ቀርቶ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል የመንገድ መሰረተ ልማት እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡ ለመጣውና ለሄደው መንግሥት ሁሉ ሲያነሱ እንደነበርና የዘመናት ጥያቄያቸው መሆኑን በማስታወስ ጥያቄው ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በአባቶቻቸውና በአያቶቻቸው ሳይቀር ተጠይቋል። ይሁንና ምላሹን በአሁን ወቅት በማግኘታቸው በእጅጉ ደስተኞች እንደሆኑና እርሳቸውን ጨምሮ ትውልዱ ዕድለኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
‹‹በአካባቢው የማይመረት ነገር የለም›› የሚሉት አቶ ግርማ፤ የመንገዱ መገንባት አካባቢውን በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከባሌ በቅርብ ርቀት ጨው ይመረታል፡፡ የሚመረተው ጨውም ለባሌ ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚተርፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የሰብል እህሎችን ጨምሮ ቡና፣ ቅመማቅመም፣ የቅባት እህሎች፣ ፍየሎች፣ በጎች፣ ከብቶችና ግመሎች ጭምር በአካባቢው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን መንገድ ባለመኖሩ ገበያውን በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በቀጣይ የአስፓልት መንገዱ ሲገነባ እነዚህ የአካባቢው ሃብቶች ገበያ ማግኘት ይችላሉ፡፡
ምርቶቹን ወደ ገበያ ለማውጣት ከፍተኛ ችግር የነበረው መንገድ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይፈታል የሚል ዕምነት ያላቸው መሆኑን አስረድተው የመንገድ ግንባታው ለባሌ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚተርፍ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በተለይም የአካባቢው አርሶና አርብቶ አደር በቀጣይ በሚያመርተው ምርት የልፋቱን ዋጋ ማግኘት ያስችለዋል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡
ለውጭ ገበያ የሚቀርበው በሞጆ ዘመናዊ ገበያ ውስጥ ለሚዘጋጀው የስጋ ምርት ግብዓት እየሆኑ ያሉት ከባሌ ቆላ አካባቢ የሚጫኑ በጎች፣ ፍየሎችና ከብቶች እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ግርማ፤ የአስፋልት መንገዱ ሲገነባ ገበያውን በስፋት ማሳለጥ እንደሚቻልና የአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
መንግሥት መንገዱ እንዲገነባ በጀቱን ማጽደቁና ሥራውን ማስጀመሩ የሚበረታታና የሚያስመሰግነው እንደሆነ በማንሳትም የአካባቢው ማህበረሰብ ደግሞ ሰላሙን በማስጠበቅ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ማህበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ትልቅ ሥራ መሥራትና ለመንገዱ መፋጠን የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
‹‹ማንኛውንም መሰረት ልማት መሥራት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው፤ ባሌዎች ደግሞ በዚህ አንታማም›› ያሉት አቶ ግርማ፤ ባሌ ሙስሊምና ክርስትያኑ ዋቄፈታው ጭምር በጋራ አብሮና ተባብሮ የሚኖሩበት በመሆኗ ሰላምን በማስጠበቅ መንገዱ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ በብሔረሰብም ቢሆን ባሌ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚኖሩባት እንደመሆኗ ለሰላም ሲባል ደግሞ አንድ ሆነው መቆም የሚችሉ እንደሆኑ ነው ያስረዱት፡፡ ባሌዎች ከዚህ ቀደም ሰላም በማጣት ወድቀው እንደሚያውቁና ከውድቀታቸው መማር እንደቻሉ በማስታወስ፤ ችግሩ እንዳይደገምና ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ቃል ተግባብተው በሰላም የሚኖሩ ህዝቦች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ግርማ ሁሉ የመንገድ ጥያቄው የዘመናት ጥያቄያቸው እንደነበር በማስታወስ ሃሳባቸውን ያካፈሉን በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ የመልዩ ቡርቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሃመድ ጦና ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት አካባቢው ከፍተኛ ምርት የሚወጣበት እንደመሆኑ ምርቶቹን ወደ ገበያ ለማውጣት መንገዱ ከፍተኛ ችግር እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ስንዴና ገብስን ጨምሮ አጃ፣ ጤፍ፣ ሽንብራና ሌሎች የሰብል አይነቶች የሚመረቱ እንደሆነና እርሳቸውም እነዚህን ምርቶች እንደሚያመርቱ የተናገሩት አቶ ሙሃመድ፤ አብሽ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ነጭ አዝሙድና ሌሎች ቅመማቅመሞች የሚመረቱ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ምርቶቹን በቀላሉ ወደ ገበያ ለማውጣት መንገዱ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሸጠው ለነጋዴው ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ሳያደርገው ቆይቷል፡፡
እናቶችም በወሊድ ወቅት ወደ ህክምና ተቋም ሲሄዱ መንገዱ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ያነሱት አቶ ሙሃመድ፤ በዚህም በርካታ እናቶችና ህጻናት ተጎጂ ሆነው መቆየታቸውን ነው ያስረዱት፡፡ ስለዚህ የመንገዱ መገንባት ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህም እጅግ ደስተኞች እንደሆኑ ገልጸው ለመንገድ ግንባታው መፋጠን ማህበረሰቡ ሰብል በማንሳትም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ተባባሪ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መንገዱ የአስፓልት መንገድ የሌለውና እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሁለትና ሶስት ቀናት መንገድ ላይ ሲያሳልፉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአንድ ቀን አዲስ አበባ መግባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የመንገድ ግንባታው በአካባቢው ለሚገኘውና የቱሪስት መስዕብ ለሆነው የሶፍኡመር ዋሻም ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት እንደሆነና የመንገድ ግንባታው ለባሌ ብቻ ሳይሆን ለአገር ጉልህ ድርሻን ያበረክታል ብለዋል፡፡
በመንገድ ጅማሮው ተገኝተው የመንገድ ሥራውን በይፋ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የመንገዱ መገንባት ለባሌ ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እጅግ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የመንገዱ መሠራት በብዙ የተፈጥሮ ሃብት የታደለችው ባሌ ያላትን እምቅ ሃብት አውጥታ መጠቀም ያስችላታል፡፡ በአካባቢው የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶችም በቀላሉ ወደ ገበያ መውጣት የሚችሉ ይሆናል፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
ኦሮሚያን ማልማት ኢትዮጵያን ማልማት እንደሆነ በመጥቀስም በባሌ ውስጥ ያለው ዕምቅ ሃብት ጥቅም ላይ መዋል ከቻለ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች፡፡ የቱሪዝም መዳረሻ የሆነውና በዚሁ አካባቢ የሚገኘው የሶፍኡመር ዋሻን ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ ለአገር አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በስንዴ ምርቷ በብዙ የምትታወቀው ባሌ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በአሁን ወቅትም እንደ አገር ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ በሚደረገው ጥረት በስንዴ ምርቷ የምትታወቅ ባሌ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላት ሲሆን የመንገድ ግንባታውም የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው መንገዱ ለአካባቢው ማህበረሰብ እጅጉን ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ነዋሪዎች ለግንባታው መፋጠን የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል። እሳቸው እንዳሉት ማህበረሰቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ በሚያደርገው ጥረት ልክ ለፍፃሜውም መትጋት አለበት። በትናንሽ እንቅፋቶች ወደ ኋላ መቅረት የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ በባሌ አካባቢ ያለውን ዕምቅ ሃብት አውጥቶ ለመጠቀም የመንገዱ መገንባት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ የአስፓልት መንገዱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመት የሚጠይቅ ሲሆን አጠቃላይ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በቂ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ባሌ ያሏትን በርካታ ጸጋዎች አውጥታ መጠቀም አልቻለችም፡፡ ነገር ግን የመንገዱ መገንባት ከዚህ በኋላ በርካታ ትሩፋቶችን ያመጣል፡፡ በተለይም የአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ ይሆናል። በአካባቢው ካለው የማህበረሰብ አካል በተጨማሪም እንደ አገር የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል፣ በየአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮችና ከተሞችን እድገት ያፋጥናል፡፡ በተጨማሪም የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲስፋፉ ከማድረግ አንፃር የእነዚህ መንገዶች መገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል ብለዋል፡፡
የባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ የአስፓልት መንገድ፣ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር 8-10 ሜትር ስፋት ሲኖረው፣ በቀበሌ የመንገድ ትከሻና የመንገድ አካፋይ ጨምሮ 13 ሜትር ስፋት፤ በወረዳ የመንገድ አካፋይና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 21 ሜትር ስፋት በዞን የመንገድ አካፋይ፣ የእግረኛ መንገድና የመኪና ማረፊያ ጨምሮ 28 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
መንገዶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት በሚጀምሩበት ወቅት በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችንና ወረዳዎችን እርስ በርስ በማስተሳሰር ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል።ከዚህም ባሻገር የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን በማድረግ መንገድ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክትን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያስገነባቸው መንገዶች ካላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል፡፡ በመሆኑም የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠናቀቅ እንዲችሉ በአካባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዥ በሆኑ ጉዳዮች ለሚፈጠሩ ማናቸውም እንቅፋቶች ማህበረሰቡ ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አሳስቧል፡፡
በባሌ ሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መገንጠያ የአስፓልት መንገድ፣ ግንባታ ጨረታ ተወዳድሮ በብር 8,798,168,439.12 በማሸነፍ የውል ስምምነቱን የፈረመው ቻይና ኮምዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ድርጅት የውጭ ሥራ ተቋራጭ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የመንገዱ ግንባታም በሶስት አመት ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015