ችግሮች ሁሉ የራሳቸው መፍትሔ አላቸው ብለው ያምናሉ። በተመሳሳይ የተለያዩ ፈተናዎች በርካታ መልካም ዕድሎችም ይዘው የሚመጡ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ። ለሚገጥማቸው ማንኛውም ችግር እርሳቸው መፍትሔ ከማፈላለግ ቦዝነው አያውቁም። ‹‹ከነገ ዛሬ የተሻለ ነው›› የሚል የሕይወት መርሆም አላቸው። ይሄ ታዲያ በሕይወትና በሥራቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል። ተወልደው ያደጉት በኢትዮጵያ ሰሜኑ ክፍል ትግራይ ነው። ወላጆቻቸው ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት እትብታቸው የተቀበረችበትን ትግራይ ተሰናብተው ከወላጆቻቸው ጋር ለመምጣት ችለዋል። ክፉ ደግ ለይተው ባላወቁበት በሶስት ዓመት የልጅነት ዕድሜያቸው የተቀበለቻቸው የኢትዮጵያ መዲናም በርካታ የሥራ በሮችን ወለል አድርጋ ከፍታላቸዋለች።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት ክፉ ደጉን ባሳለፉባት አዲስ አበባም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸውን ኮሜርስ በመባል ከሚታወቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ተመርቀዋል። ያኔ ታዲያ በንግድ ሥራ ተሰማርቼ እዚህ ቦታ እደርሳለሁ የሚል ዘመን ተሻጋሪ ዕቅድ ባይኖራቸውም ለሥራ ግን ንቁና ትጉ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ለሥራ ያላቸው ጥልቅ ፍቅር፣ ተነሳሽነትና ትጋት ዛሬም ድረስ አብሯቸው አለ። ሥራን ለነገ ብለው ማስቀመጥ እርሳቸው ጋር አይታሰብም። እንዲያውም ሥራን ለነገ ብሎ ከሚያስቀምጥ ሰው ጋር እርሳቸው ወዳጅ አይደሉም። በዚህ የተነሳም በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች የሚያጋቡት ይህንኑ ሥራ ወዳድነት እንደሆነ ከባልደረቦቻቸው ሰምተናል።
ሥራ ወዳድነት፣ ሰው አክባሪና ቅንነት መገለጫቸው የሆኑት የዛሬው የስኬት እንግዳችን “የሆሴ ትሬዲንግ ሀውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” መስራችና ባለቤት አቶ የማነ ገብረስላሴ ናቸው። አቶ የማነ፤ ለሥራ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ የማርኬቲንግ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ ማግስት ወላጆቻቸው በተሰማሩበት የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ንግድ ተሰማርተው ለሶስት ዓመታት ሠርተዋል። ወላጆቻቸውን ለማገዝ ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ንግድ ታዲያ አድጎና ተመንድጎ ዛሬ ከስኬት ማማ ላይ አድርሷቸዋል።
መነሻቸውን ከወላጆቻቸው ጋር በማድረግ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን በመሸጥ ንግድ የተለማመዱት አቶ የማነ፤ ለሥራ ካላቸው ትጋት የተነሳ ለሶስት ዓመታት ከወላጆቻቸው ጋር ሰርተዋል። ከሶስት ዓመት በኋላ ግን በግላቸው ለመነገድ ወስነው በልበ ሙሉነት ወደ ሥራ ገብተዋል። በግላቸው የጀመሩት የመጀመሪያው የንግድ ሥራቸውም የብረታ ብረት ችርቻሮ ንግድ እንደነበር ያስታውሳሉ። በችርቻሮ የተጀመረው የብረታ ብረት ንግድም ወደ አስመጪነት አድጎ ብረትን ከውጭ በማስመጣት በአገር ውስጥ የማከፋፈል ሥራ ሠርተዋል።
በብረት አስመጪነት ለተከታታይ 15 ዓመታት የሰሩት አቶ የማነ፤ በወጪ ንግዱም ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የወጪ ገቢ ንግዳቸው እያደገና እየሰፋ ሲሄድ ተጨማሪ ሥራን በማቀድ አቅጣጫቸውን ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት በማድረግ ከአራት ዓመት የግንባታ ጊዜ በኋላ የዛሬ አስር ዓመት ወደ ሥራ የገባውን ካፒታል ሆቴልን መገንባት ችለዋል። ሆቴሉ በወቅቱ ደረጃ ከተሰጣቸው ጥቂት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ተርታ አንዱና በሆቴል ኢንደስትሪው አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ የመጣ እንደነበር አስታውሰዋል።
ወጪ ገቢ ንግዱን በአግባቡ ማሳደግ የቻለው ሆሴ ትሬዲንግ ሀውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ካፒታል ሆቴልን ለመውለድ ብዙም አልተቸገረም። ሥራ ሥራን እየወለደ ያለእረፍት የሚተጋው ይህው ድርጅትም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቤት ልማት ዘርፍ ተሰማርቶ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ ይገኛል። በቤት ልማት ዘርፍ ለመሰማራታቸው ዋናው ምክንያትም በዘርፉ የሚሰሙ በርካታ ጩኸቶች ሲሆኑ፤ በተለይም እዚህም እዚያም የሚደመጡ የቤት ፈላጊዎች ሮሮ አንዱና ዋነኛው ነው።
በዘርፉ የሚሰሙ በርካታ ጩኸቶችን ያደመጡት አቶ የማነ፤ ለንግድ ሥራ ቅርብ እንደመሆናቸው ክፍተቱን በማጥናት እንዲሁም ካፒታል ሆቴልን በገነቡበት ወቅት ያገኙትን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው ወደ ሪልስቴት ግንባታ ገብተዋል። ወደ ሥራው ሲገቡ ታዲያ በጊዜና በጥራት መሥራትን መርህ አድርገው ውጤታማ እንደሚሆኑ በማመን ነበር። ውጤታማነታቸውም ለማህበረሰቡ ጥያቄ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የሪልስቴት ዘርፉን ተቀላቅለዋል።
‹‹ሥራ ላይ ያለ ሰው ሁልጊዜ ችግሮች የሚገጥሙት መሆኑን በመገንዘብ ነገር ግን ፈተናዎቹን እንዴት ማለፍ እችላለሁ ብሎ መሥራት አለበት›› የሚሉት አቶ የማነ፤ የተለያዩ ችግሮች ይዘው የሚመጡት ዕድሎችን መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህም መሰረት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕለት ዕለት የሚታዩ ችግሮችን ተቋቁመው ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ያስገነቧቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች ማስመረቅ ችለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ 22 አካባቢ 30 አባወራዎችን ማኖር የሚችል ባለ ሰባት ፎቅ የሆነውን ሮሃ ሪልስቴትን ገንብተው ማጠናቀቅ ችለዋል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ሁለተኛውንና ትልቁን የሪልስቴት ግንባታ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አስቀድመው በማጠናቀቅ ለደንበኞቻቸው እነሆ ቤታችሁ ማለት ችለዋል።
በዛሬው ዕለት ያስመረቁት የመኖሪያ መንደር ሃያት በሻሌ አካባቢ የረር ሆምስ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ሆሴ ሪልስቴት ነው። የመኖሪያ መንደሩ በ23 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን 280 አፓርትመንቶችን፣ 300 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶችን፣ 20 ቪላዎች እና 10 ሱቆችን የያዘ ነው። የግንባታ ሥራው በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ቢሆንም ግንባታው በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ እንደቻለ ያጫወቱን አቶ የማነ፤ የመኖሪያ መንደሩ አረንጓዴ ስፍራን ጨምሮ የልጆች መጫወቻ፣ የስፖርት ማዝወተሪያ፣ መኪና ማቆሚያ፣ የጉድጓድ ውሃና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
በከተማ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና እጅግ አነስተኛ የሆነውን የቤት አቅርቦት በመጠኑ ማቃለል ያስችላል በሚል በቤት ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ የማነ፤ ችግሩ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ ያምናሉ። በተለይም የግል ባለሃብቱ በግሉም ሆነ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀትና በሌሎችም አማራጮች ዘርፉን ማገዝ ከተቻለ በአገሪቱ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማስፋት እንደሚቻልም አንስተው እርሳቸውም የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ገንብቶ ከመሸጥ ባለፈም ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ለነዋሪዎች የመኖሪያ ህንጻዎችን የመገንባት ፍላጎትም አላቸው።
ሆሴ ሪልስቴት በተለያየ መጠን የገነባቸው መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችንም ማስተናገድ የሚችል ነው። ነዋሪዎቹ አቅማቸው በፈቀደው ልክ ቪላን ጨምሮ ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት፣ ባለሶስት መኝታ በተለያየ አማራጭ የቀረበውን መኖሪያ ቤት መግዛት ችለዋል። መኖሪያ በተለያዩ አማራጮችና በተመጣጣኝ ዋጋ ከመቅረባቸው ባሻገር ግንባታው ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አስቀድሞ መጠናቀቁ ቤት ፈላጊዎችን ያስደሰተ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
ለግንባታ መጓተት ዋና ምክንያት የሆነውና በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጠው የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ የማነ፤ ችግሩን ለማቃለል ግብዓቶቹ ሲገኙ አንድ ጊዜ በስፋት ይገዙ እንደነበር አስታውሰዋል። የግንባታ ዕቃዎች የቱንም ያህል ቢጨምሩ ታዲያ ደንበኞቻቸው ከተዋዋሉበት ዋጋ ተጨማሪ ክፍያ ሳይጠይቁ ቤቶቹን ገንብተው አስረክበዋል።
ማንኛውም ችግር የራሱ መፍትሔ እንዳለው የሚያምኑት አቶ የማነ፤ ለሚገጥማቸው ማንኛውም ችግር መፍትሔ ከማፈላለግ ቦዝነው አያውቁም። ‹‹ከነገ ዛሬ የተሻለ ነው›› በሚለው የሕይወት መርሃቸውም ብዙ አትርፈዋል። በተለይም መገለጫቸው የሆነው ሥራ ወዳድነታቸው የጀመሩትን ሥራ በጊዜው ከመፈጸም ባለፈ ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸዋል። ‹‹አንተ ሊደረግብህ የማትወደውን በሌሎች አታድርግ›› የሚል ዕምነት ያላቸው አቶ የማነ፤ እርሳቸው የማይገዙትን ዕቃ ለሌሎች እንደማይሸጡም አጫውተውናል። ለንግድ ቅርብ እንደመሆናቸውም ገበያው የሚፈልገው ምን እንደሆነ ጥናት በማድረግ ጊዜው የሚጠይቀውን ዕቃ አቅርቦ ገበያውን መቆጣጠር ይችላሉ።
በተለያዩ የንግድ ሥራዎች በመሰማራት ከዝቅታው ዝቅ ብለው የሚሠሩትና ለሥራ ቅድሚያ የሚሰጡት አቶ የማነ፤ በወጪ ገቢ የንግድ ሥራቸው፣ በሆቴልና በግንባታው ዘርፍ በቋሚና በጊዜያዊነት አጠቃላይ 700 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በቀጣይም በስፋት ለመሥራት ባሰቡት የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንደሆነም አጫውተውናል።
ማንኛውም ሀብት ከማህበረሰቡ ስለመገኘቱ በጽኑ የሚያምኑት አቶ የማነ፤ ‹‹ከማህበረሰቡ የተገኘውን መልሶ ለማህበረሰቡ ማዋል የግድ ነው ይላሉ›› በመሆኑም በአሁን ወቅት ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በርካታ አበርክቶዎችን ለማህበረሰቡ እያበረከቱ የሚገኙ ሲሆን ከአበርክቷቸው መካከልም ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማከናወን አንዱ ነው። በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በመልሶ ግንባታ ተሳትፎ አድርገዋል። ግንባታው የተከናወነው በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ እና ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚገኙ 35 አባወራዎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ ችለዋል።
ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋሉ ሰፋፊ ችግሮች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ የማነ፤ ዘርፉን ጠንቅቀው የሚያውቁት በመሆኑ ዳር ከመቆም ይልቅ ውስጡ ገብተው ለችግሮቹ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት ያደርጋሉ። በቀጣይም ጥረታቸውን በማጠናከር በዘርፉ ለሚገጥማቸው ችግሮቹ መፍትሔ በማፈላለግ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በስፋት ለመቀላቀል ተዘጋጅተዋል።
በተለይም በመኖሪያ አፓርትመንት ከፍታው ከ30 እስከ 32 ፎቅ የሚደርስና 360 አባዎራዎችን መያዝ የሚችል የመኖሪያ መንደር ቦሌ ላይ የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ የማነ፤ ዕቅዳቸውን ዕውን ለማድረግም አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ያጠናቀቁ ሲሆን በቅርቡም ወደ ግንባታ የሚገቡ ይሆናል። በተጨማሪም መንግሥት በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከግል ዘርፍ ጋር በጋራ የመሥራት ፕሮግራም ያለው መሆኑን በማንሳትም ከመንግሥት ጋርም በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛ ከመሆን ባለፈ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።
‹‹አንድ ሰው ብቻውን የትም አይደርስም፤ በትብብር መሥራት ግን ውጤታማ ያደርጋል›› የሚሉት አቶ የማነ፤ ከጎናቸው ሆነው የሚያግዟቸው በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸው አንስተዋል። በተለይም ለድርጅቱ ዕድገት ከእርሳቸው የበለጠ በዕውቀት፣ በሃሳብና በተለያየ መንገድ በእኔነት ስሜት እየተጉ ያሉና ድርጅቱን የሚያግዙ በርካታ ሰዎች ከጎናቸው ስለመኖራቸው ተናግረዋል። ዛሬ ለደረሱበት ስኬትም ሠራተኞቻቸውን ጨምሮ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች በሙሉ ያዋጡት ድምር ውጤት መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይም የጋራ ትብብራቸው ቀጥሎ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያላቸውን ጽኑ ዕምነት ገልጸዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም