ወጣት አቤል ኃይለ ጊዮርጊስ ባሙቡ ላፕስ የተሰኘ በማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ላይ የተሠማራ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ነው ። ውልደቱና ዕድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ነው ። ከአዳማ ዩኒቨርስቲ በውድ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል ። የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በኮንስትራክሽን ምሕንድስናና ኧርባን ፕላኒንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል ።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ ሲጀምር የተለያዩ ችግሮችን ይመለከት ነበር ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞች ብዛት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውና በዚህ ቁጥር ልክ አካል ጉዳተኞችን ሊያግዙ የሚችሉ ተሽከርካሪ ወንበሮችና ሌሎች መሣሪያዎች አለመኖር ነበር ። ይህንን ችግር ለምንድን ነው መፍታት የማልችለው? በሚል ተነሳሽነት ጥናቶችን ማካሄድ ጀመረ ።
ይህን ጥናት በሚያካሂድበት ግዜ ቀርክሃ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ውስጥ አንዱ መሆኑንና ነገር ግን እስካሁን ድረስ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳልሆነ በሌላ ጥናት አረጋገጠ ። እንደውም ጥናቱ 70 ከመቶ የሚሆነው የአፍሪካ የቀርክሃ ሀብት በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ጥናቱ አመላከተው ። ሆኖም ሀገሪቷ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ተረዳ ።
ከዚህ ክፍተት በመነሳት ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታትና ያለውን እውቀት ለመጠቀም ሀገር በቀል እውቀትን ለሀገር በቀል መፍትሔ በሚል በራሱ ተነሳሽነት ከቀርክሃ የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበር መሥራት ጀመረ ።
የመጀመሪያውን የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበር ዲዛይን ሲሠራ በሥራው ላይ የተለያዩ ክፍቶች ነበሩ ። እነዚህን ክፍተቶች በማየት በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና አፍሪካ በሚገኙ ሀገራት ሄዶ አጫጭር ስልጠናዎችንና የልምድ ልውውጦችን አድርጓል ። ይህንኑ እውቀት ወደሀገር ውስጥ ይዞ በመምጣት እርሱ ካለው እውቀት ጋር በማጣጣም ወደሥራ ለመግባት ሞክሯል ።
ወጣት አቤል ከአራት ዓመት በፊት አራት ኪሎ አካባቢ አንድ በመንገድ ላይ እየተንፏቀቀ የሚሄድ ልጅ ተመልክቶ ራሱን በልጁ ቦታ ሆኖ ሳለ ። ብዙ ሕልምና ሀሳብ ያለው ወጣት ተሽከርካሪ ወንበር በማጣት ምክንያት የሚፈልግበት ቦታ ሳይደርስ ሕልሙ ሲጨናገፍበት ታየው ። ከዚህ አንፃር ቀርክሃን በመጠቀም ለአካል ጉዳተኞች አመቺ የሆነ ተሽከርካሪ ወንበር መሥራት እንዳለበት ተሰማው ።
የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበር ከቀርክሃ ለመሥራት ሃሳብ የነበረው ቢሆንም ሥራውን የጀመረው ግን አነስተኛ የቀርክሃ ውጤቶችን በመሥራት ነበር ። ሆኖም የፈጠራ ሥራ የሚያወዳድሩ ድርጅቶች ጋር በመሄድ በዚሁ የቀርክሃ ሥራ ተወዳድሮ በማሸነፉ ድርጅቱን ለማቋቋም የሚያስችል ገንዘብ አገኘ ። ይህንኑ ገንዘብ በመጠቀም ‹‹ባሙቡ ላፕስ›› የተሰኘ በማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ላይ የተሠማራ ድርጅት አቋቁሞ ወደሥራ ገባ ። በሂደት በሚሠራቸውና በሚሸጣቸው የቀርክሃ ውጤቶች የድርጅቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ ቻለ፡፡
ወጣት አቤል በአሁኑ ወቅት የሚያመርታቸው የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበሮች ከቀርክሃ የሚሠሩ እንደመሆናቸውና ሃሳቡም አዲስ በመሆኑ ከመደበኛው ተሽከርካሪ ወንበር ለየት ያደርጋቸዋል ። ቀርክሃ ደግሞ ከብረት የተሻለ ጥንካሬ ያለው በመሆኑ ምርቶቹ ረጅም ግዜ ሊያገለግሉ የሚችሉ ናቸው ። በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ምርት ነው ። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከቀርክሃ እንደዚህ አይነት ምርት አልሠሩም ። ለዚህም ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ አግኝቷል ።
ከዚህ ባሻገር አንድ አካል ጉዳተኛ ገንዘብ ቢኖረው እንኳን ተሽከርካሪ ወንበሮችን በቀላሉ ለማግኘት አይችልም ። ከዚህ አንፃር ምርቱ በተለይ የተደራሽነት ችግርን ፈቷል ። ከዋጋ አንፃርም ከውጪ ሀገር ከሚገባው ምርት ከግማሽ በታች ይቀንሳል ።
‹‹የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበሮችን ከቀርክሃ ማዘጋጀት ስጀምር በርካታ ችግሮች ገጥመውኛል›› የሚለው ወጣት አቤል፤ ከነዛ ውስጥ አንዱ ሰዎች ለቀርክሃ ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከትና ግንዛቤ እንደነበር ይገልፃል ። ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት በቀርክሃ የተሠሩ ተሽከርካሪ ወንበሮችን አለማየቱና ሥራው አዲስ መሆኑ ለምርቱ ያላቸው አመለካከት ዝቅ እንዲል ማደረጉንም ይጠቁማል ። ነገር ግን በሂደት በርካታ አካል ጉዳተኞች ምርቱን መጠቀም ሲጀምሩ አመለካከታቸው በጥቂቱም ቢሆን እየተሻሻለ እንደመጣ ይናገራል ። በምርቱ ላይ የሚሰጡት አስተያየትም እያበረታው እንደመጣ ይጠቅሳል ።
ድርጅቱ በአሁኑ ግዜ ከሕፃናት እስከ አዛውንቶች ድረስ የተለያዩ መጠንና ዋጋ ያላቸው የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበሮችን ያመርታል ። ይህም ከዚህ በፊት የአካል ጉዳተኞች ባለባቸው የአካል ጉዳት ልክ ተሽከርካሪ ወንበሮችን የማግኘት ችግር በከፍተኛ ደረጃ ቀርፏል ።
ተሽከርካሪ ወንበሮቹ በአብዛኛው በእጅ የሚሠሩ እንደመሆናቸው ማሽን እንደሚሠራቸው የአካል ጉዳተኛ ወንበሮች የተዋጣላቸው ሊሆኑ አይችሉም ። በሂደት ግን ድርጅቱ የሚፈለገውን ጥራትና ትክክለኛነት ያሟሉ ተሽከርካሪ ወንበሮችን ለማምረት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ።
ድርጅቱ በዋናነት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚሠራ ሲሆን በተለይ አካል ጉዳተኞች ላይ አተኩረው ለሚሠሩት በትእዛዝ ምርቶቹን ሠርቶ ያስረክባል ።
ከቀርክሃ የሚዘጋጁ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ወንበሮችን ለማምረትም ድርጅቱ በቅድሚያ ጥሬ እቃውን /ቀርክሃውን/ በሚፈልገው ስፋትና መጠን ከቆላና ደጋው የሀገሪቱ አካባቢ ገዝቶ ያመጣል ። ቀርክሃ በባህሪው የጣፋጭነት ባህሪ ያለው በመሆኑና ለነብሳት ተጋላጭ በመሆኑ በትክክል ለመቆረጥ የደረሰ ቀርክሃን ነው ገዝቶ የሚቀበለው ። ቀርክሃውን ገዝቶ ካመጣም በኋላ ኬሚካል በመጠቀም የቀርክሃውን ደህንነት ይጠብቃል ። ከዚህ በኋላ ነው ቀርክሃውን በማድረቅ ወደ ምርት የሚገባው ። ይህንኑ ለመተግበር የሚችሉ ድርጅቱ ያሰለጠናቸው ሠራተኞች አሉት ።
ሥራው ተፈጥሮ ተኮር እንደመሆኑ ተቀባይነቱ አጠያያቂ እንዳልሆነ የሚናገረው ወጣት አቤል፤ ከእርሱ ባለፈ ሌሎች ወጣቶችንም የሚያነሳሳ እንደሆነ ይገልፃል። ነገር ግን ሥራውን አጠናክሮ ለመሥራት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል ። በተለይ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪዎቹ ጎማዎች በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ባለመሆናቸውና ከውጪ ለማስመጣት ደግሞ የውጪ ምንዛሪ ቀረጥ የሚጠይቁ እንደመሆናቸው ሥራው እንደማኅበራዊ ኃላፊነት ታይቶ ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግለት እንደሚገባ ያሳስባል ።
ነገር ግን ደግሞ በኅብረተሰቡና በተጠቃሚው በኩል ያለው ግብረ መልስ ቀላል ባለመሆኑ ሌሎች የቀርክሃ ውጤቶችን ለመሥራት ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ይጠቁማል ። ይህንንም ተከትሎ ድርጅቱ ከአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ወንበሮች በተጨማሪ በቀርክሃ ብስክሌት እየሠራ እንደሚገኝም ይጠቅሳል። ድርጅቱ የሠራቸው ብስክሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለውድድር በአንዳንድ ሀገራት ላይ ጥቅም ላይ እንደዋሉም ይናገራል።
ድርጅቱ ብስክሌትን የሚያመርትበት ምክንያት መንግሥት ከያዛቸው የአስር አመት እቅዶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመደገፍ መሆኑን ወጣት አቤል ይገልፃል ። ብስክሌትን ማምረትና ሰዎች ብስክሌት እንዲጠቀሙ ማበረታታት ደግሞ የድርጅቱ ኃላፊነት መሆኑን ይጠቁማል ። ብስክሌትን ከቀርክሃ ማምረት እንደሚቻል ማሳየትም የድርጅቱ ዓላማ መሆኑንም ይጠቅሳል ።
በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ ብስክሌቱን የማስተዋወቅ ዕድል እንደነበረውም ተናግሮ፤ የሰው ፍላጎት ከእርሱ ዝግጅት በላይ መሆኑን ይገልፃል ። እንደውም በአሁኑ ግዜ ድርጅቱ ማምረት ከሚችለው አቅም በላይ ትዕዛዞች እንደሚመጡም ነው የሚናገረው ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል። ከሀገር ውስጥ ፍላጎት በዘለለ የብስክሌቶቹን ፍሬሞች ወደውጪ ሀገር ለመላክ ድርጅቱ ውል ማሰሩንም ይናገራል ።
የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበሩ ብዙም ትርፍ የማይገኝበት በመሆኑና አካል ጉዳተኛ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ ስለሚመረት ብስክሌቱ ለንግድ ዘርፍ ይበልጥ የሚውል መሆኑንም ነው የሚጠቁመው ። ከብስክሌት ማምረት ሥራው የሚገኘው ትርፍ ለተሽከርካሪ ወንበሩ ምርት ዘላቂነት ጠቃሚ ሆኖ እንደሚያገለግልም ነው የሚናገረው ።
ሌሎች የፈጠራ ሀሳቦችንም በቀርክሃ ሥራ ላይ ካሰለጠናቸው ወጣቶች ጋር በመሆን እየሠራ እንደሚገኝም ያስረዳል ። ጥሬ እቃውን /ቀርክሃውን/ ከሚያቀርቡት ገበሬዎች ጀምሮ እስከሽያጩ ድረስ በቋሚነትና ጊዜያዊነት ለሚሠሩ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ይጠቁማል ። በዚህ ቀርክሃ ሥራ እስካሁን ድረስ እስከ 50 የሚሆኑ ሰዎች እንደሚሳተፉም ይገልፃል። ድርጅቱ በሚያመርትበት ቦታ ላይ ደግሞ አምስት ሰዎች በቋሚነት እንደሚያገለግሉ ይናገራል ።
በቀርክሃ ልዩ ልዩ የፈርኒቸር ውጤቶችን የሚያመርቱ በርካቶች በመሆናቸው በዚኛው ዘርፍ ላይ ድርጅቱ የመግባት ፍላጎት እንደሌለውና ከዚህ ይልቅ ለየት ባሉ የቀርክሃ የፈጠራ ውጤቶች ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚፈልግም ነው ወጣት አቤል የሚያስረዳው ። ሥራው ንግድ ብቻ ባለመሆኑና የልብ ግንኙነትም ያለው በመሆኑ አዳዲስ ነገሮችን ባልታየ አንግል የመሥራት ፍላጎት እንዳለውም ይገልፃል ። ከዚህ አንፃር በነባር የቀርክሃ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደማይፈልግ ይናገራል።
ድርጅቱ በአሁኑ ግዜ በአነስተኛ ቦታ ላይ ከቀርክሃ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ወንበሮችንና ብስክሌቶችን እያመረተ ይገኛል ። ያሉት ሠራተኞችም ጥቂት ናቸው። በቅርቡ ለሥራው የሚያገለግሉ ማሽኖች ከአንድ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት በድጋፍ ተገኝተዋል። ከዚህ አንፃር የድርጅቱ ቀጣይ እቅድ ማሽኖቹን ተክሎ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት ነው ። ሥራዎችንም ከእጅ ንክኪ የፀዳ ማድረግ ነው ። በርካታ ሰዎችን በመቅጠር ብዙ ምርቶችን በማምረት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ድርጅቱ ውጥን ይዟል ።
የድርጅቱን ቀጣይ ውጥን እውን ለማድረግና ቋሚ የሆነ ብሎም ለሀገር የሚጠቅም ሀብት ለመፍጠር የመሥሪያ ቦታ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህን የመሥሪያ ቦታ ቢመቻች መልካም ነው ይላል ወጣት ቢኒያም ። ምርቱን ለማምረት የሚያስፈልጉ አንዳንድ ጥሬ እቃዎች ሲገቡም ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መደረግ እንዳለበትም ያመለክታል ። ለዚህም የመንግሥት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል።
‹‹እንደሀገር በርካታ ችግሮች እንደመኖራቸው መጠን በርካታ ዕድሎችም እንዳሉ መረዳት ያስፈልጋል›› የሚለው ወጣት አቤል፤ እኔ የአካል ጉዳተኞችን ችግር ብቻ ነው ነቅሼ ያወጣሁት፤ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ሌሎች ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ቢችሉ ብዙ ነገሮችን ማቅለል እንደሚችሉ ይገልፃል ።
በዚህም ራሳቸውን መጥቀምና ከራሳቸው አልፈው አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚችሉ ይጠቅሳል። ለዚህም ዛሬ ነገ ሳይሉ ከአካባቢያቸው ችግር በመነሳት ችግር ፈቺ የሥራ ፈጠራዎች ላይ አተኩረው መሥራት እንዳለባቸው ይመክራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም