ወይዘሮ ሮዛ ሀብታሙ ይባላሉ። የመማርያ መጽሃፍት እጥረት የራስ ምታት ከሆነባቸው ወላጆች አንዷ ናቸው። በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው መፀሐፍ ለልጆቻቸው መድረስ ባለመቻሉ ብዙ ነገራቸው ተዛብቶባቸዋል። አንዱ ልጆቻቸውን ማገዝ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ላልተገባ ወጪ መዳረጋቸው ነው። ልጃቸውን ማስጠናትም ሆነ የከበዳቸውን ትምህርት ማገዝ ያልቻሉት እንደሌላው ትምህርትቤት በሶፍት ኮፒ እንኳን መጸሐፍቱን ሳያገኙ መቆየታቸው ነው። አብዛኞቹ ትምህርትቤቶች መጸሐፍቱን በቴሌግራምና መሰል የማሰራጫ አማራጮች ለተማሪዎችና ለመምሀራን ሰጥተው የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲሳለጥ ቢያደርጉም እርሳቸው ጋር ግን ይህ አልሆነም። በዚህም ልጆቻቸው የቤት ሥራ ለመስራት ቤት መጥተው የቸገራቸውን ሲጠይቋቸው ምንም ማለት አልቻሉም።
ከሳምንት በፊት በፍላሽ ውሰዱ የሚል መልእክት እንደደረሳቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሮዛ፤ ትምህርትቤቱ ይህን ያደረገው ተማሪዎች ፈተና ሊወስዱ በመቃረባቸው የተነሳ ብቻ ነው። የይድረስ ይድረስ ስራ እንደተሰራም ይናገራሉ። እርሱም ቢሆን በፍላሽ መፀሐፉን ወስዳችሁ ፕሪንት አድርጉ እንጂ ምን ያህል ምዕራፍ እንደሆነ አይገልጽም። ይህ ደግሞ ወላጅን ኪሳራ ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን ለማይጠቅም ነገር ወጪ ማውጣትንም ያስከትላል ። ምክንያቱም በአንድ የትምህርት አይነት ብቻ ከ140 በላይ ገጽ የሚባዛ ሲሆን፤ መጽሀፉ የሚቆይበት ጊዜ አጭር በመሆኑ ይጣላል። እናም ለወላጅም ሆነ ለተማሪ ማሰብ እንኳን ያልተቻለበት አሰራር እያዩ መሆኑን ይገልጻሉ።
ተማሪዎች መጽሀፉ በእጃቸው ስላልገባ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ከሞባይላቸው ጋር እንዲገናኙ እየሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ነገሮችን ከሞባይል ውጪ እንዳያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ልምድ ይሆንባቸውና ወደአላስፈላጊ ተግባርም ሊገቡ ይችላሉ። ስለሆነም እንደ አገር ልጆችን መታደግ የሚቻለው በአፋጣኝ መጸሐፉቱ ታትመው እጃቸው ላይ ሲገባ ነውና ሁሉም ፈቃደኝነቱን ማሳየት እንዳለበት ያነሳሉ። እስከዚያ ደግሞ ትምህርትቤቶች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንዳለባቸውም ይናገራሉ።
መጽሐፍትን አሳትሞ በፍጥነት የማድረስ ሥራ የመንግስት ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የሚናገሩት ወይዘሮ ሮዛ፤ የልጆቻችን ጉዳይ የእኛም ጉዳይ ነው። እናም የተቻለንን ሁሉ አድርገን ቋሚ የመማርያ መጽሐፍትን አሳትሞ ማሰራጨት ይገባናል። በተለይም አሳታሚዎች ፤ ማተሚያ ያላቸው ትምህርትቤቶች እንዲሁም ባለሀብቶች በዚህ ላይ ትብብር ቢያደርጉ ነገሮች ይቀላሉ። ወላጆችም ለማባዢያ የሚያወጡትን ወጪ ለዚህ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ ቢመቻች ለልጆቻችን መድረስ እንችል ነበር ይላሉ።
የዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃና አጸደሕጻናት ትምህርትቤት ርዕሰመምህር አቶ ግሩም መዝገበ በበኩላቸው፤ የመጸሐፍ ህትመትና ስርጭት ጉዳይ የአንድ አካል ችግር ብቻ እንዳልሆነ ያነሳሉ። መጸሐፍት የመማር ማስተማሩን ስርዓት በብዙ መልኩ ያሳልጣሉ። ስለሆነም ቶሎ ታትመው ተማሪዎች ጋር መድረስ ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን የመማር ማስተማሩን ሥራ በብዙ መልኩ ያደናቅፈዋል። ጫና የሚፈጥርባቸው አካላትም ይፈጠራሉ። ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች። ስለዚህ መጸህፍት የትምህርት የጀርባ አጥንት ናቸውና ችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሄን እንደሚሹ ያስረዳሉ።
እንደ ትምህርትቤት የመጸሐፍት ስርጭቱ ሌሎቹ በሚያሳስባቸው ልክ አይደለም። ምክንያቱም በትምህርት ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የትምህርት አይነቶችን ማድረስ ባይቻልም የተወሰኑትን መጸሐፍት አንድ ለአንድ በሚባል ደረጃ ማድረስ ተችሏል። ያልደረሱትን የትምህርት አይነቶች ደግሞ በተማሪው ላይ እና በመምህራኑ እንዲሁም ወላጅ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ በሶፍት ኮፒ ለሁሉም ተደራሽ እየተደረገ ነው። አስፈላጊ ሲሆንም የማባዛትና ለተማሪዎች የማሰራጨት ሥራ ይሰራል። ማለትም ተማሪዎች በቡድን ሆነው እንዲሰሩ መጸሐፉን ፕሪንት በማድረግ ይሰጣል። በተለይ የምዕራፉ ማጠቃለያ ላይ ያሉ መልመጃዎችን ተማሪዎች በአግባቡ እንዲሰሯቸው ለማድረግ ብዙ ጥረቶች እንደሚደረጉ ይናገራሉ። መምህራን የቤት ሥራ ሲሰጡም ጥያቄዎችን በቦርድ ላይ ጽፈው ነው። ይህ ደግሞ በቴሌግራም መጸሐፍቱን ለማያገኙ ልጆች የሚያግዝ ነው።
ከመጽሐፍት ስርጭትና ህትመት ጋር በተያያዘ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንደሚሉት፤ ምንም አይነት አዲስ ነገር በሚተገበርበት ጊዜ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አይሆንም። የመጽሐፍ ህትመትና ስርጭቱ ጉዳይም አንዳንድ ችግሮች የታየበት ከዚህ የተነሳ ነው። በዚያ ላይ እንደሚታወቀው በአገራችን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች የሚሆኑ መጸሐፍትን ለማተም ብቃት ያላቸው ተቋማት ብዙ አይደሉም። ሁሉም ክልል ያሳትማል። ስለዚህም ችግሩ መፍትሄ እስኪያገን ድረስ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጀ መጽሐፍ ዲጅታል በሆነ መንገድ እንዲሰራጭ ተደርጓል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከዳታ ነጻ በሆነ መንገድ ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያም እየተሠራ ነው።
የመጽሐፉ ስርጭት የክልሎች ኃላፊነት በመሆኑም የፋይናንስ፣ አሳታሚ ድርጅቶችን ያለማግኘትና በቶሎ የማድረስ ችግሮች እንደነበሩባቸው ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ይህንን ችግር ለመፍታት በሚኒስቴሩ በኩል ድጋፍ እየተደረገ ነው። በዚህም ሁሉም በሚባል ደረጃ ወደ ህትመት መግባት ችለዋል። በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ የሚሄድ ይሆናል ብለዋል።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት ልክ እየተጓዙ እንደሆነ ራሳቸውን አብነት በማድረግ ያነሱልን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ያስፈለገበት ምክንያት ተማሪዎች በሶስት መልኩ እንዲቀረጹ ነው። እነዚህም በአዕምሮ፣ በስነልቦናና በክህሎት እንዲዳብሩ ማድረግ የሚሉት ሲሆኑ፤ መጽሐፍቱ ይህንን ታሳቢ አድርገው ተዘጋጅተዋል። ዝግጅቱ ደግሞ ፈታኝና ብዙ ልፋትን የጠየቀ ነበር። ሆኖም በብዙ መልኩ ተስተካክሎ ለብዙዎች መድረስ ችሏል። ከአንዳንድ የትምህርት አይነቶች በስተቀር ተሰራጭቷልም።
አዲሱ ስርዓተ ትምህርት አዕምሮ፣ ልብና እጅን ያገናኘ እንዲሆን ለማስቻል የመጸሐፍ ዝግጅቱ ላይ ብዙ እንደተጨነቁበት የሚያነሱት ኃላፊው፤ መጀመሪያ አካባቢ የዩኒቨርስቲ መምህራን እንዲያዘጋጁት ጥረት ተደርጓል። ሆኖም በቢሊዬን የሚጠጋ ገንዘብ በመጠየቃቸው ትተውት በራስ ወደመሥራቱ ሂደት ገብተዋል። በዚህም በራስ አቅም መጠቀም ያለውን ዋጋ ያዩበት እንደነበር ያነሳሉ።
የመጸሐፍ ዝግጅቱ በራስ አቅም በመሰራቱ በብዙ ነገር እንደ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን እንደአገርም ተጠቅመናል የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ የመጀመሪያው ወጪ ቅነሳ ነው። ወጪያችንን ማለትም አሁን የተቀየረው ስርዓተ ትምህርት ያኔ ሲዘጋጅ ከወጣው ወጪ በ57 ሚሊዬን ብር የቀነሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚያም በተጨማሪ ከኦሮምያና ከአማራ ክልል በስተቀር ብዙዎቹ ክልሎች የበጀት እጥረት ስላለባቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተዘጋጀውን መጽሐፍ ወስደው እንዲጠቀሙ ሆነዋልና ለሌሎች አቅም በመሆን ሃብትን ማዳን ተችሏል። ሁለተኛው መምህራኑ ከሁሉም ክፍለከተሞች የተውጣጡና ምስጉን የተባሉ በመሆናቸው ችግሮች ሲኖሩ ወዲያው መፍትሄ እንዲሰጡበት ተደርጓል። ለማስተማርም ቀላልና ያልተረዱትን በቀላሉ ግልጽ ለማድረግ የሚያስችልበት ሁኔታን ፈጥሯል። በዚያ ላይ መምህራን ላይ አቅም መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዘላለም ማብራሪያ፤ የመጸሐፍ ህትመትን በተመለከተ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ ለስድስት አሳታሚ ድርጅቶች የተሰጠ ሲሆን፤ ጨረታው የአገር ውስጥ አሳታሚዎችን የያዘ ነው። ሆኖም አንዱ ድርጅት በጥሬ እቃው መወደድ የተነሳ በራሱ ውጪ በመውሰድ እንዲታተም አድርጓል። ይህ ደግሞ ኑ ህትመቱ ቢጠናቀቅም መጓጓዙ ጊዜ ስለሚወስድ እስካሁን መግባትና ማሰራጨት አልተቻለም። እስከ ህዳር 30 ድረስ ግን ይህ የሚጠናቀቅ ይሆናል። 80 በመቶ የሚሆነውን የመጸሐፍ ስርጭትም ይደረጋል።
የመጽሐፍ ዝግጅት ሥራው የተጀመረው በ2013 ዓ.ም እንደነበር የሚያስታውሱት ኃላፊው፤ በ2014ዓ.ም የመጽሐፍ ዝግጅቱ ለሙከራ በሚሆንበት ደረጃ በመጠናቀቁ በ44 ትምህርት ቤቶች ላይ ትግበራው እንዲጀመር ተደርጓል። ነሐሴ መጨረሻ ላይ ደግሞ ሁኔታዎች ተጠናቀቁና የመጸሐፍ ህትመት ጨረታ ተጀመረ። መስከረም መጨረሻም የጨረታ ሂደቱ አለቀ። እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ደግሞ መጸሐፍቱ ታትመው ይገባሉ። በከተማ አስተዳደሩ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን መጽሐፍት በኮፒ የተዘጋጀ ሲሆን፤ እስካለፈው ሰኞ ድረስ የነበረው መረጃ በየትምህርትቤቱ ወደ 1 ነጥብ 5 የሚደርሱ ኮፒ መሰራጨቱን ያስረዳሉ።
መጽሐፉ ያልደረሳቸው ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሶፍት ኮፒ እንዲያገኙ በማድረግ ትምህርት እንዲጀምሩ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ጫናው መምህራን ላይ የሚያርፍ ቢሆንም ለተማሪዎች ግን ብዙ ጥቅም እንደነበረው ማየት ተችሏል። አንዱ አዳምጠው የመጻፍ ክህሎታቸውን ያዳብሩበት ሲሆን፤ ሌላው አንዱ የትምህርት መስክ የሆነውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በስፋት እንዲተገብሩት እድል የሰጠበት ነው።
‹‹ስርዓተ ትምህርት ሁሌ ለትችት ቅርብ ነው። ሁሌ ይሻሻላል፤ ሁሌ አዳዲስ ነገሮች ይጨመርበታል። ስለዚህም ዘመኑን፣ ወቅቱንና አካባቢውን ለመዋጀት ሲባል ነገሮችን በአንዴ ወስኖ ወደትግበራው ለመግባት ፈታኝ ነው። ነገር ግን አሁንም መጸሐፍት ሁሌ ሀርድ ኮፒ መሆን አለበት ብለን አናስብም።›› የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ ስርዓተ ትምህርት በሰዓት፣ በቀናትና በወራት እንዲሁም በዓመታት ለውጦች የሚታይባቸው ናቸውና ለውጡን ተከትሎ መተግበር ግድ ነው። ስለዚህም አማራጮችን እያዩ መጠቀም ያስፈልጋልና ይህንን እንደሚከተሉ አስገንዝበዋል።
‹‹ትምህርትቤቶች የሚመስሉት መሪያቸውን ነው። ጥረት የታከለበት ትምህርትቤት በጥረቱ ልክ ወጥቶ ይታያል። ምንም ያልተሰራበት ደግሞ ድክመቶች ይበዙበታል›› የሚሉት ኃላፊው፤ ስለዚህም አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውጤት እንዲያመጣ የሁሉም ወገን ድጋፍ ያስፍለገዋል ሲሉ መልዕክት ያስተላልፋሉ ።በመጸሐፍቱ ላይ ያሉ ችግሮችም ሆኑ የመጸሐፍቱ አለመዳረስ የአንድ አካል ችግር ሳይሆን የሁሉም ነውና ተረባርቦ መፍታት ላይ መተኮር አለበት። በተለይም አሁን የመጽሐፍት ህትመቱ እንደአገር የሚሰራ በመሆኑ ሁሉም ክልል በፍጥነት እንዲከናወንለት ይወተውታል እንጂ በፍጥነት ስራውን የሚያጠናቅቀው ጥቂት ነው። ምክንያቱም ሁሉንም የሚያስተናግድ የህትመት ተቋም እንደአገር የለም። ስለሆነም ማህበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ መታገስ እንዳለበትም ያነሳሉ።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀድሞ ውል መያዙ ህትመቶች እየተጠናቀቁ እንዲመጡ አስችሏል። ከሌሎች ክልሎችም ተማሪዎችን ቀድመው ተጠቃሚ አድርጓል።
‹‹ ስርዓት በቁርጠኝነት የሚጠነክር ነው። አለዚያ ግን በግለሰብ ድክመት የሚገፋና የማይተገበር ከሆነ ብዙ ነገሮችን እንደአገር ያፋልሳል።›› የሚሉት ኃላፊው፤ በአዲሱ የትምህርት ስርዓት የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ፈተና ይሰጣል ተብሏል። ነገር ግን መጽሐፉ ባለመድረሱና አማራጮች ባለመስፋታቸው የተነሳ ፈተናውን የማይሰጡ ክልሎች ይፈጠራሉ። እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን ይህ ያጋጥማል የሚል ስጋት የለም። ምክንያቱም ትምህርት ሲጀመር ጀምሮ ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው። ለአብነት ቅዳሜን ለተጨማሪ ትምህርት ማዋል ተጀምሯልም። መጸሐፍቱን በሚገባ እንዲረዱትና እንዲተገብሩት ደግሞ መጸሐፍቱ ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎች ጋር ሲደርስ ሙሉ ቀን የሚማሩበትን መንገድ ይመቻቻል። ከተቻለ እሁድንም ለመጠቀም እቅድ ተይዟል።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉ ሌሎች ክልሎችም መጓዝ ከቻሉ የመጸሐፍ ጉዳይ የመማር ማስተማር ሥራውን ይፈትነዋል ተብሎ አይታሰብም።በቅርብ ቀናት ውስጥም ቀሪዎቹን መጽሃፍት ወደ ተማሪዎች ለማድረስ ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን በመጠቆም የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2015