(ካለፈው የቀጠለ)
እንግዳችን፣ ደጋግመን እንደምንናገረው፣ ለሚዲያ አዲስ አይደሉም። የዚህን ጽሑፍ ቀዳሚ ክፍል ባለፈው ሳምንት ስናቀርብ ሰፋ አድርገን እንዳብራራነው ለሚዲያ ቅርብ ብቻ ሳይሆኑ፣ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ የተገደቡ ሰው አይደሉም። በመሆኑም በአገራቸው ጉዳይ በተገኘው ርእሰ ጉዳይ ላይ ገንቢ አስተያየት ከመስጠት አይቆጠቡም። የተጣመመውን ከማቃናት፤ የጎበጠውን ከማቅናት፤ የሳተውን ከማስተካከል …. ወደ ኋላ ያሉበትን ጊዜ ማስታወስ ይከብዳል። በተለይም ኢትዮጵያን በተመለከተ ተናገረው አይጠግቡም።
የታሪክ ተመራማሪና ጸሃፊው ረ/ፕ አደም ካሚል ፋሪስ በተለይ በኢትዮ-አረብ ጉዳይ ላይ ተራቅቀውበታል። ኃይማኖታዊ አስተምህሮን ዘልቀውታል፤ የዓባይና ያስከተለውን ስልጣኔ በተመለከተ ከበቂ በላይ ፈትሸውታል፤ የሰላጤው አገራትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ቃኝተዋል። ”በኢትዮ-አረቡና አካባቢው ምን ቀራቸው?” ከተባለ መልሱ ”ምንም።” ነው። በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤም ዙርያ በርካታ መጽሃፍትን አገላብጠዋል።
ባለፈው ሳምንትም ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ያላት፤ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ መስህቦች የታደለችና ተስማሚ አየር ጻባይ ያላት ውብ አገር ናት። ስለዚህም ኢትዮጵያ ላይ ተቀምጦ ተራብኩ ማለት ወንዝ ላይ ተቀምጦ ውሃ ጠማን እንደማለት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል። የዛሬውንና የመጨረሻውን ደግሞ እነሆ ይዘን ቀርበናል።
ረ/ፕ አደም ካሚል የዛሬውን ሀሳባቸውን የሚጀምሩት ባለፈው ካቆሙበት ሲሆን፣ እሱም የኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ የተጠቃሚነት መብትን የሚመለከተው ነው።
ኢትዮጵያ 85 በመቶ በላይ የአባይን ውሃ ባለቤት ነች። ይህ ተፈጥሮ የቸራትና የማንንም መብት ሳትጋፋ ከተፈጥሮ ያገኘችው መብት ነው። ይህ መብት ለዘመናት ዕውቅና ሳይሰጠው ኖሯል። እንደውም ሌሎች አገራት ይህንን ተፈጥሯዊ መብት ወስደው ዜጎቻቸውን በተሳሳተ መንገድ ሲመሩ ቆይተዋል። ፕሮፌሰር አደም እንደሚሉት የአባይን ውሃ አላግባብ መጠቀም የሚፈልጉ አገራት በሰራዊቱም ሆነ በሌላው ዜጋ ሁሉ ሲያሰርፁ የኖሩት 6ሺህ 696 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው (2ሺህ 700 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ የሚጓዘውን)ና ከዓለም በትልቅነቱ በቀዳሚነት የሚገኘው ዓባይ ለአንድ አገር ብቻ የተሰጠ፤ ለእነሱ ብቻ የተፈጠረ አድርገው ነው፤ የነበረው ስምምነት የቅኝ ግዛት ስምምነት መሆኑን ዜጎች አያውቁም።
ኢትዮጵያ ዓባይን መገደብ መብቷ ነው። ግዴታዋም ነው። ግዴታዋ የሚሆነው የህዝብ ቁጥሯ እየጨመረ ነው፤ ይህንን ህዝብ መመገብ ያስፈልጋል። ይህ ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልገዋል። ይህ አገርና ህዝቡ ከድህነት መውጣት አለበት፤ የስራ እድል መፈጠር አለበት። እንደ አገርና ህዝብ ብዙ ብዙ ነገር መሟላት አለበት። በመሆኑም ዓባይን ገድቦ መጠቀም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። የመኖር ወይም አለመኖር ጉዳይ ነው፤ ከተረጂነት የመውጣት ወይም ያለ መውጣት ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ ነው መታየት ያለበት።
በአለማችን ከ200 በላይ ግድቦች አሉ። አሜሪካ ማንን አማክራ ነው ግድብ የገነባችው? ቻይናን ማን አትገደቢ ብሏት ነበር? ጩኸቱ ምነው እኛ ላይ በዛ? ይህንን ነው እኛ መገንዘብ ያለብን። ተገንዝበንም አንድ ሆነን በመቆም መስራት ያለብን።
ኢትዮጵያ ግድቡን ስትጀምር ሁሉን ነገር ግልፅ አድርጋ ነው። ምንም ነገር ምስጢር ያደረገችው ነገር የለም። አስረድታ ነው፤ አስገንዝባ ነው። ምንም አይነት ጉዳት በግብፅም ሆነ ሌሎች ላይ እንደማይፈጥር አብራርታለች። በጋራ እንስራ ብላለች። ብዙ ርቀት ሄዳለች። አገራት ይህንን ቢያወቁም ኢትዮጵያን ለመተባበር ግን አይፈልጉም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ሲሆን፣ እሱም ከድህነትና ተረጅነት አዙሪት ውስጥ እንዳንወጣ በመፈለጉ ምክንያት ነው።
ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም 10ኛ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ታላቁ ግድባችን ገና ከጅምሩ፣ የመሰረት ድንጋይ መጣሉን (መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም) ተከትሎ በሁለት ፈረቃ የሚሰሩ 8ሺህ 500 ሰራተኞችን በማሳተፍ ወደ ስራ የተገባበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ወደ ፊትም ምን ያህል የስራ እድል ለዜጎች እንደሚፈጥር ከወዲሁ የሚያመለክት ነው።
ኢትዮጵያ እያደገ ያለውን የህዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የተሻለ ህይወት እንዲመራ ለማስቻል አባይንም ሆነ ሌሎችን ወንዞች ገድባ ለልማት ማዋል አለባት። ይህ ደግሞ መብቷ ነው።
ኢትዮጵያም ይህንን የልማት ጥያቄዋን በተለያዩ መንገዶች ለአረቡ አለም ማስተማር አለባት። ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት ግድቡን የማደናቀፍ አቅማቸው የተሟጠጠ ቢሆንም ህዝቡ እውነቱን ይገነዘብ ዘንድ ማገዝ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የተጠቀመችው፤ ወደፊትም የምትጠቀመው የራሷን ሀብት እንጂ የሌላ የማንም አለመሆኑን ማስተማር ያስፈልጋል። ነገም ሌላ ግድብ ይኖረናልና ለዛም ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ይሆናል።
በጥናቶች እንደ ተረጋገጠው ከግድቡ የሚገኘውን ኃይል ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ የሚተርፈውን ማለትም 2ሺህ ሜጋዋት ያህሉን ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል። የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር ሲሆን፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው። የግድቡ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች 13 ሲሆኑ፤ እያንዳንዱ ዩኒት የሚያመነጨው የኃይል መጠን ከ375 እስከ 400 ሜጋዋት ነው። ይህ ለእኛ፣ ለኢትዮጵያዊያን የብልፅግና ተስፋ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ አገራት የኤሌትሪክ ኃይል ግዚ ለመፈፀም ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ። ለአብነት ኬንያን ብንወስድ።
የኢትዮ- ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ጀምሯል። የኃይል ማስተላለፍ የጀመረው የኢትዮ – ኬኒያ ባለ 500 ኪል ቮልት የማስተላለፊያ መስመር በዓመት እስከ 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የማስገባት አቅም ያለው ነው።
እንዲሁም ከኬንያ አልፎ ከታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ላሉት አገራት እስከ 2ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ የጀመረች ሲሆን፥ ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።
በዚህም ባለፈው ዓመት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶሊር ገቢ መገኘቱን መንግስት አስታውቋል። ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ነው።
የኢትዮጵያ ዕድገት የሚያሳስባቸው አካላት በአገር ውስጥ የተለያዩ ግጭቶችንና ሁከቶችን በመፍጠር አገሪቱ ከተያያዘችው የልማት አቅጣጫ ለማደናቀፍ ሲጥሩ ቆይተዋል። ባለፉት ሁለት አመታት የተካሄደውም ጦርነት የዚሁ አንዱ መገለጫ ነው።
የኢትዮጵያ አካሄድ ያሰጋቸውና ነገ ከነገ ወዲያ ከራሷ አልፋ ሌሎችንም ታነሳሳለች የሚል ስጋት የገባቸው አገራትና ተቋማት ኢትዮጵያ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በየዕለቱ የኢትዮጵያ ስም በማንሳት የአገሪቱ ገጽታ እንዲበላሽ በብዙ ሲደክሙ ሰንብተዋል። በዲፕሎማሲው ዘርፍም ኢትዮጵያ ከዓለም ማህበረሰብ የተገለለች እንድትሆን ያለመታከት ሰርተዋል።
አንዳንዶቹም ኢትዮጵያ እንደአገር እንዳትቀጥል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ፈርሳለች፤ ሀገር ሆና አትቀጥልም እስከ ማለት ደርሰዋል። ሆኖም ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ተጋድሎ የአገሪቱን ህልውና ማስቀጠል ችለዋል። ፈረሰች የተባለችው አገር ስንዴ አምርታ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ ችላለች። የአባይን ግድብ ግንባታና ኃይል አመንጭታ ለጎረቤት አገራት ብርሀን መሆን ችለላች።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት ሲያደርጉት የነበረውን ጦርነት አቁመው ወደ ሰላም መምጣታቸው ያልተዋጠላቸው አገራትና ግለሰቦች ይህንን የሰላም ሂደት ለማጠልሽት የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም። የላም ሂደቱ ተደናቅፎ ጦርነቱ መልሶ እንዲያገረሽና ኢትዮጵያ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የሰብአዊ እርዳታ አልገባም፤ የኤሌትሪክ፤ ቴሌና የባንክ አገልግሎት አልተጀመረም፤ ወዘተ የሚሉ አፍራሽ ትርክቶችን በመፍጠር የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ዘመቻ የጀመሩ አካላትን እየተመለከትን ነው። አንዳንዶቹም አፍ አውጥተው ለሰላም ያላቸውን ጥላቻ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ሰላም የሚመጣው በጦርነት እንደሆነ ያለሀፍረት የሚናገሩ የዘመኑ ጉደኞችን ሰምተናል። ሆኖም ኢትዮጵያውያን የሰላምን አስፈላጊነት በአግባቡ የሚረዱ ህዝቦች በመሆናቸው ላለፉት ሁለት አመታት ያነሱትን ነፍጥ ዘቅዝቀው ፊታቸውን ወደ ሰላም መልሰዋል።
ከወዲሁም የተስፋ ወጋገን መውጣት ጀምሯል። መከላከያ ትግራይ ውስጥ ገብቶ ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት መውሰድ ጀምሯል። የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ፤ ለተቸገሩ ወገኖች ያለውን ምግብ ሲያካፍል አይተናል። ይህ የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ዕድገት ለሚመኙ ወገኖች ያስደስታል። በተቃራኒው የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚሹ አካላት ንዴትን የሚፈጥር ነው። ስለዚህም ይህንን ሰላም ማጨናገፍና ጦርነቱን ማስቀጠል እነዚህ አካላት ለነገ የሚተውት ተግባር አይደለም።
ባጠቃላይ፣ ኢትዮያ ጠላቶቿ ብዙ ናቸው። በመሆኑም ይህ ግንዛቤ ተይዞ ነው መሰራት ያለበት። ኢትዮጵያ ከወዲሁ ካልተያዘች አትቻልም፤ ሌሎች ስራዎችንም ልቀጥል ትላለች የሚሉት ነገር ሊታሰብበት ይገባል። ኤምባሲዎቻችን አረቢኛ በሚችሉ ሰዎች መሞላት አለበት። ህዝቡ የአገር ጉዳይን አጀንዳው ማድረግ አለበት። በሁለቱም ሀይማኖቶች ተሰሚነት ስላለን እሱን ተጠቅመን መስራት ያስፈልጋል።
አንድነታችንን ካልጠበቅን፤ እየተደገሰልን ያለውን ከወዲሁ ተረድተን ለመፍትሄው ካልሰራን በኋላ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ማወቅ አስፈላጊ ነው። በመከላከያ በኩል አስፈላጊው ዝግጅትና ጥንካሬ ሊኖር የግድ ነው።
በዲፕሎማሲው መስክም የተጀመሩ ጥረቶች ወደ ኋላ መመለስ የለባቸውም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ ስም በብዙ ጎድፏል። ስለዚህም በዲፕሎማሲው ዘርፍም ሆነ በሚዲያው በኩል ይህንን ገጽታ ወደ ነበረበት መመለስ ይጠይቃል።
ሚዲያዎቻቸው በየቀኑ በተለያዩ ቋንቋዎች በእኛ ላይ የሚያካሂዱትን ዘመቻ በመቀልበስ መታገል ይገባል። የሰላም ስምምነቱ ስለተፈረመ ብቻ የውጭው አለም በአንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን ይቆማል ማለት ዘበት ነው። ስለዚህም ስለ ኢትዮጵያ በየቀኑ ማሰብ፤ መስራትና ውጤት ማምጣት የሁላችንም ግዴታ ሊሆን ይገባል በማለት ረ/ፕ አደም ካሚል ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም