ዶክተር ሐብታሙ ገበየሁ ትውልድና እድገቱ ጎንደር ገጠራማ አካባቢ ነው። ትምህርቱን በአዲስ አበባ ተከታትሏል። በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅም በህክምና ሙያ ያገለግላል። በቅርቡ ‹‹ሪቂቻ›› የተሰኘና የኦሮምኛ ቋንቋ ሰዋሰው ለጀማሪዎች መፅሃፍት አሳትሟል።
ዶክተር ሐብታሙ ይህን መፀሃፍ ያዘጋጀው በአጋጣሚ ነበር። ቋንቋን ማንም ሰው መናገር እንደሚፈልግ ሁሉ እርሱም ተጨማሪ ቋንቋዎችን የማወቅ ፍላጎት ነበረው። ጠቅላላ ሐኪም ከሆነ በኋላ በቂ ጊዜ ስለነበረው የተለያዩ መፅሃፎችን ያነብ ጀመር። ይህ የማንበብና ቋንቋን የማወቅ ፍላጎቱ በአንድ ነገር የበለጠ እንዲበረታ አስቻለው። ይህም የኦሮሚኛ ቋንቋን መናገር ነው። የቋንቋውን መዝገበ ቃላትና የንግግር መፅሃፍቶችን ማንበቡ ደግሞ ለዚህ አግዞታል።
ባለቤቱ የምታውቃቸው የተወሰኑ የኦሮሚኛ ቋንቋ ቃላት ነበሩ። እርሱም ባለው ጊዜ እርሷ የምታውቃቸውን ቃላት የማወቅና የመረዳት አጋጣሚ ተፈጠረለት። ከዛም በድረገፆች ላይ የቋንቋውን ቃላቶች በመፈለግ በርካታ የኦሮሚኛ ቃላትን ማወቅ ቻለ። በሂደት ብዙ ቃላትን አውቆ በመጨረሻ ቃላቱን ወደ አረፍተ ነገር መመስረት ከፍ አደረገው። በእርግጥ ይህንን ወዲያውኑ ማድረግ አልቻለም ነበር። ምክንያቱም የቋንቋውን የሰዋሰው ስርዓትና ትርጉም አያውቀውም።
ዶክተር ሀብታሙ ስህተቱ የቱ ላይ እንደተፈጠረ ሲረዳም ስህተቱን ለማረም እርሱ በሚያውቀው ቋንቋ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የተዘጋጀ ሰዋሰው መፅሃፍ መፈለግ ጀመረ። ነገር ግን እንደዚህ አይነት መፅሃፍ ማግኘት አልቻለም። ይሁንና በዚህም ተስፋ አልቆረጠም። ይልቁንም ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ሄዶ የኦሮሚኛ ቋንቋ ሰዋሰው ትምህርት ተማረ።
የሰዋሰው ቋንቋውን ትምህርት ቢጀምርም በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፈ የሰዋሰው መፅሃፍ ፍለጋውን ግን አላቆመም። ነገር ግን አሁንም ምንም ያገኘው ነገር አልነበረም። እናም እራሱ የመፍትሄ አካል ለማድረግ አሰበ። ትምህርቱን ሲከታተል ማስታወሻ በሚገባ እየያዘ ሲማር፣ ሰው ሲጠይቅ፣ መዝገበ ቃላትን ሲያነብና በኢንተርኔት ቋንቋውን ሲፈልግና የተረዳውን እየፃፈ ቆየ። በዚህም እያደር የቋንቋውን አካሄድ፣ ፍሰት ተረዳ።
የመዘገበው ማስታወሻ በሂደት ብዙ የሆነለት ዶክተር ሐብታሙ፤ እንደእርሱ አይነት ቋንቋውን መማር የሚፈልጉ ሰዎች የእርሱ አይነት ችግር እንዳይገጥማቸው ሲል ማስታወሻውን ወደመጸሐፍነት ቀየረው። በእርግጥም መጸሐፍ አለ ብሎ ቢፈልግም ስላላገኘ አማራጭ ይሆናል ብሎ አመነም። እንዳሰበውም ለብዙዎች ተስፋ ሆኗል።
ቋንቋን የማወቅ ፍላጎት የጀመረው ሥራ ከመጀመሩ በፊት ቢሆንም የሕክምና ባለሙያ ሆኖ በአቤት ሆስፒታል ሲቀጠር በሆስፒታሉ የሚመጡ አብዛኛዎቹ ታካሚዎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመጡ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነበሩ። ስለሆነም ከእነዚህ ታካሚዎች ጋር ለመግባባት አስተርጓሚዎችን ሁሌ መጠቀም ሰልችቶታል። በዚያ ላይ የተፈለገውን መረጃ ማግኘት ስለማይችል በሚፈልገው ልክ ሊረዳቸው አይችልምና ውስጡ ቋንቋውን እወቅ አለው።
ቋንቋውን የማወቅ ፍላጎቱ በብዙ ችግሮች ቢፈተንበትም እያየለበት የመጣውን ጉጉት መልቀቅ አልፈለገም። ስለዚህም መጀመሪያ መጸሐፍትን ማንበብ አልሆንልህ ሲለው ደግሞ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት መግባትን መፍትሄ አድርጎ ወሰደ። ከዚያ ውጤቱን ሲያየው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ሳይል የነበረበትን ፈተና ፈትቶ ለሌሎች ተስፋ ለመሆንም ጣረ። ይህም የኦሮሚኛ ሰዋሰው መፅሃፍ ዝግጅት ነው።
ዶክተር ሀብታሙ የኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርቱን ከጀመረ ሦስት ዓመት ሆኖታል። ከዚያ በፊት ግን ስለኦሮሚኛ ቋንቋ ምንም ነገር አያውቅም። የ36 ሰዓት ኮርስ ወስዷል። የተማረውም ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሳይሆን በግሉ ነው። ለሁለት ዓመት ከቋንቋው ጋር ከተዋወቀ በኋላ የያዛቸው ማስታወሻዎች ስለነበሩ የኦሮሚኛ ቋንቋ ሰዋሰው መፅሃፉን ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። በአንድ ዓመት ውስጥ ጽፎ ለንባብ አብቅቶታል።
ከማስታወሻዎቹና ከሌሎች ማጣቀሻ መፅሃፍቶች ያዘጋጀውን ባለ 264 ገፅ ጥራዝ አንድ ላይ በማድረግ ካጠናቀቀ በኋላ ራሱ የአርትኦት ሥራውንም ሰርቷል። የአሳታሚውን መብትም አስጠብቋል።
ቋንቋውን ገና የጀመረው እንደመሆኑ ስህተት ሊኖረው እንደሚችል አስቀድሞ በመገንዘብ አብረውት የተማሩና አፋቸውን በኦሮሚኛ ቋንቋ የፈቱ ሁለት ጓደኞቹ በአዘጋጀው ጥራዝ ላይ ተጨማሪ የአርትኦት ሥራ እንዲሰሩለት አድርጓል። አርትኦቱን ስላላጉላሉበትም ደስተኛ ነው። በአንድ ወር ውስጥ አጠናቀው ነው የመለሱለት። ከዚህም በላይ የጠራ ሥራ ለማውጣት ሲል ለሌሎችም ጓደኞቹ ዳግመኛ ሰጥቷል። ከዚያ መፅሃፍን ለማሳተም የሚያስፈልጉ ግባአቶችን ወሰደ።
ዶክተር ሐብታሙ የአርትኦት ሥራው በዚህ ብቻ እንዲቆም አልፈለገም። የመጨረሻ መፅሃፉን በአማርኛም ሆነ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እጅ እንደሚያስገባው ስለሚያውቅ ያለምንም እንከን እንዲወጣለት በኦሮምኛ ቋንቋ ዲግሪ ወይም ማስተር ያለው ተማሪ መፈለግ ጀመረ። ነገር ግን በዚህ ዘርፍ የተማረ ሰው ለማግኘት ቀላል አልሆነለትም። በብዙ ልፋት ነው የኦሮሚኛ ቋንቋ አስተማሪና ፅሁፎችን አርትኦት የሚያደርግ ሰው ያገኘው። ለአንድ ወር ያህል የአርትኦት ሥራው ፈጅቷልም። ከዚያ የመጨረሻ እርማቶችን ከአደረገ በኋላ መፅሃፉን ለህትመት አበቃ።
እርሱ ቋንቋውን በሚማርበት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛቸው መፅሃፎች ወይ መዝገበ ቃላት አልያም ደግሞ ንግግር ነበሩ። ይህም የኦሮሚኛ ቋንቋ ለማያውቅና መማር ለሚፈልግ ሰው በቂ አይደለም። የኦሮሚኛ ቋንቋ ሕግ ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው የተፃፈ መፅሃፍ የለም። በኦሮሚኛ ቋንቋ ላይ የተፃፉ የሰዋሰው መፅሃፎች ቢኖሩም የተዘጋጁት በኦሮሚኛ ቋንቋ በመሆናቸው መረዳት አይቻልም።
ሰዎች ራሳቸው በሚያውቁት ቋንቋ ቃላትን፣ አረፍተ ነገሮችንና አገላለፆችን ሊያውቁ ይገባል። የሚያውቋቸውን ቋንቋዎች ለመጠቀም ደግሞ የቋንቋውን ሕግ ማወቅ ግድ ነው። ዝም ብሎ ቃል ማወቅ ብቻ ጥቅም የለውም። ለዚህም ነው ዶክተር ሐብታሙ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈ የኦሮሚኛ ቋንቋ ሰዋሰው መፅሃፍ ያዘጋጀው።
ለመዝገበ ቃላትና ለንግግር በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች እንደተዘጋጁት መፅሃፎች የኦሮምኛ ቋንቋ ሰዋሰው በሁለትና ሦስት ቋንቋዎች አልተዘጋጀም። ሕጉን ካወቀ በኋላ በኦሮሚኛ ብቻ የተፃፉትን የሰዋሰው መፅሃፍት ወደ ማንበብ ይሸጋገራል። ይህንኑ ክፍተት በመረዳት መፅሀፉ ቢታተም ክፍተቱን ይሞላል በሚል ‹‹ሪቂቻ›› ወይም ድልድይ ሲል ዶክተር ሐብታሙ መፅሃፉን ሰይሞ ለንባብ አብቅቶታል። መፅሃፉም ሰዎች በአማርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋ መሰረታዊ ሰዋሰው እንዲረዱ የሚያስችል ነው።
‹‹ቋንቋ መግባቢያም ክህሎትም ነው›› የሚለው ዶክተር ሐብታሙ፤ ቋንቋን በቀላሉ መማር እንደሚቻልና ሰዎች ቋንቋን በአወቁ ቁጥር የመግባባት ችሎታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እድል እንደሚያገኙ ይናገራል። ማንም ሰው ተጨማሪ ቋንቋ ቢያውቅ የማይጠላ በመሆኑ ፍላጎት እንዳለ ሆኖ ይህን ፍላጎት እውን ለማድረግ ግን የራስ ጥረት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።
ሰዎች አፋቸውን ከፈቱበትና ከሚያውቁት ቋንቋ በተጨማሪ በሚኖሩበት ማህረበረሰብ ውስጥ ያሉ ቋንቋዎችን ቢማሩ ሊቀላቸው እንደሚችሉም ነው ዶክተር ሀብታሙ የሚናገረው። ከዚህ አንፃር በርካታ አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን በአጠረ ጊዜ በቀላሉ መማር እንደሚችሉ ይመክራል። ዋናው ጉዳይ ግን በውስጥ ያለ ፍላጎት መሆኑንም ይጠቅሳል።
ቋንቋዎች መደባቸው የሚለያይ ቢሆንም በማህረሰቡ ውስጥ ግን ይወራረሳሉና በቀላሉ ለመልመድ አያስቸግሩም። በዚያ ላይ ቋንቋ የአንድን ማህበረሰብ አስተሳሰብና ባህል የሚገልፅ በመሆኑ ሰዎች ከሚያውቋቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ቋንቋዎች የማወቅ እድል እንዳላቸው ያነሳል። ለዚህም እርሱ ጥሩ ምሳሌ እንደሆነ፤ ከዚህ በፊት ለታካሚዎቹ አገልግሎት ሲሰጥ አስተርጓሚ ይጠቀም እንደነበርና ቋንቋውን በማወቁ አሁን ላይ በቋንቋው መግባባት እንደቻለ ያስረዳል።
ዶክተር ሐብታሙ ወጣቶች በፍላጎት ብቻ ሳይሆን የመከባበር፣ የመቻቻልና የመዋደድ እሴቶችን እንዲያዳብሩ የሁሉንም ብሄረሰቦች ቋንቋ መማር አለባቸው ይላል። ይህም ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም። ቋንቋ ክህሎትና መግባቢያ እንዲሁም እውቀትን መገንቢያ እንደሆነ አውቆ መጠቀም ያስፈልጋል። የኦሮምኛ ቋንቋን አብዛኛው ማህበረሰብ የሚጠቀምበት እንደመሆኑ ሌሎች ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ቋንቋውን የራሳቸው አድርገው ቢማሩ ለቋንቋው ተናጋሪ ማህበረሰብ ያላቸውን አክብሮት ማሳያም ነውና ብንገለገልበት መልካም ነው ይላል።
እያንዳንዱ ሰው ቋንቋ የሚማረው ለራሱ እንጂ ለሌላ ሰው ብሎ አይደለም። ስለሆነም ለቋንቋ ያለው አረዳድ በሰፋ መልኩ መሆን ይኖርበታል። ሰዎች ሁሉንም ቋንቋ የኔ ናቸው ሲሉ የሚያገኙት ነገር ይበዛላቸዋል። ስለዚህም ለመብዛት፣ ለማወቅና ከፈለግነው ሰው ጋር በመግባባት ለመኖር ከፈለግን ቋንቋን እንማር ይላል።
‹‹ሪቂቻ›› የተሰኘው የኦሮሚኛ ሰዋሰው ቋንቋ ከታተመ አምስት ወራት ሆኖታል። ለህትመት ከበቃ ወዲህ ከአንባቢያን የሚመጡ ግብረ መልሶችም ገምቢ ናቸው። መፅሃፉ እንዲታተም በማህበራዊ ድረገፅ እንዲወጣ ተደርጓል። ይህንኑ ተከትሎ አንዳንድ ሰዎች መፅሃፉን ለማስተዋወቅ እገዛ አድርገዋል።
በመጀመሪያ አንድ ሺህ ቅጂ የታተመ ሲሆን፤ በዚህ ቁጥር በርካታ ሰዎች ጋር መድረስ የማይቻል በመሆኑ መፅሃፉ በማህበራዊ ድረገፅ በተለይ ደግሞ በፌስቡክና በቴሌግራም ቻናል እንዲተዋወቅ ተደርጓል። በዚህም በርካታ ተደራሲያን ጋር መድረስ ተችሏል። ተደራሲያንም የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛሉ። ስለዚህም በግምገማዬ መፅሃፉ ጥሩ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ጀርባ ታሪኬ ሲታይ እኔ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለሁም። መፅሃፉንም ያዘጋጀሁት ክፍተቶቼን አይቼ ነው። በዚሁ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱና ከኔ በተሻለ ሊፅፉ የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ። ነገር ግን እስካሁን ትኩረት የተደረገው የኦሮሚኛ ቋንቋን ለሚያውቁት ብቻ ነው። ቋንቋውን ለማያውቀው ማህበረሰብ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ቢማሩበት ማለት ያስፈልጋል። ለዚህም የእርሱ መጸሐፍ ማሳያ ይሆናል።
በቀጣይም የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህመምተኞች እንዴት የህክምና እንክብካቤ ማግኘት ይችላሉ የሚሉ መፅሐፍትን ይዞ ብቅ እንደሚል ቃል የገባው ዶክተር ሐብታሙ፤ ለዚህም መነሻው በዘርፉ የተጻፉ መጸሐፍትን ማግኘት አለመቻሉ ነው። እናም በተለይ ታካሚዎች ከሀኪሞች ጋር ሲገናኙ በቋንቋ እንዳይቸገሩ ሊያግዝ የሚችል መፅሃፍት ለማዘጋጀት እቅድ አለው። ችሎታውን እያየና ቋንቋውን እየተማረ ሌሎችንም ሥራዎችን ይዞ ብቅ ማለቱ እንደማይቀር ያነሳል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም