የተገናኙት በስራ አጋጣሚ ነው። ሁለቱ በእንስሳት ህክምና ሳይንስ የተማሩ ሲሆን አንደኛው በጠፈር ምርምር አሜሪካን አገር ትምህርቱን ተከታትሏል። በዶሮ እርባታ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በተለይ ደግሞ ዘርፉ በእውቀት የሚመራበትንና የሚሰራበትን መንገድ ለመፈለግ አንዳቸው ሀሳብ ጠንሳሽ ሌላቸው ሀሳብ ደጋፊና አብሮ የመስራት ፍላጎት በማሳየታቸው ወደ ዶሮ እርባታና እንቁላል ማስፈልፈል ስራ ገቡ።
በዚህም ተሳክቶላቸው የስጋ ዶሮዎችንና እንቁላል ለገበያ ማቅረብ ቻሉ። ቀስ እያሉ በዶሮ እርባታ፣ እንቁላል፣ በወተት ላም፣ በከብት እርባታና ማድለብ ስራ መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከአዋጭነት ጥናት እስከ ምርት አቅርቦት ድረስ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት አቋቋሙ።
ዛሬ ላይ ይህንኑ ስራቸውን አጠናክረው በቢሾፍቱ ከተማ የዶሮ ማርቢያ፣ እንቁላል ማስፈልፈያ፣ ከብት ማደለቢያና የላም ወተት ማምረቻ ማእከላት በተለያዩ ቦታዎች ከፍተዋል። ወደዚህ ስራ ለሚገቡ በርካታ ወጣቶችም ምርቶቹን በማቅረብና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ወደስራው እንዲቀላቀሉ አድርገዋል።
በዚህም በተለያየ መልኩ በራሳቸውና ከራሳቸው ውጪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ የጀመሩትን ‹‹የሌማት ትሩፋት›› ፕሮጀክት በከተማ ደረጃ ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍም የበኩላቸውን አስተዋፆ እያደረጉ ይገኛሉ።
በቅርቡም አስፈላጊውን ጥናት በማካሄድ ‹‹የኢትዮጵያ ግብርና እንዴት ይዘምን?›› በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በአይነቱ የመጀመሪያና በርካታ ወጣቶችን የሚያሳትፍ ስልጠና ለማካሄድ እቅድ ይዘዋል። ይህም ወጣቱ በግብርናው ዘርፍ ገብቶ እንዲሰራና ዘርፉን በማዘመን ራሱን እንዲለውጥ እድል እንደሚሰጥ ተስፋ ጥለዋል የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ መስራቾች።
ወጣት ዶክተር አቡኑ አንዳርጌ የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንስሳት ህክምና ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። በተማረበት የትምህርት መስክ በዶሮ እርባታ ላይ በሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል። በተለይ ደግሞ ከሰራባቸው ድርጅቶች በአንዱ ያየውን ክፍተት ስራውን እውቀት አክሎበት በራሱ እንዲሰራ አነሳስቶታል።
ከተመለከተው ክፍተት በመነሳት ሰዎች ትክክለኛ የዶሮ ምርቶችን ሳይንገላቱ እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ጥናት ማካሄድ ጀመረ። ሃሳቡ መሬት እንዲወርድና ግቡን እንዲመታ አቶ አሸናፊ ጌታሁን የተባለውና በአውስትራሊያ የሚኖረው ጓደኛው ድጋፍ ደግሞ ከፍተኛ ነበር። በስራ አጋጣሚ ቢሾፍቱ ከተማ የዶሮ መኖ በማቅረብ ያገኘው ሌላኛው ጓደኛው ዶክተር ተክሌ ሽፈራውም ስራውን ለመጀመርና አብሮ ለመስራት ያሳየው ፍላጎት የሚናቅ አልነበረም። የዶክተር አቡኑ ችግር ፈቺ ሀሳብ፣ ከጓደኞቹ የሃሳብ ድጋፍና አብሮ የመስራት ፍላጎት ጋር ተዳምሮ በዶሮ አቅርቦት በኩል የሚታየውን ችግር ሊፈታ የሚችል ‹‹ትረስት አግሮ›› የተሰኘ አማካሪ ድርጅት ፈጠረ።
ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር በካፒታል ሳይሆን ሀሳብ በመፍጠር ነበር። ነገር ግን ጓደኛሞቹ ሃሳቡን ሲፈጥሩ ሃሳቡ እንዴት ገንዘብ ሊያመጣ እንደሚችል አስልተው ነበር ስራውን የጀመሩት። መነሻ ካፒታላቸውም 200 ሺ ብር ነበር። ይህም እቃ ግዢ፣ ቢሮ ማደራጀትና በማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቱን ማስተዋወቅ ይጨምራል።
ድርጅቱ ስራውን በቢሾፍቱ ከተማ ሲጀምር በቅድሚያ የማማከሪያ ቢሮ ከፈተ። በመቀጠል ደግሞ በእንስሳት እርባታ ወጣቱና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እውቀትና ግንዛቤው ኖሯቸው ወደስራው እንዲገቡ በራሱ ማእከል ስልጠናዎችን መስጠት ጀመረ።
ስልጠናውን ከሰጠ በኋላ እውቀት ላይ የተመሰረተ የአዋጭነት ጥናት ወደ ዶሮ እርባታ ለሚገቡ ወጣቶች ሰራ። የቦታ መረጣም አደረገ። ስራውን በባለሞያዎች ካረጋገጠ በኋላ ዶሮ፣ የወተት ላም፣ ፍየል፣ በግ ከብትና የአሳ ማምርቶችን ጭምር የማቅረብ ስራዎችን አከናወነ።
ይህን ሁሉ ስራዎች ድርጅቱ ካከናወነ በኋላ በአምራቾችና ተጠቃሚዎች መካከል የገበያ ትስስር ይፈጥራል። ዶሮዎች እድሜያቸው ሲያልቅ/እንቁላል ጥለው ሲጨርሱና ወደ ስጋ ዶሮነት ሲቀየሩ/ድርጅቱ ተቀብሎ ይገዛቸውን መልሶ ለገበያ የሚቀርቡበትን አሰራር ዘርግቶ ወደ ህብረተሰቡ መግባት ችሏል። ይህንኑ ሰንሰለት በመፍጠር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደስራ ገብቷል።
ገና ስራውን በጀመረ በአምስት ወራት ውስጥ ድርጅቱ ችግር ፈቺ ስራዎችን በመስራትና ህብረተሰቡም ስራውን ደስተኛ ሆኖ በመቀበል ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በተለይ ማንኛውም በእንስሳት እርባታ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶችና ሌሎች የህብረሰተብ ክፍሎች ትክክለኛና በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ ችሏል።
በአሁኑ ግዜ ትረስት አግሮ ኢንዱስትሪ ማንኛውም ወጣትና ሌላም ሰው እንስሳት አርቢ ወደ እርባታ ለመግባት ሲፈልግ አጠቃላይ ስልጠና እንዲሰጠው የማድረግ ስራዎችን ይሰራል። መኖ ማምረት ለሚፈልጉም ስልጣናዎችን ይሰጣል። ራሱ ድርጅቱ የመኖ ማሽኖችን ከውጪ አገር በማስመጣት ያስተክላል።
ወደስራው ለሚሰማሩ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለየትኛውም ባንክና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የአዋጭነት ጥናት ሰርቶ ያቀርባል። ቦታ መረጣ አድርጎና የባለሙያ ድጋፍ አድርጎ ዶሮ፣ እንቁላል፣ የወተት ላም፣ በግ፣ ፍየልና ከብት በማቅረብ ወደ ሰዎች ስራ እንዲገቡ ያደርጋል።
ከዚህ ባለፈ ድርጅቱ በራሱ የሚያመርተው የዶሮ፣ እንቁላል በግ፣ ፍየል፣ ከብትና የወተት ላም ምርት አለው። ነገር ግን ድርጅቱ በራሱ በማምረት ብቻ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት የማይችል በመሆኑ ከሌሎች ትላልቅ ድርጅቶች ጋር በመሆን ምርቱን ከነሱ ወስዶ ለህብረተሰቡ ያቀርባል። እንቁላል ከውጪ አገር በማስመጣትም የስጋ ዶሮዎችን በማስፈልፈል በራሱ ማእከል አማካኝነት ለተጠቃሚው ያቀርባል።
ድርጅቱ በማንኛውም የእንስሳት ልማት ዘርፍ መግባት ለሚፈልጉ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑ አኳያ ለአገልግሎት የሚጠይቀው ክፍያ አለ። ማንኛውም ወጣት ወይም ሌላ ሰው በእንስሳት እርባታ ዙሪያ የአንድ ሳምንት ስልጠና ለማግኘት 1 ሺ 500 ብር ይከፍላል።
ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ ዶሮ አርቢ ገዝቶ ማርባት ከጀመረ በኋላ በአንድ ዶሮ በቀን ሁለት ብር እየከፈለ ሙሉ የክትባት፣ መንቁር ቆረጣና ሌሎችንም የጤና ክትትል አገልግሎቶች ያገኛል። በወተት ላም ላይም በወር በአንድ ላም ሁለት መቶ ብር በመክፈል ሁሉንም አይነት የክትትል አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል። ምርቱን ድርጅቱ የሚያቀርብ ከመሆኑ አኳያ እንደራሱ ምርት አድርጎ ይንከባከባል።
‹‹በዚህ የእንስሳት ልማት ዘርፍ በተለይ ደግሞ በዶሮ ላይ የሚሰሩት ስራዎች 99 ነጥብ 2 ከመቶ ያህሉ በእውቀት ላይ ተመስርቶ አይሰራም›› የሚለው ወጣት ዲክተር አቡኑ፤ ከዚህ ውስጥ 0 ነጥብ 8 ያህሉ ብቻ በዘመናዊ መልኩ እንደሚሰራበት ይናገራል። ይህም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የሚያመለክትና ድርጅቱም ዘርፉን በማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ይጠቁማል።
የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ስራዎች መሰራት ያለባቸው እንደ ትረስት አግሮ በመሰሉ አማካሪ ድርጅቶች መሆኑንም ተናግሮ፤ በተለይ ይህንን ከወጣቶች የስራ ፈጠራ ጋር አጣምሮ መስራት ከተቻለ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል። ምርቶቹ ከአገር ውስጥ ፍላጎት በዘለለ ወደውጪ አገር የሚላክበት እድልም ስለሚፈጠር የውጪ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ይጠቁማል።
ስራው የመንግስትን የልማት አቅጣጫንም ተከትሎ የሚከናወን ከመሆኑ አኳያና በተለይ ደግሞ የከተማ ግብርናን ከማስፋፋት አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ወጣት ዶክተር አቡኑ ይገልፃል። በይበልጥ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ያስጀመሩትን የሌማት ትሩፋት የተሰኘ ፕሮጀክት በሚገባ የሚደግፍ መሆኑንም ይናገራል።
በቅርቡም ድርጅቱ እስከ 10 ሺ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚገኙ ወጣቶችን በማሰልጠን በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ውስጥ ስራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ፕሮጀክት ቀርፆ ‹‹ኢትዮጵያ መስራትና ስራ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶችን ታፈራለች” የሚል ስኪል ኢትዮጵያ የተሰኘ ንቅናቄ በመመስረት ወደስራ መግባቱንም ነው የሚያብራራው። በዚሁ ስልጠና መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዲገኙ ድርጅቱ በደብዳቤ ጥሪ መቅረቡንም ይገልፃሉ።
በስልሳ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ እንዲህ አይነት አደረጃጀት ያለው የማማከር ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልተፈጠረና በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት በማየት ድርጅቱ ወደስራ መግባቱንም ያስረዳል። ከተለመደው አሰራር ወጣ በማለት ድርጅቱ ህብረተሰቡን የማገዝ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ወጣት ዶክተር አቡኑ ይጠቁማል።
እስካሁን ባለው ሂደት ድርጅቱ ከተለያዩ ትላልቅ ድርጅቶች ጋር ሰርቷል። ከጠቅላይ ሚንስትር ቢሮም ጋር አንዳንድ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። አሁንም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ የህብረት ስራ ባንኮች፣ ሌሎች ግለሰቦችና ባለሃብቶች የድርጅቱን ሃሳብ በመያዝ በጋራ ቢሰሩ ለህብረተሰቡ የተሻሉ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ያምናል።
በቀጣይም ድርጅቱ በርካታ ስራዎችን ለማከናወን የተለያዩ እቅዶችን ይዟል። ለአብነትም ከተለመደውን የዶሮ ማርባትና እንስሳት ማደለብ በመውጣት አሰራሩን ይበልጥ የማዘመን ስራ ለመስራት አቅዷል። 100 ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች እንዴት ስልጠና መስጠትና እውቀት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ብሎም ህብረተሰቡ በእንስሳት ሀብት የምግብ ዋስትናውን በምን መልኩ ማረጋገጥ እንዳለበት አበክሮ ይሰራል።
በቅርቡ ደግሞ 10 ሺ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማሰልጠን የሚያስችል ንቅናቄ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ውጥን ይዟል። ይህም በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ ያሉ ወጣቶች ገንዘብ ሳይኖራቸው ወይም በአነስተኛ ገንዘብ በአጭር ግዜ ውስጥ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ስራ እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል። ይህም ወጣቱ ስራ እንዲኖረው የሚያደርግ በመሆኑ በአገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ ያደርጋል።
የድርጅቱ አብዛኛዎቹ ደምበኞች በአዲስ አበባ ከተማ እንደመሆናቸው በከተማዋ ትልቅ የምርት ማእከል በመክፈት ደምበኞቹን ተደራሽ የማድረግ ውጥንም ይዟል። እስካሁን ባለው ሂደትም በድርጅቱ ውስጥ ለሚሰሩ 11 ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውጪ በዚሁ ስራ ማለትም በጫኝና አውራጅ፣ ምርት ለማጓጓዣ በመኪና ኪራይ አቅርቦትና በሌሎችም የቀን ገቢ ለሚተዳደሩ በርካታ ወጣቶች በተዘዋዋሪ የስራ እድል ተፈጥሯል። ሌሎች በርካታ ወጣቶችም ከድርጅቱ የምክር አገልግሎት አግኝተውና ምርት ተቀብለው የራሳቸውን ስራ መፍጠር ችለዋል።
ወጣቶች ሩቅ ያለውን ሳይሆን ራሳቸው ጋር ያለውን ነገር መመልከት ከቻሉ በርካታ ነገሮችን መፍጠር እንደሚችሉ የሚናገረው ወጣት ዶክተር አቡኑ፤ በአሁኑ ግዜ ዋጋ ስለማይሰጠው ነው እንጂ ከዚህ በፊት ብዙዎች ትምህርት የሚወስዱት በግብርናውና በእንስሳት ሀብት ዘርፍ ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይናገራል።
አሁንም ቢሆን ግብርናው በቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተሰራበት ባለመሆኑና ሰፊ የሚሰሩበት መስኮችን ያቀፈ በመሆኑ ወጣቱ በእንስሳት ሀብት ልማት ብቻ በመሳተፍ ራሱንና አገሩን ሊለውጥ የሚችልበት እድል እንዳለ ይጠቁማል። ከዚህ ባለፈ የራሱንና የሌሎችንም የምግብ ዋስትና ሊያረጋገጥ እንደሚችልም ይጠቅሳል። ከዚህ አኳያ ወጣቱ ሳያመነታ በዚህ ዘርፍ በመግባት ራሱንና አገሩን መለወጥ አለበት ሲል መልእክቱን ያስተላልፋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም