ከዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ክምሩ ሲደረመስ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን በዜና ሰማች። ለዚህም ከብዙ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ፌስታል በብዛት በቆሻሻ ውስጥ መኖሩ እንደሆነ ተረዳች። እነዚህ ፌስታሎች በቆሻሻ ውስጥ ሲኖሩ ተፈጥሯዊ የሆነው ቆሻሻ ከመሬት ጋር እንዳይገናኝ እንቅፋት እንደሚሆንበትም አወቀች።
በተለይ ፌስታል በባህሪው ትንሽ ነገር ሲጫነው ቆሻሻ እንደሚያንሸራትትና በውስጡ ውሃ ሲቋጥር ደግሞ “ሜቴይን” የተሰኘ ጋዝ እንደሚፈጠርና ይህም ኦክስጂን ካገኘ እንደሚፈነዳ ተገነዘበች። ምን አልባትም የአዲስ አበባ ቆሻሻ ለመደርመሱ ይህ ሌላኛው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም አረጋገጠች።
ይህን ክስተት ተከትሎ ከአካባቢ ጋር የሚስማማና ፌስታልን ሊተካ የሚችል የጨርቅና የወረቀት ቦርሳ ማምረት እንዳለባት ከራሷ ጋር መከረች። ሆኖም ይህ ስራ መነሻ ካፒታሉ ከፍ ያለ በመሆኑና ከፌስታል ዋጋ ጋር በገበያ ተፎካካሪ መሆን ባለመቻሉ ስራውን አቆመች።
ከእጅ የሚሰሩ የጨርቅ ቦርሳዎችን ለምን አልሰራም በሚልና እዛው ቆሻሻው የተደረመሰበት አካባቢ ለሚኖሩ ሴቶች የስራ እድል አልፈጥርም ብላ በማሰብ ጨርቅን ከቆዳ ጋር በማዋሃድ ቦርሳዎችንና ዋሌቶችን የሚያመርት ድርጅት አቋቋመች፤ የቱባ ጨርቅና ቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት መስራችና ባለቤት ወጣት ቅድስት ተስፋዬ።
ተፈጥሮ የለገሷትን መልሳ በእጥፍ ለመቸር ወደኋላ አትልም። የተንከባከቧትን ያህል ደርባ ትሰጣለች። የዛኑ ያህል ደግሞ እርሷን የሚፈታተኑና የሚጎዱ ተግባራትን መፈፀም ምላሹ የከፋ እየሆነ መጥቷል። ለዚህም በደን መጨፍጨፍ ምክንያት እየተስፋፋ የመጣው በርሃማነትና ወደአየር በሚለቀቁ በካይ ጋዞች አማካኝነት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው።
በሰው ልጆች አማካኝነት ተፈጥሮን የሚጎዱ ተግባራት አሁንም እየተፈፀሙ በመሆናቸው ተፈጥሮ በሰው ልጆች ላይ የምታሳርፈው የቅጣት በትር ከእለት እለት እየጨመረ መጥቷል። ነገር ግን አሁን አሁን የሰው ልጅ በጥቂቱም ቢሆን ከጥፋቱ እየተማረ የመጣ ይመስላል። ፊቱንም ወደ ተፈጥሮ እያዞረ ነው።
በርካታ ስራ ፈጠራዎችም ተፈጥሮን መሰረት እያደረጉ መጥተዋል። በኢትዮጵያ በጥቂቱም ቢሆን በወጣቶች የተጀመሩ አንዳንድ ተፈጥሮ ተኮር የስራ ፈጠራዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። የወጣት ቅድስት ተስፋዬ የስራ ፈጠራም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
ወጣት ቅድስት ድርጅቱ ማህበረሰብ ተኮር አካባቢን፣ ማህበረሰቡንና የኢኮኖሚውን ሚዛን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ታስረዳለች። የስራ እድል መፍጠር የድርጅቱ አንደኛው አላማ ሆኖ በቅድሚያ ከስራው ጋር በተገናኘ ለሴቶችና ለወጣቶች ስልጠና ሰጥቶ ጥሬ እቃ በማቅረብ ከቤታቸው ሆነው ስራውን እንደሚያከናውኑ ትገልፃለች። ይህም ስራ ማህበረሰብ ተኮር መሆኑን እንደሚያሳይ ትጠቁማለች።
ከአካባቢ ጋር በተያያዘም ድርጅቱ የሚጠቀምባቸው ጥሬ እቃዎች 30 ከመቶ መልሶ ጥቅም ላይ ከሚውል ጨርቅና 70 ከመቶ ጥጥ ተቀላቅሎ ከሚሰራ ክር መሆኑንም ወጣት ቅድስት ተናግራ፤ ይህን ክር በመጠቀም ጨርቁን እንደሚሰሩም ነው የምታብራራው። ይህንኑ ጨርቅ እንደ ጥሬ እቃ በመጠቀምና ከቆዳ ጋር በማዋሃድ ሴቶች ከቤታቸው ሆነው ቦርሳዎችን በተለያዩ ዲዛይኖች እንደሚያመርቱ ታስረዳለች።
እያንዳንዱ ሰው ወደከባቢ አየር የሚለቀው የካርበን መጠን አለው የምትለው ወጣት ቅድስት፤ ከዚህ አንፃር ሴቶቹ ከቤታቸው ሆነው መስራታቸው በእንቅስቃሴያቸው ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የካርበን ልቀት በመቀነስ ረገድ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን ትጠቅሳለች። እነዚህ ሴቶች ትራንስፖርት ተጠቅመው ሌላ ቦታ ሄደው ቢሰሩ ወይም ጨርቁን ለማምረት ማሽን ቢጠቀሙ ኖሮ ሊያወጡት የሚችሉት የካርበን መጠን እንደሚኖርና ከቤታቸው ሆነው በእጃቸው በመስራታቸው ግን የካርበን ልቀት መጠኑን እንደሚቀንስ ታብራራለች።
የድርጅቱ ደምበኞች ከውጪ አገራት በተለይ ከቻይና የሚመጡ ቦርሳዎችን ቢጠቀሙ ቦርሳዎቹ ሲመረቱ። ተጓጉዘው ተጠቃሚው ጋር እስኪደርሱ የካርበን ልቀት ስለሚከሰትባቸው ሰዎች ሲገዟቸውም ይኸው የካርበን መጠን በቦርሳው ላይ ስለሚያርፍ በገዢዎች ላይ የራሱን የሆነ የጤና ጉዳት እንደሚያደርስም ታብራራለች።
ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ዓልሞ የተነሳው ሰዎች የካርበን መጠን ያለባቸውን ቦርሳዎች ትተው ዳግም ጥቅም ላይ በሚውሉ ጥሬ እቃዎች በእጅ የተዘጋጁ ቦርሳዎችንና ዋሌቶችን እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው። ሰዎች በቻይና አልያም በሌላ አገራት የሚመረቱ ቦርሳዎችን ገዝተው ከሚጠቀሙ የድርጅቱን ምርት ቢገዙ ወደነርሱ የሚለቀቀው ካርበን ሊጠፋላቸው እንደሚችልም ትጠቁማለች።
እንደ ዓለም የካርበን ልቀት መጠንን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድርጅቱ እያከናወነ ያለው ስራ ከፍ ያለ አስተዋጾ የሚያበረክት መሆኑን ነው ወጣት ቅድስት የምትናገረው።
ድርጅቱ ሴቶቹ በየቤታቸው ያመረቱትን ተቀብሎ በአዲስ አበባ ባለው መሸጫ መደብር ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብም ነው የምትገልፀው። ሴቶቹ ባመረቱት ልክ ክፍያ እንደሚያገኙም ነው የምትጠቅሰው። እነዚህ ምርቶች ጥቅም ከሰጡ በኋላ በቀላሉ በመሬት ውስጥ የሚበሰብሱና ከአካባቢ ጋርም ተስማሚ መሆናቸውን ወጣት ቅድስት ታስረዳለች።
ድርጅቱ ከ30 በላይ የሚሆኑ ሴቶችንና 3 ወንዶች አምራቾችን ይዞ ምርቱን እያመረተ መሆኑንና የማምረት አቅሙም ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁማ በቀን እስከ 50 ቦርሳዎችን የማምረት አቅም እንዳለውም ትጠቅሳለች። ከዚህም በላይ ማምረትና ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ተደራሽነቱን ማሳደግ እንደሚፈልግም ታክላለች።
ይሁንና የመስሪያ ቦታ እጥረት እንዳለ ወጣት ቅድስት ገልጻ ከዚህ አንፃር የሚመለከተው አካል ችግሩን መፍታት ቢችል ድርጅቱ ከዚህም በላይ የማምረት አቅም እንዲሁም ለተጨማሪ ወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ፍላጎት እንዳለው ትናገራለች።
በተጨማሪም ድርጅቱ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ መልሶ ጥቅም ላይ መዋል በሚችሉ ነገሮች ዙሪያ ለሴቶች ስልጠና የመስጠት ውጥን እንዳለውም ትገልፃለች።
በአገሪቱ ላለው ችግር እንደ አንድ ምክንያት የሚታየው ስራ አጥነት መሆኑን ድርጅቱ እንደሚያምንበት ገልጻ በቀጣይም ድርጅቱ የስራ እድል ፈጠራን እንደ ዋነኛ ተልእኮው በመያዝ እንደሚንቀሳቀስ ትጠቁማለች።
ወጣት ሄኖክ ስዩም ኢኖቬክስ ሀንድክራፍትስ የተሰኘው ከወዳደቁና ጥቅም ከማይሰጡ እቃዎች የእደ ጥበብ ውጤቶችን የሚያመርት ድርጅት መስራችና ባለቤት ሲሆን በመጀመሪያ እርሱና ባለቤቱ ቀለል ያለ ቢዝነስ ለመጀመር እንዳሰቡ ያስታውሳል። በመቀጠልም አካባቢን የማይበክሉ፣ ይልቁንም የሚጠብቁና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ሊተኩ የሚችሉ የእደ ጥበብ ውጤቶችን ወደማምረት መግባታቸውን ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የሚሰራቸው የእደ ጥበብ ውጤቶች ቤት ውስጥ ከወዳደቁና ጥቅም የማይሰጡ እቃዎች የሚሰሩ መሆኑን ወጣት ሄኖክ ይናገራል። እነዚህም ቤትን የሚያስውቡ የአበባ ማስቀመጫ፣ የፊት መስታወት፣ የእስክሪቢቶ ማስቀመጫና ሌሎችም መሆናቸውን ይጠቅሳል። እነዚህም ከአካባቢ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ፣ ጥቅም ከሰጡም በኋላ በቀላሉ የሚበሰብሱና መኖሪያ ቤትን የሚያስውቡ መሆናቸውን ያስረዳል።
በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ምርቶች ከውጪ የሚገቡትን ተመሳሳይ ምርቶች በመተካት የውጪ ምንዛሬ እንደሚያድኑም ነው ወጣት ሄኖክ የሚጠቁመው። ምርቶቹ ከወዳደቁና አካባቢን ከማይበክሉ እቃዎች የሚዘጋጁ በመሆናቸው ተጨማሪ የስራ እድል የሚፈጥሩ ስለመሆናቸውም ያብራራል። በአዲስ አበባ ብቻ ከየቤቱ 0 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም የማይፈለጉ እቃዎች በየቀኑ ከቤት እንደሚወጡና እያንዳንዱ ሰው እነዚህን የማይፈለጉ እቃዎች ጥቅም ላይ ማዋል ቢችል ለራሱም ሆነ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል ነው የሚናገረው።
ስራውን ሲጀምሩ በቀላሉ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት ሄኖክ በሂደት ምርቶቻቸውን ወደገበያ ይዘው ሲወጡ ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኙ ስለመጡ የምርት ማሳያ ቦታ መከራየቱን ይጠቁማል።
በአሁኑ ወቅት ከወዳደቁ እቃዎች የሚያመርቷቸውን ምርቶች በስፋት አጠናክረው ማምረት። አሁን ካሉት አራት ሰራተኞች ተጨማሪ የሰው ኃይሉን ማጠናከር። በስፋት ወደማምረቻ ኢንዱስትሪው መግባት እቅዳቸው መሆኑን ገልጿል።
ምርቱ በገበያ ውስጥ የገባ ቢሆንም ህብረተሰቡ ወደነዚህ ምርቶች ፊቱን እንዲያዞር ምርቶቹን ይበልጥ በማሳመር ወደገበያ ለመውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ወጣት ሄኖክ የሚያስረዳው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም