የኮንስትራክሽን ዘርፉን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች አንዱ ዋነኛው የግብዓት እጥረት ነው:: በተለይም የሲምንቶ እጥረት እና ዋጋ መናር ዘርፉን መፈታተኑን ቀጥሏል:: ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ መሬት ላይ ወርዶ የተለወጠ ነገር አለመኖሩን የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ:: በሲሚንቶ ላይ የተከሰተው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ከማድረጉም ባሻገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል::
በቅርቡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ይህው የሲሚንቶ ጉዳይ ነው:: የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ላይ የፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናት ያቀረቡት አቶ ዘሪሁን ዘገየ እንደሚሉት የግንባታ ግብዓቶች በተለይም ለግንባታ ወሳኝ ግብዓት የሆነው የሲሚንቶ አቅርቦት ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ነው::
በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ 20 የሚሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሉ:: እነዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም የማምረት አቅማቸው የተለያየ ነው:: የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም 17 ነጥብ አንድ ሚሊየን ቶን ሲሆን ማምረት ያለባቸውን ያህል እያመረቱ አይደለም:: ወደ ስምንት ነጥብ አራት ሚሊየን ቶን አካባቢ ብቻ ነው የሚያመርቱት:: ይህ ከአቅርቦት አንጻር ስንመለከት 45 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ነው::
አቶ ዘሪሁን እንደሚሉት ፋብሪካዎቹ በሚፈለገው ልክ አለማምረታቸው ብቻ ሳይሆን ከሚመረተው የሲሚንቶ ምርት ውስጥ አራት በመቶ የሚሆነው የሚባክን ነው:: ይህ የሚባክነው ሲሚንቶ ለፕሮጀክቶች በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ ቢቻል ብዙ ገንዘብ እና ጉልበት የፈሰሰበትን ንብረት መታደግ ይቻል ነበር::
የሲሚንቶ እጥረት ጉዳይ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ጉዳይ ከመሆኑ ባሻገር በቀጣይም እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው:: በቀጣይ መንግሥት ያቀዳቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች አሉ:: በመንግሥት የተቀመጡ የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች አሉ:: መንግሥት በርካታ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ይዟል:: የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ያካሂዳል:: ግድቦች ይገነባሉ:: የሀገሪቱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማምረት ከሚጠበቅባቸው ውስጥ 45 ነጥብ 9 በመቶውን ብቻ እያመረቱ እነዚህን ፕሮጀክቶች ማሳካት የሚታሰብ አይሆንም::
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ የሲሚንቶ አቅርቦት በበርካታ ተግደሮቶች የተከበበ ነው:: ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፍተኛ ግንባታዎች ነበሩ:: የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች፣ የመንገድ ግንባታዎች፣ የቤቶች ግንባታ ነበር:: ይህ ሁሉ ግንባታ እየተካሄደ የሲሚንቶ እጥረት ያላጋጠመ መሆኑን በመጥቀስ የሲሚንቶ አቅርቦቱ በቂ እንደነበርና ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ ሀገራትም ሲላክ እንደነበር ያስታውሳሉ::
ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሲሚንቶ እየተመረተ ወደ ውጭ ሀገራት ሲላክም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን ሀገሪቱ በሲሚንቶ የወጪ ንግድ ብዙ ሚሊየን ዶላሮችንም ስታገኝ እንደነበር ያነሳሉ:: ነገር ግን ሲሚንቶ ሲመረት የነበረበት አካሄድ ትክክል አልነበረም:: ሀገሪቱ ሲሚንቶ ለማምረት ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሀገራት ታስገባለች:: ይህ አሁን መቀጠል የለበትም:: የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን በመጠቀም በሀገር ውስጥ ሲሚንቶ በስፋት ማምረት ይቻላል:: በስፋት ሀገር ውስጥ ሲሚንቶ አምርቶ በመሸጥ ኢኮኖሚውን መደገፍ ያስፈልጋል:: ካልሆነ ኢኮኖሚው ክፉኛ ይጎዳል::
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ መላክ ቀርቶ የሀገር ውስጥ ፋላጎት ለማሟላት የሚያስችል ሲሚንቶ ማምረት አልተቻለም:: ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ:: ፕሮጀክቶቹ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳያመርቱ ምክንያት ከሆኑ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ለሲምንቶ ማምረት የሚውል የጥሬ እቃ እጥረት ነው:: ከጥሬ እቃ ችግር ባሻገር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት፣ በፋብሪካዎች ብልሽት በሚያጋጥምበት ወቅት ማሽነሪዎችን መጠገን የሚችል የሰው ሀይል አለመኖር ችግር ዋነኛዎቹ ችግሮች ናቸው::
በዘርፉ ምርት እና ስርጭት ሂደት ኋላ ቀር እና ብልሹ አሰራሮች የሚስተዋልበት በመሆኑ ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው ምርቶች ወደ ቸርቻሪ ማህበራት እና ነጋዴዎች እንዳይደርስ እንቅፋት ሲሆን ይስተዋላል:: በዚህም ገበያ ውስጥ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው::
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ ፋብሪካዎች ውስጥ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ከሚፈጠሩ ችግሮች ባሻገር የአቅርቦት እጥረቱ የበለጠ እንዲከሰት ፋብሪካዎች ውስጥ ገብተው ሆነ ብለው ችግር የሚፈጥሩ አካላትም አሉ:: ገብተው የፋብሪካዎችን ቺንጋ የሚቆርጡ ጭምር አሉ:: በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ ገብተው ችግር የሚፈጥሩበት ዋነኛው ምክንያት የሲሚንቶ እጥረቱ ሲባባስ የሲሚንቶ እጥረትን እንደ ምክንያት በመጠቀም ኮንትራክተሮቹ የሲሚንቶ አቅርቦት ውል ይገባሉ፤ በውሉ መሰረት 30 በመቶ ወስደው ወደ ሲሚንቶ ንግድ ይገባሉ::
የሲሚንቶ ስርጭት ሂደቱ ላይ ባለው ኋላ ቀር እና ብልሹ አሰራር ምክንያት ምን ያህል እንደተመረተ በአግባቡ አይታወቅም የሚሉት አቶ ዘሪሁን ምን ያህል ትራንስፖርት እንደተደረገ የሚመዘግብ ማሽን የለም:: እንዲህ አይነት ማሽኖች ቢኖሩ የተመረተውን የሲሚንቶ መጠን እና ወደ ፕሮጀክቶች የደረሰውን ማወቅ ይቻላል:: ችግሮች ሲፈጠሩም ማስተካከል ይቻል ነበር::
ሀገር በቀል አማራጭ የሀይል ምንጮች ላይ አለመመርኮዝ የሲሚንቶ ንዑስ ዘርፍን ክፉኛ እየጎዱ ካሉ ችግሮች አንዱ ነው:: በሀገሪቱ ውስጥ ሰፊ የሀይል አማራጮች አሉ:: ለሲሚንቶ ፋብሪካ ሊውል የሚችል ከፍተኛ ድንጋይ ከሰል አለ:: ሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል በመጠቀም ሲሚንቶ ለማምረት የሚወጣውን የነዳጅ መጠን መቀነስ ይቻላል:: ከድንጋይ ከሰል በተጨማሪ የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ለሲምንቶ ምርት የሚወጣውን የነዳጅ ወጪን መቀነስ ይቻላል:: ይህንን መጠቀም ቢቻል የሲምንቶ ችግር ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና መጨወት የሚችል ነው ይላሉ::
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ፤ የሲምንቶ ገበያን ለማረጋጋት መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የሲሚንቶ ተመን ማውጣት ነው:: የሲሚንቶን ተመን በማውጣት ችግሩን መፍታት አልተቻለም:: የምርት እጥረት ካለ የምርት ተመን እና የትርፍ ጣሪያ በማስቀመጥ የገበያ ችግር አይፈታም:: ምክንያቱም ተመን እና የትርፍ ጣሪያ ከማስቀመጥ በፊት ምርቱ ሊኖር ይገባል:: ምርቱ ሲኖር ነው ያንን ምርት አለግባብ ሲሸጥ ከተገኘ ነው የትርፍ ህዳግ ማስቀመጥ እና በህዳጉ መሰረት እንዲሰሩ ማድረግ የሚቻለው::
ይሁንና በአሁን ወቅት የምርት ቸግር ሳይፈታ ጣሪያ መቀመጡ ችግሩን እየፈተ አይደለም:: ስለዚህ የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ የሲሚንቶ ምርት መጨመር አለበት:: በየ ክልሎቹ ለሚገኙ ማህበራት ኮታ ተሰጥቷል:: ለማህበራቱ 50 ኩንታል ኮታ ነው የተሰጠው:: 50 ኩንታል በሁለት ቀን ነው የሚጨርሱት:: 50 ኩንታሉን ወስደው ለመሸጥ ይቸገራሉ:: ኮታው አነስተኛ ስለሆነ ወደ ጥቁር ገበያ እንዳይሄድ መከልከል አልተቻለም::
ምርት እንዳይጨምር ከሚያደርጉ ችግሮች አንዱ የጸጥታ ችግር ነው:: ከለውጡ ጋር ተያይዞ ከ2010 እና 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ የሲሚንቶ እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉ ካሉ ነገሮች መካከል በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ኬላዎች መብዛት አንዱ ችግር ነው፤ የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ ሲሚንቶ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓጓዝ ኬላ ዘግቶ ያለ አግባብ ቀረጥ መጠየቅ፣ ለማሳለፍ መከልከል ይስታዋላል:: በዚህ ምክንያት ብዙ ሲሚንቶ በመንገድ ላይ በዝናብ ተበላሽቷል::
ይህ ተገቢ አይደለም የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ አሁን ላሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በየወሩ የሚሄደው የሲሚንቶ መጠን እየታወቀ፤ ሲሚንቶ እንዳያልፍ መንገድ እየዘጉ መኪናዎችን ማስቆም እና ለፕሮጀክቶች በጣም ወሳኝ የሆነው ሲሚንቶ እንዲበላሽ እና እንዲባክን ማድረግ የሀገር ሀብት ላይ መቀለድ ነው ይላሉ::
በሲሚንቶ ንኡስ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል:: የግብዓት አቅርቦት ላይ መንግሥት እገዛ የሚያደርግበትን አሰራር መዘርጋት አለበት:: ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶች በሚፈለገው ልክ የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት የግድ ነው ብለዋል::
‹‹ሲሚንቶ ማጓጓዝ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍም ሌላኛው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው›› የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ ሲሚንቶ የሚያጓጉዙ ሹፌሮች ሲሚንቶን በወቅቱ ለማጓጓዝ እንደ ቦታው ርቀት እስከ 150 ሺ ብር የሚጠጋ ገንዘብ እየጠየቁ ነው:: ሲሚንቶ በወቅቱ እንዲደርስ የሚፈልግ አካል ብሩን መክፈል አለበት:: እስከ ጋምቤላ ለመውሰድ እስከ 150 ሺ ብር እየጠየቁ ነው:: እስከ ሀዋሳ ለማድረስ ደግሞ እስከ 100 ሺ ብር እየጠየቁ ነው:: ይህ አሰራር ሲሚንቶ በተፈለገበት ሰዓት ለፕሮጀክቶች እንዳይደርስ እያደረገ ነው:: ይህንን ብልሹ አሰራር ማስተካከል የሚያስችል የአሰራር ስርዓ መዘርጋት አለበት ብለዋል::
እንደ አቶ ዘሪሁን ማብራሪያ ሲሚንቶ ችግር ለመቅረፍ ለክልሎች የተቀመጠ ኮታ አለ:: ከኮታ በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቀጠናዊ ትስስር ሚኒሰቴር ደብዳቤዎችን ይጽፋል:: ሚኒስቴሩ ደብዳቤ የሚጽፈው ለመንግሥት ፕሮጀክቶች ነው:: ይህ የሚደረገው የእሴት ሰንሰለቱን ለማሳጠር ነው:: ይህ ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ ነገር ግን በትኩረት ባለመሰራቱ ክፍተቶችን ፈጥሯል:: የሚፈለገውን ውጤትም እያስገኘ አይደለም:: እሴት ሰንሰለቱን የማሳጠር ሥራ ጠንከር ባለ መልኩ ቢሰራበት መልካም ነው:: ልዩ ትኩረትም ሊሰጠው ይገባል::
ከመንግሥት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ከባድ ችግር ውስጥ እያለፉ ያሉት የግል ፕሮጀክቶች ናቸው:: የግል ፕሮጀክቶች በስፔስፊኬሽኑ መሰረት ጣሪያ ወጥቶላቸው ቀጥታ ከፋብሪካ እንዲያገኙ ቢደረግ መሃል ላይ ያለውን እንግልትና የሰንሰለቱን ርዝመት ሊቀንስ ይችላል:: ሊዚህም የአሰራር ስርዓት ቢዘረጋለት የሲሚንቶ እጥረት በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ በጊዜያዊነት የግሉ ፕሮጀክቶች እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል::
ለዘርፉ ልማትና እድገት የሚያግዙ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ግንኙነቶችን መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ በማንሳት፤ በአሁኑ ወቅት ከውጭው ዓለም ጋር የሚኖር ጤናማ መስተጋብር ጠቃሚ በመሆኑም ትኩረት ያሻዋል:: ከውጭው ዓለም ባሻገር በሀገር ውስጥ ተናቦ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ በተለይም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ሂደት ውስጥ የክልል አስተዳደሮች ከማዕድን ማምረቻዎች ጋር ያላቸውን አሰራር ማሻሻል አለባቸው:: በአሁኑ ወቅት ለሲሚንቶ ምርት ዋና ግብዓት ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ከገበሬ ጋር በሚፈጠር ጭቅጭቅ የክልሉ አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ አልቻለም:: ከዚህም ባሻገር የጥሬ እቃ አቅርቦት ምርት አለማሳደግ ስላለ እነዚህን ችግሮች የክልል መንግሥታት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ መሥራት ከተቻለ መፍታት የሚቻል እንደሆነ አንስተዋል::
የሲሚንቶ ችግሮችን ለመቅረፍ ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች አንዱ መሰረተ ልማት መሆኑን በማንሳትም፤ ሲሚንቶ ለፋብሪካዎች ለማቅረብም ሆነ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መፍታት ተገቢ ነው:: በተለይ ጥሬ እቃዎች ካሉባቸው አካባቢዎች ወደ ፋብሪካዎች ለማቅረብ እና በቂ ምርት ማምረት እንዲቻል መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው:: በተለይም በአካባቢዎቹ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት ትኩረት የሚያሻው ተግባር ነው:: ጥሬ እቃዎች ያሉባቸው አካባቢዎች በተለይም በዝናባማ ወቅት ጥሬ እቃዎችን ለማጓጓዝ እጅግ አዳጋች በመሆናቸው የሲሚንቶ ምርት በአግባቡ እንዳይመረት ከሚያደርጉ ችግሮች አንዱ የመንገድ ችግር ነው:: በመሆኑም እነዚህን መሰረተ ልማቶች ማሟላት እና አማራጭ ግብዓቶችን በመጠቀም የሚበረታቱበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም