ተማሪ ኬሪያ ጀማል በተፈጥሮ አካል ጉዳተኛ ሆና ነው የተወለደችው። ማንኛውንም ነገር የምታከናውነው በእጇ ሳይሆን በእግሯ ነው። በሙስሊም አማኞች ዘንድ ደግሞ በእግር እንጀራ ቆርሶ መመገብ ነውር (ሀራም) ነው። ስለዚህም እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ስትማር ከቤተሰቦቿ ሳትለይ በጥሩ እንክብካቤ ውስጥ ነው ያለፈችው። ከዚያ በኋላ ያለውን ትምህርቷን ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል አትችልም። ምክንያቱም ከቤተሰቧቿ ተለይታ ርቃ ልትሄድ ነው ይህ ሲሆን ደግሞ ስትመገብ የሚያግዛት ቤት ተከራይታ ስትኖርም ሌሎች ድጋፎችን የሚያደርግላት ሰው ያስፈልጋታል።
ከቤተሰብ ስር እያለች ያለውን እያካፈሏት የቻሉትን እያደረጉላት ስምንተኛ ክፍል አድርሰዋታል። በዚህ ምክንያት አንድም ቀን አካል ጉዳተኝነቷ ተሰምቷት አያውቅም። በትምህርቷም በጣም ጥሩ ከሚባሉት ተርታ የምትመደብ ነበረች። ሆኖም ዘጠነኛ ክፍል ለመላክ ግን አቅማቸው አይፈቅድም። ብቻዋን የሚልኳት ልጅም አይደለችም። ለሁለት ሰው የሚሆን ወጪ መሸፈን ደግሞ እጅግ ከባድ ነው። እናም ላትሄድ ተፈርዶባት ሳለ ድንገት እድሏ መልካም አጋጣሚን ሰጣት። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ አሚና አህመድ አገኟት።
ወይዘሮ አሚና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካኝነት የተቋቋመው የሴቶች ሆስቴል(ማረፊያ) ዳይሬክተር ናቸው። በመምህርነት ለ36 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆኑ፤ የሴት ተማሪዎችን ጭንቀትና ጫና በሚገባ ይረዱታል። እናም ኬሪያንም እንዳዩዋት ሁኔታውን ሳትነግራቸው እድሉ እንደሚያስፈልጋት ገባቸው። ወደቦታው የምትገባበትን መንገድም አመቻቹላት። በእርግጥ ማረፊያው ዋነኛ አላማው እንዲህ አይነት ችግር ያለባቸውን ሴቶች መታደግ ነው። በተለይም ከትምህርት ጋር ተያይዞ ያሉባቸውን ፈተናዎች ከመፍታት አንጻር ከፍ ያለ ጥረት ያደርጋል።
የማረፊያ ማዕከሉ ዋና ተግባር ድሬዳዋ ከተማና ዙሪያዋ እስከ 30 እና 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ገጠር ቀበሌዎች እየወረዱ በማየት ልጃገረዶች ወደ ድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲመጡ ማድረግ ነው። ልጃገረዶቹ ደግሞ ጎጂ የምንላቸው ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙባቸው። በተለይም ካለእድሜ ጋብቻና የአካል ጉዳተኝነት ምክንያት እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ከትምህርታቸው እንዳይርቁ ማድረግ ነው። በገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ትምህርት እንዳያገኙ የሚያስችሉ በርካታ ምክንያቶች ችግሮች አሉ። ከላይ የተጠቀሱት ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ በቅርባቸው ትምህርት ቤት አለመኖሩም ሌላው ፈተና ነው። እናም እነዚህ ችግሮች በትምህርቱ ዘርፍ ገፍተው የሚወጡ ሴቶች እንዳይበራከቱ አድርጓልና ችግሩን ከመፍታት አንጻር ትምህርት ቢሮው ወደስራ ገብቷል። እንደ እነ ኬሪያ አይነቶችም መነሳትና ለዛሬ የተሸለ ሕይወት መኖር ምክንያቱ ይኸው ማረፊያ ነው።
ማረፊያው ከ38 የገጠር ገበሬ ማህበራት ተውጣጥተው የሚመጡ ተማሪዎችን የሚቀበልና በትምህርታቸው የሚያግዝ ነው። የተቋቋመው ደግሞ ከ15 ዓመት በፊት ሲሆን፤ በቤተሰብ የአቅም ውስንነት፣ በአካል ጉዳተኝነትና በባህላዊ ጫና ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ ታስቦበት ነው። እናም አካል ጉዳተኛዋ ኬሪያ በጉዳቷ ምክንያት ትምህርቷን እንዳታቋርጥ የቤተሰቧን ችግር ጭምር ተሸክሞላታል። ኬሪያ በማረፊያው ውስጥ ስትገባ ጀምሮ ብዙ ነገሮቿን በማደላደል ነው።
የመጀመሪያው ትምህርቷ እንዳይቋረጥ። ሀይማኖታዊ ሕጓን እንድታከብር አድርጓታል። ሁለተኛው ምንም እንኳን ማረፊያው ተማሪዎችን የሚቀበለው ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ቢሆንም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እህቷን ከስሯ እንዳትለይ በማድረግ እንክብካቤዋ እንዳይቀንስ አግዟታል። ከዚህም በተጨማሪ ስለቤተሰቦቿ ጭምር እንዳታስብ መደላደልን ፈጥሮላታል።
ማረፊያው ለኬሪያ ብቻ ሳይሆን እዚያ ለገቡ ሴት ተማሪዎች ሁሉ ልዩ እንክብካቤን ያደርጋል። በተለይም ከትምህርታቸው ጋር ተያይዞ ምንም እንዲጎልባቸው አይፈለግም። እናም ሲፈልጉ በቡድን፣ አልያም በተናጠል የሚያነቡበትን እድል አመቻችቶላቸዋል። በትምህርታቸው የላቁ ይሆኑ ዘንድም ልዩ ክትትል እንዲደረግላቸው ያመቻቻል። ለዚህ ደግሞ በአንድ ስፍራ መሰባሰባቸውን ይጠቀምበታል። ከቲቶር ባሻገር ትምህርታቸውን የሚያጠናክሩበት የቡድን ውይይት እንዲያደርጉ እድል ይፈጠራል። ይህ ደግሞ እንደ ኬሪያ አይነቶቹን የተሻለ ውጤት ባለቤት አድርጓቸዋል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ኬሪያ ወደ ማረፊያው ስትመጣና ከቆየች በኋላ ያለው ውጤቷ እጅግ የተለያየ በመሆኑ ነው። ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ ወደ ማረፊያው ገብታ በመጀመሪያው የትምህርት ዓመት አጋማሽ (ሴሚስተር) ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን ከዚያም ቦታውን እየተላመደችው ስትሄድና ያለው እንክብካቤ ሲጨመርበት አንደኝነቷን ማንም ሳይነጥቃት ቀጥላለች። አሁን 11ኛ ክፍል ደርሳለች።
ማረፊያው ለሴቶች ተስፋ ከመሆኑ ባሻገር ያለእድሜ ጋብቻን በመግታቱ በኩልም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። ምክንያቱም የሚቀበለው በክልሉ ካሉ የገጠር ቀበሌ ትምህርት ቤቶች ሁሉ የሚመጡ ሴት ተማሪዎችን ነው። ከአራቱ ክላስተር ስምንተኛ ክፍል የጨረሱትን እንደየችግራቸው ለይቶ ተቀብሎ ያስተናግዳል። ይህ ደግሞ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች በገጠር ተደብቀው እንዳይቀሩ ከማድረጉም በላይ ያለእድሜ ጋብቻን በብዙ መልኩ አስቀርቷል። የአቅም ውስንነት ኖሮባቸው ከትምህርት ጋር ሊቆራረጡ የሚችሉትን ሴቶችም ታድጓል ይላሉ ወይዘሮ አሚና።
በሌላ በኩልም ከማረፊያው ውጭ የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ወንድ ተማሪዎችንም ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ይደግፋል። ይህ የተደረገበት ምክንያት ደግሞ ወንዶች ከሴቶች እኩል ለመማር አይፈተኑምና ነው። ስለዚህም ማረፊያው (ሆስቴሉ) የትምህርቱን ዘርፍ በመደገፍ በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
እንደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ይህንን ማረፊያ አቋቁሞ መስራቱ ትምህርት አቋርጦ ከመሄድ፣ አግብቶ ከመቅረት፣ ችግር ሲያጋጥም አለመማርን ከመምረጥ መታደግ አስችሏል። በተጨማሪም ማረፊያው 24 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ እያንዳንዱ ክፍል ስምንት አልጋዎችን በመያዝ በ15 ዓመት ጉዞው ከ1ሺ 500 በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁምነገር አብቅቷል። አሁን በማረፊያው ውስጥ 145 ተማሪዎች ይኖሩበታል። በውጭ የሚያግዛቸው ተማሪዎችን ሳይጨምር ማለት ነው። ስለዚህም ብዙኃኑ የተሻለ ደረጃ ላይ ከማድረሱም ባሻገር ለአገር የሚያበረክቱትን እያሰፉ ይገኛሉም ብለውናል ዳይሬክተሯ።
ማዕከሉ (ሆስቴሉ) ባከናወነው ተግባር አሁን በርካቶች የሁለተኛና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ሆነዋል፤ ተመርቀው ማረፊያውንም ሆነ ሌሎችን መደገፍ የሚችሉ ዜጎች ተፈጥረዋል። ብዙዎቹ በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራታቸው ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን እያገለገሉም ይገኛሉ። ማዕከሉ የሥራ እድል የሚፈጠርበትን ሁኔታ አመቻችቷል የሚሉት ዳይሬክተሯ ምክንያቱም ብቁ ዜጎችን የማፍራት ራዕይን ያነገበ በመሆኑ ከዚያ የሚወጡ ተማሪዎች ተፈላጊ እንዲሆኑ ከአካባቢያቸው ሳይርቁ የሚሰሩበትን ሁኔታም ለማመቻቸት ነው። ይህ ደግሞ እነርሱ የወጡበትን እያስታወሱ ሌሎችን እንዲያግዙ ያስችላቸዋል።
ተማሪዎችን በማረፊያው ውስጥ ተቀብሎ የሚማሩበትን እድል ማመቻቸት መጀመሩ ሌላም እድል የፈጠረ እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ አሚና፤ የአካል ጉዳተኞችና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ሳይንገላቱ ሥራ እንዲቀጠሩም አስችሏል። ማለትም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ሳይንገላቱ የሥራ እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ካቢኔው እንደነዚህ አይነት ተማሪዎችን ለአገር መጠቀም ትክክል ነው በሚል አምኖበት ያለምንም ገደብ በዚያ የሚመደቡበትን እድል ሰጥቷቸዋል። ይህ እድል ደግሞ ተደራራቢ ችግር ላለበት ተማሪ እፎይታን የሚሰጥ ነው። በክራንችና በዊልቸር የሚሄዱትን ጨምሮ በርካታ አካል ጉዳተኛ ሴቶችም ተምሬ ምን እሰራ ይሆን ማን ይቀጥረኛል እንዳይሉ አድርጓቸዋል።
ውጤታማ በመሆናቸው የተነሳ ከስራ በፊት ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ይፈለጋልና ከዲግሪ በላይ በትምህርታቸው መግፋት ለሚፈልጉም እድሉን መስጠቱም ሌላው የማረፊያው መቋቋም ያመጣው ገጸ በረከት ነው። ስለዚህም ውጭ አገር ድረስ ሄደው የሚማሩ ተማሪዎችን ፈጥሯል። ይህ ምቹነት ደግሞ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ላለው ማሕበረሰብ ብዙ ትምህርትን የሚሰጥ ነው። አርአያ የሚሆኑ ሴት ተማሪዎቹን እያየ የአመለካከት ለውጦችን እንዲያመጣ አስችሎታል። ልጁን ትምህርት ቤት በመላኩ ደስተኛ እንዲሆንም እድል ሰጥቶታል ነው ያሉን ዳይሬክተሯ።
ወይዘሮ አሚና የቀደመውን የመማር ማስተማር ስርዓትና የሴቶችን መልካም አጋጣሚ ሲያስታውሱ ከ15 ዓመት በፊት ከ38 ቱም ቀበሌዎች መጥተው ድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚማሩ ሴት ተማሪዎች አልነበሩም። ምክንያቱ የማሕበረሰቡ አስተሳሰብና የልማዳዊ ድርጊቶች ነበር ። ‹‹ሴት ተምራ የት ትደርሳለች›› የሚለው ብሂል በስፋት ተንሰራፍቶ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ሴቶች ከማግባት ውጭ አማራጭ እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል። በመሆኑም ይህንን የተረዳው ትምህርት ቢሮ ማረፊያውን አቋቁሞ አሁን ብቅ ብቅ እያሉ የመጡ ጎበዝና አርአያ የሆኑ ሴት ተማሪዎችን አፍርቷል።
ሌላው ያነሱልን ነገር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ የሚያደርጋቸው ዋነኛ ችግር የትምህርት ቤት በቅርብ አለመኖር ሲሆን ቤተሰብም ቤት ተከራይቶ ማስተማር ያለመቻል ነው። በ1999 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ በ47 ሴት ተማሪዎች የተጀመረው ማዕከሉ (ሆስቴሉ) ግን ይህንን ችግር ፈቷል። በእርግጥ ማረፊያው ሲቋቋም ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል። ሁሉ ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ እንኳን ፈተናዎች ነበሩበት። አንዱ ኮንትራክተሩ ቁልፉን ሳያስረክብ መቅረቱ ከስምንተኛ ክፍል ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያለፉ 47 ሴት ተማሪዎች መግቢያ አጥተው መንከራተታቸው ነበር ። እርሳቸው ለምነው በየሆቴሉ ማሳደር ባይችሉ ኖሮ ፈተናው ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሌላው ደግሞ በወቅቱ ድሬዳዋ በከባድ ጎርፍ አደጋ የተጎዳችበት ጊዜ ነበርና ምኑን ከምኑ ማድረግ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ከባዱን ጊዜ ከባለሀብቶች በመለመን እንደ ቢሮ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል። ከዚያም ሻገር ብለው 600 የውሃ ቱቦዎችን ድጋፍ አግኝተዋል። ሆስቴሉን እንዲጸዳ አድርገውም ተማሪዎቹ የሚገቡበትን ሁኔታ አመቻችተዋል። በተመሳሳይ መብራትም አልነበረውምና ‹‹እንዴት ከጭለማ ወጥተው ጨለማ ውስጥ በማደር ተምረው ውጤታማ ይሆናሉ›› በማለት ወደ መብራት ኃይል ሄደው ነገሮችን አስተካክለዋል።
ልጃገረዶቹን ወደ ማረፍያው አስገብቶ ለማኖር ከአንሶላና ፍራሽ ጀምሮ ምግብና መጠጥ እንዲሁም በርካታ ነገሮች ያስፈልጉ ነበርና የመምህርቷ እግር አሁንም ለልመና ከመሮጥ አልቦዘነም ወደ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ በመሄድ የማረፊያውን መከፈት አብስረው ተማሪዎቹ አርፈው ትምህርታቸውን መማር ከጀመሩ በኋላም ደግሞ አንዳንድ ክፍተቶች መጥተውባቸው ነበር። ሆኖም እንደቀደመው ሁሉ ይህንንም መፍታት ችለዋል። ችግሩ የድጋፍ ማነስ ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንን ያመቻቹት ደግሞ በዩኒሴፍ የድሬዳዋ ተወካይ የነበሩት ናይጀሪያዊት ሴት ሆስቴላቸውን እንዲጎበኙ በማድረግ ነው።
ዩኒሴፍ በተወካዩ በኩል ከ350 ሺህ ብር በላይ እርዳታ ለ10ዓመታት ያህል አድርጎላቸዋል። ሆኖም ቋሚ ያልሆነ ድጋፍ እጅግ ፈታኝ ነውና ከ10 ዓመት በኋላ ሌላ ሥራን ጠየቃቸው። ይህም አጋዥ አካልን ማፈላለግ ነው። እንደ ትምህርት ቢሮ የተደረገው የክልሉ መንግሥት የሚደግፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢሆንም በጀቱ ግን አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር በእኩል የማይራመድ ነው። በተለይም ከተለያዩ ወቅታዊ ቀውሶች ጋር ተያይዞ በእጅጉ ፈተናው እንዲከፋ ያደርገዋል። እናም በ2013 እና በ2014 ዓ.ም ከባድ ጊዜን እንዳሳለፉ አይረሱትም። ሌላ አጋዥ ፍለጋ የግድ ያላቸውም ለዚህ ነው።
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ ዘርፉ የትምህርት ጉዳይ ነውና ትምህርትን ሊያግዝ የሚችል ሁሉ መጠየቅ አለበት። በዚህም ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ፓስታ፤ ሩዝ፤ ማኮሮኒና ዱቄት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አንሶላና ብርድ ልብስ አላቂ እንደመሆናቸው በየጊዜው ለማሟላትም አጋዥ ድርጅቶች ይጠየቃሉም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አጋጣሚዎችን በመጠቀምም ማረፊያው የሚደገፍበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ። አንዱና የማይረሱት የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበር ጥምረት ሥልጠና ለመስጠት በመጣበት ጊዜ አባላቱን ወደ ሆስቴሉ በማምጣት ልጃገረዶቹ ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ በማሳየት እያንዳንዳቸው አዝነውና አልቅሰው ከአባላታቸው ላይ አዋጥተው ያገዟቸው ነው። ይሁን እንጂ በተለይ ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ ነገሮች በሚሰጠው ገንዘብ የመግዛት አቅማቸው ስለተዳከመ የክልሉ መንግሥት የሚመድበውን በጀት መደገፍ ቢቻል መልካም ነው ባይ ናቸው።
ሆስቴሉ ጥበቃው ሳይቀር ሁለተኛ ዲግሪ እንዲይዝ ያደረገ ነው። በርካታ ዜጎችም በሥነ ምግባር እንዲታነፁ፤ የማሕበረሰቡን አመለካከት እንዲለውጡ አስችሏል። ተማሪዎች የጠለቀ እውቀት ኖሯቸው በተለያየ የትምህርት መስክ አገራቸውን እንዲያገለግሉም ረድቷቸዋል። ከዚያ በተጨማሪ ጎጂ ባህሎች ላይ ጠንከር ያለ የመፍትሄ ሀሳብን ማምጣት አስችሏል። እናም ይህ ተሞክሮ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የአገርም ሊሆን ይገባልና መጠቀሙ መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ።
እኛም የአገር ተስፋ ተማሪ እንጂ ሌላ አይሆንምና በሁሉም ዘርፍ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት እንደዚህ አይነት አሰራሮችን ልምድ ማድረግ ይገባል በማለት አበቃን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም