በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላቅ ያለ ድርሻ እየተወጣ ያለው ቡና አረንጓዴው ወርቅ እስከ መባል ደርሷል። ከምድር በታች ከሚገኙት የማዕድን ሀብቶች መካከል ደግሞ የወርቅ ማዕድን ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ክፍለ ኢኮኖሚውን ከፍ ሊያደርግ የሚችል የምድር በረከት ያላት አገር ስለመሆኗም አብዝቶ ይነገራል። በኦሮሚያ ክልል እንደ ጉጂ ዞን፣ በቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል ደግሞ ከማሺ፣ መተከልና አሶሳ ያሉ አካባቢዎች በወርቅ ሀብት ክምችታቸው በቀዳሚነት ቢጠቀሱም በመላው የአገሪቱ አካባቢዎች የወርቅ ማዕድን ሀብት እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ የወርቅ ማዕድን በቁፋሮ ከመሬት ውስጥ በማውጣት ጥቅም ላይ ማዋል ረጅም አመት ያስቆጠረ ስለመሆኑም የታሪክ ድርሳናት ምስክር ናቸው። መንግሥትም ለማዕድን ኢንዱስትሪው ልማት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከቡና ቀጥሎ ትልቅ ተስፋን ያሳደረው የወርቅ ማዕድን እጅግ ኋላቀር በሆነ የአመራረት ዘዴ መከናወኑ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈለገውን ያህል ድርሻ እንዳይኖረው እንዳደረገው እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል። ዛሬም ድረስ የወርቅ ማዕድን ልማት የሚታቀደው ባህላዊ የወርቅ አምራቾችን መሠረት በማድረግ ነው። ለአብነትም በቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል በ2014 በጀት አመት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተመረተውን የወርቅ ማዕድን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው ያመለከተውን መጥቀስ ይቻላል። እንደዘገባው ክልሉ በባህላዊ አምራቾች አማካኝነት 20 ኩንታል ወርቅ ለማምረት አቅዶ የተመረተው ግማሹ ነው። ግማሹም የተመረተው በክልሉ አምራች ከሆኑት ሦስት ዞኖች መካከል በአንዱ ብቻ ነው። ለአፈጻፀሙ ዝቅተኛ መሆን በምክንያት የተጠቀሰው በክልሉ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ ነው፡፡
በባህላዊ የወርቅ አምራቾች ላይ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ደግሞ ዘርፈብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ይነገራል። ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በግንዛቤ ማነስና በተለያየ ምክንያት ያመረቱትን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ እራሳቸውንም አገርንም ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ በመኖሪያቤታቸው ውስጥ የማስቀመጥ አዝማሚያ እንደሚስተዋልባቸው፣ ለገበያ አቅርበው ከሚያገኙት ገቢ ቆጥበው ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት አናሳ መሆን፣ በዘርፉ ላይ ለሚገኘውም የኑሮ ለውጥ ያላስገኘ ዘርፍ ሆኖ እንዲታይ ማድረጉን፣ ባህላዊውን የአመራረት ዘዴ መሠረት በማድረግ ባልደከሙበት ሥራ በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ሕገወጦችን ማበራከቱ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። በዚህ ተግዳሮት ውስጥ የሚገኘውን ወርቅ የማምረት ዘዴ በዘመናዊ አሠራር መተካት ግድ ነው።
በተለያየ ዘርፍ መጠነሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በራስ አቅም የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወቅት የማዕድን ልማቱን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ በመንግሥት በኩል የሚቻለው እየተደረገ ይገኛል።በወርቅ ማዕድን ልማት የገንዘብ አቅም፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለመሳብም በተለያየ አማራጭ መንግሥት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ለውጦችን ማምጣት እንደሚቻልም እየተገለጸ ነው፡፡
እንዲህ እየተደረገ ባለው ጥረት በግሉ ዘርፍ በተሻለ ቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም በወርቅ ማዕድን ልማት ተሰማርቶ በአገር የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ኩባንያም መፍጠር ተችሏል። ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይጠቀሳል። ኩባንያው የወርቅ ልማቱን እያከናወነ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ኦዶሻኪሶ ወረዳ ለገደንቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።ኩባንያው ቀድሞ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበረውን ድርጅት ነው የተረከበው። ኩባንያው ከመንግሥት ተረክቦ ወደ ሥራው ከገባ ጊዜ ጀምሮ በመልካምና በተግዳሮት ውስጥ ሆኖ በሥራው ይገኛል፡፡
ኩባንያው በማዕድን ልማቱ ውስጥ ስላለው ቆይታ፣ በቆይታው ለአገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ፣ የወደፊቱንም በተመለከተ ከሜድሮክ ወርቅ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ቱሉ ለማ ጋር ቆይታ አድርገናል። አቶ ቱሉ እንዳሉት እንደ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማዕድን ዘርፍ አንድ ዘርፍ በኩባንያው ውስጥ የተዋቀረ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከተደራጁት መካከል ሜድሮክ ወርቅ አንዱ ነው። ተዛማች ማዕድናትም በዚሁ ክፍል ውስጥ ይከናወናል። ወርቅና ብር ከዋና ተግባራቱ መካከል ይጠቀሳል። የወርቅ ልማቱን በዋናነት የሚያከናውነው ኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ውስጥ ቢሆንም፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ባከናወነው የወርቅ ፍለጋ ጥናት በአካባቢው ልማት ማከናወን አዋጭ መሆኑን አረጋግጧል።ወደ ምርት ሥራ ለመግባትም የፋብሪካ ተከላ ለማከናወን በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል።ሂደቱ እንደተጠናቀቀም የፋብሪካ ተከላውን ማከናወንና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶ ወደ ሥራ ለመግባት ኩባንያው ዝግጁ ነው።ባለፉት ጊዜያቶች በአካባቢው አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ባለመሆኑ ኩባንያው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል።አሁን ላይ የፀጥታው መደፍረስ እየተሻሻለ በመሆኑ በዚሁ ከቀጠለ ወይንም ዘላቂነት ካለው ኩባንያው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሚያከናውነው የወርቅ ማዕድን ልማት ሁለተኛው ፕሮጀክቱ ይሆናል።ኩባንያው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተመሳሳይ የወርቅ ፍለጋ ጥናት በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፋ ባለ የወርቅ ልማት ላይ በመሰማራት ኩባንያው ቀዳሚ ነው።በእስካሁኑ እንቅስቃሴውም በወርቅ ልማት በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ካበረከተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ልማቱን በሚያከናውንበት አካባቢ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትና ሰፊ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የሥራ ዕድል በመፍጠር ድርሻውን ተወጥቷል፡፡
ኩባንያው በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ የሚገለጽበትንም አቶ ቱሉ እንዳስረዱት፤ ዓለም አቀፍ የአሠራር ሥርዓቶችን ዘርግቶ ደረጃውን በጠበቀ የልማት ሥራ በማከናወን በተመሳሳይ ልማት ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን ተግባራት ነው በማከናወን ላይ የሚገኘው።የበለጠ ውጤታማ ለመሆንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት ያደርጋል።አዳዲስ ፕሮጀክቶችንም በመቅረጽ ሥራዎቹን ለማስፋትም እየሠራ ነው።
እራሱን ከማሳደግ ባሻገርም አነስተኛ አምራቾችንም ሆነ ባህላዊ አልሚዎችን አቅም በማሳደግ ልምዱን በማካፈል ያበረከተው አስተዋጽኦም ይኖር እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ቱሉ ‹‹ኩባንያችን ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወርቅ አልሚዎች ሞዴል ነው ማለት እችላለሁ።ባለሙያዎቻቸውን ለአቅም ግንባታ በመላክ፣ የሚፈልጉትን መረጃ በመውሰድና የአሠራር ሥርዓቶችን በማየት የሚወስዱት ነገር እንዳለ ሆኖ ጥያቄ ሲኖራቸውም የድጋፍ ምላሽ በመስጠት ትብብር ያደርግላቸዋል።
በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን እያደረገ ወይንም እየተወጣ ነው።ወደፊት ግን የበለጠ በማገዝ ኃላፊነቱን ይወጣል›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።ለወርቅ ልማቱ የሚያግዝ የተሻለ ቴክኖሎጂ ያለው በመሆኑም የማሽን እገዛ እያደረገ አነስተኛ አምራቾችን እየደገፈ መሆኑን፣ በወርቅ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ደግሞ አዳዲስ ኩባንያዎች የሚጠቅም የጥናት ሥራ አዘጋጅቶ በማቅረብ አገርን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሁሉ የቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም ይዘው በወርቅ ማዕድን ልማቱ ለመሰማራት ማዕድኑ በሚገኝባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የልማት ቦታ ወስደው ነገር ግን ወደ ሥራ ሳይገቡ ጊዜያቶችን ያስቆጠሩና አጥረው የያዙት ቦታም ለልማት ሳይውል መባከኑን በቅሬታ ይቀርባል።በዚህ ረገድ ቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል ይጠቀሳል።ክልሉ የልማት ቦታ አጥረው ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥረዋል ብሎ ካነሳቸው ኩባንያዎች መካከል ሜድሮክ አንዱ ነው።አቶ ቱሉ በዚህ ላይ ያላቸውን ምላሽ ጠይቀናቸዋል፡፡
እንደ አቶ ቱሉ ማብራሪያ እንደ ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያና ማይኒንግ ክላስተር የተነሳው ቅሬታ አይመለከተውም።ኩባንያው የልማት ቦታ ወስዶ ያላለማው የለም። በቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል ውስጥ በጥናት ሥራ ላይ ነው የቆየው። የጥናት ሥራ ሰፊ ስፍራን ያካልላል።ከብዙ ጥረት በኋላ ነው አነስተኛ በሆነ ሥፍራ ላይ ልማቱ የሚከናወነው።በተለያየ የጥናት ዘዴና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተከናወነው የጥናት ሥራ ወደ 40ሺ ኪሎሜትር ሥፍራ ነው የተሸፈነው።
በዚህ የቁፋሮ ሂደት ማዕድኑ ከተገኘ በኋላ በቤተሙከራ ውስጥ ምርምር ይከናወናል።የቤተሙከራውን ውጤት መሠረት በማድረግ ደግሞ ትንታኔ ይደረጋል።ይህ ሁሉ ሂደት የክምችት መጠኑን ለማወቅ፣ ክምችቱ ከታወቀ በኋላ ደግሞ ፋብሪካ አቋቁሞ፣ የሰው ኃይል ቅጥር ፈጽሞና መሠረተልማት አሟልቶ ልማቱን ማከናወን ለኩባንያውም ሆነ ለአገር ገቢ በማስገኘት ረገድ አዋጭ ስለመሆኑ በትንታኔው ይታያል። እንዲህ በጥናት ለይቶ ውጤት ላይ ለመድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል። ኩባንያው የረጅም ጊዜ ጥናቱን አጠናቅቆ ለፋብሪካ ተከላ ሥራ የጨረታ ሂደትን ለመወጣት በእንቅስቃሴ ላይ ሆኖ በክልሉ የፀጥታ መደፍረስ አጋጠመ።
ይሄም ጊዜ እንዲወስድና እንዲራዘም አድርጎታል። ኩባንያው ለፋብሪካ ተከላና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ድጋሚ ጨረታ ለማውጣት ተገድዷል። መዘግየቱ የተፈጠረው በምክንያት ነው። የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ከሆነ ኩባንያው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ ነው። አሁንም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
ኩባንያው በሥራ ቆይታው በተግዳሮት የሚያነሳቸውና በጥንካሬም የሚገልጻቸው ነገሮች ካሉ እንዲገልጹልን አቶ ቱሉ ላቀረብንላቸው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ፤ የወርቅ ልማት ሥራ ከከተማ ራቅ ባለ ፈታኝ የሆነ ነገር በሚያጋጥምበት ሥፍራ ነው የሚከናወነው። በተለይ ደግሞ የፀጥታ መደፍረስ ሥራን የሚያስተጓጉልና የደህንነት ሥጋት ስለሚፈጥር የበለጠ ፈታኝ ያደርገዋል። ከፀጥታ ጋር አገራዊ ችግር ሲያጋጥም የኩባንያዎች ሥራም ይጎዳል። እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ በሥራው ውስጥ መቆየቱ፣ አሁንም ለተሻለ ውጤት ለመንቀሳቀስ ጥረት መደረጉና የመላው ሠራተኛና የኩባንያው የሥራ ተነሳሽነት በጥንካሬ ይገለጻል፡፡
ኩባንያው ልማቱን በሚያከናውንበት ሥፍራም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት ላይ ስለተነሳበትም ጉዳይ አቶ ቱሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ለገደቢ ላይ ነው የተነሳው። በውጭና በአገር ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት ዝርዝር ጥናት በማካሄድ በተገኘው ውጤት ኩባንያው መጠነኛ የሆነ ማስተካከያ እንዲያደርግ ከማመላከቱ በስተቀር በጥናት ውጤቱ ኩባንያው ዓለም አቀፍ አሠራርን ወይንም ደረጃን ተከትሎ ልማቱን በማከናወን ላይ ይገኛል።መጠነኛ የሆኑትን ችግሮቹንም አስተካክሎ የምርት ሥራውን ቀጥሏል።ችግሮቹም እንደመጠጥ ውሃ የመሳሰሉ ለአካባቢ ማኅበረሰብ የመሠረተልማት ማሟላት ስለነበር ይህንንም እየፈጸመ ነው።ኩባንያቸው ዓለም አቀፍ አሠራርን በተከተለና አካባቢን በመጠበቅ አገርንና ድርጅቱን የሚጠቅም ውጤታማ ሥራ በመሥራት ኃላፊነት መወጣት የኩባንያው ራዕይ እንደሆነም አቶ ቱሉ በቆይታችን ገልጸውልናል።ኩባንያቸው በ2014 በጀት አመት ካመረተው ወርቅ የትርፍ ግብር ብቻ 910ሚሊዮን ብር መክፈሉን ጠቅሰዋል።
ኩባንያው በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲሁም ተሞክሯቸውን ይዘው ከቀረቡት መካከል አንዱ ነበር። ተሳትፎውን በተመለከተም አቶ ቱሉ እንዳስረዱት፤ ኩባንያቸው በወርቅ ማዕድን ልማት ካለው የረጀም ጊዜ ተሞክሮ እያከናወነ ስላለው ሥራና አስተዋጽኦውን በተመለከተ በማስተዋወቅ መንግሥት፣ ማህበረሰቡና ከሌላው ዓለምም የተገኘው ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ከኤክስፖው የተገኘው አንዱ ተሞክሮ ነው።በሌላ በኩልም ከፋይናንስ ተቋማት፣ ለዘርፉ ሥራ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ከሚያቀርቡት ጋር ግንኙነት መፍጠር መቻሉ ለቀጣይ የተሻለ ልማት ያግዛል። በአገር ውስጥ እንዲህ ያለ ኤክስፖ መካሄዱ ያነቃቃል። ሥራን የበለጠ ለማሳደግም ይረዳል። ከአገር ውጪ በካናዳ ደቡብ አፍሪካና በሌሎችም አገሮች የማዕድን ኤክስፖ ላይ ኩባንያው በመሳተፍ እራሱን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ የሚጠቅሙትን የሌሎችን ተሞክሮና ልምዶች ይወስዳል። በተለይም ዘመናዊ የመሥሪያ ቴክኖሎጂና በሥራ ላይ ላሉት መሣሪያዎች መለዋወጫዎችን፣ እንዲሁም ለባለሙያ የአቅም ግንባታ ለማግኘት፣ ልማቱ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተዛምዶ እንዲከናወን የሌሎችን ተሞክሮ ለመቅሰም ኤክስፖዎችን እንደመልካም አጋጣሚ ይጠቀምባቸዋል። በዚህ መልኩ በመንቀሳቀስ ድርጅቱ የበለጠ እንዲያድግ እየተሠራ መሆኑን ነው አቶ ቱሉ ያስረዱት።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም