የኛማ ሙሽራ (2 ጊዜ)
እጹብ ድንቅ ስራ
በሆታ በእልልታ እንቀበላቸው
ሙሽሪት ሙሽራው ዛሬ ነው ቀናቸው።
“ሠርግ”ን የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላቱ “ለአካለ መጠን የደረሰ ወንድ ልጅና ለአካለ መጠን የደረሰች ሴት ልጅ ባልና ሚስት ሊሆኑ የሚጋቡበት ቀንና ሠርግ፤ ተጋብተውም የዚህን ዓለም ኑሮ የሚጀምሩበት የሠርግ ቀን።” በማለት የሚፈታው ሲሆን፣ እኛም ይህንኑ ብያኔ ይዘን ሀሳብ መለዋወጣችንን እንቀጥላለን።
ሠርግ እንደው ዝም ብሎ ሰዎች ለአካለ መጠን ስለ ደረሱ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ኃይማኖታዊ መሰረት ያለ ሰብአዊ ተግባር ሲሆን፣ የሚከተሉት አናቅፅ የሚነግሩንም ይህንን ነው።
መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፪ (22)፣ ቁጥር ፪ (2)
በሦስተኛውም ቀን በቃና ዘገሊላ ሰርግ ነበረ፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ታደሙ። (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ (2)
ከእነዚህ ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ (በሌሎች ኃይማኖቶችም የሚኖር ይመስለናል) ጥቅሶች የምንረዳቸው በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ ሲሆን፤ የሠርግን አስፈላጊነት፣ የሠርግ ደጋሽን ከፍታ ቦታ፣ ሠርግ የሚሠረግበት ቦታ ክቡርነትን እንረዳለን። ከዚህ አኳያ በመናፈሻው የተጋቡት ጥንዶች እድለኞች ሆነው እናገኛቸዋለን።
በእግዚአብሔር ዘንድ ሠርግ ከልብሱ ጀምሮ ልዩ ቦታና ክብር አለው። የስራ ልብስ እንዳለ ሁሉ፤ የሠርግም ልብስ አለ። ለዚህም “የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደ’ዚህ ገባህ? አለው፤ እርሱም ዝም አለ።” የማቲዎስ ወንጌል ምእራፍ ፳፪ (22)፣ ቁጥር ፲፪ (12) የሚለው ብቻ በቂ ማመሳከሪያ ነው።
“እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ።” (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምዕራፍ 3፣ ቁጥር 11) የሚለውም እንደዚሁ ከሠርግ አልባሳት፣ ውበትና ውድነት ጋር የተያያዘ ነውና ሠርግ የዋዛ ትርጓሜ ያለው ጉዳይ አይደለም።
የሠርግ ጥሪውም ሆነ ስፍራው (አዳራሹ ወይም “የሠርግ ቤት” በሚል የሚታወቀው) ልዩ ክብር አለው። መጽሐፉ “ማንም ለሠርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና …” (የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፬ (14)፣ ቁጥር ፰ (8) እንደሚለው ሠርግ የተከበሩ፣ ለሠርገኛው የቀረቡ … ሰዎች የሚታደሙበት እንጂ እንደ መሸታ ቤት ማንም የሚዋከብበት ስፍራ አይደለም። ወደ መሬት እናውርደው።
ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ከሆኑት አንዱ ሠርግ ነው። በየትኛውም ዓለም ሠርግ አለ። እንደየባህሉ፣ አድባርና አውጋሩ በየትም ስፍራ ሰው ይዳራል፤ ይሠረጋል። የቁጥርና አንዳንድ ልዩነቶች ካልሆኑ በስተቀር በየትኛውም አገር ሙሽራ አለ፤ የትም ቢኬድ ሠርገኛ አለ። ይበላል፤ ይጠጣል … ወዘተርፈ። እኛም አገር የሚሆነው፣ እየሆነም ያለው ይኸው እንጂ ሌላ አይደለም።
ምንም እንኳን ጥር “የሙሽሮች ወር” ከሚለው ወጣ ያለ ቢመስልም፤ ያለ ምንም የኃይማኖት ልዩነት በአንድ መሞሸር በራሱ የሚፈጥረው ስሜትም ሆነ፣ የሚያስገኘው ማህበረ-ባህላዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በነበረን አገራዊ እሴት ላይ ሌላ አገርኛ ጨመርን ማለት ይኸው ነው። አሁን የዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳያችን እንምጣ።
ከቻይና መንግሥት በተገኘው ድጋፍ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው ስፍራ መልማት ከጀመረ በኋላ በዘመናዊ መልክ የተገነባው የወዳጅነት ፓርክ (ፍሬንድሺፕ ስኩዌር) ጳጉሜ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት መሆኑ ይታወሳል።
የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሁለተኛው ምዕራፍ ባለፈው እሁድ (ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም) ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት ሆኗል።
የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት መጠናቀቁን በማስመልከት፣ “ለምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ልዩ ስጦታ” ይሆን ዘንድ ለአዲስ ተጋቢ ሙሽሮች ልዩ ስጦታ ቀርቧል። ስጦታውም፡-
“ጋብቻቸውን ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም አቅደው ሳይሳካላቸው የቆዩ 50 ጥንዶችን በመሥፈርት መርጦ የጋብቻ ሥርዓታቸውን በሥፍራው እንዲፈጽሙ ታቅዷል። በመሆኑም መሞሸር ያሰቡ ወይም ሊሞሸሩ አቅደው በልዩ ልዩ ምክንያት ሳይከውኑት የቀሩ፣ በዚህ ዘመናዊ እና ያማረ ስፍራ ሠርጋቸውን ከሚፈጽሙ 50 ጥንዶች መካከል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል። በፕሮጀክቱ ምረቃ ዕለት ሠርጋቸው ከሚፈጸም 50 ጥንዶች አንዱ ለመሆን የሚከተለውን ቅጽ ሞልተው እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ድረስ በshegerprize@pmo.gov.et ኢሜይል በመላክ እንዲሳተፉ”
የሚለውን ባካተተ መልኩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፌስቡክ ገፅ አማካኝነት ለመላው ህዝብ ተሰራጭቷል። በዚሁ መሰረትም የሚመለከታቸውና በሠርግ ዐጸዱ መሞሸር የፈለጉ ተመዝግበዋል። በወጣው መስፈርት መሰረት ተወዳድረው ያለፉት 50ዎቹ የልዩ ስጦታው ተጠቃሚ ሆነዋል።
የፓርኩ ምርቃት በሆነው የወዳጅነት የሠርግ ዐጸድ ላይ 50 ጥንዶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን አከናውነዋል። በአዲስ አበባ ከተማ (ከባሻ ወልዴ ችሎት እስከ እሪ በከንቱ ባለው ስፍራ) የተገነባው የሸገር ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት የተለያዩ የሕፃናት መዝናኛዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የኪነጥበብ ዝግጅት ማሳያዎችን፣ ካፌና ሬስቶራንቶችን … ይዟል። በተጨማሪ የተለያዩ ሁነቶች የሚስተናገዱባቸውን ዘመናዊ አዳራሾችንና ማዕከላትን የያዘ መሆኑንም መመልከት ተችሏል። የሸገር ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ሕፃናት ባህልና ታሪካቸውን እያወቁ የተለያዩ ዕውቀቶችን የሚቀስሙበት ዘመናዊ የሕፃናት መዝናኛና ሰብእና መገንቢያ ማዕከልንም ያካተተ ነው።
በምረቃው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤
ለቀጣዩ የአገራችን ዕድገት መሠረት ለመጣል ልጆች ላይ ትኩረት አድርገን ከአሁኑ መሰራት ያለበት መሆኑ፤ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አሁን የሚታየው ችግር ልጆች ላይ ካለመሥራት የመጣ እንደሆነ፤ መንግስታቸው የተሻለች አገር ለመገንባት መሠረቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱን የሚቀጥል መሆኑን፤ በቀጣይ አገራዊ ግንባታ በአዕምሮና በሥነልቦና የዳበረ ትውልድ ለመገንባት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ፤ ልጆች አገራቸውን እያደነቁና እየወደዱ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ከቻሉ በቀጣይ ለአገር ግንባታ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሚሆን፤ አገር የሚመሠረተው በጠንካራ ትውልድ መሆኑ፤ ጠንካራ ትውልድ ያላት አገር ችግሮችን ተቋቁማ ማለፍ የማትቸገር ስለመሆኗ፤ ትውልዱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከተቻለ የበለጠ ፍሬያማ መሆን እንደሚቻል፤ በዚህ አግባብ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕፃናት ቅድመ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ መሆናቸውን፤ እንዲሁም፣ በፓርኩ ውስጥ የሚዝናኑ ልጆች በዘመናዊ መንገድ እንዴት ፈተናዎችንና ችግሮችን ማለፍ እንደሚችሉ እየተማሩ አካላቸውንና አዕምሯቸውን ማዳበር የሚችሉ ስለ መሆናቸው ወዘተ መናገራቸውም የዚሁ አካል ነው።
የፕሮጀክቱን መጠናቀቅና የምረቃ ስነስርአቱን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መረጃ እንዳመለከተው፣ አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እና ለስሟ የሚመጥን ገጽታ እንዲኖራት ታልሞ ሲሠራ የቆየው የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት በስኬት ተጠናቋል።
ለሀገር ኩራት፣ ለጎብኚዎች መዳረሻ፣ ለመዲናችን ነዋሪዎች የዘወትር መገልገያ እንዲሆን የተዘጋጀውና የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሁለተኛ ምዕራፍ ለአገር ኩራት መሆኑም በእለቱ ተገልጿል። በተሰራጨው ጽሑፍ ላይም ተመልክቷል።
በአገር በቀል እፅዋት የተዋበው ፓርክ የሚገኝበት ስፍራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት አንስቶ ወደ አሮጌው ቄራ መውረጃና እሪ በከንቱ ወንዝን ተሻግሮ (ዘመናዊ ድልድይ ተሰርቶለታል) የሚዘልቅ ሲሆን፤ ፓርኩ ከመገንባቱ በፊት “አካባቢው ለልማት …” በሚል ፈርሶ ከ10 ዓመት በላይ ስፍራው ያለ አገልግሎት ተቀምጦ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። (በነገራችን ላይ፣ የአካባቢውን የ“ድሮና ዘንድሮ” ገፅታና ንጽጽር ለመግለፅ ልዩ ችሎታን የሚጠይቅ መሆኑን እዚህ ላይ ሳይናገሩ ማለፍ ይከብዳል።)
ከላይ እንደገለፅነው፣ የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት የሕፃናትና ወጣቶች መዝናኛ ፓርክ መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ፣ በምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ዕለት ጋብቻቸውን ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም አቅደው ሳይሳካላቸው የቆዩ 50 ጥንዶችን በመሥፈርት መርጦ የጋብቻ ሥርዓታቸውን በሥፍራው እንዲያከናውኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል። በዚሁ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ጋብቻው ተካሂዷል።
በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን ኬክ የቆረሱ ሲሆን፤ “የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለትን በከፈትንበት ዕለት በሠርግ ዐጸዱ ጋብቻችሁን የፈጸማችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሙሽሮቹና እድምተኞቹ የደስታ ተካፋይ ሆነዋል። “ጋብቻ የሀገር መሠረት ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነው ቤተሰብ የሚመሠረትበት ነው። ኢትዮጵያውያን በሀገራችን፣ ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ድንቅ ስፍራ በሠርጋችሁ ደስታ አድምቃችሁ አስጀምራችሁታል።” ሲሉም የአፀዱን የአሁንና የወደፊት ፋይዳ አመላክተዋል።
ከሠርጉ ፕሮግራም አስቀድሞ፣ ማለትም በጠዋቱ የልጆች መዝናኛ ስፍራው ምርቃት ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልእክት ያለ ሲሆን፤ ከመልእክቶቻቸውም ዋና ዋናዎቹም፣
ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችም በየክልሎቹ መገንባትና ቀጣዩ ትውልድ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ፤ ፈተናዎችን የሚቋቋም ጠንካራ ትውልድ መገንባት የሚቻለው ከታችኛው የዕድሜ ክልል አንስቶ እንደ ሆነ፤ ለዚህ ደግሞ ሕፃናት ማንበቢያ፣ ማሰቢያ፤ እንዲሁም፣ አካላዊና አዕምሯዊ ብቃታቸውን የሚያዳብሩባቸው ስፍራዎች በብዛት የሚያስፈልጉ መሆኑን፤ መንግሥትም በርካታ የሕፃናት መዋያዎችንና ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ፤ ከዚህ ባለፈ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕፃናትን መመገብ የተቻለ ስለመሆኑ፤ ከመዋዕለ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከተከናወኑ ሥራዎች ባለፈ እንደ ወዳጅነት ፓርክ፣ ምዕራፍ ሁለት ዓይነት ፓርኮች ለትውልድ ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን፤ ፓርኩ በከተማዋ መሃል የሚገኝና ዜጎች ልጆቻቸውን ለማዝናናት ሲፈልጉ በቅርበት የሚያገኙት ደረጃውን የጠበቀ ስፍራ መሆኑና ይህም ተመራጭ እንደሚያደርገው፤ የወዳጅነት ፓርክ ሁለተኛው ምዕራፍ ስፖርትን፣ ጨዋታንና ማኅበራዊ መስተጋብርን … ያቀናጀ ስለመሆኑ፤ ልጆች እየተጫወቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንዲተዋወቁ፣ እንዲያነቡ፣ ስፖርት እንዲሰሩ … መልካም አጋጣሚን የሚፈጥርላቸው ስለመሆኑ፤ ወላጆችና አያቶች ከልጆቻቸው ጋር መጥተው ማኅበራዊ ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት ስፍራ እንደሚሆን፤ አዲስ ተጋቢዎች በሠርግ ዐጸዱ ጋብቻቸውን የሚመሰርቱ መሆናቸው፤ ይህም በበኩሉ የነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች እንድትሆን የተሻለ ትውልድ እያፈራን እንድንቀጥል መሰረት ስለመሆኑ … ከተናገሩት ይገኙባቸዋል።
የወዳጅነት ምዕራፍ ሁለትን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለአንድ ሳምንት በነፃ መጎብኘት የሚችል መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያስታወቁት በዚሁ ወቅት ነበር።
በመጨረሻም፣ በሠርግ አፀዱ ለተጋቡት በሙሉ መልካም የትዳርና የሕይወት ዘመን እንዲሆንላቸው እየተመኘን፤ “እንደዚህ አይነት ማእከላት ይብዙልን!!!” እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም