ግንባታን ውብ እና ማራኪ ከሚያደርጉት መካከል የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች ይጠቀሳሉ። ህንጻ የታለመለትን አገልግሎት በአግባቡ መስጠት እንዲችል፣ ህንጻውን የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ከመከላከል ባሻገር ከመበስበስ እና ከዝገትም በመከላከል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ይገለጻል።
ከሴራሚክ፣ ከእንጨት፣ ከወረቀት፣ ከፕላስቲክ እቃዎች እና ከብረት፣ ወዘተ. የሚመረቱት እነዚህ የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች፣ ለግንባታው ዘርፍ እጅግ ወሳኝ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች አቅርቦት ላይ የተከናወነው ተግባር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት የነበራት አንድ የሴራሚክ ፋብሪካ ብቻ ነው።
በቅርቡ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ባካሄደው አውደ ጥናት ላይ ንግግር ያደረጉት የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ወንድሙ ሴታ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ውስጥ የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች ከፍተኛ ፍጆታ አለ። ሁሉም የግንባታ ፕሮጀክቶች የማጠናቀቂያ እቃ ይፈልጋሉ። የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎች እጥረት እና የዋጋ መናር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እየተፈታተኑ ካሉ ችግሮች አንዱ ነው።
የህንጻ ማጠናቀቂያ ምርቶች ከፍተኛ ፍጆታ እና ፍላጎት ቢኖርም፣ በአገሪቱ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች ማምረቻ ፋብሪካዎችን በማቋቋም እና በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት ይስተዋላል። ሴራሚክን በአብነት በመጥቀስ ሲያብራሩ አገሪቱ የነበራት አንድ የታቦር ሴራሚክ ፋብሪካ ብቻ ነው። እሱም ያረጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቂ አቅም የለውም።
ለሴራሚክ የሚሆን ግብዓት በአገር ውስጥ እንዳለም ተናግረው፣ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እየዋለ ግን አለመሆኑን ነው ያመለከቱት። ተመርቶ እየቀረበ ያለው ሴራሚክም የጥራት ጉድለት የሚስተዋልበት፣ ዋጋውም ከፍ ያለና የቅሬታ ምንጭ ሲሆን የሚስተዋል እንደሆነ ያብራራሉ። በሌሎች የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች ላይ የተከናወነው ተግባርም እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም ለማጠናቀቂያ ለወለል ንጣፍ የሚውል ሴራሚክ በአብዛኛው ከውጭ አገራት ይገባል፤ ይህም በገበያ ተለዋዋጭነት ወጪው በየጊዜው ከፍ እያለ ዘርፉን እየፈተነ ይገኛል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሴራሚክ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መምጣቱ ይነገራል።
በግንባታ ማጠናቀቂያ ላይ የተፈጠረው ችግር በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩ ባሻገር በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይም አሉታዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በግንባታ ማጠናቀቂያ እጥረት ምክንያት በርካታ ፕሮጀክቶች እስከመቋረጥ መድረሳቸውን ነው የጠቆሙት።
እንደ አቶ ወንድሙ ማብራሪያ፤ የኮንስትራክሽን ማጠናቀቂያ እቃዎችን ለማምረት የሚያስችል አቅም አገር ውስጥ አለ። በተለይም ማርብል እና ግራናይት ለማምረት የሚያስችል በቂ ክምችትም አለ። ከጎጃም እስከ ሐረር፤ ከጋምቤላ እስከ ቤኒሻንጉል በቂ ክምችት አለ። ግን ያንን ክምችት አውጥቶ በአግባቡ ፕሮሰስ አድርጎ ለግንባታ በሚያስፈልገው የጥራት ደረጃ ልክ ማምረት ላይ ግን ችግር ይስተዋላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ፍንጭ እየታየ ነው የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ በተለይም በቅርቡ በተካሄደው የማዕድን ኤክስፖ ላይ በጣም ብዙ ኩባንያዎች የግንባታ ማጠናቀቂያዎችን ወደ ማምረት እየገቡ መሆናቸውን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መሸፈን የሚቻልበት እድል መኖሩንም ጠቁመዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጨማሪ የግንባታ ማጠናቀቂያ ፋብሪካዎች ወደ ስራ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ ላይ አንድ ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ ስራ እየገባ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአማራ ክልል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የአረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካም እንዲሁ ወደ ስራ ገብቷል ሲሉ ያብራራሉ። አረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካ በቀን እስከ 20 ሺህ ሜትር ስኩየር ሴራሚክ የማምረት አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል።
እነዚህ ሁለቱ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ከገቡ የሴራሚክ ችግሩን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአገሪቱ ያለውን የሴራሚክ ምርት እጥረት ለመፍታት ሁለቱ ፋብሪካዎች መጨመራቸው ግን በቂ አይደለም ይላሉ። ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ማቋቋምና ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም ገልጸው፣ ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልገው ሙሉ ጥሬ እቃ አገር ውስጥ እንዳለም አመልክተዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ዘሪሁን ዘገየ እንደሚሉት፤ ከ2006 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ሶስት ነጥብ 34 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የተለያዩ አይነቶች የሴራሚክስ ምርቶች በአገር ውስጥ ተመርተው ግብይት ተፈጽሞባቸዋል። ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ አምስት ነጥብ 79 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የሴራሚክስ ምርት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። ይህም የሚያመላክተው አገሪቱ ሴራሚክ ለማስገባት ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ ነው።
ሴራሚክን ጨምሮ ሌሎች የህንጻ ማጠናቀቂያ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አብዛኛውን ግብዓት ከውጭ አገራት የሚያስገቡ መሆናቸውም የምርት እጥረቱ እና የዋጋ መናር እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ይጠቁማሉ። በአንዳንድ ወቅቶች የማጠናቀቂያ ምርቶች እጅግ ከመወደዳቸው የተነሳ በአገር ውስጥ ጭምር በዶላር ይሸጡ እንደነበር ጥናት አቅራቢው በመጥቀስ፣ አቅራቢዎቹ ለምን በዶላር ሆነ ተብለው ሲጠየቁ ማጠናቀቂያ ምርቶችን በዶላር ስለምናስገባ ነው በማለት በዶላር ግብይት እንዲፈጸም ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል። ይህም የቅሬታ ምንጭ ሆኖ እንደነበር ነው ያስታወሱት።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ይህ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደሩም ባሻገር የሰውን የመግዛት አቅም የሚያዳክም በመሆኑ ልዩ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። ይህንን ችግር ለመፍታት ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
የሴራሚክስ የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት በአሁኑ ወቅት ጥረቶች ቢደረጉም፣ የህንጻ ባለቤቶች ለአገር ውስጥ ምርት የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆኑ የአገር ውስጥ ምርት በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ምክንያት ሆኗል ሲሉም ያብራራሉ። ከአመለካከት ጀምሮ ለአገር ውስጥ ምርት ያለው ግንዛቤ የተዛባ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በአገር ውስጥ የሴራሚክ ምርት ላይ የተዛባ ግንዛቤ እንዳለም ነው ያመለከቱት፤ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የአገር ውስጥ ምርቶች በጥራት፣ በጥንካሬ፣ በውበት፣ በበቂ መጠን አለመመረታቸው ተመራጭ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ዘርይሁን መረጃ፤ ከግንባታ ማጠናቀቂያዎች መካከል ለአብነት ለግንባታዎች የሚውሉ አንዳንድ የአገር ውስጥ ውብ ንጣፎች (ታይሎች) ከውጪው ጋር ሲነጻጸሩ በእርግጥም ጥራታቸው የወረደ ነው። እነዚህ አንደኛ ውሃ ወደ ውስጥ ያሰርጋሉ፣ ሁለተኛ ቆሻሻ ለማስለቀቅ ሲፋቁ የመፈረካከስ ባህሪ አላቸው፤ ስለዚህ ጥራታቸው ላይ ችግር አለ። ከዚህ የጥራት ችግር የተነሳ ሰው የአገር ውስጡን እየተጠቀመ አይደለም። በመሆኑም መሰል ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ጥራታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።
ሌሎቹ ከፍተኛ ችግር የሚስተዋልባቸው የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች ቀለም እና መስተዋት ናቸው። በሁለቱም በኩል ሰፊ ችግር ይስተዋላል። ይህን ችግር ለመፍታት በርካታ ተግባሮች መከናወን አለባቸው።
የህንጻ ማጠናቀቂያዎች እጥረት እና የዋጋ ንረት በግንባታው ዘርፍ ላይ እያስከተለ ካለው ተጽዕኖ ባሻገር ለአጠቃላይ ምርት የዋጋ ንረትም የበኩሉን ሚና ይጫወታል። የዋጋ ንረትን ለመቋቋምና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የአገር ውስጥ የህንጻ ማጠናቀቂያ ምርቶች ከውጭ የሚገባውን እንዲተኩ መደረግ አለበት። ለዚህም አስገዳጅ ህጎችን አውጥቶ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
ሴራሚክን ጨምሮ የሌሎች የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች ጥራትና ዋጋ ላይ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ የሚቻለው በዘርፉ ብዙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ሲቻል ነው የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ሴራሚክ እና ሌሎች የግንባታ ማጠናቀቂያዎች ከውጭ ከሚገባው በቅናሽ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ፤ ድርጅቶች ስፔስፊኬሽን ሲያስቀምጡ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል። አብዛኞቹ የህንጻ ማጠናቀቂያ ምርት ገዢዎች ግዥ ለመፈጸም የአገር ውስጥ ምርቶችን ስፔስፊኬሽን ውስጥ የማስገባት ችግር አለባቸው። ስፔስፊኬሽን ውስጥ እንዲገቡ እየተደረጉ ያሉት እቃዎች ግን የውጭ ናቸው። ይህም በአገር ውስጥ ያለው ምርት እንዳይበረታታ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በመሆኑም የአገር ውስጥ ምርቶች ስፔስፊኬሽን ውስጥ እንዲገባ የሚያስገድድ አስገዳጅ ህግ መዘጋጀት አለበት።
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከውጭ አገራት የሚገባውን በአገር ውስጥ መተካት፣ ወደ ውጭ መላክ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ፣ በገበያ ትስስር የአገር ውስጥ የግንባታ የገበያ ትስስር ውስጥ እንዲካተት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ፤ ባለፈው ዓመት የኮንሰልታትንስ ወርክ ማኑዋል/ የአሰራር መመሪያ/ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፅድቋል። በዚህ በስፔስፊኬሽን ውስጥ የአገር ውስጥ ምርቶች መጠቀስ አለባቸው የሚል ተካቶበታል። የአገር ውስጥ ምርቶች ካልተጠቀሱ ስፔስፊኬሽኑ ውድቅ መሆን አለበት። በተደጋጋሚ ስፔስፊኬሽን ውስጥ እነዚህ ነገሮች አስገዳጅ ሆነው መግባት አለባቸው የሚል ቅሬታ ይነሳ ስለነበር ነው ይህ እንዲገባ የተደረገው።
በአገር ውስጥ የማይመረቱ እና ሊገኙ የማይችሉ ምርቶቹ ከሆኑ ብቻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እውቅና ሲሰጠው ከውጭ በመጣ ምርት መስራት ይቻላል የሚል መመሪያ ውስጥ እንዲካተት ተዳርጓል። እነዚህ ህጎች ለኮንትራክተር እና ኮንሰልታንት ሰፊ ግንዛቤ ተሰጥቶ ወደ ውጪ የሚሄደውን የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መቀነስ ይቻላል፣ የአገር ውስጥ ምርትንም ማበረታታት ይቻላል ተብሎ ነበር።
የአገር ውስጥ ምርት ሲበረታታ ፋብሪካዎቹ ስለሚጠናከሩ የግንባታ ማጠናቀቂያ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር የስራ እድልም መፍጠር ይቻላል። አሁንም ለእዚህ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት። ሁሉም አካል ለተፈጻሚነቱ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
በዚህ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት፣ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር በጆይንት ቬንቸር መስራት ያስፈልጋል። አብረው የሚሰሩ የውጭ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን የማምጣት እድል አላቸው፣ አገር ውስጥ ያለው ደግሞ የራሱን ማምረቻ መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ ይችላል። ሁለቱ በመተጋገዝ ምርትን ማሳደግ ይችላሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ስራ ያቆሙ የማጠናቀቂያ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት ስራ ማስገባት ይቻላል። በዚህም ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ ይቻላል።
አገሪቱ ባላት አቅም የማጠናቀቂያ ምርቶችን ማምረት ብትችል ብዙ ሚሊየን ዶላሮችን ማዳን እንዲሁም ብዙ የቆሙ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠልም ይቻላል። በመሆኑም ለዚህ ሰፊ ስራ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች አምራች ፋብሪካዎች ግብዓቱን ለማምረት የሚያስፈልጋቸው ዘመናዊ እና ውድ ማሽኖችን ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ በዚህ ረገድ በትኩረት ካልተሰራ የግንባታ ዘርፉን አሁን ካለበት ችግር ማውጣት አይቻልም። በመንግስት እና በግለሰቦች የሚገነቡ ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ አዳጋች ይሆናል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015