ብዙ ጊዜ በዚህ አምድ ስር ታሪካቸው የሚቀርብላቸው፤ ስራና ተግባራቸው በባለውለታነት የሚነገርላቸው … ሰዎች (በተፈጥሮ ሰው የሆኑ) ናቸው። ዛሬ ከዚህ ወጣ በማለት ተቋማት (በሕግ ሰው የሆኑ)ትን ማንሳት ፈለግን።
ተቋማት ህጋዊ እውቅና እስካላቸው ድረስ ማንነት አላቸው፤ ተጠያቂነት አለባቸው፤ የመክሰስ መብት እንዳላቸው ሁሉ የመከሰስ ግዴታም አለባቸው። በመሆኑም በባለውለታነት የመታወስም ሆነ የመዘከር እድሉና መብቱ አላቸው ማለት ነው።
”ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ነፃ የሆነ ትውልድን ማየት”ን ራእዩ አድርጎ የተነሳው፣ ”ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ” የዛሬ ምርጫችን ነው። ምርጫችን ይሆን ዘንድ ምክንያቱ ደግሞ ነገ (ህዳር 22) የኤችአይቪ/ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር መሆኑ ነውና ስለ ”ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ” ጥቂት እንበል።
በወቅቱ፣ ኤችአይቪ/ኤድስ እንደ ሰደድ እሳት በተቀጣጠለበት ወቅት ማንም ለማንም መድረስ በማይችልበት ወቅት፤ ማንም ምንም የማድረግ ግንዛቤው በሌለው ወቅት …. በዛ ቀውጢ ወቅት … ነበር ”ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ” በራሳቸው፣ በቫይረሱ በተጠቁ፤ በጉዳዩ ባለቤቶች አማካኝነት ብቅ ያለው። መቼ?
በወቅቱ በመንግስት በኩል የችግሩ አሳሳቢነት ከጤና አልፎ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መሆኑ ግልጽ ስለነበረ በ1990 ዓ.ም የመጀመሪያው የኤችአይቪ/ኤድስ ፖሊሲ ተቀረጸ። ችግሩ ምላሽ ማግኘት ያለበት መሆኑ ታምኖበት ይህ ፖሊሲ በመቀረጹ የመንግስት ሴክተሮች፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የግሉ ዘርፍ፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ማህበረሰቡ በሙሉ በአንድነትና መተቀናጀ መልክ በአጋርነት ሲሰሩ እንዲቆዩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጠረ።
ይህን ተከትሎ በአዋጅ ቁጥር 276/1994 አገር አቀፉ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በመውጣጣት ተቋቋመ፤ በ1994 ይህ ምክር ቤት ከተለያዩ ሴክተር መስሪያቤቶች፣ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች፣ በተቀናጀ መልኩ በቁርጠኝነት እንዲመሩ ተደርጎ የተቀረጸና የተቋቋመ ምክር ቤት ነበረ። በዚህም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አሁን ለተደረሰበት የኤችአይቪ/ኤድስ መቀነስ ውጤቶችና ስኬቶች ተብለው ለሚቆጠሩት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት በየደረጃው እስከወረዳ ድረስ ተደራጅቶ የምክር ቤት ጉባኤውን በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲደረግ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፤ ምክር ቤቱም በወቅቱ የነበረውን ችግር እንደ አገራዊ አደጋ በማየት ትኩረት ተደርጎበት እና አገራዊ አጣዳፊ አደጋ በመሆኑ ምላሹም በአጣዳፊነት አግባብ እንዲከናወን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አሁን ለተደረሰበት ስኬት ለመሸጋገር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። ከምክር ቤቱ ጋር ተያይዞ የስራ አመራር ቦርድ በየደረጃው፣ በየክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች በሚወክሏቸው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ዘርፈ – ብዙ ምላሹን በስፋት የሚደግፍና የሚገመግም እንደነበር ገልጸዋል።
ይህንን ለማስተባበር መዋቅር በማስፈለጉ ምክንያት የምክር ቤቱን መቋቋም ተከትሎ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል። በመሆኑም ጽህፈት ቤቱ የቦርዱ ሴክሬተሪያት በመሆን፤ ዓመታዊ እቅዱን፣ የእቅድ አፈጻጸሙን፣ ሌሎች በየወቅቱ የሚነሱ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በአጀንዳነት በማቅረብ ለዘርፈ ብዙ ምላሹ ምላሽና አቅጣጫ እንዲሰጥ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አስረድተዋል።
የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝና ስርጭት ላይ በዘርፈ ብዙ ምላሹ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክተው ሰጥተውት በነበረው ገለፃ ቫይረሱ በአገራችን መኖሩ የታወቀው ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን የመጀመሪያዋ ህመምተኛ ሪፖርት የተደረገችው በ1978 ዓ.ም ነው። የዚህ ጽሑፍ አንባቢም ጽሑፉን ከዚሁ አውድ አኳያ ይረዳልን ዘንድ እንጠይቃለን።
ጥናት አቅራቢዋ፣ በወቅቱ ይህ ችግር ሲፈጠር አደጋው እጅግ በጣም አስደንጋጭ ስለነበር በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አገር ዓቀፍ ግብረ-ኃይል ተዋቀረ። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኤድስ መቆጣጠሪያ መምሪያም እንደዚሁ ተቋቋመ። ይሁን እንጂ፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በግል ተነሳሽነት በጉዳዩ ላይ ”አለሁ” ያለ አልነበረም።
ኃላፊዋ (ዶክተር ጽጌረዳ) እንዳሉት ከ1979 እስከ 1982 ዓ.ም በተደረጉት ጥናቶች መሰረት ወረርሽኙ በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሰራጭቶ ነበር። ያልዳሰሰው አካባቢም ሆነ የህብረተሰብ ክፍል አልነበረም። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት በተለይ በሴተኛ አዳሪዎች፣ በረጅም ርቀት ተሽከርካሪ ሹፌሮች፣ እንዲሁም በወታደሮች አካባቢ በማተኮር የተሰሩ ነበሩ። በአገራችን ኤችአይቪ/ኤድስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ፣ እስካሁን ድረስ በሞት ምጣኔ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት ውስጥ ዋነኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳቱ የደረሰባቸው ወገኖች ላይ የነበረው አድሎና መገለል እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር።
በሽታው መከሰቱ የሚገለጽበት እና ለመከላከል የሚቀርቡ ዝግጅቶች በአስፈሪ ሁኔታ ስለነበር የወቅቱን የግንዛቤ ውስንነት አሸንፎ በመውጣት ህብረተሰቡን ለማስተማር የመጀመሪያዋ እና ፈርቀዳጅ የነበረችው ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ በላይነሽ ጥላሁን ናት።
ዶክተሯ “አሁን ላይ በሕይወት ባትኖርም ሴት መሆኗ፣ የቫይረሱ ተጋላጭነቷ እና መገለሏ ሳይበግራት ለችግሩ ተጠቂዎች ድቅድቅ ጨለማ እይታ በነበረበት ጊዜ የመጀመሪያ ሆና፣ እራሷን አውጥታ፣ ሕዝብን በማስተማር ከፍተኛ መንገድ ስለከፈተች፤ ለሌሎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች መደገፊያና መንከባከቢያ ማህበራት መመስረት እና በእነዚህ ለመጡ ውጤቶች አርአያ በመሆኗ ጽህፈት ቤቱ እንደ ጀግና ይቆጥራታል” ሲሉም ወይዘሮ በላይነሽ ጥላሁንን ገልጸዋታል። ከዛስ?
በ1995 ዓ.ም የተቋቋመው ”መቅድም ኢትዮጵያ”ም ሆነ፣ ዓላማዎቹን፣ ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖችና ወላጅ አልባ ሕፃናት እንክብካቤ እንዲያገኙ መርዳት፤ ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖችና ወላጅ አልባ ሕፃናት መብት እንዲከበር መታገል፣ ኤች·አይ·ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት መሰለፍ፤ በትምሕርት፣ በድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራሞች አማካኝነት የአባላቱ ጥያቄዎች የሚሟሉበትን መንገድ በማፈላለግ የአባላቱን መብት ማስጠበቅ አላማ አድርጎ ወደ ተግባር ገባ፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ሆነ ዶክተር ጽጌረዳ እንደዳሰሱት፣ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለቱ እና ሌሎችም በየክልሉ የተቋቋሙ በርካታ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ያቋቋሟቸውና የሚሳተፉባቸው፤ ድጋፍና እገዛም የሚያገኙባቸው ማህበራት ነበሩ። እነዚህም በየክልሉ በጥምረት መልክ ከተዋቀሩ በኋላ በፌዴራል ደረጃም ”የጥምረቶች ጥምረት” ወይም ”ኔፕ ፕላስ” በሚል የሚታወቁና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ማህበራት ተቋቋመ። ከእነዚህም መካከል (ዝቅ ብለን የምናያቸው) እስካሁንም ድረስ በሽታውን በመከላከል፣ ማስተማርና በየጤና ተቋማቱ በህክምና አገልግሎቱ ዘርፍ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ እና እያገዙ የሚገኙ ማህበራት፣ ክበባት… አሉ። ሌሎችስ?
ተመሳሳይ አላማን በመያዝ፣ በ2005 ዓ. ም በሴቶች አማካኝነት ”ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ማህበራት ጥምረት” በሚል መለያ ማህበር ተቋቁሞ፤ ትኩረቱን በሴቶች ላይ በማድረግም በአጠቃላይ በመከላከሉና መቆጣጠሩ፤ እንዲሁም በድጋፍና እንክብካቤው ዘርፍ ሰፊ ድርሻን አበረከተ። አሁንም አቅሙ የፈቀደለትን ያህል በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እያበረከተ ይገኛል።
በዚህ አገራዊና የህልውና ጉዳይ በነበረ ታሪክ ውስጥ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እድሮች የኃይማኖት ተቋሟት፣ የማይረሳና በጣም ሰፊ ድርሻ ነበራቸው። ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ሰፊ በመሆናቸው የኤችአይቪ/ኤድስ ትምህርት በመስጠት፣ አድሎና መገለልን በመታገል፣ ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው ወገኖች፣ አልጋ ላይ ላሉ ህመምተኞችና ለቤተሰቦቻቸው የቤት ለቤት እንከብካቤ በመስጠት እነዚህ መዋቅሮች ሰፊና በታሪክ የማይረሳ ስራን ሰርተዋል። (ከዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ የተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ መስራች የሆነው ዘውዱ ጌታቸውን አስመልክተን ባለፈው ሳምንት በዚሁ ገፅ ላይ አቅርበን የነበረውን ጽሑፍ ያስታውሷል።)
እነዚህ ህዝባዊና ማህበራዊ ተቋማት ያንን አስከፊ ችግርና መከራ ከመቋቋም፤ መድሃኒት የሚወስዱትንምበማስተማር ከመድሃኒቱ ጋር ተቆራኝተው እንዲቆዩ ከማድረግ አኳያ የማይተካ ሚናን ሲጫወቱ እንደ ነበር በየወቅቱ ሲቀርቡ የነበሩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እየቀረቡ ያሉትም እነዛን አይነት ተግባራት በአሁኑ ወቅትም ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን እያሰመሩበት ይገኛሉ። የዶክተር ጽጌረዳ ጥናትም ይህንኑ ያረጋግጣል።
”ለመሆኑ እነዚህ በቫይረሱ ተጠቂ በሆኑ፣ ብዙዎችን ለታደጉ፤ በተለይም ወገንን ከከፋ እልቂት ያዳኑ (አራቱን ”መ”ዎች ያስታውሷል) ተቋማት ምን ምን ቢያደርጉ ነው ለዛሬ የባለውለታዎቻችን አምድ የበቁት?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ትክክል ነው። እነዚህ ተቋማት ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ያላደረጉት ነገር የሌለ ሲሆን፤ የብዙዎቹም ተመሳሳይ ነበር። ለማሳያ ይሆነን ዘንድ በተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ አማካኝነት የተከናወኑትን እንመልከት።
ከተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ (ራሱ ድርጅቱ Dawn of Hope Ethiopia association በማለት ይተረጉመዋል) ከድረ-ገፅ የተገኘው መረጃ እንደሚነግረን ”የኤች·አይ·ቪ/ኤድስ በሽታን ለመከላከል እና ባለበት ደረጃ ለመግታት «ትውልድ ይዳን፤ በእኛ ይብቃ» በሚል ክቡር አላማ ተነሳስተው ዘውዱ ጌታቸው እና አሥር ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን ሰኔ 1990 ዓ.ም የመሰረቱት ማህበር ነው። ይህ ማህበር ለትርፍ ያልቆመ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የሀይማኖትና ሌሎችም ወገንተኝነት ነፃ የሆነ ማህበር ነው። ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሺህ በላይ ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ አባላት ሲኖሩት በመላው ኢትዮጵያም 12 ቅርንጫፎች ነበሩት” (ሐረር፣ ሁመራ፣ ሻሸመኔ፣ ባህርዳር፣ ናዝሬት፣ አዲስ አበባ፣ አዋሳ፣ ደብረዘይት፣ ደብረብርሃን እና ዲላ) ሲሆን፤ በአሁኑ ሰአት ሀዋሳና አንዳንድ አካባቢዎች ያሉት በስራ ላይ መሆናቸው ይነገራል።
ማስተማር እና መቀስቀስ ተግባራቱን በተመለከተም፣ የምክር አገልግሎት፣ የቅድመ ምርመራ፣ ድህረ ምርመራና ቀጣይ የምክር አገልግሎት መስጠት፤ ከቫይረሱ ጋር ተስማምቶ ለመኖር መከተል ስላለባቸው መመሪያዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ፤ ሕብረተሰቡ ስለኤች·አይ·ቪ/ኤድስ ያለውን ግንዛቤ አሳድጎ ራሱን እንዲጠብቅና በዚህም የወረርሽኙን ተዛማጅነት ለመቀነስ በአባላት አማካኝነት በተለያዩ መድረኮች ትምህርት መስጠት ወዘተ መሆናቸው ስለ ኤችአይቪ/ኤድስ በተሰነዱ መዛግብት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ክብካቤና ድጋፍን አስመልክቶም፣ በኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች ማስታገሻ የመድሃኒት ግዢ ድጋፍ መስጠት፤ በኤድስ ሳቢያ ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት የሚገባውን ድጋፍ ማድረግ፤ በኤድስ ሳቢያ ታመው አልጋ ላይ ለዋሉ አባላት ሁለገብ ድጋፍ መስጠት እንደ ነበርም መዛግብቶቹና የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ከሰብአዊ መብት ማስጠበቅ አኳያም ከኤች·አይ·ቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች መገለልና መድልዎ እንዳይደርስባቸው መከላከልና በዚህ ረገድ የሚከሰቱ አጋጣሚዎችን ለሕግ አካላት ማቅረብና የመብት ማስጠበቅ ስራዎችን የመስራት ተግባራት ተከናውነው ለበሽታው መቀነስ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ምናልባት እዚህ ላይ ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያንና መቅድም ኢትዮጵያን እናንሳ እንጂ ሌሎች የሉም ወይም አልነበሩም ማለት አይደለም፤ ከእነዚህ መካከልም ህብረት አምባ፣ ጥላዬ፣ ቃል ኪዳን (አሁን የለም) … እና ሌሎችንምን መጥቀስ ይቻላል። ይህንን ስንል በየትምህርት ተቋማቱ፣ መስሪያ ቤቶች፣ ድርጅቶች … ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ክበባት ሳንረሳ ነው።
ከላይ ያነሳናቸው ሀሳቦች ባለውለታዎችን ከማንሳትና ማስታወስ ባለፈ ሌላም አሁናዊ ፋይዳ አላቸውና ወደ እነሱ እናምራ።
የአሁኑ ይዞታ (በ2014 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ. በ2014 ከ35 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ. ተህዋሲ ጋር ይኖራሉ። ከእነዚህ መካከል 1.2 ሚሊዮን ያህሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በየአመቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች በኤድስና ተያያዥ ምክንያቶች ይሞታሉ። ከዚህ ቁጥር መካከል 47ሺህ ያህሉ በኢትዮጵያ ይገኛል። እ.ኤ.አ. በ2012 ከ170ሺ በላይ ህጻናት ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ። ከ 900ሺ በላይ ህጻናት ደግሞ ወላጆቻቸውን አጥተዋል። እውነታው ይህ ሲሆን፣ ጉዳዩ ወደ ሚመለከተው ጎራ በማለት ጉዳዩን በጥልቀት መረዳት ይቻላል።
የኤችአይቪ/ኤድሰ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ከነበረበት ከ1990ዎቹ አጋማሽ እና የጸረ-ኤችአይቪ ህክምና ከመጀመሩ ከ1997 ዓ.ም አንጻር በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ቢቻልም ዛሬም በየዓመቱ 15ሺህ የሚሆኑ ወገኖቻችን አዲስ በኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙበት ሁኔታ አለ።
ከዚህ የምንረዳው ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር ዛሬም እንደ ትናንትናው ዘውዱ ጌታቸውን፣ ወይዘሮ በላይነሽ ጥላሁን .. የመሳሰሉ ጀግኖች፤ ቃል ኪዳን፣ ጥላ፣ ተስፋ ጎህ፣ መቅደስ፣ ሕብረትን … የመሳሰሉ ነፍስ አድን ተቋማት የሚያስፈልጉን መሆኑን ነውና ነገ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ስናከብር በዚሁ መንፈስ ይሆን ዘንድ እናሳስባለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም