ፊት ለፊት መተያየት ትርጉሙ ብዙ ነው፤ አንድን ወገን ፊት ለፊት ማየት ደስታውንም ሀዘኑንም ለመረዳትም ሆነ ለመጋራት እድል ይሰጣል፡፡ ፊት ደግሞ ብዙ ይናገራል፤ መናፈቁን፣ መከፋቱን፣ መራራቱን ሆነ መጨነቁንም አይደብቅም፡፡ ፊት ለፊት መተያየት የውስጥን ትኩሳት ለመረዳት ያስችላል፡፡
ፊት ለፊት በመተያየት ከሳህ/ከሳሽ፣ ጠቆርክ/ ጠቆርሽ፣ ተመቸህ/ተመቸሽ ለመባባልም በሁለቱ ወገኖች መካከል መፈላለግ ወይም መነፋፈቅ ሊኖር የግድ ይላል፡፡ ሰው በጠላትነት ከተፈራረጀ ፊት ለፊት ተያይቶ ስሜት ለስሜት መናበብ አይችልም። ሰላም ለእናንተ ይሁን የመባባል አቅምም አይኖረውም፡፡
ገጽ ለገጽ መታያየት አንዱ የሌላውን ስሜት ተረድቶ የቸገረን ነገር በአብሮነት መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል፡፡ይሑንና ፊት ለፊት ለመተያየትና ለመተዛዘን ያስችል ዘንድ የሚከፈል መስዋዕትነት አለ፡፡
አንዱ ሌላውን በርህራሔ ለማየት የሁለቱንም ወገን እሽታ ይሻል፤ በሁለቱም ወገን ወደእሽታ ለመምጣት ደግሞ ኩራት ቢሆን ጀግንነት፣ አሸናፊነት ቢሆን ማን አለብኝት ጥጋቸውን ሊይዙ የግድ ነው፤ እብሪት ይሁን ግድየለሽነትም ድራሻቸው ሊጠፋ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ አይነቱን የማይበጅ ስሜት ለማጥፋት ቁርጠኝነት የአንበሳውን ድርሻ ይጫወታል።
ከሰሞኑም የሆነውም ይኸው ነው፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ ማቅናቱ ይታወሳል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ የመጓዙ ምስጢር ወገን የሆነውን የትግራይ ሕዝብና የሕወሓት አመራሮችን ፊት ለፊት ለማግኘትና የሰላም ስምምነቱን ማጠንከርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም እርግጥ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ አገር በብዙ ተፈትናለች፡፡ በርካታ ዋጋም ከፍላለች፡፡ እንዲያው ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ…›› ይሉት አይነት ነገር ሆኖ እንጂ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈትነዋል። የመከራ ጽዋንም ለመጎንጨት ተገደዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ልክ እንደ መሰረት ልማት የመልሶ ጥገና የማይደረግለት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት እንደዋዛ ረግፏል፡፡
መንግስት የቱንም ያህል ተገድዶ የገባበት ጦርነት ቢሆንም የዜጎችን ነጻነት ለመጠበቅ ሲል በብዙ ማስኗል፡፡የአገር ኢኮኖሚ በእጅጉ ተጎድታል። ከምንም በላይ ወንድም በወንድሙ ላይ ሰንዝሯል።
ጦርነት በሽታ ነው፡፡ የአገርን ደምስር ይበጣጥሳል፡፡ ጦርነት ቀጣፊ ነው፤ የሰውን ይሕወት ያጭዳል፡፡ጦርነት ወረርሽኝ ነው፡፡ ከአንደኛው ወገን ወደሌላኛው ወገን ያለርሕራሔ ይዛመታል፡፡
በአንጻሩ ሰላም እስትንፋስ ነው፡፡ በሕወት እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ሰላም ተድላ ነው፡፡ ከሁሉ ጋር በደስታና በፍስሃ እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ሰላም መንገድ ነው፡፡ ወደወደድነው እንድንጓዝ ይረዳናል፤ የናፈቅነውንም ፊት ለፊት እንድናይ ያበረታታናል፡፡
በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው ልዑክ ይህንኑ ሰላም ይዞ ወደ መቀሌ ባቀናበት ወቅት ከክልሉ ነዋሪ ጋር ገጽ ለገጽ ከመተያየት ጎን ለሁለት ዓመታት ዘልቀው የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት አልቦዘነም፡፡ ፊት ለፊት ከመተያየትም ሆነ ከቃላት በዘለለ በተግባር በርካታ ነገሮች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ ብዙ ስራም ተጀምሯል፡፡
የፌዴራል መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠትም በአገሪቱ የመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛውን ሚና በወጣት ረገድ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ናቸው የተባሉት የተለያዩ ታላላቅ ተቋማት ኃላፊዎች በስፍራው እንዲገኙ አድርጓል፡፡
‹‹ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃል…›› ይሉት ነገር እንዳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መንገድ ባለስልጣን እና ሌሎችም አንጋፋ ተቋማት ኃላፊዎች በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በተመራው ልዑክ ውስጥ ተካተው በመቀሌ ተገኝተው በአይናቸው በብረቱ ፊት ለፊት ወገናቸውንም የደረሰውንም ፈተና ተረድተው መላ መላ እንዲሉ መደረጉ የመንግስትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት አመላካች ነው፡፡
በዚህ መልኩ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የደረሰውን ችግር እርስ በእርስ ተደጋግፎ በመፍታት ወደ ቀጣዩ የሕይወት መስመር ለመምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያውያን ደጆች ሰላም እየሸተተ ነው፡፡ ይህን ሰላም ይበልጥ ለማስቀጠል ደግሞ የሁሉንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
ሰላም ሰጪና ተቀባይ የለውም፡፡ በጋራ ለጋራ ሲባል ዓላማ ሲሰራ ግን ፍሬውም እጅግ ጣፋጭ ይሆናል፡፡አንዱ ሰላም ሰጪ ሌላው ደግሞ ሰላም ተቀባይ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰላም በመተባበርና በመግባባት የሚመጣ ሲሆን ጣዕሙም የጋራ ይሆናል።
ጦርነት ጥሎ ያለፈው የአካል ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ጠባሳም ጭምር ነው፡፡ ጦርነት የብዙዎችን ሕይወት የበላ ሰለሆነ መራር ሀዘኑን አሸክሞ አልፏል፤ ጦርነት እሳት ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም፡፡
ኢትዮጵያ ደጅ መታየት የጀመረው ሰላም ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ ሁላችንም ለሰላም የየበኩላችንን እናበርክት፡፡ ያለሰላም አንዲት እርምጃ መራመድ ከባድ እንደሆነ ያለፉት ሁለት ዓመታትን ብቻ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ ሰላም ሊታጣ የሚችለው በጦርነት ብቻ እንዳልሆነም መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በአጠገባችን ያለውን አለመግባባት እንደዋዛ አይተን የምናልፍ ከሆነ ነገ አድጎ ለጦርነት እንደሚጋብዘን መረዳት መልካም ነው፡፡ መረዳት ብቻ ሳይሆን ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት ማሳየትም ተገቢ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ ምድር የእያንዳንዱ ደጅ ሰላም ይሆን ዘንድ በጋራ መስራት ለትውልድ የሚተርፍ በጎ ተግባር መሆኑን ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል፡፡
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015