ይህን ቀን ማንም ኢትዮጵያዊ አይረሳውም።አዎ! ይህ ቀን የሀገር ባለውለታ፣ የብዙዎች አሌንታና የሀገር ዳር ድምበር ጠባቂ የሆነው እንቁው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገር በቀል ባንዳዎች ከጀርባው የተወጋባት ቀን ነው።ሰራዊቱ ለዛ ሀገር ህዝብ ስንት ነገር እንዳላደረገ ተክዶ በግፍ የተጨፈጨፈበት ቀንም ነው።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ታሪክ የተጻፈበት ቀን ነው።ሀገሪቷን ለሃያ ሰባት አመታት በብሔር ከፋፍሎ የራሱን ጥቅም ብቻ እያጋበሰ ሲያስተዳድራት የነበረው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በእስኪርቢቶ ተሸንፎ የአራት ኪሎ ቤተመንግስትን ተሰናብቶ መቀሌ ከተሸኘ በኋላ እኔ ያልገዛኋት ሀገር ትፍረስ በሚል ለሃያ አመታት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲጠብቀው የነበረውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጀርባው የወጋበት ቀን ነው።
በዚህ ድንገተኛ ጥቃት ከሀዲ ቡድኑ ብዛት ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በግፍ ጨፈጨፈ።አብዛኛዎቹን ከባድ መሳሪያዎችም በእጁ ካስገባ በኋላ ከኔ በላይ ማንም የለም አለ።መከላከያ ሰራዊቱን መንካት ኢትዮጵያን መንካት ነውና ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ ንጋት ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ስለድርጊቱ አብራርተው የአፀፋ እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ አስተላለፉ።
ወትሮም ኢትዮጵያ ስትነካ የማይወደው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከደረሰበት ጥቃት ዳግም አገግሞ ለሀገሪቷ ሉዓላዊነትና ለመላው ኢትዮጵያውያን ሲል ወደ ጦርነቱ ገባ።በግዜው ሰራዊቱ ወደ ጦርነቱ ሲገባ እጁ ላይ ብዙም የጦር መሳሪያ አልነበረውም።ሆኖም ባለው መሳሪያ ራሱን አደራጅቶና ህዝቡን ደጀን አድርጎ አሸባሪ ቡድኑን ገጠመ።
ቀድሞም የተገፋችው ኢትዮጵያ ናትና ሰራዊቱ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ሲል ሀቅን ይዞ ወደ ጦርነቱ በመግባቱ በድል ላይ ድል ይጎናፀፍ ጀመር።በጥቂት ጊዚያት ውስጥም አብዛኛዎቹን የጠላት ታጣቂዎችንና ይዞታዎችን መደምሰስ ቻለ።በጠላት ይዞታ ስር የነበሩ ከባድ መሳሪያዎችንም አብዛኞቹን ደምስሶ ጥቂት የማይባሉትንም ማረከ።በዚህ ግስጋሴውም እለት በእለት ድል እያገኘ ጠላትን ገሚሱን ደምስሶ ገሚሱን ደግሞ ማርኮ ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቀሌን ተቆጣጠረ።
ሰራዊቱ መቀሌ ከገባ በኋላ ህዝቡን የማረጋጋት፣ የመጠበቅና ሌሎችንም ስራዎች ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም ጥቂት የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎች መረጃ እየሰጡ ከኋላው ለማስወጋት በተደጋጋሚ ሞክረዋል።በዚህም ጥቂት በማይባሉ የሰራዊቱ አባላት ላይ ሞትና መቁሰል ተከስቷል። በዚህም መንግስት ቢያንስ ህዝቡ የጥሙና ጊዜ ይሰጠው፤ እርሻም ይረስ ብሎ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አስወጣ።
ድሮም የጦርነት ልክፍት ያለበት አሸባሪ ቡድኑ ከወራት በኋላ በክረምት ወቅት ጊዜው ባለፈበት የጦርነት ታክቲክ ከህፃናት እስከ አዛውንት በማሰለፍ በህዝብ ማዕበል የአማራና አፋር አጎራባች አካባቢዎችን መውረር ጀመረ።የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም የከፋ የህዝብ እልቂት እንዳይከሰት ወደኋላ አፈገፈገ።ለዚህ ኃይል የሚመጥን ሰራዊት መገንባት እንደሚያስፈልግም መንግስት አመነ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ ወጣቱ የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀል ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ማህፀነ ለምለሟ ኢትዮጵያ ልጆቿን ለሰራዊቱ በፍቃደኝነት እንካችሁ አለች።ሰራዊቱን በየጊዜው የሚቀላቀለው የወጣት ቁጥርም ማእበል ሆነ።ሰራዊቱም በመሳሪያና በሰው ኃይል ይበልጥ ተደራጀ።የህዝቡ ደጀንነትም ይበልጥ ተጠናከረ።በዚህ ጊዜ አሸባሪ ቡድኑ ወረራውን አጠናክሮ ደብረሲና ደርሶ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተደምስሶ ወደመጣበት ተመለሰ።
ቡድኑ የሞት ሽረት አድርጎ ለሶስተኛ ዙር ወረራ በቅርቡ ቢነሳም ህልሙ ሊሳካለት አልቻለም።እለት በእለት በጥምር ኃይሉ በሚደርስበት ድቆሳ አቅሙ ተዳክሞ ጀምበር አዘቅዝቃበታለች።በራሴ ሜዳ እየተዋጋው እስከመጨረሻው እዝልቃለሁ ብሎ ቢፍጨረጨርም አልሆነለትም።በነዚህ ሁሉ ተጋድሎ ታዲያ አብዛኛዎቹ ወጣት የመከላከያ ሰራዊት አባል ጠላትን እየተፋለሙና መስዋት እየከፈሉ በታላቅ ጀብዱ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከብረዋል።በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር እንደምትፀናም አስመስክረዋል።
መቼም ዝክረ ሰሜን እዝ ሲወሳ ወጣቷ አስር አለቃ በላይነሽ ደባልቄ የፈፀመችውን ጀብድ መዘንጋት አይገባም። 20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር ሰሜን ዕዝ ካሏት የጦር ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ ክፍለ ጦር አንደኛ ብርጌድ አንደኛ ሻለቃ አባል የሆነችው ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገብረ ዮሃንስ አጃቢ ብትሆንም ሰውየው ጁንታ መሆኑን ግን አታውቅም።
አሸባሪ ቡድኑ የእብሪት እርምጃቸውን ከመጀመሩ ከሶስት ቀናት በፊት ሰራዊቱ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መንገድ በመዝጋት ለከፍተኛ ርሃብና ጥም ዳርጎታል። በጊዜው ቡድኑ ሁሉም የሰራዊት አባል የግል ትጥቁን በአንድ ክፍል በማስቀመጥ በህብረተሰብ የድጋፍ ስራዎች ላይ እንዲረባረብ አደረገ።
በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ሁሉንም የጥበቃ ቦታዎች በትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላት እንዲሸፈኑ በማድረግ፣ የከሃዲው ቡድን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምንም አይነት ዝግጅትና ትጥቅ ባልነበረው ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ተኩስ ከፈተ። ሆኖም ታላቅ ጀግንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የወረሰው ጀግናው የመከላከያ ኃይል የማይታሰቡ ጀብዶችን ጭምር በመፈፀምና ወደ ኤርትራ በመሸሽ ራሱን ማዳን ችሏል።
በዚህ ሁሉ ግፍና በደል መሃል የሻለቃዋ ዋና አዛዥና ለዘመናት የመራቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የካደው ኮሎኔል ሰለሞን ገብረ ዮሃንስ ራሱን መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ በጁንታው የተሰጠውን ተልዕኮ መፈፀም እንደጀመረ አስር አለቃ ገበያነሽ ሁኔታውን በንቃት ትከታተል ነበር።
ውትድርና በኢትዮጵያዊነት ፍቅር መታጠብና በጀግንነት ካባ መድመቅ መሆኑን ጠንቅቃ የምታውቀው እንስቷ ጀግና ፣ ራስን ለሀገር አሳልፎ መስጠት ታላቅ ኢትዮጵያዊነት መሆኑንና ይህም ብቻውን ጀግንነትን እንደሚወልድ በመረዳት ከሀዲውን ኮሎኔል ከስሯ እንዲንበረከክ አድርገዋለች።
“ሰራዊታችን በታፈነበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት 2 ሰዓት ላይ በከባድ መሳሪያ የታጀበ ተኩስ ወደ ካምፓችን ተተኮሰ፣ በዚህ ሰዓት ወደ መፀዳጃ ቤት ራሱን ለተደበቀው ካሃዲው አዛዥ ተብዬ እኔ በትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጥይት ከምሞት አንተን ገድዬ ራሴን አጠፋለሁ አልኩት›› ስትል በጊዜው የተፈጠረውን ሁኔታ አስረድታለች።
‹‹ተኩሱ በርትቷል፣ ሁሉም ራሱን ለማዳን ወደህሊናው የመጣለትን አማራጭ እየተጠቀመ ይሯሯጣል።በመጨረሻም ኮሌኔሉ ከተደበቀበት መፀዳጃ ቤት እንዲወጣና እኔ የምለውን ብቻ እንዲፈፅም እሽ የማይል ከሆነ ግን እንደምገድለው አስጠነቀቁት›› ትላለች ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ክስተቱን ስትተርክ።
እሱም በፍርሃት ውስጥ ሆኖ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ ወደነገርኩት ቦታ መጣ።ሽጉጡንና ማዕረጉን እንዲሰጠኝ አደረኩ።ከዛም ጫማውን እንዲያወልቅ አድርጌ በየመንገዱ ከማገኛቸው የሰራዊት አባላት ጋር በመተባበርና ሙሉ ሌሊት የእግር ጉዞ በማድረግ ኤርትራ ይዤው በመግባት ታማኝ እና ሙሉ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ አመራሮች አስረከብኩት” ስትል አውግታለች።
ሰራዊቱ በራሱ ወገኖች የደረሰበትን በቃላት የማይገለፅ ግፍና በደል ተሸክሞ ቂምን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍቅርን አስቀድሞ ለድል በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ስሜቷን አጋርታለች።
ሌላኛው ወጣት ባለጀብዱ አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ ሲሆን ከደቡብ ክልል ከፋ ዞን የበቀለ የመከላከያ ሰራዊት አባል ነው።የመከላከያ ሰራዊቱን የተቀላቀለውም በ2009 ዓ.ም ነው።ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰጠውን ሀገራዊ ተልእኮ ተቀብሎ ሲፈፅም ቆይቷል።አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ወረራ ቡድኑን ለመደምሰስ በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ተፋልሞ ጠላትን ድባቅ መቷል።
በተለይ ከሰሜን ወሎ በኩል ብርቱ ክንድ ያረፈበት አሸባሪ ቡድኑ በወረባቦ በኩል የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ለመውረር በሚፍጨረጨርበት ጊዜ ወጣቱ አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተናንቆ በያዘው ክላሽ በመደምሰስ አምስት ስናይፐሮችን ከነሙሉ ትጥቅ ማርኳል።አርባ ስምንት የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎችንም ደምስሷል።
አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ ተቅበዝብዞ የመጣውን አሸባሪ ቡድን ድባቅ በመምታት አምስት ስናይፐር ብቻ ሳይሆን የማረከው የጠላት ብሬል እንዳይሰራ በማድረግ ተጨማሪ ጀብድ ፈፅሟል።
በወረባቦ በኩል በነበረው አውደ ውጊያ ታላቅ ጀብዱ ከፈፀመው አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ ጋር አብሮ በግንባር ሲፋለም የነበረው ጓደኛው አስረስ ማሙሽ ‹‹አምስት የቡድን መሳሪያ ጠምደን እየተታኮስን እያለ እርሱ ለብቻው ግራና ቀኝ እያስተባበረ ነበር›› ይላል። የእነርሱ ብሬል ተኳሽና ሬዲዮ ኦፕሬተር እየመጡ ሳለ በዚሁ መሀል አምስት ስናይፐር የታጠቁትን በተከታታይ በክላሽ በመግደል መሳሪያዎቹን መማረኩን ይናገራል። ብሬላቸው እንዳይሰራም ዋናውን መውጊያ እንደሰበረውም ይገልፃል።
ወታደርነት ስለሀገር ፍቅር መስዋትነት የሚከፈልበት ከራስ በላይ ለወገን ክብር ዘብ የሚቆምበት ታላቅ ሙያ እንደሆነም ነው አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ የሚናገረው።‹‹ከራስ በላይ ሀገርና ወገንን ነው የምንጠብቀውም›› ይላል በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት።
በሌላ በኩል ደግሞ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቲዎስ በሰራዊቱ የሚሰጡትን ግዳጆች በውጤታማነት በመፈፀም ታላቅ ታሪክ ካስመዘገቡ ወጣት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ውስጥ አንዱ ነው።አሸባሪ ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በሻምበል አመራርነት ጦሩን በመምራት ምሽግ በመስበርም ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል።በትግል ላይ እያለ ቢቆስልም ወደኋላ ሳይል ለሀገሩ የገባውን ቃልኪዳን በተግባር አረጋግጧል።
እርሱ ቢቆስልም ሲመራት የነበረችው ሻምበል ወኔውን አይታ ካለችበት ቦታ ለአራት ቀናት ሳትነቃነቅ አሸባሪ ቡድንኑ ተፋልማ ምሽጉን አስለቅቃለች። እርሱም ቁስሉን ችሎ ከሻምበሏ ጋር አብሮ ቆይቶ ትልቅ ጀብዱ ፈፅሟል።
‹‹ያለን አንድ ሀገርና አንድ ሕይወት ነው›› የሚለው ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ፤ የማይተካ ሕይወታችንን ለሀገራችን ስንል እንከፍላለን ሲል በወኔ ይናገራል።አባቶቻችን መስዋትነት ከፍለው ያሻገሯትን ሀገራችንን ኢትዮጵያ እኛ ወጣቶችም መስዋት ከፍለን ሀገራችንን ማሻገር ይጠበቅብናል ይላል።ለዚህም ታዲያ ወጣቱ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እንዳለበት መልእክቱን ያስተላልፋል።
ሌላው በዚህ የህልውና ዘመቻ ጀብድ ከፈፀሙ ወጣቶች ውስጥ አንዱ የመከላከያ ሠራዊት አምስተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባል ቁመተ መለሎው 10 አለቃ አብርሃም ነው። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከስድስት ዓመታት በላይ አገልግሏል።
አስር አለቃ አብርሃም የሚያሽከረክራትን ታንክ ልክ እንደ እጁ መዳፍ ያውቃታል።በጋሸና እና ደብረዘቢጥ ግንባሮች ላይ የአገሬን ንብረት ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም በሚል እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ አድርጓል።
በውትድርና ቆይታዬ ሁሉ እንደ ደብረዘቢጥ እና ጋሸና ያህል ፈታኝ ቀናትን ያሳለፍኩበት ወቅት የለም፤ ይሁንና ከጓዶቼ እና ደጀን ሕዝቡ ጋር በመሆን ወራሪውን አሳፍረነዋል፤ በደብረዘቢጥም ሆነ በጋሸና ግንባር አኩሪ ድል አስመዝግበናል ሲል ይገልጻል።
አስር አለቃ አብርሃም ከጋሳኝ አንስቶ እስከ ደብረዘቢጥ በነበረው ውጊያ ላይ ታንክ እያሽከረከርኩ ግንባር ላይ ሲዋጋ ነበር። በወቅቱ ሃሽሽ የወሰዱ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ታጣቂዎች ታንኩ ድረስ መጥተው በብሬል እና በተለያዩ መሳሪያዎች ታንኩ ላይ ጥይት አዘነቡ።
በድንገት ግን የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የታንኩን መነፅር መቱበት። የታንኩን የተለያዩ ክፍሎች ማበላሸታቸውንም ቀጠሉ። በቅርበት መጥተውም ከበቡት። ይሁንና ድፍረት አልባ በመሆናቸው ታንኩ ላይ ወጥተው ለመያዝ እንኳን ወኔ አልነበራቸውም።
እሱም የታንክ መነጸሩ ቢሰበርበትም ለጠላት ታንክ አላስረክብም ብሎ ታንኩን ማሽከርከር ተያያዘ። በድፍረት እና በወኔ እየነዳ የተሻለ ቦታ በመያዝ ከጥሻ ወጣ። በኋላም ዳግም ጥቃት ጀመረ። ደብረዘቢጥ እና ገረገራ በቁጥጥር ሲውሉ በዚችው ታንክ ድል በማድረግ ውጊያውን በጀግንነት ተውጥቷል።
የአስር አለቃ አብርሃምና የታንኳ ታሪክ በጋሸና ግንባርም ተደግሟል። በአካባቢው በተደረገ ከባድ ውጊያ ላይ የታንኩ የኋለኛው ሰንሰለት ቸርኬ ተመቶ ይወልቅበታል።ይህንኑ በመረዳቱም ለቡድን አጋሮቹ የመድፍ ጥይቶችን እንዲተኩሱ የሚያስችል አቅጣጫ በመያዝ ተኳሾቹ በወዲያኛው ማዶ ያለውን ጥቃት መከላከል የሚያስችል ከባድ ምት እንዲያሳርፉ አደረገ። በኋላም የኋላ ቸርኬ ሰንሰለት ማሽከርከሪያው የተመታውን ታንክ የመጎተት ያህል እየነዳ ወደነጻ ቀጠና በማድረስ ታላቅ ጀብድ በታንኳ ፈፅሟል።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በራሷ ጉያ ተወሽቀው ሳቋን እየቀሙ ውርደቷን የሚያፋጥኑና መበተኗን ገሃድ ለማውጣት ሌት ተቀን የሚሯሯጡ ወጪት ሰባሪዎች ቅዠታሞች ቢኖሩትም ክብሯን የሚያስጠብቁ፣ ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ የሀገራችውን ክብር የሚያስቀድሙ፣ የማይታመን ጀግንነት የሚፈፀሙ አስር አለቃ ገበያነሽን የመሰሉ በርካታ የቁርጥ ቀን ጀግኖች አሏት።
ይህ የጀብድ ታሪክ የእነ አስር አለቃ ጌታቸው ገዛኸኝ፣ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቲዎስ፣ አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄና የአስር አለቃ አብርሃም ብቻ አይደለም።የብዙ ወጣት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጀብድ እንጂ!
አዎ! በየአውደ ግምባሩ በፊትም፤ አሁንም በርካታ ወጣቶች ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ሲሉ ታላላቅ ጀብዶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ።እነርሱ መስዋት ሆነው ትውልድ በማስቀጠል ደማቅ ታሪክም እየፃፉ ነው።በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ የተረከቧት ይች ታላቅ ሀገር ዝናዋና ክብሯ ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንድትሻገር ዛሬም መስዋት እየሆኑ ነው።ለዚህ ጀብዳቸው ደግሞ ታሪክ ሁሌም ይዘክራቸዋል።ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ስለኢትዮጵያ ብለው ሲፋለሙ ላለፉ ወጣቶች!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም