ቴክ አፍሪካ ዉሜን (Tech Africa Women /TAW/) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚደገፍ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ሲሆን ተቀማጭነቱን በቱኒዚያ ባደረገና ዲጂታል ቢዝነስ ግንባታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራ ‹‹ቤትኪዩብ›› በተሰኘ ተቋም ይተገበራል:: የፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማም የአፍሪካ ወጣት ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ማብቃትና በሴቶች የተመራ ጠንካራ የቴክኖሎጂ መነሻ ቢዝነስ መገንባት ነው::
የስራ ፈጠራ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ ከነሃሴ 2022 ጀምሮ ለአምስት ወራት ያህል ከኢትዮጵያ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያና ቱኒዚያ በተውጣጡ ወጣት ሴት የዲጂታል ቢዝነስ ሃሳብ አመንጪና ጀማሪዎች መካከል ሲከናወን ቆይቷል:: ከ331 አመልካቾች ውስጥ 74 የሚሆኑት ተመርጠው በካምፕ ሆነው አዲስ ለሚጀምሩት የዲጂታል ቢዝነስ ማጎልበቻ ጠቃሚ ግብአት የሚሆን የሶስት ቀን ስልጠና ተሰጥቷቸዋል:: የእርስ በእርስ ውድድር አካሂደውም አሸናፊ ቡድኖች ተመርጠው የ2 ሺ ዶላር ሽልማት አግኝተዋል::
ከ74ቱ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ደግሞ ስምንቶቹ ተመርጠው ለአስራ ሁለት ሳምንት አዲስ የሚጀምሩትን የዲጂታል ቢዝነስ የኦን ላይን ትምህርቶችን በመውሰድ ሲያበለፅጉ ቆይተዋል::በመጨረሻም ከአራቱ አገራት ውስጥ የተመረጡት የመጨረሻዎቹ ስምንት ወጣት ሴት የዲጂታል ቢዝነስ መነሻ ስራ ፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ስራዎቻቸውን አዲስ አበባ ላይ አቅርበው ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ ‹‹ኡጃና›› የተሰኘ የስነ ተዋልዶ ጤና ምርቶችንና የምክር አገልግሎቶችን ለወጣቶች የሚያቀርብ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ፕላትፎርም በመፍጠር ታንዛኒያዊቷ ጁሊያና ቡሳሲ የ7 ሺ ዶላር አሸናፊ ሆናለች::
ለመጨረሻው ዙር ውድድር ሁለት ወጣት ሴት ኢትዮጵያውያን የዲጂታል ቢዝነስ መነሻ ስራ ፈጠራ ሃሳብ ይዘው በመቅረብ ብርቱ ፉክክር ቢያደርጉም ድል አልቀናቸውም:: ይሁንና የጀመሩትን የዲጂታል ቢዝነስ ስራ ፈጠራ ይበልጥ በማበልፀግ ገቢ ለማመንጨት ጠቃሚ ግብአቶችን ከፕሮግራሙ ማግኘት ችለዋል::
ጁሊያና ቡሳሲ በታዘንዛኒያ የህክምና ባለሞያና የህዝብ ስራ ፈጠራ ባለቤት ናት:: በቴክ አፍሪካ ዉሜን ስራ ፈጠራ ፕሮግራም ለመጨረሻው ውድድር ከቀረቡ ስምንት ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንዷ ስትሆን ‹‹ኡጃና›› የተሰኘ የስነ ተዋልዶ ጤና ምርቶችንና የምክር አገልግሎቶችን ለወጣቶች የሚያቀርብ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ፕላትፎርም /ቢዝነስ ሞዴል/ በመፍጠር የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች:: በዚህም የ7 ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች::
ያገኘችው ሽልማት እንዳስደሰታት የምትገልፀው ወጣቷ፤ በቀጣይ ፕላትፎርሙን የመሞከር ስራ እንደምታከናውንና ጠቃሚ ግብአቶችን በመሰብሰብ የቢዝነስ ሞዴሉን ይበልጥ የማበልፀግ ስራ እንደምታከናውን ታስረዳለች:: በአፍሪካ ያሉ ማንኛውም ወጣት ሴቶች ሃሳብና ትልም እስካላቸው ድረስ ለማህበረሰቡ አውጥተው ለማጋራት መፍራትና ወደኋላ ማለት እንደማይገባቸውም ትገልፃለች::
እርሷም ይህን የፈጠራ ሃሳብ ካመነጨች ረጅም ግዜ እንደሆናት ተናግራ፤ ብርታቱን እስክታገኝ ድረስ ሃሰቡን ወደተግባር ለመለወጥ ስታመነታ መቆየቷን ታስረዳለች:: ነገር ግን ቴክ አፍሪካ ዉሜን የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ሲጀመር የፈጠራ ሃሳቧን እውን የምታደርግበት አጋጣሚ መፈጠሩን ትናገራለች::
ፕሮግራሙም የፈጠራ ሃሳቧን ለመገንባትና ዲጂታል ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የስነ ተዋልዶ ጤና ምርቶችንና አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ፕላትፎርም አማካኝነት ለወጣቶች ለማቅረብ የሚያስችል የቢዝነስ ሞዴል ለመፍጠር እንዳስቻላት ታብራራለች:: ይህም በአጭር ግዜ ውስጥ ፍሬያማ ይሆናል ብላ እንዳላሰበች ትጠቅሳለች::
‹‹በሞያዬ ሃኪም ነኝ ነገር ግን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ስራ ፈጣሪ መፍትሄ ማምጣት አልችልም ማለት አይደለም›› የምትለው ወጣት ጁሊያና የአፍሪካ ወጣት ሴቶች የቢዝነስ ሃሳብ እስካላቸው ድረስ በየትኛውም የሞያ መስክ ውስጥ ሆነው ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ስራ መፍጠርና በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚችሉ ትናገራለች:: ለዚህም ሃሳባቸውን ወደተግባር ሊለውጡ የሚያስችሏቸውን ማንኛውንም እድሎች መጠቀም እንዳለባቸው ትመክራለች::
ወጣት ዝማሬ ታደሰ በዚሁ በሞያዋ ሃኪም ስትሆን በዚሁ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ለመጨረሻው ውድድር ከቀረቡ ስምንት ምርጥ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንዷ ናት:: ‹‹ጤና ሰብ›› በተሰኘ መተግበሪያ አማካኝነት የፆታና የስነ-ተዋልዶ ትምህርትና የምክር አገልግሎት ለሴቶች የሚሰጥ የቢዝነስ ሞዴል ይዛ ነው ለውድድሩ የቀረበችው:: ይህን ፕላትፎርም ለማዘጋጀት ያነሳሳት ደግሞ ሴቶች የፆታና ስነተዋልዶ ጤና ትምህርትና የምክር አገልግሎት እንደልብ አለማግኘታቸው ነው::
በዚህ ቢዝነስ ሞዴል መሰረት ሴቶች ስልክ በመደወልና ድረገፅ በመጎብኘት የፆታና የስነተዋልዶ ጤና ትምህርትና የምክር አገልግሎት ያገኛሉ:: በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎችም ሴቶቹ ትምህርቱንና የምክር አገልግሎቱን ለማግኘት ያስችላቸዋል::
በዚሁ መተግበሪያ አማካኝነት ትምህርቱንና የምክር አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሴቶች ርቀት ሳይገድባቸው ካሉበት ቦታ ሆነው ይመዘገባሉ:: በተመሳሳይ በዚሁ ዘርፍ ሞያው ያላቸው የህክምና ባለሞያዎችም በመተግበሪያው ላይ ይመዘገባሉ:: በዚሁ መሰረት ሴቶቹ ወደ መተግበሪያው ገብተው የፈለጉትን የህክምና ባለሞያ በፆታ፣ በስፔሻሊቲና በህክምና ልምድ መርጠው ቀጠሮ ያሲዛሉ:: በቀጠሯቸው አማካኝነት ደግሞ ከመረጡት ሃኪም ጋር ተገናኝተው የትምህርትና የምክር አገልግሎቱን ያገኛሉ::
ሚስጥራቸውን ለመጠበቅ ደግሞ ስማቸው ሳይታወቅ ትምህርቱንና ምክር አገልግሎቱን የሚያገኙበት አሰራርም በዚሁ መተግበሪያ ላይ ተዘርግቷል:: ለሚያገኙት የፆታና የስነተዋልዶ ጤና ትምህርትና የምክር አገልግሎት ሴቶቹ ክፍያ ይከፍላሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎን በርካታ ተከታዮች ባሉት የዚሁ ፕላትፎርም አንዱ አካል በሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ኩባንያዎች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እዲገኝ ይደረጋል::
አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እንደልብ አለመስፋፋትና ፈጣን አለመሆኑን እንደ አንድ ችግር በመለየት ተጠቃሚዎች በስልክ ጥሪ አማካኝነት አገልግሎቱን የሚያገኙበት አሰራር ለመዘርጋት ስራዎች እየተሰሩ ነው:: ሆኖም የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን በማውረድ በቀላሉ አገልግሎቱን መጠቀም ይችላሉ::
ይህ ፕላትፎርም በዋናነት በአረብ አገራት የሚገኙ ሴቶች ላይ ኢላማ አደርጎ የሚሰራ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ዝማሬ፤ በተለይ ሴቶቹ ካለባቸው የስራ ጫናና ህጋዊ ሆነው እስካልተቀመጡ ድረስ ወደ ህክምና ቦታ ሄደው አገልግሎቱን የማግኘት እድላቸው የጠበበ ከመሆኑ አኳያ ከዚሁ ከኢትዮጵያ ትምህርቱንና የምክር አገልግሎቱን ቢያገኙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የምትናገረው::
ሴቶቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ አገልግሎቱን በቀላሉ የማግኘት እድል እንደሚኖራቸውም ነው ወጣቷ የምትናገረው:: የአገልግሎት ክፍያውንም ለማሳለጥ እንደቴሌ ብር የመሰሉ የኦንላይን ክፍያ ስርዓት እንደሚዘረጋ ትገልፃለች:: በአረብ አገራት የሚገኙ ሴቶች ደግሞ ለቤተሰቦቻው ገንዘብ እንደሚልኩ ሁሉ ለሚያገኙት አገልግሎት ገንዘብ በመላክ አልያም ደግሞ ‹‹ፔይ ፓል›› በመጠቀም መክፈል እንደሚችሉም ትጠቁማለች::
በተጠቃሚው ዘንድ የዲጂታል እውቀት አለመኖርም አንዱ ችግር መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ የዲጂታል ፕላትፎርሙ እንዳለ ሆኖ የቴሌግራም ቦታ በመጠቀም አገልግሎቱን ለብዙሃኑ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ትጠቁማለች::
የትምህርትና የምክር አገልግሎቱን ጥራት ለማረጋገጥ የህክምና ባለሞያዎቹ በመተግበሪያው ገብተው ከመመዝገባቸው በፊት የሚሞሉት ፎርም እንደሚኖርም ወጣት ዝማሬ ትጠቅሳለች:: እንዲሁም ሃኪሞቹ የሚስማሙበት ህጎችና መመሪያዎች እንደሚኖሩና የህክምና ፍቃዳቸው ጥራት ታይቶ ወደፕላትፎርሙ እንዲቀላቀሉ የሚደረግበት አሰራር ስለመኖሩም ትናገራለች::
በአሁኑ ግዜም የጎግል ፎርም በማዘጋጀት የተወሰኑ ሃኪሞች እንዲመዘገቡ መደረጉንና በቀጣይ ወደስራው ሲገባ ሌሎች ሃኪሞችም በዚሁ ፕላትፎርም ውስጥ እንዲመዘገቡ በማድረግ የሃኪሞቹን ቁጥር የመጨመር እቅድ እንዳለ ትጠቁማለች::
ቴክኖሎጂው በርካታ ስራዎች ሊሰራበት የሚችል ትልቅ ዘርፍ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ዝማሬ፤ ልክ እንደእርሷ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም ቴክኖሎጂ ተኮር ስራ ፈጠራዎች ላይ በማተኮር ለህብረተሰቡ መፍትሄ እንዲያመጡ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ምክሯን ትለግሳለች::
ሚስተር አህመድ ተሃድሪ የቴክ አፍሪካን ዉሜን ፕሮግራም ፕሮጀክት ማናጀር ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት የስራ ፈጠራ ፕሮግራሙ በአፍሪካ ወጣት ስራ ፈጣሪ ሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ሲሆን ሴቶቹ አዲስ የቢዝነስ ሃሳብ ሲጀምሩ ሃሳባቸው መሬት ላይ እንዲወርድና ገንዘብ እንዲያመነጭ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል:: ፕሮግራሙም የተጀመረው እ.ኤ.አ አቆጣጠር በነሃሴ ወር 2022 ነው::
ከዚህ አንፃር በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአራት የአፍሪካ አገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ሴኔጋልና ቱኒዚያ 331 ወጣት ሴቶች አመልክተው 74ቱን በመምረጥ በካምፕ ሆነው አዲስ ለሚጀምሩት የዲጂታል ቢዝነስ ማጎልበቻ የሶስት ቀን ስልጠና ተሰጥቷቸዋል::
በመቀጠል ደግሞ ከ74ቱ ውስጥ ስምንቱን በመምረጥ ለሶስት ወራት ያህል በኦን ላይን የተለያዩ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ በማድረግ የቢዝነስ ሃሳባቸውን እንዲያበለፅጉ ተደርጓል:: ተወዳዳሪዎቹ የተመረጡበት መስፈርት ደግሞ በቢዝነስ ሞዴላቸው ውስጥ ያካተቱት ገበያ መጠን፣ ተወዳዳሪነታቸው፣ ልምዳቸው፣ የጀመሩት ቢዝነስ እንዴት ውጠታማ ሊሆን እንደሚችል ያቀረቡት ምክንያትና ሊያመጣው የሚችለው በጎ ውጤት ነበር::
በመጨረሻም ስምንቱ ተወዳዳሪዎች የቢዝነስ ሃሳባቸውን በአዲስ አበባ አቅርበው ታንዛኒያዊቷ ጁሊያና ቡሳሲ የተሻለ የዲጂታል ቢዝነስ ሃሳብ በማቅረቧ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች::
በቀጣይ ዓመት በዚሁ ፕሮግራም አማካኝነት ሌሎች ተጨማሪ አስራ ስደስት የአፍሪካ አገራትን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ተይዟል:: ይህም በርካታ የአፍሪካ ወጣት ሴቶች አዳዲስ የዲጂታል ቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ አመንጪዎች በፕሮግራሙ እንዲሳተፉ ይጋብዛል:: በተለይ ደግሞ ወጣት ሴቶች የቢዝነስ ሃሳብ ኖሯቸው ሃሳባቸውን እውን በማድረግ ረገድ ተገቢውን ክህሎት እንዲያገኙ በማስቻል ፕሮግራሙ የጎላ ሚና ይኖረዋል::
ከዚህ ባለፈ ፕሮግራሙ አፍሪካውያን ስራ ፈጣሪዎችን እርስ በእርስ በማገናኘት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ በገበያ እንዲተሳሰሩና በቅንጅት እንዲሰሩ የላቀ ሚና ይጫወታል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015