ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? በደንብ እያነበባችሁ ነው አይደል? ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል። ማንበብ የተሻለ አቅም ለመፍጠርም ሁነኛ መፍትሄ ነው። ማንበብ ፍላጎታችሁን ለማሳካትም ወሳኝ ነው። ስለዚህም ሁልጊዜ አንባቢ መሆን አለባችሁ። ጨዋታችሁ ጭምር ከንባብ ጋር መገናኘት አለበት። ምክንያቱም ማንበብ መፀሐፍትን ብቻ ሳይሆን የምንሰራውን ሥራ ጭምር ነው። እናም ውጤታማና ጎበዝ ተማሪ መሆን ከፈለጋችሁ ጥሩ አንባቢ መሆን ይኖርባችኋል። በማንበባችሁ ተጨማሪ እውቀትን ማዳበር ትችላላችሁ።
ልጆች ማንበብ ከስልጠና ጋር ሲሆን ደግሞ የተሻለ አቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ስልጠና እየወሰደች ራሷን ያበቃችውና በጣም ጎበዝ ተማሪ የሆነችውን ልጅ ለዛሬ እንግዳ አድርጌ አቅርቤላችኋለሁ። ተማሪ ሶሊያና አባይነህ ትባላለች። በኪዳነምህረት ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በትምህርቷ ደግሞ በጣም ጎበዝ በመሆኗ መምህራኖቿ፣ ወላጆቻ፣ ጓደኞቻ ሁሉ ይወዷታል።
ሶሊያና ጎበዝ የሆነችበት ምክንያት በሁለት መልኩ እንደሆነ ታምናለች። የመጀመሪያው ትምህርቷን በአግባቡ መከታተሏና የተለያዩ ስልጠናዎች ላይ መሳተፏ ናቸው። ለአብነት ሽልማት ያገኘችበት ‹‹የአቫከስ›› ስልጠና አንዱ ነው። አቫከስ የሚባለው ስልጠና ተማሪዎች በሒሳብ ትምህርታቸው የላቁ እንዲሆኑ የሚያደርግ ስልጠና ሲሆን፤ በየክልሉ ይከናወናል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚደረገው ውድድር ላይ እርሷ ተሳታፊ ነበረችና ሁለተኛ በመውጣት ዋንጫ ተሸልማለች። በዚህ ስልጠና የሚሳተፉት ተማሪዎች በጣም በርካታ ናቸው። ከብዙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ናቸው። ስለዚህም እነርሱን ሁሉ አሸንፋ ነው ለሽልማት የበቃችው።
ሶሊያና ስልጠናውን በመውሰዷ ብዙ ተጠቅማለች። አንዱ ፈጣንና ቀልጣፋ ተማሪ እንድትሆን አስችሏታል። ሌላው ደግሞ ማባዛት፣ መደመር፣ መቀነስና ማካፈልን በቃሏ ጭምር እንድትተገብረው አድርጓታል። በጣም ከባድ ናቸው የሚባሉ ቁጥሮችን ሳይቀር በስሌቶቹ መሰረት ትሰራቸዋለች። በተለይ ደግሞ የማስተዋልና የማስታወስ ችሎታዋ ከጊዜ ወደጊዜ እንደጨመረላት ትናገራለቸ። ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ መምህራን በሚያስተምሩበት ጊዜ ቀድማቸው መልሱን መመለሷ ነው።
ልጆች ሶሊያና ታናሽ ወንድሟንም ታስጠናዋለች። በዚህም የተሻለ አቅሟን ገንብታለች። እንደውም በጋራ መስራትና ማንበብ ለበለጠ ውጤታማነት አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አላት። ይህንን እምነቷን ደግሞ ትምህርት ቤት ጭምር ትጠቀምበታለች።
ሶሊያና ትምህርቷን በምታጠናበት ጊዜ የተለየ ዘዴ ትጠቀማለች። ይህም የተለየ የሥዕል ችሎታ አላትና እርሱን በመጠቀም የማትረሳበትን መንገድ ትፈጥራለች። ሁልጊዜም ስዕሎችን ስትሰራ አብስትራክት አድርጋ ነው። ይህ ደግሞ ለመመራመር አመቺ ነውና ያስደስታታል።
ልጆች ሶልያና ምን መሆን እንደምትፈልግ ታውቃላችሁ? ምኞቷ ኢንጅነር መሆን ነው። ምክንያቷ ደግሞ በጣም ያስገርማል። ምን መሰላችሁ በመንገድ ላይ ስትሄድ ብዙ ጊዜ ጎዳና ላይ ተኝተው ሰዎችን ታያለች። የሚለብሱት ልብስም በጣም ያሳዝናታል። ብርዱን እንዴት ይቋቋሙታል የሚለውም የሁልጊዜ ጭንቀቷ ነው። እናም ይህንን መፍትሄ መስጠት ትፈልጋለችና ኢንጂነር መሆንን ተመኘችው። ምክንያቱም የዚህ ሙያ ባለቤት ስትሆን ቤት መገንባት ትችላለች። ስለዚህም ለእነዚህ ድሆች ቤት በመስራት እፎይታ ለመስጠት ታስባለች። ህልሟን ለማሳካት ደግሞ ከአሁኑ ጀምራ የሳይንስ ዘርፉ ላይ ት ኩረቷን አድርጋ ትሰራለች።
እንደ ሶሊያና እምነት ልጆች የተለየ ስጦታ አላቸው። ስጦታቸው ግን የሚዳብረው በአንድ ነገር ነው። ስኬታማ ለመሆን ጠንክረው ሲሰሩና የተባሉትን ሲያደርጉ ነው። በተለይም ወላጆቻቸውን ማክበርና ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል የሁልጊዜ ሥራቸው መሆን አለበት። የሚሰጧቸውን እድሎችም መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። ለአብነት ቤተሰብ የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ብሎ ብሩን ከፍሎ ሲያስተምራቸው እነርሱ የተሻሉ ሆነው መገኘት አ ለባቸው።
ሶልያና ለእናንተ ለልጆች የምትመክረው ነገር አላት። ይህም ፍላጎታችሁን ሊያሳካላችሁ የሚችል የትምህርት መስክ ሊኖራችሁ ይገባል የሚል ነው። ለእርሷ ሒሳብ ትምህርት የተሻለ ስኬትን እንደሚሰጣት ታምናለች። ምክንያቱም ብዙ ነገሮች መፍትሄ የሚያገኙት በሒሳብ ቀመር ነው ብላ ታስባለች። በዚያ ላይ በሁሉም ትምህርት ውጤታማ የመሆኗ ምስጢር በዚያ ላይ ትኩረቷን አድርጋ መስራቷ እንደሆነ ታምናለች። እናም ልጆችም ለቆሙለት አላማ መታገልና መትጋት አለባቸው የሚል ምክር አላት።
ሌላው ያነሳችው ነገር ብቻቸውን ምንም ነገር ማድረግ የለባቸውም የሚለውን ነው። በጋራ በመስራታቸው የማያውቁትን ያውቃሉ፣ አዲስ ነገር ለመፍጠር ይነሳሳሉ፣ ክፍተቶቻቸውን ይደፍናሉ። ስለዚህም አብሮ መስራትንና ማጥናትን ቢለማመዱት ትላለች። በተጨማሪም ተጨማሪ ትምህርት በሚማሩበት ጊዜ ሳይጨናነቁ መሆን አለበት። ምክንያቱም በመጨናነቅ ውስጥ መርሳት ይኖራል። ስለሆነም ራሳችሁን የምታሳርፉበትን ዘዴ መፍጠር ይኖርባችኋል ስትል ትመክራለች። ለምሳሌ እርሷ እስከ 11፤30 ትምህርት ቤት ውስት ትቆያለች። ከትምህርት ቤት በኋላ ግን ዘና የሚያደርጓትን ተግባራት ነው የምትፈጽመው። ስለዚህም ጨዋታ፣ ንባብና የቤት ሥራ መስራት እንደየድካማቸው መጠን መጓዝ እንዳለባቸው ታሳስባለች።
ልዩ ችሎታን አውቆ መስራት የፈጠራ ሥራ ለመስራት ወሳኝ ነገር ነው። ስለዚህም መነሻችሁ መሆን ያለበት ምን መስራት እችላለሁ የሚለውን መረዳት ነው። ከዚያ ለእርሱ የሚሆነውን ሙከራ በየጊዜው ማድረግ ይኖርባችኋል። በተለይም ከትምህርታችሁ ጋር አያይዛችሁ ለመስራት ከሞከራችሁ ውጤታማ ትሆናላችሁም ባይ ናት።
ተሸላሚ መሆን በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በመምህራንና በሌሎች አካላት ተወዳጅ ያደርጋችኋል። ጎበዝ ተማሪ የምትሆኑበትን መንገድም ይጠርግላችኋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግር ፈቺና ለአገር ጠቃሚ ሰው እንድትሆኑ በር ይከፍትላችኋል። ችግር ፈቺነታችሁ ደግሞ ከአካባቢያችሁ የሚጀምር ነውና የፈጠራ ሥራ ስትሰሩ ይህንን እያሰባችሁ አድርጉ ምክሯ ነው። ምክሯን እንደምትተገብሩት በማመን ለዛሬ የያዝነው እንቋጭ። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ሀሳብና እንግዳ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን እሁድ ኀዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም