የአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ ነው። ከእነዚህ ችግሮች መካከልም የግንባታ ግብዓቶች እጥረትና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የአቅም ውስንነት ተጠቃሾች ናቸው። የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርም በቅርቡ በግንባታው ኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ባዘጋጀው አውደ ጥናት በግንባታው ኢንዱስትሪ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት የዘርፉን ልማት ለማፋጠን ያስችላል የተባሉ ጥናታዊ ጽሁፎች እንዲቀርቡ በማድረግ ምክክር አድርጓል። በጥናታዊ ጽሁፎቹ ከተለዩት ችግሮች መካከል የግብዓት እጥረት፣ የግንባታ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አለመኖር፣ የጥራት ችግሮች እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ተጠቅሷል።
የከተማና መሠረተልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንደሚሉት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በርካታ እንቅፋቶች ያሉበት ነው። የግብዓት እጥረት፣ ብቃት ያለው እና አመለካከታቸው የተስተካከለ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በብዛት አለመኖራቸው፣ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶች በሚጠናቀቁበት ጊዜ ወጪያቸው በጣም ከፍተኛ መሆን፣ የብዙዎች የግንባታ ፕሮጀክቶች የጥራት መጓደል፤ አንዳንድ ጊዜ የተሟላ የግንባታ አገልግሎት ስለማይቀርብ የተያዙ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ሳይፈጸሙ መቅረት ተጠቃሽ ናቸው።
‹‹በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ የኮንስትራክሽን ግብዓት ነው›› የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ከሰው ኃይልና ከቴክኖሎጂ በላይ ትልቁን ወይም ደግሞ 70 በመቶ የሚሆነውን መጠን የሚይዘው ግብዓት መሆኑን አንስተዋል። ሁሉም ግንባታ ሲሚንቶ፣ ብረትና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን የሚፈልግ እንደሆነም አስረድተዋል።
እነዚህ መሰረታዊ የሚባሉ ግብዓቶች ግን በበቂ ሁኔታ በአገር ውስጥ የማይመረቱ ከመሆኑም ባሻገር ከውጭም ለማስገባት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ታንቋል። የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት የተሄደበት መንገድ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁን የደረሰበት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል ይላሉ።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግሥት የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት አንዱ መፍትሄ ነው። በዚህ ረገድ እየተሠራበት ነው። ከብረት ኢንዱስትሪ ጋር ተያይዞ ያለውን የብረት እጥረት ችግር ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ተቋማት ብረቶችን በመሰብሰብ ለብረት ፋብሪካዎች በግብዓትነት እንዲውሉ በማድረግ የግብዓት እጥረት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ኢንጂነር ወንድሙ የሚያብራሩት።
የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ መልኩ ችግሮች አሉባቸው። አንዳንዶቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የማምረት አቅማቸውን በሙሉ ባለመጠቀማቸው ምክንያት፣ አንዳንዶቹም ለማምረት በቂ ግብዓት ባለማግኘታቸው የተነሳ በቂ ምርት ለገበያ እየቀረበ አይደለም።
እንደ ኢንጂነር ወንድሙ ማብራሪያ፤ የአገር ሲሚንቶ የማምረት አቅም መድረስ ከነበረበት ደረጃ ላይ የደረሰ አይደለም። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት ከደረስንበት ደረጃ አንጻር አገሪቱ ከ50 እስከ 60 ሚሊየን ቶን የሚሆን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ላይ መድረስ ነበረባት። ጥናቶች እንደሚያሰዩት የአገሪቱ ሲሚንቶ የማምረት አቅም ገና በ17 ሚሊየን ቶን ላይ ነው ያለው። ይህ የሚያሳየው አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የሲሚንቶ አቅም በአገር ውስጥ ለማሟላት ገና ብዙ እንደሚቀራትና 25 በመቶ ላይ መሆኗን ነው። ከዚያም ውስጥ የአብዛኞቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም 45 በመቶ ላይ ነው ያለው። ስለዚህ አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የሲሚንቶ ምርት ውስጥ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚያህለውን ብቻ ማሟላት በሚያስችል ደረጃ ላይ ናት።
በአሁኑ ወቅት በማምረት ላይ ያሉት ፋብሪካዎች ችግሮቻቸው ተፈትቶ በአግባበቡ ማምረት የሚችሉበትን፤ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የሲሚንቶ እጥረትን ለመፍታት አዳጋች ነው ይላሉ።
ሌላኛው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ፍጆታ ያለው የማጠናቀቂያ እቃዎች ነው። ሁሉም ግንባታ ፕሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ የማጠናቀቂያ እቃ ይፈልጋሉ። አብዛኞቹ ማጠናቀቂያዎች ማርብል፣ ግራናይት፣ ሴራሚክ ማምረት የሚያስችል ጥሬ እቃ በአገር ውስጥ አለ። ትንሽ እሴት መጨመር ነው የሚያስፈልገው። በተለይም ለማርብል እና ግራናይት በቂ ክምችት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በበቂ ሁኔታ አለ። ያንን ክምችት አውጥቶ በአግባቡ እሴት ጨምሮ ለግንባታ የሚያስፈልገውን የጥራት ደረጃ በማምረት ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ያነሳሉ።
እንደ ኢንጂነር ወንድሙ ማብራሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ ያለውን ጥሬ እቃ በመጠቀም የአገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት እንደሚቻል ተስፋ እየታየ ነው። በቅርቡ የማዕድን ኤክስፖ ላይ በጣም ብዙ ኩባንያዎች ወደዚህ ሥራ ገብተው ወደ ማምረት እየገቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገባውን ምርት አስቀርቶ በአገር ውስጥ ምርት መተካት የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ታይቷል። ላለፉት 30 ዓመታት አንድ የሴራሚክ ፋብሪካ ብቻ የነበረው ሲሆን እሱም ታቦር ሴራሚክ ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው ረዘም ላላ ጊዜ ያገለገለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቂ አቅም የለውም። በመሆኑም በአሁን ወቅት ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ሥራ እየገቡ ነው። ዱከም ላይ አንድ የማርብል ፋብሪካ ወደ ሥራ ገብቷል። አረርቲ ላይ እንዲሁም አንድ ፋብሪካ ወደ ሥራ እየገባ ነው። ሌሎች በመገንባት ሂደት ላይ ያሉ ፋብሪካዎችም አሉ። ነገር ግን በአገሪቱ በነዚህ ሶስትና አራት የማርብል ፋብሪካዎች የማምረት አቅም የሚተካ ፍላጎት ብቻ አይደለም ያላቸው ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማምረት የሚያስችል ጥሬ እቃ 95 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥ አለ። ይህን ጥሬ እቃ ተጠቅሞ መሥራት ከተቻለ የግብዓት እጥረት ችግሮች ይፈታሉ። የግንባታ ዲዛይኖች በሚዘጋጁበት ወቅትም በአብዛኛው የአገር ውስጥ ግብዓት የሚጠቀም ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ ተይዞ እየተሰራ ነው። ሰሞኑን የተካሄደው አውደ ጥናትም የአገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን በመጠቀም የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ለማዘጋጀት የበኩሉን ሚና እንደሚያበረክት ነው ያብራሩት።
የኮንስትራክሽ ዘርፍ ግብዓት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ያለው ሌላኛው ችግር ህገ ወጥነት ነው። የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በህገወጦች እጅ በመግባት ለዘርፉ ከባድ ራስ ምታት ሲሆን እየታየ ነው የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ህገ ወጥነቱ የግብዓት እጥረቱ የፈጠረው ነው። ህገ ወጥነትን ለመፍታት እጥረቱን መፍታት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ነው። ህገ ወጦችን በማሳደድ ብቻ ህገ ወጥነትን መከላከል አይቻልም። በእርግጥ የግብይት ሰንሰለቱንም በማሳጠር አላስፈላጊ አካላትን ከመሃል በማስወጣት ህገ ወጥነትን መከላከል ይቻላል። ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ሲቻል ነው ይላሉ።
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሌላኛው እንቅፋት ሆኖ የቆየው የአገር ውስጥ የግንባታ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ጠንካራ የኮርፖሬት አደረጃጀት መፍጠር አለመቻላቸው ነው። የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ወደ ኮርፖሬት ለማሳደግ እንዲቻል የተጠና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የሚያሳይ ጥናታዊ ጹሁፍ በመድረኩ ቀርቦ ውይይትም ተደርጎበታል።
ኢንጅነር ወንድሙ በኢትዮጵያ ያሉ የግንባታ ኩባንያዎች ከሌላው ዓለም አንፃር የጥቂት ዓመታት ልምድ ያላቸው መሆናቸውን በመጠቆም፤ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ አደረጃጀታቸውን ማሻሻል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ኩባንያዎቹ በጥምረት በመሥራት እርስ በእርሳቸው የኮርፖሬት ባህል መፍጠር እንደሚገባቸው አብራርተዋል።
በዚህም የአገር ውስጥ የገበያ ድርሻቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ተናግረው መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጅነር አቶ ወንድሙ፤ ጠንካራ የግንባታ ኢንዱስትሪ ለመገንባት በማክሮ ኢኮኖሚውና ሌሎች ፖሊሲዎች በመደገፍ የዘርፉን ብቃትና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱ ጀማል በበኩላቸው፤ የኮንስትራክሽን ዘርፍን እየጎዱ ካሉት ችግሮች መካከል የግንባታ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አለመኖር አንዱ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው ኩባንያዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚያስችል አቅም አልፈጠሩም። ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳድረው በጨረታ አሸንፈው ፕሮጀክት ሊይዙ የሚችሉ ኩባንያዎች ጥቂት ናቸው። የአገር ውስጥ የግንባታ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ከተበታተነ አደረጃጃት ወጥተው ጠንካራ የኮርፖሬት አደረጃጀት መፍጠር ይገባቸዋል።
ኩባንያዎቹ ተበታትነው መሥራታቸውና ትላልቅ ግንባታዎች ላይ መሳተፍ የሚያስችል አቅም አለመገንባታቸው ደግሞ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ያብራሩት አቶ አብዱ፤ ኩባንያዎቹ ችግሩን ለመቅረፍና ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን በጥምረት መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። አውደ ጥናቱ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ልማት ፖሊሲው አቅጣጫ አገር በቀል የኮንስትራክሽን ተዋናዮች በግንባታ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መገንባት ላይ ያተኮረ እንደሆነም ገልጸዋል።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አቅርቦት ለማሳለጥ የሚያስችል ሰንሰለት አለመዘርጋቱ ሌላኛው ፈተና መሆኑም ተነስቷል። በፋብሪካዎች የሚመረቱ ግብዓቶች በሚፈለገው ጥራት እና ጊዜ ማቅረብ ከፍተኛ ችግር ይታያል። የግንባታ ምርት ሆነው ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ማጠናቀቂያ የኤሌክትሪክ፣ የኬሚካል እና ወዘተ ግብዓቶችን በሚፈለግበት ወቅት ተወዳዳሪነትን ባረጋገጠና የጥራት ደረጃዎችን በጠበቀ ሁኔታ ማግኘት ከፍተኛ ፈተና ሆኗል።
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሌላኛው ችግር ተደርጎ የቀረበው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ገጽታን የሚያሳይ የመረጃ ቋት አለመኖር ነው። ይህን ክፍተት ሊሞላ የሚችል ጥናታዊ ጽሁፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀርቧል። የኮንስትራክሽን ኢንዳስትሪ ገጽታን የሚያሳይ ዘመናዊ የመረጃ ቋት በማደራጀት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚረዱ ጥናቶችን ለማካሄድ የሚያስችል ተዓማኒነት ያለው የመረጃ ቋት ማደራጀት እንደሚያስፈልግ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱ ጀማል አብራርተዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ገጽታን የሚያሳይ መረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰበሰብ የማድረግ ሥራ በቀጣይ እንደሚሠራ ያብራሩት አቶ አብዱ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በቅድመ ግንባታ፣ በግንባታ እና በድህረ ግንባታ ጊዜ የሚጠበቅባቸውን መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉበት ስርዓት ይዘረጋል። ለፖሊሲ እና ለሌሎች ዝግጅቶች ግብዓትነት የሚውሉ የኢንዱስትሪውን መረጃ የሚሰበስብ፣ የሚያደራጅና የሚተነትን አቅም በየደረጃው መፍጠር እንዲቻል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም