የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መሰረተ ልማት አውታሮች፣ ፋብሪካዎች እና መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎላ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል። ኢንዱስትሪው ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛውን የሰው ሀይል የያዘና ለሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ዋነኛው አንቀሳቃሽ ነው። በከተሞች የሰው ሀይል በመቅጠር ረገድ ከሆቴል እና ሬስቶራንት ቀጥሎ ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ዘርፍ ስለመሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።
ከፌዴራል መንግሥት ካፒታል በጀት ውስጥ ከ55 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንደሚውል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዘርፉ ከእያንዳንዱ ዜጋ የዕለተ ተዕለት ሕይወት ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የተቆራኘ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱ መረጃዎች አመላካች ናቸው።
ይህ ዘርፍ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ስር የሰደዱ ህመሞች አጋጥመውታል። በግንባታ ግብዓቶች እጥረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከባድ ችግር ውስጥ ወድቋል። በግንባታ ግብዓቶች ላይ የተፈጠረው ችግር ዘርፉን ከመጉዳት ባሻገር በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ ጫና አሳድሯል። ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በኮንስትራክሽን ግብዓት እጥረት ምክንያት በርካታ ፕሮጀክቶች እየተጓተቱ ይገኛሉ፤ የተቋረጡም አሉ።
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ካሉት የግብዓት ችግሮች መካከል አንዱ የብረት እጥረት ነው። ለኮንስትራክሽን ሥራ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት መካከል ብረት አንዱ ነው። የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ 13 የብረት ፋብሪካዎች ነበሩ። ሆኖም በነዚህ ፋብሪካዎች የሚመረተው የብረት ምርት የዘርፉን ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም።
በቅርቡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የመሰረታዊ ብረታ ብረት ጉዳይ ነው። በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዙሪያ የተካሄደ የጥናት ውጤት ያቀረቡት አቶ ዘሪሁን ዘገየ እንደሚሉት፤ መሰረታዊ ብረታ ብረት ፌሮ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ የስቲል ቱቦላሪ እና የመሳሰሉትን ያካትታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 13ቱ ፋብሪካዎች እያመረቱ ያሉት በዓመት ከሚጠበቅባቸው የብረት ምርት ውስጥ ስምንት በመቶውን ብቻ እንደሆነ ያብራራሉ። ይህም ከፍተኛ የብረት ምርት እጥረት መኖሩን ያመለክታል። አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ መሰረት የአርማታ ብረት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም፣ የብረት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት በጣም አነስተኛ ነው። ከምርት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የብረት ዋጋ መናር ይስተዋላል። የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ በመምጣቱም በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።
በአገር ውስጥ የሚመረተው ብረት ከፍላጎት ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ብረት ከውጭ አገራት ይገባል። በዚህ ምክንያት አገሪቱ ካላት የውጭ ምንዛሬ ውስጥ ቀላል የማይባለው መጠን ለብረት ግዥ እንደሚወጣ ይናገራሉ። በዓመት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለብረት ግዥ እየወጣ እንደሚገኝም ጠቁመው፣ ስለዚህ ብረት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን ቢቻል ብዙ ተቋርጠው ያሉ ፕሮጀክቶችን የማስጨረስ አቅም መፍጠር ይቻላል። በዚህ ረገድ ሰፊ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅ ችግሮቹ ያመላክታሉ ሲሉ ያብራራሉ።
አቶ ዘሪሁን እንደሚያብራሩት፤ የብረት እጥረት እንዲከሰት የተለያዩ ተግዳሮቶች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል የብረት ፋብሪካዎች የሚጠቀሟቸው ጥሬ እቃዎች ከውጭ አገራት የሚያስገቡ በመሆኑ ነው። የብረት ፋብሪካዎቹ ብረትን ለማምረት 85 በመቶው የሚሆነውን ግብዓት ከውጭ አገራት ያስገባሉ። ከውጭ የሚገባው ጠገራ ብረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ይጠይቃል፤ በመሆኑም ፋብሪካዎች ብረት በሚፈልጉት መጠን ለማግኘት ይቸገራሉ። ችግሩ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት ሆኗል።
በአገር ውስጥ ቁርጥራጭ ብረቶችን አቅልጦ ብረት የመስራት ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም ቁርጥራጮቹ የሚሰበሰቡበት መንገድ ችግር ያለበት ነው። በብልሹ አሰራሮች የተሞላ ነው። ቁርጥራጩ በአግባቡ ለአምራቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ አይደለም። በአቅራቢዎች እና በአምራቾች መካከል ጤናማ ያልሆነ የገበያ ትስስር አለመኖር ችግሩን አባብሶታል ሲሉ አቶ ዘርይሁን ያብራራሉ።
አቶ ዘሪሁን በብረት ፋብሪካዎች ላይ የሚደርሰው የኃይል አቅርቦት መቆራረጥም ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል፤ የኃይል መቆራረጡ የፋብሪካዎቹን የማምረት አቅም ከመፈታተኑም ባሻገር በብዙ የውጭ ምንዛሬ የተገዙ ማሽነሪዎችን ለብልሽት እየዳረገ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት። ዘርፉን ከተግዳሮቶች ለማላቀቅ የፋብሪካዎቹን የኃይል እጥረት ችግር መቅረፍ ወሳኝ ነው ይላሉ።
ጥናት አቅራቢው እንደሚሉት፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ያለመኖር፣ የፋይናንስ ስርዓት ወጥነት የጎደለው መሆንና የተጠናከረ የቁጥጥር ስርዓት አለመኖሩ እንደ ዋና ችግር ይጠቀሳል።
ችግሩን ለመቅረፍ የአጭር የረጅም እና የመካከለኛ ጊዜ እቅዶችን ነድፎ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ዘርይሁን ይጠቁማሉ። ችግሩን በአጭር ጊዜ ለማቃለል የግንባታ ፕሮጀክትን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ለአንድ ህንጻ ወይም ግንባታ ፕሮጀክት የሚያስፈልግ የብረት መጠን በማዕቀፍ ግዥ ለፕሮጀክቱ ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል ይላሉ።
በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ያገናዘበ መሰረታዊ የብረታ ብረት ስትራቴጂክ ምርቶች የውጭ ምንዛሬ እንዲመደብ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ፣ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የተለያዩ ዘመናዊ ስልቶችን መዘርጋት፣ በአገር ውስጥ ያለው የማዕድን ክምችት መሰረት በማድረግ የጥሬ ብረት ማዕድን ልማት ሥራን ወደ ትግበራ ለማስገባት ከክልል መስተዳደር፣ ከፋይናንስ እና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ዘሪሁን ያስገነዝባሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ብረትን ጨምሮ ሌሎች የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከውጭ አገራት የሚገባውን በአገር ውስጥ መተካት፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ፣ ግብይቱ በአገር ውስጥ የግንባታ የገበያ ትስስር ውስጥ እንዲካተት ማድረግ ዘርፉን ካለበት ችግር ለማላቀቅ ተጨማሪ መፍትሄዎች ናቸው።
ባለፈው ዓመት የአማካሪዎች የሥራ መመሪያን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማጸደቁን ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ በዚህ ውስጥ ከተቀመጡት መካከል በስፔስፊኬሽን ውስጥ የአገር ውስጥ ምርቶች መጠቀስ አለባቸው የሚል ተካቶበታል። የአገር ውስጥ ምርቶች ካልተጠቀሱ ስፔስፊኬሽኑ ውድቅ መሆን አለበት። ይህ የአገር ውስጥ የብረት ምርትን ለማበረታታት ከተያዙ አቅጣጫዎች አንዱ ነው።
ምርቶቹ በአገር ውስጥ የማይመረቱ እና ሊገኙ የማይችሉ ከሆኑ ብቻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እውቅና ሲሰጠው ብቻ ከውጭ በመጠን ምርት መስራት ይቻላል የሚል መመሪያ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በእነዚህ ህጎች ዙሪያ ለኮንትራክተር እና ኮንሰልታንት ሰፊ ግንዛቤ ተሰጥቶ ወደ ውጭ የሚወጣውን የዶላር ፍሰት መቀነስ ይቻላል፣ የአገር ውስጥ ምርትም ማበረታታት ይቻላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
የአገር ውስጥ ምርት ሲበረታታ ፋብሪካዎቹ ስለሚጠናከሩ የግንባታ ማጠናቀቂያ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር የሥራ እድል መፍጠርም ያስችላል። አሁንም ለእነዚህ ሥራዎች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት። ለተፈጻሚነቱም ሁሉም አካል ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በዚህ ዘርፍ የሚስተዋለው ሌላኛው ችግር የቴክኖሎጂ ሽግግር ችግር ነው። በዘርፍ ያሉ ማሽነሪዎችን የሚያንቀሳቅስ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል እጥረትን ለመፍታት የውጭ እና የአገር ውስጥ አምራቾች በጆይንት ቬንቸር የሚሰሩበት መመሪያ ወጥቷል። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት፣ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር ጆይንት ቬንቸር ወሳኝ ነው። ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን የማምጣት እድል አላቸው፣ አገር ውስጥ ያለው ደግሞ የራሱን ማምረቻ መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ ይችላል። ሁለቱ በመተጋገዝ ምርትን ማሳደግ ይችላሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ የብረት ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ የማጠናቀቂያ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካዎችን ወደ ምርት ማስገባት ይቻላል ሲሉ አመልክተዋል።
ዘርፉን እያጋጠሙ ያሉ ቁልፍ ችግሮችን ለመቅረፍ መወሰድ ካለባቸው ቁልፍ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል ብረታ ብረት የሚገኝባቸውን የመንግሥት ድርጅቶችን በመለየት ያገለገሉ ብረታ ብረቶች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሰራጩ የሚደረግበት አሰራር መዘርጋት ችግሩን ለመቅረፍ ቁልፍ አማራጭ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ጠቁመዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ጉዳዩን አስመልክቶ በቅርቡ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፤ በአገሪቱ ያሉትን ቁርጥራጭ ብረቶችን በመሰብሰብ ለነዚህ ፋብሪካዎች ግብዓት እንዲሆኑ በማቅረብ ፋብሪካዎቹ እያጋጠማቸው ያለውን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም አረጋግጠዋል።
ለፋብሪካዎች የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ፋብሪካዎች የአቅማቸውን ያህል እንዲያመርቱ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ የብረት ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ ግብዓት አምራች ፋብሪካዎች ወደሥራ ሲገቡ እናመርታለን ብለው ያስቀመጡትን እቅድ ያህል እያመረቱ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስገነዝበዋል። እያመረቱ ካልሆነ ደግሞ ማምረት ያልቻሉበትን ምክንያት እንዲያቀርቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተጠቆመው፤ ዘርፍን በሚመለከት ከዚህ በፊት የነበሩ ህጎችን ማስፈጸም ያስፈልጋል። ህጎቹ እንዳይፈጸሙ የሚያደርጉ ችግሮች ካሉ መፈተሽ አለበት። የግንዛቤ ችግር ካለ የግንዛቤ ችግር መፈታት አለበት። በግንባታ ዘርፍ ውስጥ በሚሳተፉ አካላት ላይ የግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች ከተሰሩ ችግሩን ማለፍ ይቻላል። ችግር ፈቺ አዳዲስ ህጎችን እስከ ማውጣትም መሄድ ያስፈልጋል።
ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ወጥ እና የተጠናከረ የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ችግር የሚፈቱ የምርምር እና የጥናት ተቋማትን ማጠናከር፣ የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት እየተሰሩ ያሉ ጥናቶችን መደገፍ ከተቻለ ዘርፉ አሁን ካለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ከመውጣት ባሻገር ኢኮኖሚውን የማረጋጋት እድል ይፈጠራል።
የመድረኩ ተሳፊዎች እንዳሉት፤ በፖሊሲ የተደገፉ የኮንስትራክሽን ዘርፍን የሚደግፉ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዋና ችግር እየሆነ ያለው የፋይናንስ አማራጭ እጦት ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለመደገፍ አማራጭ የፋይናንስ ተቋማት መኖር አለባቸው። በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ማሽነሪዎችን ሊዝ ማድረግ የዘርፉን ችግር ይፈታል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የልማት ባንክ ሊዝ ፋይናንስ እየሰራ ያለው በግብርና ዘርፍ ብቻ ነው።
በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገት አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ የግንባታ ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ፣ ጥራትና ወጪ መጠናቀቅ እንዲችሉ ለግንባታ ወሳኝ የሆነው የግንባታ ብረቶች እና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት ለማሳደግ መሥራት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፤ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። መንግሥት የብረትን ጨምሮ የሌሎች የግንባታ የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ የእሳት ማጥፋት አይነት ሥራ ላይ መጠመድ የለበትም። ጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሩን በመሰረታዊነት መቅረፍ የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ አለበት። መንግሥት ምርት ማከፋፈል ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በቂ ምርት እንዲመረት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል። በቂ ምርት እንዲኖር ከማስቻሉም ጎን ለጎን ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዱን መቀጠል አለበት።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም