የመጀመሪያ ዲግሪውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ ነው ያገኘው። ይሁንና ለጥበብ ባደረበት ትልቅ ፍቅር ምክንያት ይሰራበት ከነበረው የልማት ድርጅት በመተው ለአራት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የስነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ክፍል በስነ ቅብ ሌላ የመጀመሪያ ዲግሪ እና የማስተርስ ዲግሪውን ሰርቷል፡፡ ላለፉት 11 ዓመታት በተለያየ የትምርት ተቋማት በመምህርነት ያገለገለው ይህ ወጣት ከእነዚህም መካከል ዩኒቲ ዪኒቨርሲቲ እና የተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አርቴክቸር ትምህርት ክፍል መምህርነት እያገለገለ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም ባህርዳር ከተማን በስነ-ጥበብ የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ አልሞ በራሱ ተነሳሽነት ከፍተኛ ሥራ እየሰራ የሚገኝ ብርቱ ወጣት ነው፡፡
በሥዕል እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ለሌች ወጣቶች አርአያ የሆነውም መምህር እያዩ ገነትን የዛሬው ለወጣቶች አምዳችን እንግዳ አድርገነዋል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእይታ ጥበብ ማለት ምን ማለት እንደሆነና በሥሩ ምን ምንን እንደሚያካትት ግለፅልንና ውይይታችንን እንጀምር?
መምህር እያዩ፡– ጥበብ እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ምድር ላይ መኖር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ራሱን ለመግለፅ፤ ለመግባባት፤ ለመነጋገር እንደዚሁም በልቡና በምናቡ ያለውን ነገር ከተደራሲው ወይም ደግሞ ከሚያነበው፤ ከሚያደምጠው ጋር ለመግባባት የሚያስችል ለሰው ልጅ የተሰጠ መለኮታዊ እውቀት ነው።የሰው ልጅ ቋንቋ ከመፍጠሩ በፊት በምስል ነው ይግባባ ነበር።ስለዚህ እኔም የእይታ ጥበብ ሲባልም ጥበብ ብዙ ዘውግ ቢኖረውም ከዚያ መካከል የሚታይ፤ ታይቶም የሚተነተን፤ ትናትን፤ ዛሬንና ነገን የሚያገናኝ፤ አንድን ነገር የሚጠቁም፤ የሚሞግት ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ያለህን ተሰጥኦና ሙያ በመጠቀም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ማከናወንህ ይታወቃል፤ እስቲ ስለእነዚህ ስራዎቹ በጥቂት አብራራልን?
መምህር እያዩ፡– እንዳልሽው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ውስጥ ተሳትፌያለሁ።ከእነዚያ መካከል ጎልተው የሚወጡት ለምሳሌ የአርትስኩል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ባህርዳር ምንምአይነት የአርት ተቋም ስለሌለ አብዛኛው ተሰጥኦ ያለው ወጣት እድሜው ሲደርስ እያዘነ ለጊዜው እጁ ላይ ባገኘው የትምህርት ዘርፍ ነው የሚገባው።በተለይም እኔ ያንን ባደረኩባቸው ጊዜያት ከባህርዳር ብዙ ልጆች ስለሚመጡ ምን የተለየ ነገር አለ? የሚል ጥያቄ ይፈጠርብኝ ነበር።ከዚያ የተነሳ ቢያንስ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እኔ ያገኘሁትን እድል ማግኘት አለባቸው በሚል የባህርዳር ሁለገብ ሞዴል የወጣት ማዕከል በሰጠኝ ሶስት ሺ ብር ድጋፍ ብዙ ቁሳቁስ ገዝቼ ለሁለት ዓመታት 80 ወጣቶችን በክረምት አሰልጥኛለሁ። ከእነዚህም መካከል አስር የሚሆኑት አሁን ላይ አርትስኩል መግባት ችለዋል።
ሙያዬን ተጠቅሜ ህዝብን ላገለግል የምችልባቸው እድሎች ሳገኝ ወደኋላ አልልም።ያሉትን እድሎች ሁሉ በመጠቀም ወገኖችን ማገዝ ያስደስተኛል።ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ባነሳልሽ ወንፈል ኤድ የሚባል ድርጅት አማራ ክልል ገጠራማ እና ምንም አይነት እድል በሌላቸው አካባቢዎች ለምሳሌ ሰቆጣ አካባቢ በሚገኙና ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ለሚማሩ ህፃናት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለመስራት ታስቦ እኔም በክፍያ እንዳግዛቸው ከተስማማን በኋላ ሁኔታውን ሳያው በጣም የሚያሳዝን ስለነበር እኔ ራሴ በነፃ ድጋፍ አደረግኩላቸው።የሚገርምሽ ያ ስዕል ከ40 ሺ ዶላር በላይ ተሸጦ ያንን ዓለማ ደግፏል።ይህም በህይወቴ በጣም ከተደስትኩባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
ከዚህም ባሻገር የስነ-ጥበብ የስነ ልቦና ህክምና በተመለከተ በተለይ ችልድረን ፈንድ ኦፍ ካናዳ ከሚባል ተቋም ጋር በተለያየ ቀውስ ውስጥ ያሉ ልጆችን ለአንድ ወር በሚሆን ስልጠና ህመማቸውን እንዲያወጡ፤ ስሜታቸውንና ራሳቸውን እንዲገልፁ በማድረግ የበኩሌን አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ። ኮቪድ በተከሰተበት ወቅትም ዶክተር ዮርዳኖስ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ውስጥ ያለውን ችግር ገለፀችልኝና እኔም ለማገዝ ተስማማሁ።ግን የተወሰነ የቀለም በጀት ብቻ ነው የተገኘው፤ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በሆስፒታሉ በሚገኙ ሙሉውን የህፃናት ክፍልና ኮሪደር በነፃ አስውቢያለሁ።
ልጆች በተለያየ የጤና ችግር ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሲመጡ የስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ስለማያገኙና አብዛኛው ሆስፒታል ገፅታ ለእይታ የማይማርክ በመሆኑ የስቃይ ቦታ አድርገው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው።ነገር ግን ሆስፒታል የስቃይ ቦታ ሳይሆን ስቃይ የሚታከምበትና የሚድንት ቦታ ነው። ለዚህም ነው ሃሳቡ ሲቀርብልኝ ሳላንገራግር ስራ የጀመርኩት፤ ግን ደግሞ የሚሰራው በብረት ቀለም ስለሚሰራ ሽታው ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብኝ ነበር።ሆኖም እግዚአብሔር ረድቶኝ ሰርቼ አሰርክቤያቸዋለሁ።አሁን ከገጠር የሚመጡ ሰዎች ያንን ስዕል እያዩ የሚሰጡት ግብረመልስ በጣም የሚያስደስት ነው።እንዲህ አይነትና መሰል ስራዎች በስፋት አከናውኛለሁ።
በተጨማሪም የባህርዳርን ኮሪደሮችን ለማስዋብ ከፍተኛ ጥረት አድርጊያለሁ።ባህርዳር የቱሪዝም ከተማ እንደመሆንዋ ፐፕሊክ አርት ያስፈልጋል፤ ባዶና ትልልቅ ግድግዳዎች በስነ-ጥበብ መሞላት አለባቸው በሚል የአማራ ብልጽግና ፅህፈት ቤት ግድግዳ ላይ 70 ሜትር በሶስት በሜትር በሚሆን ስፍራ ላይ ለይኩን ወንዲፍራው ከሚባል ሰዓሊ ጋር በመሆን ባህሉን በሚያጎላ መልኩ ታይምለስ የሆነ ስዕል በሞዛይክ አብረን ሰርተናል።ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ባህላዊ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስራዎችን ሰርቻለሁ።በከተማዋ ባሉ ኮሪደሮች ሁሉ የአገሪቱ ታሪክ፤ ወግ እንዲታይ ሰው እየተዝናናም በሚያየው ነገር ከባህሉ ጋር እንዲገናኝ ጥረቶችን አድርጊያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ሥነ- ጥበብ ዘርፍ ለአገር ያለውን ጠቀሜታ በሚመለከት ማህበረሰቡ መረዳትን እንዴት ትገልፀዋለህ?
መምህር እያዩ፡- በዚህ ረገድ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አድጓል ብዬ አላምንም፤ እርግጥ ነው በመንግስት ደረጃ ለስነ- ውበት የተሻለ አረዳድ እየመጣ ነው።ግን ያ አመለካከት እያንዳንዱ ክልሎችና ከተሞች ድረስ አልወረደም። በተለይም እንደባህርዳር አይነት በታሪክም፤ በተፈጥሮም የታደለች ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሙዚየም ያለመኖሩ ለዘርፉ የተሰጠውን ዝቅተኛ ቦታ ያሳይሻል።በዚህ ውብና የጥበበኞች መፍለቂያ ከተማ አንድ የጥበብ ኮርነር አለመኖሩ በግሌ ያሳዝነኛል።በዚህ ከተማና ዙሪያዎቿ ባሉ ገዳማት ሃይማኖታዊ እሴታቸው እንዳለ ሆኖ ወደ ውስጥ ጠልቀሽ መጨረሻ ላይ የምታይው ግን የአባቶችን መንፈሳዊ ስዕሎች ነው።ለቱሪስቱ ያንን አሳይተሽ አሁን ደግሞ ያሉ ጠቢባን ይህንን ይሰራሉ ማለት ካልቻልሽ የትውልድ ክፍተት አለ ማለት ነው፤ ለተመልካቹም የቀደመው የስነ-ጥበብ ቅርሳችን እውነት አይመስልም።ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ዘርፉ ያለውን አገራዊ ጠቀሜታ በሚመለከት ንቃተ ህሊና አለ ለማለት አያስደፍሩም።
በግልና በተበታተነ መንገድ ሰዓሊው ወይም የጥበብ ባለሙያው ከሚጥረው ውጪ ለመደገፍ፤ የበለጠ ያንን ነገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመውሰድ፤ በተለይ የቱሪስቱን ቆይታን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት እምብዛም ነው። እኔም በራሴ ተነሳሽነት እየሰራሁ ያለሁት አንዱ ስራ የቱሪስቱን ቆይታ የሚያራዝሙ የስነ-ጥበብ ሥራዎችን ላይ የሚያተኩር ነው። በአንድ ሰዓት ውስጥ ባህርዳርን ጥሎ ሊወጣ የሚችል ቱሪስት ምሳ የሚበላበት ቦታ ላይ እዛው እንዲቆይ የሚያደርጉ የጥበብ ስራዎችን ማየት አለበት ብዬ አምናለሁ።ለምሳሌ አንድ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ የማውቀው ሰው የእኔ የጥበብ ስራዎች ለማየት ከቤልጂየም ባህርዳር ድረስ በመምጣት ስዕል ገዝቶኝ፤ የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኝቶና አንዳንድ ባህላዊ እቃዎችንም ጭምር ገዝቶ ነው የሄደው።ይህ የሚያሳይሽ በአንድ ሰዓሊ ምክንያት አንድ ሰው ሃብት ይዞ መጥቶ እዚህ አውጥቶ መመለስ ማለት ለአገር ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች የሚያበረታታ የትምህርት ስርዓት ያለመኖሩ ለጥበቡ ያለማደግ ምክንያት እንደሆነ ይነሳል።አንተ በዚህ ሃሳብ ትስማማለህ?
መምህር እያዩ፡- አዎ፤ እንግዲህ ሁሉም ነገር ከመሰረቱ ጋር ይገናኛል።በየትኛውም ሙያ የመጨረሻው ፍሬ የሚወሰነው ዘሩ ላይ ነው።ዘሩ ላይ ልክ ያልሆነ ነገር ካለ ያንን ተከትሎ ስለሚበቅል የተስተካከለ ፍሬ አንጠብቅም።በተለይም ደግሞ አንድ ሰው ዝንባሌው ባለበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሲሆን ነው ውጤታማ የሚሆነው።ፈጣሪ የሰጠውን ተሰጥኦ ነው፤ ሊሰራ የሚችለውና የሰራው ነገር ደግሞ በሌሎች ሲታይ የሚስብ፤ የሚማርክ ነው።ነገር ግን ሰው ችሎታው እንኳን ቢኖረው ልቡ በሌለው ነገር ላይ ከሆነ አንድ ጊዜ ከማድረግ በዘለለ ብዙ ጊዜ ሊያደርገው አይችልም።ከዚህ የተነሳ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።ስለሆነም ከመሰረቱ መታሰብ አለበት ብዬ አምናለሁ።ማህበረሰቡም በአብዛኛው ልጆቻው ዶክተር፤ ኢንጅነር ወይም ፓይለት እንዲሆኑለት ነው እንጂ የሚፈልገው ሰዓሊ እንዲሆን አይፈልግም።ምክንያቱም ሰዓሊ በማህበረሰቡም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን የሚወከልበት መንገድ መጥፎ ነገር ስለሚበዛው ነው።
አንድ ወጣት ሰዓሊ ከሆነ ሱሰኛ ይሆናል፤ ወይም ራሱን የሚገልፅበት መንገድ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይሆናል የሚል ፍራቻ ስላለ ችሎታ እንዳለው እያወቀ መቀበል አይፈልግም።ግን እውነቱን ለመናገር እንደፈረንሳይ ያሉ አገራት ሞናሊዛን የመሰለ አንድ ስዕልን ለማየት በየአመቱ 40 ሚሊዮን ሰው ወደ አገሪቱ ይሄዳል።ያ ብቻ አይደለም፤ በቆይታው ሆቴል ይይዛል፤ ለምግብ ያወጣል፤ ሌሎችን ነገሮችን ይግዛል።ያም ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።ከዚህ ጋር ተያይዞ እኔም ፈረንሳይ በተካሄደ የአርት ፌስቲቫል ላይ ተካፍዬ አውቃለሁ።
እኔ አገርን ወክዬ ስሄድ ብሔራዊ ባንክ ከ200 ዶላር በላይ ማቅረብ አንችልም ብሎኝ ያቀድኩትን ሁሉ መፈፀም ሳልችል ቀርቻለሁ።በወቅቱ ተቀባይነት ለማግኘት የግድ ሯጭ መሆን አለብኝ ወይ? ብዬ በጣም አዝኜ ነበር።በዚያ ዓለም አቀፍ መድረክ አገሬን አስተዋውቄ ስመጣ አበባ መስጠት ቢቀር ትንሽም ቢሆን እውቅና ያለመሰጠቱ አሳዝኖኛል።ከዚህ አንጻር ልጆችን ልክ እግር ኳስ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ የስነ-ጥበብ ፕሮጀክቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን ማስተማር ፋይዳ አለው።
በተጨማሪም በየከተሞቹና ገጠሩ ማሰልጠኛዎች ሊከፈቱና ማንኛውም ተሰጥኦ ያለው ወጣት ወደዚህ ኢንዱስትሪ መምጣት አለበት ብዬ አምናለሁ።ይሄ እየሰፋ ሲሄድ ለቱሪዝም እድገት የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረዋል።ምክንያቱ ስነ-ጥበብ አለማቀፍ ቋንቋ ነው።ስለዚህ የትም አገር ያለ ሰው ሊግባባት የሚችል ነው።ስለሆነም ከኬጂ ጀምሮ በሙዚቃ፣ በስነ-ጥበብ፣ ቲያትር ነክ ነገሮች ማጠቃለያ እነሱን አቅም የሚያሳድጉ ነገሮች በፖሊሲም ደረጃ መኖር አለባቸው ብዬ ነው የማስበው።
እርግጥ ነው፤ ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ስነ-ጥበብ ሙያ እንዲገቡ የማይፈልጉበት ምክንያት በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ነው።በአብዛኛው ከባህል አንፃር በሚዲያም፤ በፊልሞችም ሰዓሊዎች የሚገልፁት ለምሳሌ አንድ ወላጅ ልጁ ልክ እንደ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ከሆነ ሰዓሊ መሆኑን ላይጠላው ይችላል።ምክንያቱም እሳቸውን በማህበረሰቡ ዘንድ የገነኑበት መንገድ በጣም ትልቅ ስለነበረ ነው።በተጨማሪም ለስዕል ሙያ መከበር ትልቅ ሚናም ስላበረከቱ በዚያ ምክንያት አብዛኛው ሰው ለእሳቸውና እንደእሳቸው ለሚሆን ሰዓሊ ክብር አለው።ግን ደግሞ ሁሉንም ባለሙያ በደምሳሳው እንደሱሰኛ የሚፈረጁበት ሁኔታ አለ።
አሁንም ድረስ በስዕል ማደግ ይቻላል ብሎ ለማሰብ የሚሰጋው ሰው ቁጥር ቀላል አይደለም። ግን ይሄ መጨረሻ መታሰብ የሚገባው ጉዳይ እንጂ የመጀመሪያ ሊታሰብ የሚገባው ምንድን ነው አቅሜ ወይም ችሎታዬ ብሎ ነው።ስነ-ጥበብ ማለት ስዕል መሳል ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ እኔ ስዕል ብቻ አይደለም የምሰራው፤ ጎን ለጎን ለመማሪያ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ኢሉስትሬሽኖች እሰራለሁ።ያንን ማድረግ ስዕል ከመሳል ጋር አይጋጭም።ገቢ ማግኘት የሚያስችል ተዛማች የሆኑ ስራዎች መስራት ይቻላል። እኛም ቢሆን ይሄነው ብለን የሚብለጨለጭ ወይም የምናሳየው ሃብት ባይኖረንም በሙያችን የምንወደውን እና የምንፈልገውን ነገር ሆነን እየኖርን ነው።ስለዚህ ስነ-ጥበብ የገቢ ምንጭ አይሆንም የሚለው አስተሳሰብ ስጋት እንጂ ተጨባጭ ሁኔታን አያሳይም ለማለት እወዳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
መምህር እያዩ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015