ፕሮፌሰር አለማየሁ ኃይለማርያም ታዋቂውን ጸሐፊ ኒኮላስ ክሪስቶፍ (ማርች 2004)ን ጠቅሰው፤ “አፍሪካ በቀውስ የምትታመስ አህጉር ነች፡፡ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ድህነት እየጨመረ የመጣባት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመስ፣ የዘር ማጥፋት ሰብአዊ ወንጀሎች የሚፈጸሙባት እና አስደንጋጭ የሆነ የሙስና ዘረፋ የሚካሄድባት ብቸኛዋ አህጉር ሆናለች፡፡ አፍሪካ ተስፋ ይኖራታልን?“ ያሉትን ጨምሮ ስለ አፍሪካ ብዙ ተብሏል።
በስልጣን ጥም፣ በመፈንቅለ መንግስት ወዘተም ብዙ የተጻፈባት ናት። ይሁን እንጂ፣ ይህ ሁሉ የመስራች አባቶች ራእይም ሆነ ፍላጎት አልነበረም። የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች ፍላጎት የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ላይ ሲናገሩት እንደነበረው የቀደሙ የፓንአፍሪካኒስት አባቶች ራዕይ አንድነት፤ እድገት፤ ብልፅግና፤ ሰላም፤ አፍሪካዊ ወንድማማችነት … ነበር። ቀስ እያልን ዝርዝሩን እንመለከተዋለን። አሁን ወደ መስራች አባቶች እንሂድ።
ነጮቹ እንደሚመኩባቸውም ሆነ እንደሚኮሩባቸው፣ ”ፋውንዲንግ ፋዘርስ” በማለት እንደሚያንቆለጳጵሷቸው ሁሉ፣ ዘመናዊት አፍሪካም መስራች አባቶች አሏት። ለዛውም ከአፍሪካም አልፈው ለአለም የተረፉ። ይሁን እንጂ፣ እንደ እነሱ እኛ አፍሪካዊያን ስናንቆለጳጵሳቸው አይታይም፣ አይሰማም።
ለነገሩ ይህ መፈንቅለ መንግስት የሚሉት ሾተላይ እየደጋገመ በሚመታት አፍሪካ እንዴት ተደርጎ ነው የአሁኑ የበፊቱን የሚያደንቀው፣ እንዴትስ ሆኖ ነው የበፊቱ በአሁኑ የሚወደደው?
የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች፣ አፍሪካን በተመለከተ ሙቱ ቢሏቸው የማይሞቱ፣ ተረሱ ቢሏቸው የማይረሱ … ናቸው። ምን ያህል ከጊዜው የቀደሙ እንደሆኑ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ሲያነሷቸው የነበሩ ሀሳቦች፣ ሲያራምዷቸው የቆዩት አቋሞቻቸው፣ ሲያከናውኗቸው የነበሩት ተግባራቶቻቸው ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ እንጂ የእለት እንጀራ ብቻ አልነበሩም። በመሆኑም፣ ከትውልድ ትውልድ ሲነሱ፣ ሲወደሱና ሲናፈቁም ጭምር ይስተዋላል። ለዚህ አንድ ጥሩ ማሳያ ቢኖር ሰሞኑን እዚህ አዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ነው።
በኢትዮጵያ አነሳሽነትና አዘጋጅነት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ለሶስት ቀናት የቆየውና በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ዋና አላማ የፓንአፍሪካኒዝምን እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስተዋወቅና አብሮነትን ማጠናከር ሲሆን፤ በዓለምአቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አፍሪካ እንደ አህጉር ያላትን ሚና እንዲጠነክር ለወጣቶች ማሳየት፤ እንዲሁም፣ በአፍሪካ አገራት መካከል የጋራ ትስስርን ማጎልበት ሌላኛው የጉባኤው ዓላማ እንደነበር ሲገለፅ መሰንበቱ ይታወቃል። በአፍሪካ ትብብርና ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደ ተደረገባቸውም ታውቋል። በሕይወት የሌሉ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ታጋዮች (መስራች አባቶች) ቤተሰቦች በጉባኤው ላይ የታደሙ ሲሆን፤ ለታጋዮቹም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ሽልማት ተበረክቶላቸዋል።
በዚሁ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ ላይ ከተከናወኑት ተግባራት አንዱ 17 ለሚሆኑ ቀደምት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ለሕብረቱ ምስረታ እና መጠናከር ላበረከቱት ወደርየለሽ አስተዋፅኦ በቤተሰቦቻቸው በኩል እውቅና መስጠት ሲሆን፤ ከ17ቱ አንዱና ቀዳሚው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለጠነከረችና ከተፅእኖ ነፃ ለሆነች አፍሪካ ነፃነት እና አንድነት ላበረከቱት አስተዋፆ የተሰጠው እውቅናና ሽልማት ይገኝበታል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በጉባኤው ማጠቃለያ መርሐ-ግብር ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የመልእክታቸውም ጭማቂ፤
• አፍሪካውያን ወጣቶች የወደፊቷ አለም መሪዎች ናችሁ፤
• በአህጉሪቱ የሚታዩትን የአስተዳደር ችግሮችን የመፍቻ መንገዶችን በመጠቀም፤ እንዲሁም፣ የስራ አጥነት ችግርን በፈጠራ ስራዎች በመሸፈን አፍሪካን ከግብዓት አቅራቢነት ወደ ከፍተኛ አምራችነት ማሳደግ አለባችሁ፤
• አፍሪካውያን ወጣቶች ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የዕድገት ራዕዮችን በመቅረጽና ለስኬቱ በመስራት የአህጉሪቱን ዕድገት በማረጋገጥ የዓለምን እይታ መቀየር አለባችሁ፤
• የቀድሞ አባቶችን ራዕይ አውቃችሁ ተግባራዊ ለማድረግ መጣር አለባችሁ። የሚል ሲሆን፤ ከዚህ የምንረዳው አቢይ ጉዳይ ቢኖር፣ የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች ራዕይ ምን ያህል ዘመን ተሻጋሪ እንደ ነበር ነው፣ ምንም እንኳን በየጊዜው በስልጣን ጥመኞች እየተደነቃቀፈ ሳንካ ቢገጥመውም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ርቆ የተቀበረ አለመሆኑንና የመሳሰሉትን ያሳየም ነው።
“በ2030 ከአጠቃላዩ የዓለም ወጣት ከፍተኛ ድርሻ የምትይዘው አፍሪካ ትሆናለች። አፍሪካ አሁን የሆነችውን ብቻ ሳይሆን፣ ያላትን ዐቅም አገናዝበው ልትሆን የሚገባትን የሚቀምሩላት ወጣት ልጆቿ ናቸው። ፓንአፍሪካዊነትን በአመራራቸው የገለጡ የትናንት ፈር ቀዳጆች ለዚህ ጽኑ መሠረትን ጥለዋል። አህጉራችሁ ያላትን ዐቅም ተጠቅማ ለሁሉም ዜጎቿ ምቹ እንድትሆን ማስቻል በተለይም ከአፍሪካውያን ወጣት መሪዎች ይጠበቃል። ስለዚህም የተጣለባችሁን ተስፋ እውን እንድታደርጉት አደራ እላለሁ።” የሚለው ይገኝበታል።
በአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ የቀደሞ መሪዎች በፓንአፍሪካኒዝም ዙሪያ የነበራቸው አመለካከትና ሲያራምዱት የነበረው አፍሪካዊ ፍልስፍና ምን እንደ ነበር የተለያዩ አገራት የቀድሞ መሪዎች (የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ሙላቱ ተሾመን፣ የጋና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ድራማኒ ማሀማን ጨምሮ) ለወጣቶቹ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል።
በልምድ ማካፈሉ ወቅት የተለያዩ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን፣ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ዘመን ያሳለፈችውን ፈታኝ ጊዜ በማለፍ አሁን ባሉ ተስፋ እና እድሎች መጠቀም የሚያስፈልግ መሆኑ፤ የአፍሪካ ባህላዊ እሴቶችን በማዳበር የራሳችን ሞራልና ማንነት መጠበቅ እንደሚገባ፤ ዛሬ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጯቸው ሀሳቦች አፍሪካዊ ማንነታችን እያሳጡን በመሆኑ፤ የዚህ ዘመን ወጣቶች ይንን በመከላከል እና በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው፤ አፍሪካውያን በሰላም ግንበታ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እና የተፈጥሮ ሀብትን በበቂ መጠን መጠቀም የነገ ትውልድ መሪዎች አቅም መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑ፤ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን መፈለግ እንደሚገባ (በአምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል)፤ በተለይም የወጣቶችን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቀም በፈጠራ የዳበረች አህጉርን ለመገንባት አፍሪካዊያን ዛሬ ነገ ሳይሉ መነሳት ያለባቸው ስለመሆኑ፣ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።
አፍሪካውያን በህብረት ሲቆሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነታቸው መጠን እንደሚጨምር እና በዚህ ረገድ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ሰፊ እንቅስቃሴ መደረግ እንዳለበት፤ ለሁሉም የፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሀሳብን በሚገባ ማዳበር እንደሚገባ (በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብረሃ ”የፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ እና ታሪክ” የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል)፤ በኢትዮጵያ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው ይህ አይነቱ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤን የመሰሉ ጉባኤዎች በስፋት ሊካሄዱ እንደሚገባ፤ በአፍሪካ ለሚፈጠሩ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ አፍሪካውያን ችግሮችን የሚፈቱበት መንገድ የራሳቸው አገር በቀል እውቀት ሊሆን እንደሚገባ ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉር የምትወከልበት ስርዓት በድጋሚ መታየት ያለበት መሆኑም በጉባኤው ላይ ከተነሱት መካከል እንደ ነበሩም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለመሆኑ ”የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች” ስንል ምን ማለታችን ነው?
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ”የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች” የሚለው የአፍሪካ ወንድማማችነትን የሚያቀነቅነው ንቅናቄ (ፓንአፍሪካኒዝም) መቀንቀን ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ያለውን፤ በተለይም አፍሪካ ከነጭ አገዛዝ ነፃ እየወጣች ከመጣችበት 1950ዎቹ እና 60ዎቹ ወዲህ ያለውን የጊዜ ሰሌዳና የነፃነት እንቅስቃሴን የሚመለከት ሲሆን፤ የዚህ ወቅት የለውጥ ጠንሳሾችና አራማጆችን የሚመለከት አገላለፅ ነው።
ጠንሳሾቹና አራማጆቹ፣ ”የዘመናዊት አፍሪካ መስራች” ያልናቸው አባቶች በመሰረቱት በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በተካሄደው ከመላው አፍሪካ ለተወጣጡ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ እውቅና የተጣቸው ሲሆን፤ እነሱም፡-
አፄ ኃይለሥስላሴ ኢትዮጵያ፣ ንጉስ ሀሰን ሁለተኛ /ሞሮኮ፣ ጁሊየስ ኒሬሬ /ታንዛኒያ፣ አህመድ ሴኩቱሬ /ጊኒ፣ ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር /ሴኔጋል፣ ጆሞ ኬንያታ /ኬንያ፣ ጋማል አብድል ናስር/ ግብፅ፣ ክዋሜ ንኩርማህ /ጋና፣ ኬኔት ዴቪድ ካውንዳ /ዛምቢያ፣ ኔልሰን ማንዴላ /ደቡብ አፍሪካ፣ ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ /ዚምባብዌ፣ አቡበከር ታፋዋ ባሌዋ /ናይጀሪያ፣ ሞዲቦ ኬታ /ማሊ፣ ዊሊያም ቲዩብማን /ላይቤሪያ፣ አህመድ ቤን ቤላ /አልጀሪያ፣ ፍሌክሲ ሆፎየት ቦይኚ /አይቮሪኮስት፣ ሳሞራ ማሼል /ሞዛምቢክ ናቸው።
የሕብረቱ ወቅታዊ ቁመና እና የመስራች
አባቶች ራእይ
የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ሲሆኑ በእሳቸው የሀላፊነት ዘመን በርካታ ችግሮች ተከስተዋል። እየተከሰቱም ነው።
ችግሮቹን ለመፍታትም ህብረቱ ከቀድሞው በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶቹን፣ በተለይም ”አይፈቱም”፣ ”የአፍሪካ ሕብረት አይቻለውም” የተባለውን ግጭት (ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሲካሔድ የቆየው ውይይትና የተደረሰበት የተኩስ ማቆምና የሰላም ስምምንት ልብ ይሏል) የመሸምገሉ ሁኔታ ተሳክቶላቸው እየተመሰገኑና እየተደነቁ ይገኛሉ። እሳቸው ብቻ አይደሉም፣ አይሰራም የተባለው የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄም ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ በብዙዎች ዘንድ የሀሳቡ አመጭ የሆኑቱ መስራች አባቶች እየተደነቁና ሀሳባቸውም መሬት እየወረደ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆም የቀድሞዎቹን ”የዘመናዊት አፍሪካ መስራች አባቶች”ን በመተካቱና ችግሮችን መፍታቱ ላይ በርትተው በመስራት ምትክነታቸውን እያስመዘገቡ ባሉት ውጤት እያሳዩ ነው።
እንደ አገር ሲታይም፣ ኢትዮጵያ ሁሉ ነገሯን፣ ልክ እንደ ቀድሞዎቹ ኢትዮጵያዊያን መስራች አባቶች ሁሉ፣ ዋና ዋና ችግሮችን በተመለከተ መፍትሄው መምጣት ያለበት ከራሳችን ከአፍሪካዊያን ነው። የአፍሪካዊያንም ችግር መፈታት ያለበት በራሳቸው ነው እንጂ የማንም ጣልቃ ገብነት ሊኖር አይገባም በሚል አቋም ፀንታ ለሕብረቱ ግርማ ሞገስ እየሆነች ትገኛለች።
ከሕዳሴው ግድብ ጀምሮ አሁን ለገጠማት ከፍተኛ ችግር በሙሉ መታየትም ሆነ መዳኘት ያለበት በአፍሪካ ህብረት በኩል ብቻ ነው በሚለው አቋማ በመፅናትና ተፅእኖም በመፍጠር ጉዳዮች ወደ አፍሪካ ሕብረት እያመሩ፤ በዛው በኩልም መፍትሄ እያገኙ፤ ሂደትና የአለምን ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
አጀንዳ 2063 እንደ አንድ የአፍሪካ መስፈንጠሪያ ቦርድ
የአፍሪካ ሕብረት የ50 ዓመት የአንድነት፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተገለጸበት አጀንዳ 2063 ዋነኛ ግብ አፍሪካን በመሰረተ ልማት በማሰተሳሰር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት መመስረትን፤ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገውን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህንን ተግባራዊ በማድረጉም ሆነ የመስራች አባቶችን ራዕይ እውን እንዲሆን በማስቻሉ በኩልም ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች ትገኛለች።
በመጨረሻም
አፍሪካ ምንም ሳታጣ ምንም የሌላት አህጉር ሆና ሺዎች አመታትን አሳልፋለች። በኢምፔሪያሊዝም ተደቁሳለች። በእጅ አዙርም ሆነ በግልፅ ቅኝ አገዛዝ እየተገላበጠች አራለች። ተዘርፋለች። አፍሪካዊያን እርስ በእርስ ይጋደሉ ዘንድ በተዘጋጁ ወጥመዶች ውስጥ በመግባት ተጨራርሰዋል ። በ”አፍሪካን መቀራመት” (የጀርመኑ ጉባኤ) የእንስሳ ፍልስፍና ተውጠው በአገራቸው ባይተዋር ሆነው ኑረዋል። ተቆጥሮ አያልቅም። የፓንአፍሪካኒዝም መነሻ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ መድረሻውም ከዚህ ሁሉ ቆሻሻ ፅድት ያለች አፍሪካን ማየት ነው። ይህ ደግሞ፣ በአሁኑና መጪዎቹ ትውልዶች እውን እንደ’ሚሆን የአሁኑ የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ጥሩ ማሳያ ነውና ያበረታታል፤ ሊበረታታም ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም