ሰሞኑን ለንባብ የበቃው የ”The Economist” የፈረንጆች ገና ልዩ ዕትም መጽሔት ፤ የራሽያ ዩክሬን መውረር ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ የስንዴ ፣ የዘይትና የሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ በማለቱ ከ90 በላይ በሚሆኑ ሀገራት አለመረጋጋት መፍጠሩን ያትታል። በአሜሪካ ፣ በእንግሊዝና በአውሮፓ በተከሰተው የዋጋ ግሽበት የተነሳ የገንዘብ ፓሊሲያቸውን ጠበቅ አድርገዋል ። የአሜሪካ ግምጃ ቤት ከ2018 ዓም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የብድር የወለድ ምጣኔውን ከፍ አድርጓል ።
የእንግሊዝ ባንክ ከ1980 ዓም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁ ከፍ አድርጓል ። ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግን በገንዘብ ፓሊሲው ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ካለመወሰዱ ባሻገር ፤ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እየተረጨ ነው። የአዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የሚካሄዱ ሜጋ ፕሮጀክቶች መቀጠላቸውን ስንመለከት ብሔራዊ ባንክም የገንዘብ ፓሊሲውን ጠበቅ ማድረግ የዋጋ ግሽበቱን ከመቆጣጠር አንጻር እምብዛም ለውጥ አያመጣም ማለቱ፤ መንግስትም ከዋጋ ግሽበቱ አንጻር ፊሲካል ፓሊሲውን በተለያዩ ምክንያቶች ለመከለስ አለመፈለጉ ፤ ከሌሎች ኅልቆ መሳፍርት ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ ከምንገኝበት ሀይፐር ኢንፍሌሽንና የኑሮ ውድነት የምንወጣበትን መንገድ አርቆታል ።
ከአሁን አሁን የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ ላይ ወሳኝ መታጠፊያ ሊሆኑ የሚችሉ ውሳኔዎች ሊተላለፉ ይችላሉ ተብሎ ቢጠበቅም አንገብጋቢ ችግርነቱን የሚመጥን የተለየ ትኩረት አለማግኘቱና አቅጣጫ አለመቀመጡ ግራ ያጋባል። የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱም ተባብሶ ቀጥሏል። ብሔራዊ ባንክ በበጀት አመቱ የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን የሚያሰክኑ መጠነኛ እርምጃዎችን ቢወስድም የተጠበቀውን ያህል ሆኖ አለተገኘም ። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ታክቲካዊና ስትራቴጂካዊ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ተብሎ ቢታሰብም ከ”ሰንበት ገብያ”ባሻገርና እሳት ከማጥፋት ውጭ ይሄነው የሚባል ነገር ይዞ አልመጣም ።
የሲሚንቶን ነገር እዚህ ላይ ልብ ይሏል ። የግብይት ስርዓቱን ስብራትና አጉራዘለልነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ። እነዚህን ሁሉ ተቋማት አስተባብሮ መፍትሔ ይዞ ሊመጣ ይችላል ተብሎ የተጠበቀው የፕላንና ልማት ሚንስቴርም ይዞት የመጣ አዲስ የተጠና መፍትሔ አልታየም ። አለ ከተባለም ውጤት አላመጣም ። እርምጃዎች መሬት ላይ በተግባር ካመጡት ተጨባጭ ለውጥ ጋር ተነጻጽረው ስለሚመዘኑ ነው አጥጋቢ አይደሉም የሚል መደምደሚያ ላይ እየተደረሰ ያለው ።
በዚሁ ጋዜጣ ደጋግሜ እንደምለው የኑሮ ውድነት ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ ስራ አጥነት ፣ ድህነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ብሔርና ሀይማኖት የላቸውም ። አማራ ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ ፣ ሱማሌ ፣ ትግሬ ፣ ወዘተረፈ አይደሉም ። ኦርቶዶክስ፣ እስላም ፣ ክርስቲያን ፣ ዋቄ ፈና ፣ ወዘተረፈ አይደሉም ። ኢትዮጵያዊ ከፍ ሲልም ሰው ናቸው ። እነዚህ የኢኮኖሚ መሠረታዊ አላባውያን ማለትም የዋጋ ግሽበቱና የስራ አጥነቱ ቢያንስ ባለነጠላ አኃዝ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጤናማ ከሆነ ሕዝብን በአዎንታ ሳይነጋገር አንድ ያደርጋሉ።
ሕዝብን ለድጋፍ ለአንድነትና ለፍቅር ያነሳሳሉ። በተቃራኒው እነዚህ መሠረታውያን ጤናማ ካልሆኑ የዋጋ ግሽበቱ አሻቅቦ የኑሮ ውድነቱ ከተባባሰ ፤ የስራ አጥነቱ ካሻቀበና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ፍትሐዊ ካልሆነ ሕዝብን በአሉታ ማለትም ለተቃውሞና ለአመጽ በአንድነት ያነሳሳሉ ። ይህ ኢኮኖሚያዊ ስኬታችንም ሆነ ውድቀታችን ከፓለቲካው በላይ ጉልበት እንዳለው ያስረዳል። ከፓለቲካችን በላይ ለኢኮኖሚያችን ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ የሚለው ለዚህ ነው ።
በዚህ ሰሞን በተለያዩ ሰበቦችና ምክንያቶች የተቀሰቀሱ ቀውሶች ፓለቲካዊ ካባ ይደረብላቸው እንጅ በውስጠ
ታዋቂነት የኢኮኖሚያዊ ብሶትና ተስፋ መቁረጥ ቅርሻዎች ናቸው ። የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የሚደረገው ጥረት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥን፣ አጥጋቢና ወጥ አለመሆኑን ለታዘበ ፤ ለዘላቂ መፍትሔ ተጨባጭ ፣ ግልጽና ተፈጻሚ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ካልተነደፈ ፤ የተለያዩ ጥያቄዎች ለማንሳት ያስገድዳል ።
የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ከቀጠለ ከጽንፈኝነትና የሴራ ፓለቲካ በላይ የህልውና አደጋ ፤ የኑሮ ውድነቱ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የመሆን አሉታዊ አቅሙ በቅጡ ግንዛቤ ተይዞበታል !? የኑሮ ውድነት ወላፈኑስ ያለ ልዩነት እኩል ዜጋውን እየተሰማው ነው !? የመንግስት ባለስልጣናትስ የኑሮ ውድነት እንደ ተራው ሕዝብ ይሰማቸዋል !? ካልተሰማቸው እንዴት የመፍትሔው አካል ይሆናሉ !? እንዴትስ ለመፍትሔው ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይችላል!?
ሁለት አስር አመታትን ያስቆጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የዜጋውን ኑሮ በብርቱ እየፈተነው ፤ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወደለየለት ማህበራዊና ፓለቲካዊ ቀውስነት እንዳይባባስ እያሰጋ ይገኛል ። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ኢኮኖሚው ለቀደሙት 27 አመታት የአንድ ቡድንና የጭፍራው መጠቀሚያ በመሆኑ በተከሰተው ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ አሻጥር ፣ ስግብግብነት ፣ አልጠግብ ባይነት፣ ግጭት ፣ ጦርነትና አለመረጋጋት ተጨምሮበት ኑሮው አልቀመስብሏል ።
በአናቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፤ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት ፤ ከገበሬ ማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገ ደላላ ፤ የገነገነ ሙስና ፣ በግብይት ሰንሰለቱ የተንሰራፋው ስርዓት አልበኝነት ፤ ዋጋን በአድማ መወሰን ፤ ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር ፤ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ፤ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በመንግስት መዋቅር ዘንድ ወጥ የሆነ ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ፤ የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ አለመሆን ፤ ወደብ አልባ በመሆናችን በየአመቱ ቢሊዮኖችን የምናወጣ እና ስለመብቱ የሚቆረቆርና የሚጠይቅ ጠንካራ ሸማች አለመፈጠሩ እንደ ዚምባብዌና ቬኒዞይላ ባይሆንም በሰዓታት ልዩነት ለሚተኮስ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲዳረግ ሆኗል።
በየፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ግሽበትንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል ። አምስት ሊትር የምግብ ዘይት ሰሞኑን 1010 ብር መግባቱ ሳያንስ ፤ ሲያሻው ከገብያ ይጠፋል ። ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ እየተዘጋጀን ባለንበት የስንዴ ፊኖ ዱቀት በኪሎ ወደ 68 ብር ተተኩሷል ። ገና ሲቆርሱት ዱቂት የሚሆን ዳቦ 6 ብር ገብቷል ። ጤፍ እንደዚሁ በኪሎ 63ና ከዚያ በላይ ገብቷል ። ቡና በኪሎ ወደ 500 በር አሻቅቧል ። ሽንኩርት ፣ ቲማቲም አጠቃላይ አትክልትና ፍራፍሬ አልቀመስ ብሏል ። አቡካዶ በኪሎ 80 ብር ፣ ቢጨምቁት ጠብ የማይለው አንድ ሎሚ 10 ብር ገብቷል ። ቲማቲም ከሰሞኑ በአንጻራዊነት ቀንሷል ቢባልም እንደለመደው ተመልሶ ማሻቀቡ አይቀርም ። እህልና ጥራጥሬውም ብሶበታል ።
በዚህ ሳቢያ በመዋቅራዊና በተቋማዊ ችግር የተነሳ ጽኑ ታማሚ ሆኖ ለኖረው ኢኮኖሚ ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። የለውጡ መንግስት ባለፉት አራት አመታት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ያደረገው ጥረት ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም ። አልበርት አነስታይን፤” ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ፤ ችግር መፍታት
አይቻልም፡፡ “እንዳለው ከሳጥኑና ከተለመደው አተያይ ወጣ ብሎ መፍትሔን ማማተር ግድ የሚለ አሳሳቢ ወቅት ላይ ብንገኝም ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ የሚፈለገውን ያህል እየሰራን አይደለም ። እንዲያውም ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ይገኛል ።
ስነ ምግባር የጎደላቸው አንዳንድ የመንግስት አመራሮች በዚህ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው ችግሩን እንዳወሳሰበው በዚያ ሰሞን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው መድረክ ይፋ ሆኗል ። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦቦ ሽመለስ አብዲሳ ባለፈው በተካሄደው ጨፌ ኦሮሚያ ይሄን ሀቅ ደግመውታል ። ከዚህ ውይይት በፊት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ክትትል መሠረት በየመካዝኑ ተከዝነውና ተደብቀው የሚገኙ የምግብ ዘይት ፣ የስንዴ ዱቄት ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመያዝ ሲንቀሳቀስ በየአካባቢው ያለ አመራር ለመተባበር እንዴት እግሩን ይጎትትና ለማደናቀፍም ይጥር እንደነበር መግለጹ የኮሚሽኑን ግኝት ተጨባጭ ያደርገዋል ። መንግስት መዋቅሩን ካላጠራ ችግሩ ተባብሶ የስርዓቱም የሀገሪቱም አደጋ መሆኑ አይቀርም ።
ይሄን ስርዓት አልባ የግብይት አሰራር መንግስት በማያዳግም ሁኔታ በሕግ አግባብ ስርዓት ሊያሲዘው ካልቻለ፤ ከማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገውን ደላላ ከግብይት ሰንሰለቱ ካላስወጣ ፤ በድጎማ ከውጭ የሚገባን ዘይትና ስንዴ ለነጋዴው 70 በመቶ ፤ ለሸማቹ 30 በመቶ የነበረውን የስርጭት ቀመር ቀይሮ የተገላቢጦሽ ካላደረገ ፤ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ተመንና የትርፍ ሕዳግ ካልተቀመጠ ፤ ገብያውን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ካላደረገው ፤ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጉያ ወጥቶ ስልጣኑና አደረጃጀቱ ተሻሽሎና ተጠናክሮ እንደገና ካልተደራጀ ፤ በግብይት ሒደቱና ሰንሰለቱ የሚስተዋለው አጉራዘለልነትና ውንብድና በሕግ የበላይነት ስርዓት እንዲይዝ ካልተደረገ ፤ ችግሩ ተባብሶ ተባብሶ ወደለየለት የጸጥታና የደህንነት ችግር እንዳይባባስ ያሰጋል ።
የዋጋ ግሽበቱ ከ40 በመቶ በላይ ተተኩሶና በየቀኑ እየተባባሰ ባለበት ፤ የኑሮ ውድነቱ ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑሮ የማይቀመስ ካደረገው ፤ የስራ አጡ ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ እንዴት ስለኢኮኖሚያዊ ስኬት ማውራት ይቻላል ። እንዴት ስለብልጽግና ማለም ይታሰባል። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይሄን ኢኮኖሚያዊ ትብታብ አሁን ላለው መንግስት በእዳ የተላለፈለት እንጅ ለብቻው የፈጠረው አይደለም ። ሆኖም ይሄን ትብታብ የመፍታት ኃላፊነት ትክሻው ላይ ወድቋል ። እንደ ሰበብ/excuse/ሊጠቀምበትም አይችልም ። የጦርነቱ ጫናም ቀላል አይደለም ። ኮቪድና የራሽያ ጦርነት የፈጠረው የዋጋ ግሽበትም ተጽዕኖው ከባድ ነው ።
በባህሪው ገብያ/ኢኮኖሚ ድንጉጥ ነውና ። አይደለም ጦርነትና የግጭት አዙሪት የተሳሳተ ፓሊሲና የገብያ ትንበያ/speculation/ገብያን ያስበረግጋል ። ይሄን ችግር ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ሸማቹ ሕዝብ የመንግስት ቁርጠኝነት በሙላት ሲገለጥ አለማየቱ ነው ። በዚህ የተነሳ ከዛሬው ነገ እንዳይከፋ አስፈርቶታል ። አስጨንቆታል ። የኑሮው ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል ። በተለይ በግብይት ስርዓቱ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ። ከአቅርቦትና ከፍላጎት አለመመጣጠን ፤ ከኮቪድና ከራሽያ ጦርነት ፤ በሀገራችን ከሚስተዋሉ ቀውሶችና ግጭቶች ባልተናነሰ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ስርዓት አልባ የሆነው የግብይት ስርዓት ነው ። ለዚህ ነው በግብይት ስርዓቱ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ እየተባለ የሚወተወተው ። ስርዓት ይበጅ የሚባለው ።
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከብር ለውጥ ጀምሮ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም ግብርናን ፤ የቆላ ስንዴን ፤ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ፤ የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው። ሆኖም ምርት ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ብልሹው የግብይት ስርዓት ካልታረም ፤ ደላላው ከገብያው ካልወጣ ፤ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በሕግ ስርዓት ማስያዝ ካልተቻለ ፤ ማህበራዊ ስብራታችን ካልታጀለ
ምርታማነታችን የቱንም ያህል ቢያድግ ከዚህ አዙሪት መቼም ቢሆን ሰብረን መውጣት አንችልም ። ወቅቱ ስንዴን ጨምሮ ምርት ተሰብስቦ ወደ ገብያ የሚቀርብበት ቢሆንም ገብያው በደላላ ስለሚወሰን የዋጋ መቀነስ አይታይም ።
ሆኖም ይሄ ችግር በመንግስት የተናጠል ጥረት ብቻ አይፈታም ። ዩኒቨርሲቲዎች ፣ እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ያሉ ማህበራት ፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣ እንደ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ያሉ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ። በተለይ ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ ተቋማት ይሄን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምር በማድረግ የፓሊሲ ሀሳብ ማመላከትና ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል ።
ይሄን ሁሉ ተቋም ተሸክመን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዴት እንደ ስፔስ ሳይንስ እስከ መቼ እንደተወሳሰበብን ይቀጥላል ። በእርግጥ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የተፈጠረው በምርት እጥረት ነው ፣ በግብይት ስርዓት ችግር ፣ እሴት በማይጨምር ደላላ ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ፣ በዩክሬንና በራሽያ ጦርነት ፣ በኮቪድ 19 የተነሳ ፤ ወዘተረፈ ነው !? መልሱን በጥናት ማግኘት የማያዳግም መፍትሔ ለማስቀመጥ ይረዳል። በተረፈ ችግሩንና ተጠያቂነቱን ያለአድራሻ ማስቀመጥና ጣት መቀሳሰር ከተዘፈቅንበት አረንቋ አያወጣንም ።
የውጭ ንግዳችን ከሀገር ውስጥ ገብያው ይልቅ የውጭ ምንዛሬ ማሳደድ ላይ መጠመዱ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል። የቅባት እህል ወደ ውጭ ልኮ የፓልም ድፍድፍ ገቢ ያደርጋል። አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ ልኮ መድሀኒት በውጭ ምንዛሬ ያስገባል ። የውጭ ንግድ መሠረቱንና አይነቱን ማስፋት ሲገባው ከሸማቹ ጉሮሮ እየቀማ ወደ ውጭ ይልካል ። ይሄ የተፋለሰና ወለፈንዲ የሆነ አሰራር በጥናት ተፈትሾ መስተካከል አለበት ። የሀገር ውስጥ ገብያን እያራቆቱ ምርትን ወደ ውጭ መላክ ለዜጋው አለማሰብ ነውና። ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገውን ሩጫ እዚህ ላይ ልብ ይሏል። የፊኖ ዱቄት በኪሎ ወደ 70 ብር ተጠግቶ፤ ሲቆረስ ዱቄት የሚሆን ዳቦ 6 ብር እየተሸጠ ባለበት ሀገር ገብያው ሳይረጋጋ ስንዴን ኤክስፓርት ለማድረግ መጣደፍ ምን ይሉታል ።
መንግስት የግብይት ስርዓቱን ስድ መልቀቁ የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን አባብሶታል ። ስለሆነም በሕግና በአደረጃጀት ነገ ዛሬ ሳይል ስርዓት ሊያሲዘውና የቁጥጥርና የክትትል አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ። የመኖሪያና የንግድ ቤት ኪራይ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ ችግሮች ዋናው ነውና ተመን ሊወጣለት ይገባል ። በመሠረታዊ ሸቀጦች የትርፍ ሕዳግና የዋጋ ተመን ሊወጣ ግድ ይላል ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ሰሞኑን ለአትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ውስጥ የንግድ ሥርዓቱ ፈር የለቀቀ እንዲሆንና የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው በገበያ ሥርዓቱ ውስጥ የሸቀጦች የትርፍ ህዳግ ገደብ አለመቀመጡ ነው፡፡
በመሆኑም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት መንግሥት የሸቀጦች የትርፍ ህዳግ ገደብ ሊያስቀምጥ ይገባል ብለዋል ፡፡ ሌላው ለሸማቾች ሲል ዘይት ፣ ስንዴና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ቢያደርግም የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት ስለአልዘረጋ ገብያው ሊረጋጋ አልቻለም። መንግስት በዚህ ፓሊሲው ከ27 ቢሊየን ብር በላይ ቢያጣም ለሸማቹ ጠብ ያለ ነገር የለም ። ይህ ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሕግ ክፍተት መኖሩን ያሳያል ። ስለሆነም በማያዳግም ሁኔታ ስርዓት ሊበጅለት ይገባል ።
ትኩረት በኑሮ ውድነት አለንጋ እየተገረፈ ላለው ሸማች!!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015