የግል ትምህርት ቤቶች በአገሪቱ ያላቸው የትምህርት አገልግሎት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ማንም አይክድም። በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የመንግስቱን ትምህርት ቤት ባስናቀ መልኩ ጥሩ መሻሻሎችን ያመጡ ናቸው። ተወዳዳሪነትን ከመፍጠርም አኳያ የማይተካ ሚናን ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ ለድሃው ማህበረሰብ የሚቀመሱ አልሆኑም። ምክንያቱም የሚጠይቁት የትምህርት ቤት ክፍያ በቀላሉ የሚገባበት አይደለም።
አንዳንዴ ሲታዩ ደግሞ የንግድ ተቋማት እንጂ አገልጋይ ተቋም ጭምር አይመስሉም። ሰበብ እየፈለጉ ማህበረሰቡን እየበዘበዙት እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። የሶፍት፤ የተጨማሪ መጸሐፍት፤ የሳሙና ምናምን እያሉ ድሃ እንዳያስተምር ያደርጉታል። የወላጆች ገቢ ባላደገበት ሁኔታ በየጊዜው የተማሪዎችን ክፍያ ማናር ደግሞ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን አገርንም ለችግር የሚዳርግ እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። እናም ይህንን ታሳቢ በማድረግም እንደመንግስት የተለያዩ ውሳኔዎች እየተላለፉ ይገኛሉ።
አንዱ ከክፍያ ውጪ መጽሐፍትን አሳትሞ መሸጥ አይቻልም የሚለው ሲሆን፤ እየተሰማ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ወረቀት ጨምሯል በሚል በክፍል ደረጃ በተለየ መልኩ የመጸሐፍት ዋጋ ሲጨምሩ ብዙዎች ላይ ይስተዋላል። መነሻችን የሆኑት ቅሬታ አቅራቢ አቶ መብራቱ ከበደ ይህንን ያረጋግጣሉ። ለቅድመ አንደኛ ክፍል ተማሪ እስከ ሁለት ሺህ ብር እየተጠየቁ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ቀጥለውም የግል ትምህርት ቤቶች በየጊዜው በሚጠይቁት ክፍያ ምክንያት ወጪያቸው በተለያየ መልኩ እየጨመረባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ለአብነትም ከትምህርት ቤት ክፍያው በተጨማሪ የመመዝገቢያ በሚል 1500 ብር መክፈላቸው፤ የሳይኒታይዘር፣ የልብስ ሳሙና ወዘተ በሚል የተጠየቁት ገንዘብ ለአንድ ተማሪ ብቻ ሳይሆን ለአራትና አምስት ተማሪ ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ። ነገሮችን እያደረጉ ያሉት ልጃቸውን በምንም መልኩ ላለማሳፈር ብለው እንደሆነ ይገልጻሉ። ሕጉ ቢወጣም ተግባራዊ እየሆነ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር እየተፈተኑ እንደሆነም የሚናገሩት አቶ መብራቱ፤ በተለይም አዲሱ የትምህርት ዘመን የጀመረ በመሆኑ ምላሽ ሳያገኙ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እንደተገደዱና ይህም እንደሚያንገበግባቸው ያነሳሉ። ልጃቸውን የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ቅዱስ ሚካኤል ትምህርት ቤቶች የሚባል ሲሆን፤ እርሳቸው ልጃቸውን ቢልኩም አንዳንድ ወላጆች ግን በሁለት ምክንያት ልጆቻቸውን እስካሁን እንዳላስገቡ ያስረዳሉ። የመጀመሪያው የመክፈል አቅም ስለሌላቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ሕጉን ስላላከበራችሁ አናደርግም ያሉ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
እንደ ትምህርት ቢሮ ተቋማቱ መጽሐፍት በራሳቸው አሳትመው መሸጥ አይችሉም። ተገቢ ያልሆኑና እነርሱ ሊያደርጓቸው የማይችሉ ነገሮች ላይም ክፍያዎችንም መጠየቅ የለባቸውም ተብሏል። ነገር ግን ከሕግ ውጪ ሆነው ይህንን እያደረጉ ይገኛሉ። የተጠየቁትን ጭምር በአግባቡ ለመመለስ ዝግጁ አይደሉም። ስለሆነም መንግስት ይህንን አይቶ መፍትሄ በአፋጣኝ ሊሰጠን ይገባል ይላሉ።
ድርጊታቸው የትምህርት ተቋማት የሚመሩበት ሕግ የለም እንዴ? ትምህርት በንግድ ሕግ ሊዳኝ አይገባም ወይ ያስብላል። ምክንያቱም ትምህርት ለሁሉም ዜጋ መብት መሆን እንዳለበት ቢታመንም እነርሱ ግን በአንዱ ሲገደቡ በሌላው እንድናወጣና ልጆቻችንን እንዳናስተምር እያደረጉ ናቸው። በአቅም ማነሥ ምክንያት ልጆችን ቤት እንዲቀሩ የማድረግ ሥራ እየሰሩም ይገኛሉ። እናም ለሕጉ እውን መሆን መንግስትና የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦች ጭምር መታገል እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።
የግል ትምህርት ቤቶች ላይ እየታዬ ያለው የተጋነነ ወርሃዊ ክፍያ ሀይ ሊባል ያልቻለው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አንድ መላ ባለማበጀቱ ብቻ እንዳልሆነ የሚያነሱት አቶ መብራቱ፤ በትምህርት ተቋማቱ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችም መመርመር አለባቸው ይላሉ። በምክንያትነት የሚጠቅሱትም መፍትሄዎች ቶሎ ያለመምጣታቸውና ለጥቆማ ተብለው የተቀመጡ ስልኮች አለመስራታቸውን ነው። ስለዚህም መማርም ሆነ ልጅ ማሥተማር ቅንጦት እንዳይሆን በታማኝነት ሁሉም ማገልገል እንዳለበት ያሳስባሉ።
ችግሩ ከግል ትምህርት ቤቶች አንጻር በሁሉም ክልሎች ያለና የሚተገበር ቢሆንም እንደ አዲስ አበባ አልጎላምና ይህንን የሚመለከተውን አካል ምን እየሰራ እንደሆነ ለማነጋገር ችለናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮረና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ ጀምሮ ነው ይህንን ተግባር ማከናወኑን የቀጠለው። በዚህም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የገጽ ለገጽ የትምህርት አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውንም በተለያዩ መንገዶች እንዲያከናውኑ እና የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያም ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲሆን አዟል።
መመሪያውን ተግባራዊ ያላደረጉ የግል ትምህርት ቤቶችም እንደነበሩ ታይቷል። እናም ባለስልጣኑ ይህንን ተከታትሎ የግል ትምህርት ቤቶቹን በመለየት መጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ከዚያም እንቢኝ ሲሉ ለአንድ ዓመት የእውቅና ፍቃዳቸውን በማገድ ውሳኔ አስተላልፎ ተግብሮታል። ሆኖም ዛሬም ከድርጊታቸው ሲቆጠቡ አይታይም። እናም ይህንን አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ውይይት አድርጓል። በወቅቱም የ2015 የትምህርት ዘመንን በተመለከተ በ2014 ዓ.ም ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ምንም ዓይንት ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ መግባባት ላይ ደርሷል።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሕይወት ጉግሳ እንደተናገሩት፤ ላለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ጭማሪ ሳያደርጉ የቆዩ ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል እና ከወላጅ ጋር በሚያደርጉት መግባባት መሰረት ጭማሪ ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን ከወላጅ ፍላጎት ውጪ ምንም ሊያደርጉ አይገባቸውም። ይህንን ጥሶ የተገኘ ግን እርምጃ ይወሰድበታል። በመመሪያው መሠረት ያላግባብ ያስከፈሉ ካሉም ገንዘብ እንዲመልሱ ይደረጋል።
ችግሮቹን ለመፍታት ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ በመጀመሪያ ዙር ምልከታ 26 ችግሩ ለታየባቸው ተቋማት የተገኙ ሲሆን፤ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል። ሁለተኛ ዙር ደብዳቤ የሚሰጣቸውም አሉ። እስከአሁን 50ና 60 ይሆናሉ። በተጨማሪም ለሦስተኛ ዙር 520 የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና የባለስልጣኑ ባለሙያዎች በጋራ ምልከታ እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ ችግሩ እስከሚቆም ድረስም የሚቀጥል እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ማንኛውም ችግር አስተማሪ የሚሆነው እርምጃ በመውሰድ ሳይሆን ችግሮችን በመመካከር በመፍታት እንደሆነ የሚገልጹት ወይዘሮ ሕይወት፤ ትምህርት የሚመራበትን ሕግ መረዳት ላይ ከተቋማቱ ጋር በተደጋጋሚ እየመከርንበት ነው። ትምህርትቤቶች ጥሰትን መሰረት አድርገው ለመተማመን መሞከር እንደሌለባቸውም በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ ሞክረናል። ይሁንና ብዙዎቹ ከዚህ ችግራቸው መላቀቅ አልቻሉም። ያለን ላይ መደመርን መተማመኛ ማድረግን ይፈራሉ። ስለሆነም ባለስልጣኑ ይህ እስኪታረም ድረስ የሚሰራ ይሆናልም ይላሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ የግል ትምህርት ቤቶቹ ጉዳይ ያልተገባ ክፍያ ችግር ብቻ የሚታይበት አይደለም። በመማር ማስተማሩ ላይ ጭምር ጥላ የሚያጠሉ ተግባራትን ሲፈጽሙ ይስተዋላል የሚሉት ወይዘሮ ሕይወት፤ በትምህርት ተቋማቱ ከተገኙት የአሰራር ችግሮች ውስጥ አንደኛው ከሌሎች አገራት የተቀዱ ሥርዓተ ትምህርትን በአገሪቱ የሥርዓተ ትምህርት መመዘኛ መስፈርቶች ሳይጠና ተማሪዎች እንዲጠቀሙ ማድረጋቸው ነው። ይህም ተማሪዎች ከአገር ውስጥ ባህል፣ ሥነ ሥርዓትና ጥበብ ጋር እንዲራራቁ በማድረግ በውጭ አገራት ባህል የሚማረክ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ሁለተኛው ተማሪዎች በተገቢው ሰዓት መማር ያለባቸውን የትምህርት አይነት በሌሎች የትምህርት አይነቶችን እንዲተኩ ማድረግ ሲሆን፤ ይህም ተማሪዎች የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ተደራራቢ የትምህርት ጫና እንዲፈጠርባቸውና ተማሪዎች ለጭንቀት እንዲዳረጉ ይጋብዛል። ሌላውና ሦስተኛው ችግራቸው ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በአገር ውስጥ ቋንቋ መማር ያለባቸውን ትምህርቶች በእንግሊዝኛ እንዲማሩ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ በአገሪቷ በአፍ ቋንቋ የመማር መብትን የሚፃረር ነው። ስለዚህም ተቋማቱ ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
እንደ ወይዘሮ ሕይወት ገለፃ፤ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች አገራቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲደግፉና አገራዊ አስተሳሰብ ይዘው እንዲያድጉ ተደርጎ የተቀረፀ ነው። በዚህም በርካታ ምሁራንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። እነዚህ አካላት ያልተሳተፉበትን የትምህርት ሥርዓት ለተማሪዎች ማስተማር አገርን ከማሳደግ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። በተጨማሪም ልጆች ከፍ እያሉ ሲሄዱ ትምህርት እንዲጠሉ ከማድረግ ባለፈ ልጆች ተገቢውን የአገር ፍቅር እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል። እናም ተቋማቱ ይህንን አስበው መስራት ይኖርባቸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕግን በሚጥሱ የትምህርት ተቋማት ችግር ምክንያት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ውስጥ አራት አይነት ትምህርት ቤቶች ተፈጥረዋል የሚሉት ሥራ አስኪያጇ፤ አንደኛው በመንግስት ስርዓተ ትምህርት ጥራት ያለው ትምህርት እየሰጠ ያለው ሲሆን፤ ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ በስነምግባር የታነጸ ተማሪ እየፈጠረ ያለው ነው። ሁለተኛው በመንግስት ስርዓተ ትምህርት መሰረት የሚያስተምሩ ነገር ግን ከፍተኛ የወላጅ ጫና ያለባቸው ናቸው። ወላጆች የመንግስት ስርዓተ ትምህርትን የምታስተምሩ ከሆነ እናንተ ጋር ምን እንሰራለን ስለሚሏቸው ወጣ ገባ ለማለት የተገደዱ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
ሦስተኛው የመንግስትንም የራሳቸውንም የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ለቁጥጥር ሲኬድባቸው ፖሊሲውን እየተገበሩ ለማስመሰል የሚያቀርቡ። እነዚህ የአፍ መፍቻ ቋንቋን እንደ ቋንቋ ብቻ የሚያስተምሩ ናቸውም። በአራተኛ ደረጃ የሚነሱት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የመንግስትን ስርዓተ ትምህርት የማያስተምሩ ናቸው። ከሌላ አገር የመጣ ስርዓተ ትምህርትን ይተገብራሉ። ከ1500 በላይ ተቋማት በዚህ አይነት አተገባበር ውስጥ ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። እናም ይህንን ለማስተካከል ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃልና ወላጆች እያገዙን ካልሄዱ ሁኔታው ከባድ ይሆናል ብለዋል።
አጋዥ መጸሐፍት በሚል እያዘጋጁ ተማሪዎችን ለጭንቀት መዳረግም ትምህርት ቤቶቹ ከፈቃድ ውጪ የሚሰሯቸው ተግባራት እንደሆኑ የሚያነሱት ወይዘሮ ሕይወት፤ አጋዥ መጸሐፍ መዘጋጀት ካለበት ትምህርት ቢሮ ባሉት ባለሙያዎች አማካኝነት የሚያደርገው ይሆናል እንጂ ያልተገመገመና ለተማሪዎች የማይመጥን መጸሐፍ ማዘጋጀት አይፈቀድም። እዚህ ላይ መግባባት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ባለሥልጣኑ ጠንካራ የትምህርት ክትትልና ጥራት ፍተሻ እያደረገ የሚቀጥል ሲሆን፤ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ግን ሊያግዙት ይገባል። በእኩል ደረጃ ችግሮችን ለመለወጥ መትጋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ሀሳብ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቀደም ብሎ በተደረገው አጭር ምልከታ 12 የግል ትምህርት ቤቶች ጭማሪን አስመልክቶ የወጣውን መመሪያ ጥሰው ተገኝተዋል። በዚህም ከመመሪያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለወላጅ መልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል። መልሰናል ያሉ ትምህርትቤቶች ተገኝተዋል። ይሁንና አሁንም የክፍያንና መሰል ጭማሪዎችን ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ አሁንም ጥቆማ እየደረሰ ነው። በዚህም ዛሬ ድረስ ተቋማቱን ለመየት ተከታታይ ሥራ በተዋቀረው ቡድን አማካኝነት እየተከናወነ ይገኛል። ለዚህ ያግዝ ዘንድ ደግሞ እንደ ባለስልጣኑ ለክትትል የሚላኩ ባለሙያዎች አቅጣጫ ተሰጥቶዋቸው እንዲሄዱ ተደርጓል። ባለሙያዎቹ የተከፈለበትን ደረሰኝ ጭምር ተመልክተው እንዲያረጋግጡ የሚያደርግ የመገምገሚያ ሰነድም ተዘጋጅቷል። ከተቻለም በየአንዳንዱ ተቋም የተወሰኑ ወላጆችን ማነጋገር የሚቻልበት አሠራር ተዘርግቷል። የተለያዩ ጥቆማዎች በመኖራቸው አሠራሩን እንደሚያሻሽለው ይታመናል።
ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ ክፍያ ውጪ በየትኛውም መልኩ ክፍያ ማስከፈል አይችሉም፣ አንድ የትምህርት ተቋም ፍቃድ የተሰጠው ለማስተማር እንጂ፤ መጽሐፍም ሆነ ደብተር ለመሸጥ አይደለም። ስለዚህም ከተሰጠው ፍቃድ ውጪ የተንቀሳቀሰ ተቋም ከተገኘ ርምጃ ይወሰድበታል። ምክንያቱም ዓላማው የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም፣ የኑሮ ውድነት ችግርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መስራትን ያስቀደመ ነውና ይህንን የሚያደሩጉ አካላትን እንደማይታገሱም ያነሳሉ።
የትምህርት ጉዳይ የንግድ ጉዳይ አይደለም፤ የአገር መገንባት ጉዳይ እንጂ። ስለዚህም ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሕጉን አክብረው መስራት ይኖርባቸዋልና እንደ ዜጋና እንደ አገር አስበው ቢሰሩ መልካም ነው እያልን ለዛሬ የያዝነውን በዚህ አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም