መኪና ላላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መኪና የሚያቆሙበትን ቦታ ማግኘት ትልቁ ጥያቄ ከሆነ ቆይቷል። የአዲስ አበባና ከተለያዩ ክልሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ባለተሸከርካሪዎች በከተማዋ የሚስታዋለውን አሰልቺውን የትራፊክ መጨናነቅ በትዕግስት አልፈው የሚፈልጉበት ቦታ ከደረሱ በኋላ መኪና ማቆሚያ ቦታ ለማግኘት ብዙ መባዘን ይጠበቅባቸዋል።
በመኪና ማቆሚያ ቦታ እጦት ምክንያት ባልተገባ ቦታ ለማቆም ይገደዳሉ፤ ይህ ደግሞ ለተሸከርካሪ እቃዎች እና በመኪና ውስጥ ላስቀመጧቸው እቃዎች ስርቆት እንዲሁም ለትራፊክ ቅጣት እያጋለጣቸው ይገኛል። ተሸከርካሪዎች የሚሰረቁበት ሁኔታም ይስተዋላል።
በከተማዋ እየተባባሰ በመጣው የመኪና ማቆሚያ ቦታ ችግር ምክንያት ከመኪና አሽከርካሪዎች ባልተናነሰ እግረኞችም ሲቸገሩ ይታያል። በመንገድ ዳር እና በእግረኞች መንገድ ላይ መኪናዎች እንዲቆሙ የሚደረግበት ሁኔታ የትራፊክ እንቅስቃሴን ከማስተጓጎሉ ባሻገር የእግረኞችን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል።
በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማዋን መኪና ማቆሚያ ችግር በመጠኑም ቢሆን ሊያቃልሉ የሚችሉ የመኪና ማቆሚያዎች እየተገነቡ ናቸው። በመገናኛና በመርካቶ አንዋር መስኪድ አካባቢ ቀደም ሲል የመኪና ማቆማያዎች ተገንብተዋል፤ ባለፈው አመት ደግሞ በመስቀል አደባባይ ግዙፍ የመኪና ማቆሚያ በመሬት ውስጥ ተገንብቷል። የመስቀል አደባባዩ የመኪና ማቆሚያ በአካባቢው ያለውን የመኪና ማቆሚያ ችግር በወሳኝ መልኩ ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው።
በቅርቡ ደግሞ የአንድነት ፓርክ መኪና ማቆሚያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተመርቆ እነዚህን የመኪና ፓርኮች ተቀላቅሏል። የመኪና ማቆሚያው የከተማዋን በተለይም በአንድነት ፓርክ አካባቢ ሲታይ የቆየውን የመኪና ማቆሚያ እጥረት ይፈታል።
የመኪና መቆሚያው በአንድ ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ግንባታው የመሬት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ የዋለበትም ነው። ከመሬት በታች አራት ወለሎችን /G-4/ እንዲይዝ ተደርጓል። በተጨማሪም ከመሬት ወደ ላይ ባለ አራት ወለል ህንጻም /G+4/ አለው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩትና እኛም ተዘዋውረን እንደተመለከትነው፤ ከወለል በታች ያሉት አራቱም ወለሎች ሙሉ በሙሉ ለመኪና ማቆሚያነት የሚያገለግሉ ናቸው። ወለሎቹ / ቤዝመንቶቹ/ አውቶብሶችን ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም አላቸው።
እጅግ ሰፊ የሆነው ይህ የአንድነት የመኪና ማቆሚያ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች የመኪና ማቆሚያዎች ያልተገጠሙ ቴክኖሎጂዎች ተደርገውበታል። የመኪና ማቆሚያ ደህንነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ከ200 በላይ የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመውለታል። ካሜራዎቹም ተሽከርካሪው የቆመበትን ጊዜ ይቆጥራሉ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኪና ማቆሚያን የሚያረጋግጥ የክትትል ቅኝት ሥራ ይሰራሉ፤ እንደ አስፈላጊነቱ የመኪና መለያ /ሰሌዳ/ እንዲሁም የተገልጋዩን ማንነት መለየትም ያስችላሉ።
በዚህ የመኪና ማቆሚያ ለሰዎች ብቻ አይደለም አሳንሰር/ ሊፍት/ የተገጠመው። ለመኪናዎችም ነው። ይህ አሳንሰር መኪኖችን ከወለል በታች ካሉ የማቆሚያ ቦታዎች ጋር በቀላሉ ለመተሳሰር ከመርዳቱም በተጨማሪ የዝቅታ ፍርሀት ያለባቸውንም ሰዎች ታሳቢ ተደርጎ የተገጠመ ነው።
በተጨማሪም ዘመናዊ የተሸከርካሪዎች መረጃ መመዝገቢያና፣ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት መፈጸሚያ፣ የደህነነት መጠበቂያ ሥርዓቶችን ያሟላም ነው። ለአብነትም ተሽከርካሪ የሚቆምበትን ቦታ መያዝ እና አለመያዝ የሚያሳዩ በርካታ ስክሪኖች አሉት፤ ይህም በጣም ዘመናዊ ያደርገዋል።
ከመኪና ማቆሚያ ውጪ ባሉ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ አራት ወለሎችም አሉት። ወለሎቹ ለቢሮ አገልግሎት፣ ለመስሪያ ቤት፣ ለተገልጋዮች መሰብሰቢያ፣ የጥበብ ትርኢቶች እና ሌሎች ዝግጅቶች ማካሄጃ የሚውሉ ስፍራዎች አሉት። የተለያዩ መዝናኛዎች እና አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባንኮች፣ ካፌዎች፣ ወዘተ፣ ገብተው እየሰሩ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የተገነበ ነው።
ህንጻው የተሰራበትና አበቦችና ሌሎች አትክልቶች የለሙበት መንገድ ግቢውንና አካባቢው ይበልጥ ውብ አርገውታል። አካባቢውን / በተለይም አንድነት ፓርክን፣ የሳይንስ ሙዚየምንና የመሳሰሉትን የአካባቢውን ገጽታዎች በቅርብ ርቀት ለመቃኘት የሚያስችል መሆኑ በራሱ የሌላ ውበት ባለቤት አርጎታል።
የመኪና ማቆሚያውን ከአንድነት ፓርክ ጋር የሚያገናኝ ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገድም/ ዋሻ/ ተገንብቶለታል፤ የአንድነት ፓርክን መጎብኘት የሚፈልጉ መኪና የያዙ ጎብኚዎች መኪናዎቻቸውን አስተማማኝ በሆነው የአንድነት መኪና ማቆሚያ ውስጥ በማቆም በዋሻው ውስጥ አልፈው ፓርኩን መጎብኘት ይችላሉ። ሌሎች የአንድነት ፓርክ ጎብኚዎችም በእዚህ ህንጻ በኩል አርገው በዋሻው ውስጥ አልፈው ነው ፓርኩን የሚጎበኙት።
ከአካባቢው በቅርብ ርቀት ለሚገኙት ሳይንስ ሙዚየም፣ አብርሆት ቤተ መጽሃፍት እና የወዳጅነት አደባባይ በእግር ጉዞ ርቀት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ዝና ብለው በእግር መጓዝ የሚፈልጉ ሁሉ መኪናቸውን በአንድነት ፓርክ ለመቆም የሚያስችል ሌላ ተመራጭ ስፍራ ነው።
የመኪና ማቆሚያው ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በነጻ የፓርኪንግ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፤ በርካታ ተገልጋዮችም በነጻ የፓርኪንግ አገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
የመኪና ማቆሚያውን ወለሎች አንድ በአንድ በእግር እየወረድን ጎብኝነው። በእያንዳንዱ ወለል በርከታ መኪኖችን ማቆም የሚያስችሉ ውብ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል። በየወለሉ የተለያዩ ስፍራዎች ለአሽከርካሪዎች መረጃ የሚያስተላልፉ ልዩ ልዩ ምልክቶች ተደርገዋል፤ መግቢያ መውጫውን የሚያመላክቱ፣ ሊፍቱን ደረጃውን የሚጠቁሙ መረጃዎች በየአቅጣጫው በግልጽ ተመልክተዋል። አንዳንዶቹ ወለሎች መኪና ቆሞባቸዋል፤ አንዳንዶቹ መኪኖችን ይጠብቃሉ።
ወይዘሮ ጊፍቲ ሳሙኤል የስራ ቦታቸው ከአንድነት መኪና ማቆሚያ ጀርባ በሚገኘው ፓላስ ህንጻ ላይ ነው፤ ባለሱቅ ናቸው። ቀድሞ በአካባቢው መኪና ማቆሚያ እንዳልነበረ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት እሳቸውም ሆኑ ደንበኞቻቸው መኪና ለማቆም እጅግ ይቸገሩ ነበር።
ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኙ መንገዶች ቀኝና ግራ መኪና ለማቆም አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይም ጠዋት ከ4 ሰዓት በፊት በአካባቢው መኪና ማቆም አይቻልም፤ ማታ ከ11 ሰዓት በኋላ መቆም አይቻልም። በዚህም ምክንያት ለደንበኞቻቸው አገልግሎት ለመስጠት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ቆይተዋል። ደንበኞች በሚፈልጉበት ሰዓት መኪና ማቆሚያ በማጣታቸው እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
የአንድነት መኪና ማቆሚያ ግንባታ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ግንባታው ተጠናቆ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በጉጉት ሲጠባበቁ እንደነበሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ጊፍቲ፣ የፓርኩን ግንባታ እያንዳንዱን ሂደት በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ፕሮጀክቱ መቼ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለው በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ማየታቸው እጅግ አስደስቷቸዋል። ፕሮጀክቱን በቅርብ ጊዜ ከተገነቡ የተሳኩ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሉ ገልጸውታል።
ፓርኩ ገና ስራ መጀመሩ ቢሆንም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ለሁለት ቀናት መጠቀማቸውን የሚጠቅሱት ጊፍቲ፤ ይህን ቃለ ምልልስ በሰጡን ቀን ለሶስተኛ ቀን ወደ ፓርኩ መምጣታቸው ነው። መኪና ማቆሚያው ለስራ ቦታቸው ቅርብ ከመሆኑ ባሻገር ለመኪናቸውም ደህንነት እጅግ ምቹ ሆኖ አግኝተውታል። በፓርኩ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማየት እና በቀጣይ የአገልግሎቱ ቋሚ ተጠቃሚ ልሁን ወይስ አልሁን የሚለውን ለመወሰን ወደ ፓርኩ በተደጋጋሚ መመላለሳቸውን ተናግረው፣ የመኪና ማቆሚያው ቋሚ ደንበኛ ለመሆን መወሰናቸውን ተናግረዋል።
የክፊያ ተመን ሲወጣ ተጠቃሚውን ለማብዛት ክፊያው ተመጣጣኝ ቢሆን መልካም ነው ያሉት ጊፍቲ፣ የሰውን ገቢ ያማከለ ቢሆን ተገልጋዮችንም ሆነ ፓርኩን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የፓርኪንግ ችግር ያለባት ከተማ መሆኗን የጠቆሙት ጊፍቲ ፤ በተለይም ካዛንቺስ አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ የሚበዛበት እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የመኪና ማቆሚያ ችግር እንዳለ ይገልጻሉ። እሳቸው አንድነት መኪና ማቆሚያ ይህን የአካባቢውን የመኪና ማቆሚያ ችግር የሚቀርፍ እንደሚሆን እምነቱ አላቸው።
በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስታዋለውን የፓርኪንግ ችግር ለመፍታት ተመሳሳይ መኪና ማቆሚያዎች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የመሰል መኪና ማቆሚያዎች መበራከት ለተገልጋዮች ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ለከተማዋ ውበት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
በፓርኪንጉ ውስጥ የባንክ፣ የቴሌ፣ የካፌ እንዲሁም የአየር መንገድ የቲኬት አገልግሎቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች መኖራቸው ለአካባቢው፣ መኪናውን ለሚያቆሙት እንዲሁም ለፓርኩ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል። በተለይም አብዛኞቹ በፓርኩ ውስጥ የተከፈቱ አገልግሎች በአካባቢው የሌሉ መሆናቸው ለአካባቢው ማህበረሰብ ያላቸው ፋይዳ የላቀ መሆኑንም ይገልጻሉ።
ፓርኩ ከአሁኑ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል። በርካታ ወጣቶች አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ወደ ስራው መግባታቸው በስፍራው ከሚሰሩ ወጣቶች መረዳት ችለናል። ደሳለኝ አጥናፉ በፓርኩ ውስጥ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች አንዱ ነው። ደሳለኝ ወታደር ነበረ፤ በውጊያ ወቅት ቆስሎ ህክምናውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ አስፈላጊውን ስልጠና ወስዶ በመኪና ማቆሚያው ውስጥ የስነ ስርዓት አስከባሪ ሆኖ እየሰራ ነው። እንደሱ በተመሳሳይ ወደ 48 የሚደርሱ ሰዎች ስራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ተናግሯል።
ማቆያ በለጠም እንዲሁ ሌላ የስራ እድል የተፈጠረለት ወጣት ነው፤ ማቆያ ስራ አጥ ነበረ፤ ፓርኩ የስራ ማስታወቂያ ሲያወጣ ተወዳድሮ መቀጠሩን ይገልጻል። በመኪና ማቆሚያው ውስጥ ካሸር ሆኖ ማገልገል ጀምሯል። በደረጃ 4 ተወዳድረው 15 ልጆች በካሸርነት ተቀጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ሌሎችም በተለያዩ ስራዎች ተቀጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ በተመረቀበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ተሰናስለው አዲስ አበባን አዲስ ገጽታ በማላበስ የብልጽግናን አይቀሬነት የሚመሰክሩ ናቸው ብለዋል። የአንድነት መኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር በመሆን አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ከሚያደርጓት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል።
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ የፕሮጀክቶቹ ትርጉም ብዙ ነው። ለሌሎች ፕሮጀክቶች ትልቅ ትምህርት የሚሰጡም ናቸው፤ ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ አዳዲስ ልምዶች ተገኝቷል፣ ግንባታቸውን በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት በማጠናቀቅ የሌብነትን በር መዝጋት ተችሏል ብለዋል።
በተለይም የፕሮጀክት ጊዜ በመራዘም ምክንያት የሚጨምሩ በስፔስፊኬሽን ውስጥ ያልገቡትን በማስገባት ዋጋን በማዛባት የሚበላው የህዝብ ገንዘብ እንዳይበላ በማድረግ ብዙ ልምድ እንደተገኘበትም አብራርተዋል። እስካሁን የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ለሌሎች ፕሮጀክቶችም እንደ ምሳሌ በመውሰድ የሚታቀድበት እና የሚተገበርበት ሁኔታ አንዲፈጠር ማስቻላቸውን ነው ያብራሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መኪና ማቆሚያውን መርቀው ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ፣ ለአዲስ አበባ፣ ለኢትዮጵያ ልጆች፣ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚመጥን ነው። የነገይቱን ኢትዮጵያ ምስል የሚያሳይ ነው።
መጀመሪያ ቢሯችንን ቀጥሎ ግቢያችንን፣ ከዚያም አካባቢያችንን እንዲሁም ሀገራችንን በሚለው መርህ በቤተመንግስት አካባቢ ትናንት፣ ዛሬን እና ነገን የሚያገናኙ በርካታ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል ብለዋል።
ዛሬ ድልድይ ሆኖ ትናንትናን ከነገ የማያገናኝ ከሆነ የሀገር እና የተቋም ግንባታ በተሟላ መልኩ እንደማይከናወን ጠቅሰው፣ ትናንትናን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ የሚያገናኙ ፕሮጀክቶች ስንሰራ ከብልጽግና መንገድና ዐሻራ፣ ከብልጽግና ጉዞ ጋር የሚቃኝ ዕሳቤ ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። ማንኛቸውም ስራዎች ለኢትዮጵያ የሚገባትን ብልጽግና የሚያመጡ መሆናቸውን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ከለውጡ በኋላ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ትናንትናን እና ነገን የሚያገናኙ ናቸው ብለዋል። ፕሮጀክቶች ለትውልዱ ለአዕምሯዊና አካላዊ ጤንነት ከፍ ያለ ጥቅም ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፕሮጀክቶች ቃል በተገባላቸው መሰረት እየተፈጸሙ መሆኑንም ጠቁመዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015