በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ጦርነት በአማራ ክልል ካደረሰው ሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል:: ከክልሉ መንግስት የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ በጦርነቱ 292 ቢሊየን ብር የሚገመት ቁሳዊ ውድመት ደርሷል:: ትምህርት ቤቶች፣ የጤናና የግብርና ተቋማት፣ ወዘተ ወድመዋል::
እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባሮች በፌዴራል መንግስት እንዲሁም በአማራ ክልል መንግስት መከናነወን ጀምረዋል:: በአንዳንድ አካባቢዎች የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የተመረቁበት ሁኔታም ታይቷል::
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ጥቅምት ወር ፣ በኮምቦልቻና በከሚሴ ከተሞች ያካሄዳቸውን የመልሶ መገንባት ስራዎች ማስመረቁ ይታወሳል:: በመሰረተ ልማት ተቋማቱ ምረቃ ወቅት እንደተጠቆመው፤ በጦርነቱ ወቅት በእያንዳንዱ ተቋም አንድ ወንበር እንኳን ያልተገኘበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ኮምፒውተርና ዶክመንቶች እንዲሁም ህጻናት የሚማሩባቻቸው ወንበሮች በሙሉ ተቃጥለዋል፤ወድመዋል::
በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት፤ ህብረተሰቡ የወደሙትን መልሶ መጠገን ሳይሆን፣ ከነበረው ከፍ ባለ ደረጃ ለመገንባት በመግባባት ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተሻለ መገንባት እንችላለን በሚል ወኔ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጦ ነው ወደ መልሶ ግንባታው የተገባው::
ለግንባታውም 150 ሚሊዮን ብር በመመደብ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱንም ነበር ሚኒስትሯ በወቅቱ የተናገሩት:: የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠ በኋላ እውነት በተባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ወይ? የሚል ፍራቻ እንደነበራቸውም አስታውሰዋል:: ይሁንና በመልሶ ግንባታው ጊዜ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ከሚታወቀውና ከስምምነቱ ውጪ ውልን በማራዘም ጊዜ ከመግዛት ተላቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሉ አራት ወር ሆኖ በሦስት ወር የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ማየት እንደታቸለም ገልጸዋል::
የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢያዝን እንኳሆነ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም በኩል 150 ሚሊዮን ብር በመመደብ የተወሰኑ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራ ማከናወኑን አስታውቀዋል:: በዚህም በሚኒስቴሩ ድጋፍ በሰባት ከተሞች ማለትም በሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴና ሸዋሮቢት የ18 መሰረተ ልማቶች ፕሮጀክቶች መልሶ ግንባታ ሥራ መካሄዱን ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በሚኒስቴሩ በኩል 12 ክፍሎች ያላቸው ስምንት ትምህርት ቤቶች፣ ሦስት ጤና ጣቢያዎች፣ ሰባት የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴና ሸዋሮቢት ከተሞች ላይ ተገንብተዋል:: ፕሮጀክቶቹ ትልቅ ትምህርት የተወሰደባቸውና ለወደፊት መልሶ ግንባታናሥራም መሠረት የተጣለባቸው ናቸው::
የአማራ ክልል መንግስትም የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽህፈት ቤት አቋቁሞ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራውን ባለፈው ህዳር ወር በይፋ ጀምሯል:: ሰፊ ጊዜ ተወስዶ፣ በቂ ጥናት ተደርጎ ፣ ስትራቴጂክ እቅድ ወጥቶ ነው ስራው የተጀመረው:: መልሶ የመገንባት እና የማቋቋም ስራው በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቋል::
የአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አባተ ጌታሁን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በስምንት ዞኖችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ወረራ ብቻ 292 ቢሊዮን ብር ቁሳዊ ውድመት ደርሷል።
የአማራ ክልል በጦርነት ውድመት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ከሀምሌ 1 ቀን 2014 ጀምሮ ጽህፈት ቤት አቋቁሞ እየሰራ ነው፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ስትራቴጂክ እቅድም ባለፈው ሀምሌ ወር 2014 ዓ.ም በቦርድ ጽድቆ ወደ ስራ ገብቷል። እቅዱ በዋናነት የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርናን ጨምሮ ከ18 ዋና ዋና መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት የተነደፈ ነው። ከዕቅዱ በ2015 በጀት ዓመት የሚሰሩትን ለይቶ መስራት ተጀምሯል።
ከሁሉም መስሪያ ቤቶች አንድ አንድ ተወካዮች ያሉበት የዓመት እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ባለፈው ህዳር 23 በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ የመልሶ ማቋቋም ስራ በሰሜን ወሎ ዞን፣ ወርቄ ቀበሌ ላይ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ወርቄና ያያ በሚባሉ ሁለት አካባቢዎች በሚገኙ 023 እና 024 ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ እነዚህ ቀበሌዎች 234 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች፣ አንድ ጤና ጣቢያ፣ አንድ ትምህርት ቤት፣ ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው ነው ያብራሩት።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የወደሙትን መኖሪያ ቤቶች መልሶ የመገንባት እና ማቋቋም ስራው ተጀምሯል። የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የወደመባቸውን ቤቶች ለመገንባት ለእያንዳንዱ ሰው 50 ቆርቆሮና ሰባት ፓኮ ሚስማር በመስጠት ስራው እንዲጀመር ተደርጓል:: የአካባቢው ማህበረሰብ በእርሻና በእንስሳት እርባታ የሚተዳደር ነው:: በእዚህ አካባቢ የነበረ የእንስሳት ክሊኒክም ወድሟል::
በጦርነቱ በዋናነት ስምንት ዞኖችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ዶክተር አባተ፤ ከዚያ በፊት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባሉበት ሁሉም የክልሉ ባለስልጣናት፣ የዞንና የከተማ አመራሮችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተሳተፉበት እቅዱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት፣ በቀጣይም እያንዳንዱ ተወካይ በቀበሌ ደረጃ ወርዶ ሀብት ማሰባሰብ እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጦና ፕሮፓዛል ተዘጋጅቶ ነው ስራው የተጀመረው።
የመልሶ ማቋቋምና ግንባታው የክልሉ መንግሥት በመደበው አንድ ቢሊዮን ብር በጀት መጀመሩንም ስራ አስኪያጁ ጠቁመው፣ ይህ ገንዘብ ለዘጠኝ ዋና ዋና ቁም ነገሮች እንዲውል ለማድረግ እየሰራን ነው ይላሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዚህ ስራ ከሚከናወኑ ተግባራት የመጀመሪያው የትምህርት ቤት ግንባታ ነው:: የወርቄውን ጨምሮ 22 ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ:: በሁሉም ዞኖች በዋናነት በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፤ ደሴ ከተማ፣ ኮምቦልቻ ከተማ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና ሰሜን ሸዋ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ተለይተዋል፤ ዞኖቹና ከተማ አስተዳደሮቹ ከክልሉ የሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር በመመካከር በቦርድ በማስደቅ 22 የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ::
እንደ ዶክተር አባተ ገለጻ፤ በጦርነቱ አንድ ሺ 151 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ከነዚህ ውስጥ በትምህርት ሚኒስቴር 45 ትምህርት ቤቶች፣ በክልሉ ደግሞ 22 ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው። ይሄ የመጀመሪያና የመነሻ ፕሮጀክት ነው::
በጤና ተቋማት 10 ክሊኒክ፣ አንድ ሆስፒታል (የቆቦ ሆስፒታል ስስት ጊዜ እንዲወድም ተደርጓል፤ የዚህ ሆስፒታል የወደመው ክፍል መልሶ ግንባታ ይካሄዳል); በግብርና ዘርፍ የተለያዩ የእንስሳት ክሊኒኮች፣ ግብርና ኮሌጆች፣ የምርምር ተቋማት፣ በአጠቃላይ ወደ 64 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል:: ወጣቱን መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚገባም ተናግረው፣ የወጣቱ ትውልድ ስነ ምግባር ላይ መስራት ያስፈልጋል:: ‹‹አልተጠቀምንበትም እንጂ እኛ እድለኞች ነን:: በርካታ የህብረተሰብ ክፍላችን ወጣት ነው›› ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ለዚህም የስነ ምግባር መገንቢያ ማእከላት እንደሚያስፈልጉ ይገልጻሉ:: በመሆኑም 17 የወጣት የሥነምግባር መገንቢያ ማዕከላትን/ ለሁሉም ዞኖች/ ማዕከል ያደረገ የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ግንኙነት ያለው ስራም ይካሄዳል:: ስራ ፈጠራ ላይ አንድ ማእከል የሚባል ነገር አለ፣ አንድ ማእከል ወደ አስራ አምስት ሺ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል:: በመልሶ ግንባታው አስር የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ይገነባሉ::
ጎን ለጎን አመራሩ ስራ ፈጠራ ላይ ያለው እውቀት እንዲዳብርና የተሻለ ሰራተኛ እንዲሆን በሀገር ደረጃ ካለው ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በሶስት ዙር የፐብሊክ ኢንተርፕረነርሽፕ (Public Entrepreneurship) ስልጠና ተሰጥቷል:: ለ210 አመራር ስልጠናው ተሰጥቷል:: እያንዳንዳቸው አንድ ሺ ሰው የሚገለገልባቸው ማዕከላት መልሶ ግንባታ ይካሄዳል፣
በውሃ ዘርፍ 31 የሚሆኑ የተለያዩ ጉድጓዶችን፣ ምንጮችን የመገንባት፣ 421 ሄክታር መሬት ሊያለማ የሚችል የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ለመገንባት ኮንትራክተሮች ውል ወስደው በሁሉም ዞኖች ሄደው ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል። ለዚህ ሁሉ አንድ ቢሊዮን አንድ መቶ 29 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ውድመቱ በጣም ብዙ ነው:: ቁሳዊ ውድመቱ ብቻ ወደ 292 ቢሊየን ብር ነው፤ ችግራችን ቁሳዊ ትርጉም ብቻ እየሰጠን ነው እንጂ፣ በገንዘብ ሊተመን የማይችል የከፋ የሰብአዊ፣ ስነልቦናዊ፣ማህበረ ባህላዊ ውድመቶችም ደርሰዋል::
‹‹በዚህ አመት ምን ያህል ትሰራላችሁ›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ‹‹ትምህርት ቤቶቹን፣ የውሃ ተቋማቱን፣ የጤና ተቋማቱን ወዘተ ከቻልን በቀጣይ አምስት አመት እንጨርሳለን:: በዚህ አመት ይህን ያህል እንሰራለን ማለት አልችልም፤ ባገኘነው ሀብት ልክ እንሰራለን›› ሲሉ አብራርተዋል::
እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ ውድመቱ ከባድ ነው፣ የሚፈልገውም ድጋፍ ከፍተኛ ነው። አለም አቀፍ ሁኔታው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አለ:: ወደ ግራም ወደ ቀኝም መዋዠቅ አለ፤ ከእኛ ጋር የሚሰሩ የምናደንቃቸው አለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ:: 53 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተለይተው በተናበበ መንገድ እየተሰራ ነው።
በስትራቴጂክ እቅዳችን መሰረት የዓለም ባንክ፣ ዩኤንዲፒ፣ ወርልድ ቪዥን ከክልሉ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ጽህፈት ቤት ጋራ በቅንጅት እየሰሩ ናቸው። የአለም ባንክ እየጀመረ ነው፤ ዩኤንዲፒና ወርልድ ቪዥን እያገዙን ናቸው፤ በጣም በጥሩ ሁኔታ መሬት ወርደው እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች አሉ፤ በተለይ ዩኤንዲፒ እጅግ በጣም ሊመሰገን ይገባዋል::
የአለም ባንክ ሰባት ወረዳዎችን መርጧል፤ ለትግራይ፣ ለአማራ ፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 300 ሚሊየን ዶላር ለአንድ አመት መድቧለ3፤ ስራው እድገት አሳይቷል፤ እኛም በቀጣይ አብረን ጥሩ እንሰራለን ብለን እያሰብን ነው::
አንዳንድ ያለመናበብና የድግግሞሽ ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት:: ክልሉን ሊያግዙ የሚፈልጉ አካላት በዚህ ጽህፈት ቤት አማካይነት ሀብቱ በአንድ ቋት ውስጥ ተቀምጦ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲሰራ ክልሉ የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል::
ዶክተር አባተ እንዳብራሩት፤ በጦርነቱ የተፈጸመው ሁሉ ይዘገንናል:: በቀጥታም በተዘዋዋሪም የደረሰው ውድመት ሰው የሚባል አካል ይፈጽመዋል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም:: ከዚህ በላይ ላለመውደም ሁሉም ሰው በውይይት እንዲያምን ማድረግ ያስፈልጋል:: በጣም የተማርን ነን የሚሉት በየዩቲዩቡና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያካሂዱት የጥላቻ ዘመቻና የጦርነት ቅስቀሳ እንዲያቆሙ ሚዲያዎች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው:: ሚዲያ ትልቅ ሀይል ነውና ሚዲያዎች መልሶ ሌላ ውድመት እንዳይከሰት መስራት ይጠበቅባቸዋል::
‹‹ ቆቦ ከተማ ላይ ሶስት ጊዜ የወደሙ ተቋማትን የተመለከተ ያሳዝናል:: በትግራይ፣ በአማራና በአፋር የተፈጸመው ጥፋት ዘግናኝ ነው፤ የእርስ በርስ ጥፋት ነው›› ያሉት ዶክተር አባተ፣ ‹‹እኛ እንደ ሰርገኛ ጤፍ ነን:: ልንለያይ የማንችል ነን:: ሁሉም ወደ ቀልቡ ተመልሶ ከጦርነት ታቅቦ ነገሮች በውይይት ቢፈቱ መልካም ነው፤ ይሄ ዘላቂው መፍትሄ ነው:: ጦርነት አያዋጣም ፤ ትልቅ ጥፋት ነው:: ሚዲያ ትልቅ ሀይል ነው:: ጋዜጠኞችም ትልቅ ሀብት ናችሁና ሁላችንም ከዘርና ከሃይማኖት ወገንተኝነት ወጥተን ብንስራ ጥሩ ነው›› ሲሉም አስገንዝበዋል::
‹‹የወደሙትን ተቋማት ተጋግዘን መልሰን ማልማት አለብን፤ አንድ ጥናት ያመለከተውን ብቻ ይዘን ነው 292 ቢሊየን ብር ውድመት ደርሷል ያልነው:: ትምህርት ቤቶች የሉንም፤ ፊቱንም በኢትዮጵያ የተሻለ ትምህርት ቤት የለም፤ አሁን ደግሞ ብሷል፤ የጤና ተቋማት፣ የግብርና ተቋማት ወድመዋል:: ‹ጋን በጠጠር ይደገፋል› እንደሚባለው ሁላችንም ተረዳድተን የወደመውን ለመተካት መስራት አለብን፤ ነጠብጣብ ነው ጎርፍ የሚፈጥረውና አንረዳዳ›› ይላሉ::
የሚገኘውን ሀብት በተቻለ መጠን ቆጣቢና ኢኮኖሚያዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበው፣ በአማራ ክልል ቁጠባን ታሳቢ ያደረገ ከላይ እስከ ታች ድረስ የተናበበ አሰራር መከተል አንደሚገባም አስገንዝበዋል::
ሀብትን በትክክል በመጠቀም የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራው ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀው፣ ለዚህ ስራ ስኬታማነት የአገር ውስጥ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መላ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ዶክተር አባተ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፓርተር
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215