በዚህ ዘመን ሙዚቃቸው እንደ አዲስ እየተደመ ጠላቸው ካሉ አንጋፋ ድምጻውያን መካከል አንዱ አንጋፋው አርቲስት መልካሙ ተበጀ ነው። በየትኛውም የምሽት ክበብ ቢገባ የመልካሙን ሙዚቃ አንድ ወጣት ድምጻዊ ሲጫወተው መስማት የተለመደ ነው። ሚክስ እየተደረጉ እንደ አዲስ ከተዘፈኑ ሙዚቃዎች ውስጥም የመልካሙን ሙዚቃ በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ነው። የፊልም ማጀቢያ ሆነው በድጋሚ የተዘፈኑ ሙዚቃዎችም አሉት።
መልካሙ ተበጀ የተወለደው በ1938 ዓ.ም በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ክብረ መንግስት በሚባል ቦታ ነው። መልካሙ የሙዚቃ ፍቅር ከህጻንነቱ ጀምሮ አብሮት ያደገ ነው። ቤተሰቦቹ ለስራ ጉዳይ ወደ ሃረር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወሩ አብሮ በመምጣት በአምሃ ደስታ ትምህርት ቤት ይገባል። በትምህርት ቤት የተለያዩ በዓላት በተለይም በወላጆች ቀን በሚያደርገው ተሳትፎ የሙዚቃ ስሜቱ ከእሱ አልፎ በተመልካች ዘንድ እየጎላ በመሄድ ነሐሴ 15 ቀን 1957 ዓ.ም በብሄራዊ ቲአትር የታዳጊ ኦርኬስትራ (ዳዊት ኦርኬስትራ) በድምጻዊነት ተቀጠረ። ከዚያን በኋላ በርካታ ስራዎችን የተጫወተ ሲሆን ራሱ ከመዝፈኑ ባለፈ ለብዙ ድምጻውያንም ዜማ እና ግጥምም ሰጥቷል።
ራሱ መልካሙ ከተጫወታቸው ዜማዎች መካከልም አብዛኞቹ የራሱ ድርሰቶች ናቸው። ከነዚህም መካከል «የሲዳሞ ቆንጆ»፣ «በይ እንግዲህ ተለያየን»፣ «ቸብ ቸብ»፣ «ዳህላክ» እና «ሙዚቃ» የተሰኙ ዜማዎቹ እራሱ ደርሶ ከተጫወታቸው ዘፈኖች መካከል በዋቢነት ሊዘከሩ የሚችሉ ናቸው። የሲዳሞ ወጣት ራሱ መልካሙ የትውልድ ስፍራው ሲዳሞ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ስለ ትውልድ ስፍራው ወጣት ሴት የተጫወተው ነው። ቸብ ቸብ አርጉላት አሁን ላይ ዋነኛ የሰርግ ማድመቂያ ሙዚቃ ሆኖለታል። ልቤ አይስቅልሽም እና ባር ባር ሲለው ሆዱ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርጸው ለብዙ ዓመታት የህብረት ትርኢት የሙዚቃ ፕሮግራም ላይ ህዝብ ያያቸው እና የወደዳቸውም ናቸው። ኧረ መላ ምቱ ብዙ ፍቅረኞች ታሪክ ውስጥ ያለ ተወዳጅ ሙዚቃ ነው። መልካሙ ለብቻው ከተጫወታቸው ሙዚቃዎች በተጨማሪ ከሂሩት በቀለ ጋር የተጫወተው ሙዚቃም አለው።
መልካሙ ከድምጻዊነቱ ብሎም ከግጥምና ዜማ ደራሲነቱ ባሻገር ቲአትርም የመድረስና በተዋናይነት የመሳተፍ ችሎታ ያለው አንጋፋ ከያኒ ነው። የድርሰት ችሎታውን ካስመሰከረባቸው ስራዎቹ አንዱ የሆነውና እራሱም በተዋናይነት የተሳተፈበት «ቢሮክራሲያዊ የከበርቴ አሻጥር» የተሰኘው ድርሰቱ አንዱ ነው። መልካሙ በበርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎች ከመጫወቱ ሌላ በጸጋዬ ገብረመድህን በተደረሰው «አቡጊዳ ቀይሶ» በአያልነህ ሙላት በተደረሰው «ሻጥር በየፈርጁ» እና በሌሎችም ቴአትሮች ተሳትፏል። መልካሙ ተበጀ ስለ ማህበራዊ ሕይወት፣ ስለወጣነት ስለ ተፈጥሮ ስለፍቅር እና ስለ ሌሎችም ብዙ የተጫወተ መልከ መልካም አንጋፋ ከያኒ ነው።
ተወዳጁና አይረሴው አርቲስት መልካሙ ተበጀ በዚህ ወቅት በአሜሪካ ዲሲ ይኖራል።
ከመልካሙ እውቅ ሥራዎች መካከል…
* ነኝ ወይ ላንቺ ክፉ
* አመሰግናለሁ
* ደህና ሁኚ
* ያን ጎራ ያን ሰፈር
* የልቤን አዳራሽ
* ቸብ ቸብ አርጉላት
* ልቤ አይስቅልሽም
* የስብራቴ
* የናፍቆት ሰ ላምታ
* ባለማተቢቱ
* አንድ ዓመት ወደድኳት ጥቂቶቹ ሲሆኑ
በራሱ ግጥምና ዜማ የተሠሩት ሙዚቃዎቹ
* የሲዳሞ ቆንጆ
* ስንቱን አሳለፍነው
* አልጓጓም
* እንታረቅ
* ሂሩትዬ
* እንቆቅልሽ ኑሮ
* የድህነት ሚስቴ
* አንቺ ተማሪ
* አትፍረዱብኝ…..
እነዚህ ግጥምም ዜማም በመልካሙ ተበጀ የተደረሱ ሲሆን “በእንባ ተለያየን” የሚለው ተወዳጅ ሙዚቃው ዜማው የወንድሙ ቶላ ሲሆን ግጥሙ የራሱ የመልካሙ ተበጀ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም