ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እያደረገች ያለችው ግስጋሴ በብዙ በርካታ መሰናክሎች እየተፈተነ ነው። ፈተናዎቹ የቱንም ያህል የበዙ ቢሆኑም፤ እንደ አገር ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ አምርራ የያዘችውን ትንሳኤዋን ለማብሰር ዛሬም አብዝታ እየተጋች ነው። በዚህም እያስመዘገበች ያለችው ስኬት ተስፋ ሰጭ ነው። በአሸናፊነት ጎልታ የምትወጣበትም ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም አመላካች ነው፡፡
አገሪቱን እንደ አገር ከሚፈታተኑዋት ክፉ ጠላቶቿ መካከል አንዱና ቀዳሚው ድህነት እንደሆነ ይታወቃል። ድህነት የህዝቦቿ የረጅም ጊዜ ጠላት ከመሆን ባለፈ አንገት የሚያስደፋው ታሪኳ አካል ጭምር ነው። ይህ አንገት የሚያስደፋ ታሪክ በሥራ ለመለወጥም የተጀመረው ህዝባዊ መነሳሳት ከፍ ያለ ነው።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለልማት ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት በሁሉም ዘርፍ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ወገቧን ታጥቃ የተነሳችው። ‹‹ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት›› በሚልም ያላትን አቅም እና ቁርጠኝነት አቀናጅታ መንቀሳቀስ ጀምራለች፡፡
ኢትዮጵያ ከሚለው ገናና ስሟ ፊት እየተሰነቀረ የሚያጠለሻትን ድህነት ለማሸነፍ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንገድ እየተንቀሳቀሰች ነው። ድህነት መገለጫዋ ሆኖ የጠየመ ገጽታዋን ለመመለስ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከውናለች። ከተከናወኑት አያሌ ተግባራት መካከልም በይቻላል ስሜት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያስመዘገበች ያለችው ታሪክ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
መንግሥት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እየለማ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴ በምግብ እራስን ከመቻል ያለፈ ትርጉም ያለው ነው። አንደኛው ድህነትን መሰናበቻ ሲሆን ለምዕራባውያኑ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚመለከቱበትን መነጽር ማስተካከል የሚችል ነው። /ዘንድሮ በሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል/።
እርግጥ ነው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ የተትረፈረፈ ምርት አምርቶ በምግብ እራስን መቻል ከድህነት ነጻ ያወጣ ይሆናል። ነገር ግን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ብቻ ድህነትን ድል መንሳት አይቻልም። ይልቁንም በተፈጥሮ ሃብት የታደለችው ኢትዮጵያ ከተትረፈረፈው ሃብቷ በእኩልነትና ፍትሃዊ በሆነ ክፍፍል ሁሉንም ዜጎቿን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ስትችል ነው ድህነትን በተጨባጭ ማሸነፍ የምትችለው፡፡
ለዚህም ነው በአሁን ወቅት በምግብ እራስን ለመቻል ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን በእኩልነትና ፍትሃዊ ባልሆነ ክፍፍል ዜጎች በአገራቸው ባይተዋር የሆኑበትን ብልሹ አሰራር/ሙስናን/ለማስወገድ በጋራ ርብርብ የተጀመረው፡፡
እንደ አገር ሙስና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ለአገር የህልውና አደጋ እየሆነ መጥቷል። አገሪቷ የቱንም ያህል በተፈጥሮ ሃብት የናጠጠች ብትሆንና ምርትና ምርታማነቷ ቢያድግ፤ ዜጎች ከተትረፈረፈው ሃብት በእኩልነትና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑ የማይቀር ነው።
ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በሌለበት ድህነትን በራሱ ማሸነፍ አይቻልም። ሙስናና ብልሹ አሰራርም በራሱ የአገራዊ/የዜጎች ድህነት ምንጭ ነው። በራሱም የድህነት ያህል አንገት የሚያስደፋና ገጽታን የሚያጠለሽ ማህበራዊ ነቀርሳ ነው።
ይህንን የአገርና የህዝብ ጠላት የሆነን ካንሰር ለመከላከል/ለመታገል ሁሉም ዜጋ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ድህነትን በሥራ ማሸነፍ እንደሚቻል ሁሉ ሙስናንም በተግሳጽ፣ በአስተምሮ እና በህግ አግባብ መከላከል ይቻላል።
አገራችን ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች በገባችበት ጦርነት በሙስና የቱን ያህል እንደተናጣት የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህም መላው ህዝባችን ለመክፈል የተገደደው ዋጋ የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
ሙስና አገሪቱን ከጦርነቱ ባልተናነሰ ሲፈታተናት ታይቷል። ለዚህም እልፍ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። ዛሬ በአንድም በሌላ ለፍቶ፣ ጥሮ፣ ግሮ፣ በላቡ ወዝ ከሚያድረው ይልቅ ሌብነት ከነውር ሳይቆጠር እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ መታየት ጀምሯል። ይህ ደግሞ ሰው ከመሆን ውሃ ልክ እየወረድን እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡
ዛሬ ለፍተው ጥረው ግረው አልሞላ ያላቸው እልፎች እንዳሉ ሁሉ ከምንም ተነስተው የሃብት ማማን የሚቆናጠጡትም የትየለሌ ናቸው። በዚህም ሙሰኛውን ከንጹህ መለየት እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በተለይም አሁን አሁን በየቦታው አይነቱን እየቀያየረ እንዲሁም አፈሩና መሬቱ እንደተመቸው ዘር እየተንሰራፋ የመጣው ሙስና ከመንግሥት አቅም በላይ እየሆነ ያለ ይመስላል።
ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስር እየሰደደ የመጣውና እየተንሰራፋ ያለው ይህ ሙስናም የአገሪቷ ካንሰር እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች ይገለጻል። መንግሥትም ጋብ ካለው ጦርነት ማግስት ሙሉ ትኩረቱን በሙስና ላይ ማድረጉም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
አገሪቷ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከገጠማት ጦርነት በተጨማሪ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈችም ቢሆን ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። ይሁን እንጂ ‹‹በአንድ እጅ አጨብጭቦ በአንድ በሬ ስቦ አይሆንም›› እንደሚባለው አይን ያወጣው ሌብነት የመንግሥትን እና የዜጎችን ልፋት ውሃ እየቸለሰበት ይገኛል።
ታድያ ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ግስጋሴ እንዳይገታና ጉዞዋን አጠናክራ መቀጠል እንድትችል ሌብነት ከመንገዷ ሊወገድ የግድ ነው። ምክንያቱም ሌብነት ባለበት ወደ ብልጽግና የሚደረግ ጉዞ አይሳካምና ነው።
ሌብነት /ሙስና እጅግ ጸያፍና ክብር የሚነካ ከመሆን ባለፈ አገርና ህዝብን የሚጎዳ ነው። ያም ሆኖ ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እዚህም እዚያም መልኩን እየቀያየረ የሚስተዋለው ሙስና አስፈሪነቱ አስፈርቷል። በተለይም ደሃ ከሆነች አገር ላይ ከድሆች የሚመዘበረው ሀብት አገርና ህዝብን ወደ ድህነት አረንቋ የሚወስድ በመሆኑ ከነገ ይልቅ ዛሬ በጥፍር ቢሆን ቆሞ ማሰብን ጠይቋል፡፡
በመሆኑም በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታወጀው የፀረ-ሙስና አብዮት ወደ ተግባራዊ እርምጃ መሸጋገር ጀምሯል። መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት መሰረት በማድረግ እንዲሁም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሙስናን እና ሙሰኞችን የማሳደድ ዘመቻ ወደ ተግባር መሸጋገሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። የተከፈተውን ዘመቻ ተከትሎም በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
መረጃዎቹ ታድያ የአንድ ሰሞን ዜና ሆነው መቅረት የለባቸውምና ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በብርቱ መታገል ከሁሉም ይጠበቃል። ‹‹የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም›› እንዲሉ አበው የተጀመረው የፀረ-ሙስና አብዮት ተፋፍሞ ሊቀጣጠል ይገባል። ከአገርና ከህዝብ ጉሮሮ የሚመነትፈውን መንታፊም በአደባባይ ሌባ ለማለት መድፈር ያስፈልጋል፡፡
እርግጥ ነው እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የእያንዳንዱን ዜጋ ተነሳሽነትና ርብርብ የሚጠይቅ ቢሆንም የሹማምንቱ ቁርጠኝነት ደግሞ የበለጠ ያስፈልጋል። በተለይም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሽጎ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› አይነት ጨዋታ የሚጫወተውን ወደፊት አምጥቶ ተጠያቂ ለማድረግ ከህዝቡ ይልቅ የአመራሩ ቁርጠኝነት ለነገ የሚተው አይደለም። የማያዳግምና አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድም ተገቢ ነው።
ዜጎች በአገራቸው ሠርተው ከመኖር ባለፈ ሁለንተናዊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ አበርክቷቸውም በዛው ልክ የጎላ እንደሆነ ይታወቃል። ታድያ ዜጎች በሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎም ይሁን በሌላ ብዙ የሚያተርፉ እንዳሉ ሁሉ፤ ሙስና በሚያመጣው ጫና በአገራቸው ባይተዋር የሚሆኑ ዜጎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህም ዜጋ ባገሩ ሰርቶ እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ አገሩን እንዲጠላ፣ ሁልጊዜ ተጠራጣሪ እንዲሆንና እንዲሰደደም ያደርገዋል፡፡
በአገሪቱ አሁን እየታየ ያለው እውነት ወጥቶ ወርዶ ከሚለፋው ይልቅ ባቋራጭ የሚከብረው የትየለሌ እየሆነ ነው። በተለይም በነጻነት ተንቀሳቅሶ፤ በታማኝነት ታምኖ፤ መሥራት ብርቅና ወረት እየሆነ በመጣበት በዚህ ጊዜ ሙስና እና ብልሹ አሠራር የሕልውና አደጋ መሆኑ በሚገባ እየተረጋገጠ መጥቷል። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፋ እና ሥር እየሰደደ የመጣው የሙስና ወንጀል እና ብልሹ አሠራርም ሕዝብ በመንግሥት አሠራሮች ላይ እምነት እንዲያጣ እና እንዲያማርር ምክንያት ከሆነም ሰነባብቷል።
በቀጣይም ዘረፋው በዚሁ ከቀጠለ የአገርና የህዝብን ንብረት ተደራጅተው የሚመዘብሩ ስግብግቦች አገሪቷን እራቁት እንዳያስቀሯትና ህዝቡን የበለጠ እንዳያማርሩት ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን የስጋት ምንጮችን ከስሩ ማድረቅ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል። ለዚህም የህልውና አደጋ ሆኖ ያፈጠጠብንን ሙስና በጽኑ ለማውገዝ በአገር ደረጃ የተጀመረውን የጸረ-ሙስና ትግል መታገል ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015