ያለእድሜዋ ሽበት አበቀለች እንጂ ፊቷን ላየ ገና ወጣት እንደሆነች ታስታውቃለች። ፈገግታ ደግሞ መለያዋ ነው ። ቁመተ መለሎና መልከመልካም ናት። ይኸው መልኳና ቁመቷ ጠቅሟት የትምህርት ማስረጃዋን አክላበት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ለዓመታት ሠርታለች። በዚሁ ሥራዋም በርካታ ሀገራትን ተዘዋውራ የማየት ዕድሉ ገጥሟታል።
የበረራ አስተናጋጅነት ሥራ ሁሌም ጽድትና እምር ብሎ መገኘትን ይጠይቃል። ለእርሷም ማማርና መጽዳት የዘወትር ተግባር ነበር። ሁሌም ፊቷን አስውባና ፀጉሯን ተሠርታ በሥራ ገበታዋ ላይ ትገኛለች። በተለይ ደግሞ ፊቷን ለማስዋብ ሁሌም የተለያዩ መዋቢያዎችን(ሜካፖችን)ትጠቀማለች። የተለያዩ ሀገራት ስለምትሄድ መዋቢያዎቹን ለማግኘት ብዙ አትቸገርም።
በጊዜ ሂደት ግን የምትጠቀማቸው የፊት መዋቢያዎች ፊቷን ጤና ይነሱ ጀመር። በቃ መዋቢያው አልተስማማትም። በፊቷ ቆዳ ላይም ቀስ በቀስ የጎንዮሽ ጉዳት አመጣ። በዚህ ጊዜ ታዲያ አንድ ውሳኔ መወሰን ነበረባት። መዋቢያ ቅባቶችን መጠቀሙን ማቆም። ያለማመንታት ወሰነች።
መዋቢያዎቹን መጠቀም ካቆመች በኋላ አንድ ሀሳብ መጣላት። በተፈጥሮ መንገድ ወደ ተዘጋጁ የመዋቢያ ውጤቶች መዞር። መጀመሪያ በተፈጥሯዊ መንገድ ስለሚዘጋጁ የመዋቢያ ውጤቶች ማንበብና መመራመር ያዘች። በመቀጠል እነዚህ ምርቶች በተጠና መልኩ ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ቢውሉ በርካታ የጤና በረከት እንዲሚኖራቸው ተረዳች።
በዚሁ መንገድ የፊት ማስዋቢያ ምርቶችን በራሷ አዘጋጅታ ራሷ ላይ ሞከረች። ውጤቱ አስደናቂ መሆኑንና የፊቷ ቆዳ ለውጥ ማምጣቱን ተገነዘበች። ለሁሉም ችግር መፍትሔ አለውና እርሷም በዚህ መንገድ የገጠማትን ችግር ፈታች። ችግሯን ከፈታች በኋላ ግን በቃኝ ብላ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ከዚህ ይልቅ ለራሷ ያመጣችው መፍትሔ ለሌሎችም ቢተርፍ ብላ አሰበች።
የተፈጥሮ መዋቢያ ውጤቶችን ማምረት የሙሉ ጊዜ ሥራዋ ለማድረግ ወሰነች። የበረራ አስተናጋጅነት ሥራዋንም በመተው ሙሉ ትኩረቷን በዚሁ ሥራ ላይ አደረገች። እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ በመዋቢያ ውጤቶችን እያመረተች ለገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች። የተፈጥሮ ምርት ጥቅምን የተረዱ ጥቂት የማይባሉ ወይዛዝርቶችም ምርቶቿን እየተጠቀሙላት ነው። የእኔት ኧርዝ የተፈጥሮ መዋቢያ ውጤቶች ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሜሮን ነጋ።
ወይዘሮ ሜሮን ነጋ ከዚህ በፊት እየገዛች ስትጠቀምባቸው የነበሩ የፊትና የቆዳ መጠበቂያ ውጤቶች በቆዳዋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረው እንደነበር ታስታውሳለች። ብዙ ጊዜ ምርቶቹን ገዝታ ስትጠቀም በውስጣቸው ያለውን ይዘት እንደማታይም ነው የምትናገረው። በዚህም ምክንያት ቆም ብላ በማሰብ ወደ ተፈጥሯዊ የመዋቢያ ምርቶች ፊቷን ለማዞር እንደወሰነች ታስረዳለች።
እንደውም ‹‹እነዚህን ከተፈጥሮ እፅዋት የሚመረቱ የመዋቢያ ውጤቶችን በራሴ እቤት ውስጥ በማምረት ለምን አልጠቀምም?›› በሚል ማዘጋጀት እንደጀመረችም ነው ወይዘሮ ሜሮን የምትገልፀው። ምርቶቹን አዘጋጅታ መጠቀም እንደጀመረች በፊቷ ቆዳ ላይ ፈጣን ለውጥ እንዳየችም ታስረዳለች። ያየቸውን ለውጥ ተከትሎም ራሷን በስልጠናና በተለያዩ ነገሮች ማብቃት እንዳለባት መረዳቷንም ትገልፃለች።
በዚሁ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ለማግኝት ስልጠና መውሰዷንና የፊት ሳሙናዎች በተፈጥሯዊ መንገድ እንዴት እንደሚዘጋጁ ስልጠናዎችን ከወሰደች በኋላ ሀገር ውስጥ ባሉ ምርቶች በተለይ ደግሞ ቀርከሃን በመጠቀም የፊት ሳሙናዎችን እ.ኤ.አ በ2018 ማምረት እንደጀመረች ታስረዳለች። በሂደት ደግሞ ከካሮት፣ ከአቮካዶና ከቁልቋል እፅዋቶች ፈሳሽ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ማምረት እንደቻለች ትናገራለች።
በተለይ ደግሞ የሞሪንጋ እፅዋት በሀገሪቱ እንደልብ የሚገኝ በመሆኑ ይህን እፅዋት በመጠቀም ተጨማሪ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ይዛ ወደ ገበያ ብቅ እንዳለችም ነው ወይዘሮ ሜሮን የምትናገረው። ምርቶቿን ይዛ ወደ ገበያ ከወጣች በኋላ ጥሩ ውጤት እያየች እንደምትገኝም ትገልፃለች። ሆኖም ምርቶቹ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ረጅም ጊዜ እንደፈጀባት ነው የምትናገረው። በዚህም ተፈጥሯዊ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የተረዱ ምርቶቿን እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ትጠቁማለች።
ወይዘሮ ሜሮን እንደምትለው ተፈጥሯዊ የመዋቢያ ምርቶቹ የሚመረቱት እዚሁ አዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሲሆን ቦሌ መድኃኒዓለም ሞል ድርጅቱ ባለው የራሱ መደብር ውስጥ ለገበያ ይቀርባሉ። ባምቢስ ሱፐርማርኬት ውስጥም ምርቶቹ ይሸጣሉ። በእንጦጦ ፓርክ ውስጥም እንዲሁ ምርቱ ለገበያ ይቀርባል። ከዚህ ባለፈም በተለያዩ ቦታዎችም ምርቶቹ ይከፋፈላሉ።
ምርቶቹን ለማምረት የተለያዩ ማሽኖች ሥራ ላይ ቢውሉም የመጨረሻዎቹ ምርቶች ተፈጥሯዊ ሂደታቸውን ተከትለው መመረት ስለሚገባቸው በአብዛኛው የሚመረቱት በእጅ ነው። በዚህ አመራረት ሂደትም 12 ሰዎች ይሳተፋሉ። በአሁኑ ግዜም ሦስት ዓይነት ሳሙናዎች ይመረታሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከቀርክሃ የሚዘጋጅ ሳሙና ሲሆን ወደቻርኮል እንዲቀየር ከተደረገ በኋላ በውስጡ አቮካዶና የሱፍ ዘይት ገብቶበት ይመረታል። ይህም በፊት ላይ ለሚወጣ ብጉርና ማዲያት ለማጥፋት ከፍተኛ ጥቅም አለው። በቆዳ ላይ የሚገኙ አላስፈላጊ ቆሻሻዎችንም ያጠፋል። ሁለተኛው ከሞሪንጋ እፅዋት የሚመረተው የሳሙና አይነት ሲሆን ይህም ለአደጋ ተጋላጭና ስስ የፊት ቆዳ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳል። ሶስተኛው የሳሙና አይነት ደግሞ ከቀረፋ የሚዘጋጀው ሲሆን ለብጉርና በተለይ ሁለት አይነት የፊት ቆዳ ላለው ሰው የሚያገለግል ነው ።
በሌላ በኩል ከቁልቋል የሚዘጋጀው ቅባት በፀሐይ የተጎዳ ቆዳን ወዝ ለመስጠት ይረዳል። ያለዕድሜ የሚከሰተውን የቆዳ ማርጀትንና መጨማደድን ይከላከላል። በውስጡም ቫይታሚን ኤ፣ኢ፣ኬ እና ኦሜጋ ስሪ ንጥረ ነገሮችን ይዟል።
ሌላው ከአቮካዶ ዘይትና ከባህር ዛፍ ቅጠል የሚሠራው የቅባት አይነት ሲሆን ለፀጉርና ለጀርባና ወገብ መታሻ ያገለግላል። በተለይ ደግሞ ፎሮፎርንና ራስ ማሳከክን ይከላከላል። የራስ ቅልንም ያርሳል። ይህም ጥሩ ፀጉር እንዲኖርና እንዲያድግ ያደርጋል።
የአቮካዶና ሮዝመሪ ቅባትም ድርጅቱ የሚያመርት ሲሆን በተለይ ፀጉር እንዲለሰልስና እንዲነቃቃ ያደርጋል። የፀጉር መሰነጣጠቅንና መድረቅንም ይቀንሳል። ከካሮት የሚዘጋጀው ቅባትም ለፊት ጥቅም ላይ መዋል ይችላል። በውስጡም ቫይታሚን ኤ እና ኢ አለው። ይህም የቆዳን መለጠጥ ይበልጥ ይጨምራል።
በጥቅሉ እነዚህ ቅባቶች በተፈጥሯዊ መንገድ የፊት ቆዳ በቀላሉ እንዳይጎዳ ያደርጋሉ። የቅባት ምርቶቹ በአብዛኛው የሚዘጋጁት ከሚበላ የምግብ ዘይትና ከእፅዋት በመሆኑ በውስጣቸውም ምንም አይነት ጎጂ ኬሚካል ስለማይኖር ጥቅም ላይ ሲውሉ በቆዳ ላይ የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትሉም።
ለዚህም ምርቶቹ ፍተሻ ተደርጎባቸው በቆዳ ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትሉ በኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ባለስልጣን ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።
ወይዘሮ ሜሮን እንደምትገልፀው ምርቶቹ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች የሚቀርቡ ሲሆን በቀጣይ ይበልጥ በማስተዋወቅ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ውጥን አለ። በተለይ ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ሰዎች በተፈጥሯዊ መንገድ የተዘጋጁ የመዋቢያ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ መፍጠር በመሆኑ ይህን አጠናክሮ ከሠራ በኋላ ምርቶቹን በብዛት ወደ ገበያ በማውጣት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል።
በአሁኑ ግዜ ድርጅቱ የገበያ ውጣውረድ እንዳለ ሆኖ በቀን እያንዳንዱን ምርቱን ከሺ በላይ ያመርታል። በፊት ገበያውን ሲቀላቀል ከገጠመው ችግር አንፃር በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። የምርቶቹ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው ምርቶቹን በስፋት ወደ ገበያ እያስገባም ነው።
ከዚህ በመነሳትም በቀጣይ ድርጅቱ ምርቶቹን በስፋት በማስተዋወቅና ምርቶቹንም በመጨመር በስፋት ወደገበያው የመግባት እቅድ አለው። ዓለም አቀፍ ገበያዎችንም ማፈላለግና ምርቶቹን ለውጪ ገበያ የማቅረብ ሃሳብም ይዟል።
‹‹ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በተለይ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ገና ብዙ አልተሠራም የምትለው›› ወይዘሮ ሜሮን እያንዳንዱ ወጣት ምን ልሥራ የሚለውን ነገር ከራሱ መጀመር እንዳለበት ትጠቁማለች። እርሷም የራሷን ቢዝነስ የጀመረችው ከገጠማት ችግር በመነሳት መሆኑንም ትጠቅሳለች።
ከዚህ አንፃር ወጣቶች ለራሳቸው ጊዜ ሰጥተው ምን መሥራት እንዳለባቸው ማጤንና ከምንም በላይ ደግሞ የሚወዱትን ነገር በማወቅ በዚህ ረገድ የጎደለውን በመለየት ወደቢዝነስ ቢገቡ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ታመለክታለች። ያልተሠራበት ነገር ምን እንደሆነ ማወቅና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ክፍተት መለየት ከእነርሱ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ትጠቁማለች።
ወይዘሮ ሜሮን ወጣቶች የወደዱትን ነገር አንዴ ካወቁ፣ በሀገሪቱ ያለውን ችግርና ክፍተት ከተገነዘቡና ያልተሠራበትን የቢዝነስ መስክ ከለዩ ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሥራ ሙሉ ከሰጡ ትርፍ በኋላ ላይ የሚመጣ ነገር ነው ትላለች። ከምን በላይ ከባዶ ተነስቶ ማምረት ወጣቶች ራሳቸውን ከመለወጥ በዘለለ በሀገሪቷ ኢኮኖሚም ላይ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ትናገራለች።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሳተፍ የገጠማት ችግር የመሥሪያ ቦታ መሆኑን ጠቁማ፤ችግሩ ቢፈታ ከዚህም በላይ የማምረት አቅም እንዳላትም ነው ወይዘሮ ሜሮን የምትገልፀው። ይህ ችግር በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም አዲስ ቢዝነስ ሲጀምሩ የሚገጥማቸው በመሆኑ በተለይ መንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ሊሠራ ይገባል ትላለች።
በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ማኅበረሰቡ ቦታ እንዲሰጥና ገዝቶ የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብር መልዕክቷን ታስተላልፋለች። መንግሥትም እንዲህ አይነቱን ሥራ የሚሠሩ ወጣቶችን ማበረታታትና መደገፍ እንዳለበት ትጠቁማለች። በተለይ ጊዜው የሥራ ፈጣሪዎች በመሆኑ መንግሥት ለዚህ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባም ነው የምትገልፀው።
እኛም ብዙ ወጣቶች ከወይዘሮ ሜሮን ብዙ ነገር ይማራሉ ብለን እናምናለን። በተለይ ደግሞ ከሚወዱት ነገርና ከሚገጥም ችግር በመነሳት እንዴት ቢዝነስ መጀመር እንደሚቻል ወይዘሮ ሜሮን ጥሩ ምሳሌ ልትሆን የምትችል ወጣት በመሆኗ ሌሎች ወጣቶችም የእርሷን ተሞክሮ በመውሰድ የራሳቸውን ቢዝነስ ሊጀምሩ እንደሚችሉ እንገምታለን።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም