ሙሰኞች የአገር ስጋት ሆነዋል ሲሉ የችግሩን ክብደት አመላክተዋል። ሙሰኞቹም የመጨረሻ ጽዋቸውን ከመጨለጣቸው በፊት የያዙትን ሰይፍ በሕዝብ ላይ መምዘዝ ጀምረዋል። በቀበሩት ፈንጂም ሕዝብን በጅምላ ለማጥፋት የጥፋት ተልዕኮን አንግበው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። በማንነትና በብሔር ሽፋን ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ብዙ ድንጋዮችን መፈንቀል ጀምረዋል። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባና በወለጋ የተፈጠሩት ሁከቶችና ብጥብጦች ማሳያዎች ናቸው።
የብሔር ብሔረሰቦች አምባ የሆነችው አዲስ አበባ በርካታ ሴራዎች ተጠንስስውላት፤ በርካታ እልቂት ታውጆላት ስትናጥ ከርማለች። ሙሰኞች ከመጋረጃው ጀርባ ተደብቀው ንጹሐን ተማሪዎችን በማያውቁት ፖለቲካ በማወናበድና የተለያዩ አጀንዳዎችን በማራመድ የሙስና ዕድሜያቸውን ለማራዘም በብዙ ታትረው ሲሰሩ ከርመዋል። ለእነሱ የማይጠረቃ ፍላጎት ንጹሐን ተማሪዎችን ጭዳ ለማድረግም በርካታ ርቀት ተጉዘዋል። ሆኖም ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የተሰወረ ነገር የለምና ምኞታቸው እንደጉም የሚያበንን የሕዝብ መድረክ ተካሂዶ ዓላማቸውን ማክሸፍ ተችሏል።
በተለይም የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለፉት ቅዳሜና እሁድ ከተማሪ ወላጆች ጋር ባደረገው ውይይት የሙሰኞችና የሁከት ጠማቂዎች ሴራ አደባባይ ወጥቶ ተሰጥቷል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች ራቁታቸውን ቀርተዋል። መንግስትና ሕዝብም እየተመካሩ በመስራት ከጀመሩት የጸረ ሙስና ትግል ለአፍታም ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ የሆነ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል።
ሰሞኑን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃም ሙስና በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶችና የሰላም እጦቶች ዋነኛ መንስኤ ነው። ሙስና ባለበት ግጭት፤ ብጥብጥና ሁከት የሰርክ ክስተቶች ናቸው። በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይህ ነው። በተለይም መንግስት በሙሰኞች ላይ ግልጽ የሆነ ጦርነት ማወጁ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከየተደበቁበት በመውጣት በዘረፉት ገንዘብ እዚህም እዚያም ሁከትና ብጥብጥ እንዲነገስና መንግስት ከያዘው አገርን የማበልጸግ ዓላማ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አልመው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም በሙሰኞች ሴራ ወደኋላ የሚመለስ ነገር እንደሌለ በግልጽ ተቀምጧል።
ለሙሰኞች ጊዜ መስጠት የተያዘውን የብልጽግና ጎዳና ወደ ኋላ ከመመለሱም በሻገር አገሪቱ በማያባራ ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ እንድትኖር መፍቀድ ማለት ነው። ስለሆነም ከአፎቱ የተመዘዘው የጸረ ሙስና ካራ ሙሰኞችን ሳይቆርጥ ወደ ሰገባው መመለስ አይኖርበትም። የሙስና ዋና ተጠቂ የሆነውም ሰፊው ህዝብ ሙሰኞች የሚሰሩትን ደባ በመገንዘብ፤ በየስፍራው የሚፈጥሯቸውን ሁከትና ብጥብጦች በማውገዝና ብሎም ሙሰኞችን አሳልፎ በመስጠት የጸረ ሙስና ትግሉ ዋነኛ አጋር ሊሆን ይገባል። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ከወሬ ይልቅ ተግባርን ብቻ ነውና!
በምስራቅ ወለጋ የተፈጠረውን ክስተት ስሰማ ከጥቂት ሳምንታት ገጥሞኝ የነበረን አሳዛኝ ክስተት አስታወሰኝ ። እለቱ እሁድ ነበር። ወደ አመሻሽ አካባቢ። ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር በመኖሪያ ቤቴ አካባቢ ሻይ ቡና እያልን … የባጥ የቋጡን እናወጋለን።
በተለይ የሰሜኑን ጦርነት ለመቋጨት እየተደረገ ባለው ጥረት በእጅጉ መደሰቱን በስሜት ነገረኝ። እኔም በሃሳቡ እንደምስማማ በመግለጽ፤ የሰሜኑን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በልቤ ትልቅ ተስፋ እንደፈጠረ ነግሬው ‘በጉዳዩ ላይ ወደ ማብራሪያ ልሻገር ስል ፤ የወዳጄ የስልክ ጥሪ አቋረጠኝ … ።
ተንቀሳቃሽ ስልኩን አንስቶ ሞቅ ባለ ድምጸት፤ Akkam jirtaa Hiriyaa Koo..(ጓደኛዬ እንዴት ነህ …) አለ ፤ ከደዋዩ ሰው ምላሽ ተከተለ።
የወዳጄ ፊት በአንዴ ፍም መሰለ ፤ ዝግ ባለ ድምጸትም Malttu ummamee? (ምን ተፈጠረ?) ሲል ወዳጄ ጠየቀ…. ምላሹ ተከተለ ፤
በሰማው ነገር ግራ የተጋባው ወዳጄ፤ Fayeetu ajjifame?…enyuttu ajjesse? (ፈዬ ተገደለ?…… ማነው የገደለው?) ሲል ጠየቀ። (ፈዬ የዚህ ወዳጄ ታናሽ ወንድም ሲሆን፤ የህዝብ ትራንስፖርት ሹፌር ነው)፤ shaneitu ajjeesse (ሸኔ ነው የገደለው… ) የሚል ምላሽ ተሰማ ፤ እየተርበተበተ …essattii ajjefame(የት ነው የተገደለው …) ሲል በተስፋ መቁረጥ ሁኔታ ጠየቀ።
ስልኩን የደወለለት ሰው Nannoo magala maqiitti…..(መቂ ከተማ አካባቢ…) በማለት የታናሽ ወንድሙን ሞት እንደዋዛ አረዳው።
ጠዋት በስልክ አውርቶት በደስታ የተለየውን ታናሽ ወንድሙን ሞት የሰማው ይህ ወዳጄ ባለበት ደርቆ ቀረ ። ስለ ፖለቲካ ሳይሆን ስለ ሥራ ብሎ ከቤቱ የወጣው ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ ማለፍ ልብ ይሰብራል።
በእለቱ እንደ ፈዬ ሁሉ ስድስት በሚሆኑ ንጹሃን ላይ አሸባሪው፣ ጨፍጫፊው ሸኔ ሞት ፈርዶባቸዋል፤ በተከፈተባቸው የጥይት ሩምታ በርካቶች ቆስለዋል፣ ንብረት አውድሟል። ምስራቅ ወለጋ ላይ ንጹሃንን በተለይ የአማራ ተወላጆች ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ መግደል፣ መዝረፍ፣ ማፈናቀል የእለት ግብሩ የሆነው አሸባሪው ሸኔ በምስራቅ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋ መሰል ድርጊቶችን መፈጸም መጀመሩ ጉዳዩን ከባድ ያደርገዋል።
ይህ ሁኔታ ‘እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም’ የሚለውን ቆየት ያለ አባባልን ያስታውሰናል። ይህ ሁኔታ የአሸባሪው ቡድን እንቅስቃሴ ከጅምሩ በእንጭጩ መቋጨት አለመቻሉ የስጋትነቱ ደረጃ እየጨመረ እንዲመጣ ይጠቁመናል።
በአሁን ወቅትም ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን አሸባሪው ቡድን የጥፋት በትሩንን በሕዝቡ ላይ እያሳረፈ ይገኛል። የኦሮሚያን ክልል የሚያስተዳድረው መንግስት ሆነ የፌደራል መንግስት በኩል አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት ብዙ ስራዎች መሰራታቸው ይታወቃል። እየተሰሩም ይገኛል።
እዚህ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ማስታወስ ይገባል። “አሸባሪው ቡድን ትጥቁን ፈትቶና በሀይል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አቁሞ ወደ ሰላም ከመጣ መንግስት ለሰላም እና ለፖለቲካ ንግግር በሩ ከፍት ነው።
“ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል ንጹሐንን እየገደለና እያፈናቀለ እንዲሁም የልማት ስራዎችን እያደናቀፈ ይገኛል። ከቡድኑ ጋር ያለው ችግር የሚፈታው ቡድኑ የኃይል እንቅስቃሴን አቁሞ ለፖለቲካዊ ንግግር ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው። ህግ የማስከበሩ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ነበር ያሉት።
ይህም በመንግስት በኩል ቁርጠኝነት እንዳለ አመላካች ነው። ነገር ግን የተሰሩት ስራዎች ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል? የሚለው ምላሽ ይፈልጋል። በእኔ ግምገማ ግን ውጤቱ አርኪ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ይህን ለማለት ያስደፈረኝ ደግሞ ከሰሞኑ በምስራቅ ወለጋ አንገር ጉቴ የተፈጠረው ክስተት ነው።
በዚሁ አካባቢ የአሸባሪው ቡድን አጸያፊ የጭፍጨፋ ገድል ዳግም በንጹሐን ላይ ሲነበብ፤ ዜጎች በብሔራቸው እየተመረጡ ተገድለዋል። በእርግጥ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን ወደ ምስራቅ ወለጋ አንገርጉቲ ከተማ አቅንቶ ችግሩን ለመቆጣጠር ችሏል። ግጭቶች ሳይከሰቱ ምላሽ መስጠት፣ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ምላሽ ከመስጠት በብዙ እጥፍ ይሻላል።
ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ምላሽ መስጠት ደግሞ ምላሽ ካለመስጠት እንደሚሻል አይካድም። ነገር ግን የማይካደው ሃቅ የ ሸኔ አላማ ቢስ እንቅስቃሴ አንድ ቦታ እንዲቆም አድርጎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ ውሎ ሲያድር ችግሩ ውስብስብ የመሆኑን አይቀሬ ነው።
በዚህ ረገድ ደግሞ የፌደራል መንግስት ሆነ የክልሉ መንግስት ትልቅ የቤት ስራ ይኖርባቸዋል። በተለይ ደግሞ ክልሉን የሚያስተዳድረው መንግስት የኦሮሞ ህዝብም ሆነ በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ አሸባሪው ሸኔ እያደረሰ የሚገኘውን መከራ፣ ግፍና ሞት ማስቆም ይኖርበታል።
ከሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ ክልሉን ‘የኦሮሞን ሕዝብ አንገት እየቀሉ የኦሮሞን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ ከሚለው የአውሬዎች ስብስብ ነጻ ሊያደርግ ይገባዋል። የሕዝቡን ሰቆቃ ማስቀረት የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ እንባውን ማበስ ያስፈልጋል።
ይህን ለማድረግ የክልሉ መንግስት ሙሉ አቅም ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። ራሱሙ በአደባባይ ማረጋገጫ ሰጥቷል። በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አመራሩን ፣ የጸጥታ መዋቅሩን በሚገባ መመርመርና መፈተሽ አለበት።
የጠላትን ዓላማ ለማሳካት የሚጣጣሩ ግለሰቦችን በጉያው ይዞ የሚደርግ ዘመቻ ውጤቱ ያው ክስረት ፣ ክሽፈት ይሆናል። ስለዚህ ለጠላት መረጃና ካራ እያቀበሉ ሕዝብን የሚያስለቅሱትን ከሃዲዎችን ከውስጡ መመንጠር ይኖርበታል።
ራሱን አጽድቶ ከሕዝብ ጋር ወደተቀናጀ እርምጃ መሻገር ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም። ነገር ግን አሁን ባለው አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ የአሸባሪው’ ሸኔ ነገር ‘እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም’ እንዳይሆን አገሩን እንደሚወድ አንድ ዜጋ እሰጋለሁ ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015