ናትናኤል ከፍያለው በአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈተና ወስዶ ውጤት እየተጠባበቀ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ ህፃናት ፓርላማ አባልም ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል።
ቀደም ሲል እርሱ ሲማር በነበረበት ወቅት በአብዛኛው የመማር ማስተማር ሂደቱ መምህራን ተኮር ነበር። በእርሱ ጊዜ ከተማሪው ይልቅ የመምህራኑ ሚና ይጎላል። ትምህርቱ አብዛኛው የሚሰጠውም አስተማሪው በፈለገው መንገድ እንጂ በተማሪው ፍላጎት አይደለም። እርሱም በዚሁ የማስተማር ስልት ትምህርቱን ለዓመታት ሲከታተል ቆይቷል።
መምህራን በጨዋታ መልክና ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ-ዘዴን በመከተል ትምህርትን ለተማሪዎቻቸው ባለመስጠታቸው በተማሪ ናትናኤል የትምህርት አቀባበል ላይ እምብዛም ችግር አልተፈጠረም። ምክንያቱም ተማሪ ናትናኤል ሊገጠመው የሚችለውን ችግርም በራሱ ጥረት ለማለፍ ሞክሯል። እንዲያውም እርሱ የህፃናት ፓርላማ አባልና የክፍል ተወካይ በመሆኑ ትምህርት አሰጣጡ እንዲስተካከል አስተማሪዎችን የመጠየቅ እድሉ ነበረው።
ከዚህ በተቃራኒ ከእርሱ ጋር ሲማሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በተለመደው የአስተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ- ዘዴ ብዙም ተጠቃሚ አልነበሩም። መማር ማስተማሩ ተማሪዎችን ያሳተፈ አልነበረምናም በብዙ ተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል።
‹‹በቀጣይም ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ተመሳሳይ የማስተማር ስነዘዴ ይገጥመኛል የሚል ስጋት አለኝ›› የሚለው ተማሪ ናትናኤል፤ ይህ ሁኔታ ከቀጠለ እኔን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች በቀጣይ ምን አልባት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችሉ ይሆናል። እናም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከቀደመው የተሻለና ተማሪን ያሳተፈ የማስተማር ስነዘዴን ቢከተሉልን ሲል ሀሳቡን ያስቀምጣል። ለዚህም መምህራን ከተማሪዎቻውም ጭምር ሃሳብ መውሰድ እንደሚገባቸው ይጠቅሳል።
ተማሪ ናትናኤል አባል ሆኖ የሚሰራበት የአዲስ አበባ ከተማ የህፃናት ፓርላማ ድምፅ ለሌላቸው ህፃናት ድምፅ ሆኖ ያገለግላል። በተለይ ደግሞ በተለያየ መልኩ የጉልበት ብዝበዛ ለሚደርስባቸውና ትምህርታቸውን ለመከታተል ችግር ለሚገጥማቸው ህፃናት ወኪል ሆኖ ይሰራል። ህፃናት መብታቸውንና ግዴታቸውን በእኩል መንገድ እንዲያስኬዱም በተለያየ መልኩ ስራዎችን ያከናውናል። ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ-ዘዴ ተግባራዊነትም ፓርላማው በትኩረት የሚያየው ጉዳይ ነው።
ከተለመደው መምህር ተኮር የማስተማር ስነ-ዘዴ ለመውጣት ‹‹ፕሌይ ማተርስ›› የተሰኘ ጨዋታንና ተማሪን መሰረት ያደረገ የማስተማር ስነ-ዘዴ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ውስጥ ማለትም በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋርና ሱማሌ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እ.ኤ.አ በ2020 ይፋ ሆኗል።
ፕሮጀክቱም በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ እድሜያቸው ከሦስት እስከ 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ስደተኞችንና ስደት ተቀባይ ማህበረሰብ ልጆችን ተጠቃሚ አድርጓል። በኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቴ፣ዋር ቻይልድ፣ ፕላን ኢንተርናልና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ሲደገፍም ቆይቷል።
ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ጨምሮ በታንዛኒያና ዩጋንዳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችንና የስደት ተቀባይ ማህበረሰብ ልጆችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተነግሯል። ይህንኑ ፕሮጀክት በተለያዩ የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ለማስፋትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ብሎም በአዲሱ ስርአተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ትምህርት አመራሮች መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉቀን ንጋቱ እንደሚሉት፤ ፕሌይ ማተርስ ፕሮጀክት ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነዘዴን በመጠቀም የስደተኞችንና የተቀባይ ማህበረሰቡን ልጆች አጠቃላይ ትምህርትን፣ ደህንነትንና እድገትን ለማሻሻል ተሰናድቷል። ፕሮጀክቱ በዋናነት በትምህርት ላይ በተለይ ደግሞ መምህራንና ህፃናት ላይ አተኩሮ ይሰራል። ዋነኛ ዓላማውም በጨዋታ መልክ የማስተማር ስነዘዴ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻል ነው።
የማስተማር ስነ- ዘዴው በኢትዮጵያ በቅድመ መደበኛ ትምህርትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ተማሪን ማእከል ከሚያደርገው የትምህርት ስርአት ጋር አብሮ የሚጣጣም ነው። ስለዚህም በአዲሱ ስርአተ ትምህርት ተካቶ እንዲሰራበት በተለያዩ ደረጃዎች ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
መንግስትም የመምህራን ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴን የመጠቀም አቅማቸውን ለማሻሻል በአገልግሎት ላይ ላሉ መምህራን የቅድመ አገልግሎት ስልጠና እና ቀጣይነት ያለው የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና እድሎችን የማመቻቸት ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ይህም በተለይ ልጆችን ያማከለ ቴክኒኮችን በመጠቀም ትምህርቶችን በብቃት ለማድረስ የሚያስፈልጉ ዝቅተኛ የትምህርት ደራጃ ፣ስልጠናና የማስተማር ስነ-ዘዴ እውቀት ለሌላቸው በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ ላሉ መምህራን ጠቃሚ እንደሚሆን ተረጋግጧል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ የፕሌይ ማተርስ አካሄድ ስልታዊና ተቋማዊ እንዲሆን ለማድረግ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ባለበት አራት ክልሎች ትግበራ ላይ ባለው በተከታታይ የመምህራን ሙያ ማሻሻያ ፕሮግራም ውስጥ በመምህራን ልማት መርሃግብር፣ በመንግስት ተከታታይ ሙያዊ ልማት ማእቀፍ ውስጥ ተማሪ ተኮር ማስተማር ስነዘዴ ማካተት የሚቻልበትን እድሎች ይቃኛል፡፡
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉአለም ደስታ እንዲሚናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተዳድሩት ክልሎች ናቸው። መንግስትም የአካታችነት መርህን በመከተል ስደተኞች ከአካባቢው ስደት ተቀባይ ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋል። እየተደረገም ይገኛል።
በዚህ ሂደት ታዲያ በርካታ ውጣውረዶች አጋጥመዋል። ለአብነትም እስካሁን እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱት ህፃናት መካከል 46 ነጥብ 7 ከመቶው ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ብቻ ናቸው የትምህርት እድል እያገኙ ያሉት። ትምህርቱን ደግሞ ለሁሉም ስደተኞችና ጥገኞች ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ሃብት ይጠይቃል። መንግስትም ለስደተኞች የራሱ የሆነ በጀት የለውም፤ ሀብቱንም መሸፈን አይችልም። ከዚህ አኳ ያ በጀት እየተገኘ ያለው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽንና ሌሎች አጋር ረጂ ድርጅቶችን በመቀስቀስ ነው፡፡
በዚህ የፕሮጀክት ትግበራ ትልቁ ክፍተት የሀብት ችግር ነው። በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈንድ ለማፈላለግ እጅግ አዳጋች ነበር። ይህም በትምህርት አሰጣጡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶች ላይም አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል። ትምህርቱም በቀነሰ ቁጥር በትምህርቱ ሴክተር ላይ የሚፈጥረው የራሱ አንድምታ ይኖረዋል።
የትምህርት ምገባም የዚሁ ፕሮጀክት አንዱ አካል በመሆኑና ይህ ምገባ ሲቀንስ ተማሪዎች ምግብ የማያገኙ ከሆነ ከትምህርት ገበታቸው ይቀራሉ። ቤተሰቦቻቸውም የምግብ ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ ልጆቻቸው በሌላ የሥራ መስክ ላይ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። እናም ተማሪዎች ከትምህርታቸው ይሰተጓጎላሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት፤ ከ183 ሺህ በላይ ስደተኛና ጥገኝነት ጠያቂ ተማሪዎች በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ተቋምም ሆነ በክልሎችም ባሉ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
እንደአጋጣሚ ፕሮጀክቱ ስደት ተቀባይ ማህበረሰብ ውስጥም ጭምር ተግባራዊ ስለሚደረግ እነሱንም ይበልጥ ያሳትፋል የሚል ተስፋ አለ። ስደተኞቹ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነትና የኑሮ ዘይቤ ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን ፕሮጀክቱ በራሳቸው መንገድ ትምህርታቸውን በጨዋታ መልክ እንዲማሩ ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሙድ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፕሌይ ማተርስ የተሰኘው ፕሮጀክት የተጀመረው ህፃናት ትምህርታቸውን ወደው እንዲማሩ ነው። በተለይ ደግሞ በአራቱ ክልሎች የትምህርት ጥራት ጉዳይ ችግር ውስጥ ያለ በመሆኑ ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር ፕሮጀክቱ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በአራቱ ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢዎች ውስጥ ያሉ ስደተኛና ስደት ተቀባይ ማህበረሰብ ልጆች በአብዛኛው ማንበብና መፃፍ አይችሉም። የዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን ደግሞ በተለይ ልጆች በጨዋታ መልክ ትምህርቱን እንዲረዱት የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ፋይዳው የጎላ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ-ዘዴው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ቢገባ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን እውቀት ይጨምራል። ስለሆነም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የህጻናት ትምህርት ነውና ያሉትን ክፍተቶች ፕሮጀክቱ የሚያሟላ መሆኑን ያምናል። ስለዚሀም አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በህፃናት ላይ ለሚሰራው ሥራም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
እንደሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፤ ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱን ብቻ ሳይሆን እንደሀገር የአስር ዓመት እቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከአስር ዓመቱ እቅድ ውስጥ ደግሞ ራሱን የቻለ አዲስ መዋቅር አቋቁሟል። ይህንኑ መዋቅር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ በሚባለው ቢሮ ውስጥ በማካተት የአረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞችና ተጠቂ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈና የቤተሰብ ጉዳይ በዚህ ውስጥ ተካቶ እየተሰራ ይገኛል።
የህፃናትን ስብእና የመቅረፅ፣ ሀገራቸው ወደው የዲሞክራሲ ስርዓቱን ተለማምደው እንዲያልፉ በትምህርት ቤቶችና ክበባት ውስጥ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ የህፃናት ፓርላማዎችን የማቋቋም ሥራዎችም ተሰርተዋል። በዚህም ተስፋን ሊያለመልሙ የሚችሉና ትውልድን በአዲስ መልኩ የመፍጠር ሁኔታዎች እየታዩ መጥተዋል።
አስተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴ ረጅም ዓመታትን የተሻገረና በኢትዮጵያ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ሲደርግ የቆየ የማስተማር ስነ ዘዴ ነው። አሁን ጊዜው ተቀይሯል። ከአስተማሪው ጥቂት ብቻ ነው የሚጠበቀው። ሁሉንም ፈትፍቶ ለተማሪው እንዲያጎርስም አይጠበቅም። በመማር ማስተማር ሂደት ሚናውን የሚጫወተው ተማሪው ነው። ለዚህ ደግሞ ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴን መጠቀም ግድ ይላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015