ኢትዮጵያ ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ባለፉት አመታት እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው በጀት አመት ብቻ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል። ይህን ያህል መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ የተገኘው በበጀት አመቱ 300 ሺ ቶን ቡና በመላክ ሲሆን፣ ገቢውም ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ታሪክ የመጀመሪያው ለመባል በቅቷል።
ሀገሪቱ ከዘርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ቢሆንም፣ ያላት እምቅ አቅም ከዚህም በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚያስችላት የዘርፉ አካላት ይጠቁማሉ። በተለይ በቡና ጥራት በተለይም በስፔሻሊቲ ቡና አቅርቦት ላይ አተኩራ ብትሰራ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለገበያ የሚቀርብ ቡና የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ እስከ ደረጃ ሶስት ያሉት ስፔሻሊቲ ቡና፣ አራተኛና አምስተኛ ደረጃዎቹ ደግሞ ኮሜርሻል ቡና በመባል ይታወቃሉ። ሀገሪቱ ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ቡና አብዛኛውን እጅ የሚይዘው ኮሜርሻሊቲ ቡና ሲሆን፣ የተቀረው ስፔሻሊቲ ቡና ነው።
ኢትዮጵያም ከዚህ የቡና ግብይት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ለውጭ ገበያ በምትልከው ቡና ጥራት ላይ አተኩራ መስራት እንዳለባት በእጅጉ ታምኖበታል። የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ባለፈው ነሐሴ ወር ለንባብ በበቃው የባለስልጣኑ መጽሄት ላይ ሀገሪቱ ለዘመናት ስትጠቀምበት በቆየችበት መንገድ ኮሜርሻል ቡናዎችን ብቻ እየላከች ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም ሲሉ ያስገነዘቡትም ይህንኑ ያመለክታል፤ ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ የቁጥ ቁጥ ገቢም መላቀቅ እንዳለባት በጥናት መገንዘብ መቻሉንም ነው ያስገነዘቡት። ‹‹ከዚህ ወጣ ብለን አይናችንን ከፈት አድርገን የስፔሻሊቲ ቡና ገበያን ማማተር ይኖርብናል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከቡና ገዢዎቻችን አብዛኛዎቹ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ከተለመደው የቡና ቃና ወጣ ብለው ማጣጣም ይፈልጋሉ ሲሉም ያብራራሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው እንዳመለከቱትም፤ ኢትዮጵያ እኤአ ከ2015 እስከ 2017 ለዓለም ገበያ ያቀረበችው ኮሜርሻል ቡና 4፣ 5 እና ዩጂ ደረጃ የነበረው ሲሆን፣ የገበያ ድርሻውም 66 በመቶ ነው። ይህ ቡናም በኪሎ ግራም እስከ 1 ነጥብ 06 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው የተሸጠው። በአንጻሩ ደረጃ 1፣2፣3 ያላቸው ቡናዎች ግን 34 በመቶ ብቻ የገበያ ድርሻ ነው ያላቸው። እነዚህ ቡናዎች የተሸጡበት ዋጋ ግን በኪሎ ግራም በአማካይ ከ2ነጥብ39 እስከ 2ነጥብ 66 የአሜሪካ ዶላር ነው። በቀላል ምሳሌ 1000 ኪሎ ግራም ኮሜርሻል ቡና ተልኮ የተገኘው አንድ ሺ ስልሳ ዶላር፣ 400 ኪሎ ግራም ተልኮ ከሚገኘው የስፔሻሊቲ ቡና ዋጋ ጋር ተመሳሳይ ነው። በእነዚህ መካከል የ600 ኪሎ ግራም ቡና ልዩነት ይታያል። በጥራት የተመረቱት ደረጃ 1፣2፣3 ቡናዎች፣ ከደረጃ 4፣5 እና ከዚያ በታች ከሆኑት ከእጥፍ በላይ የዋጋ ልዩነት ያሳያል።
የተጠቀሱት መረጃዎች በስፔሻሊቲ ቡና ላይ በትኩረት የመስራትን አስፈላጊነት በሚገባ ያመለክታሉ። በኮሜርሻልና ስፔሻሊቲ ቡናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያነጋገርናቸው የቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ በስፔሻሊቲ ቡና ላይ ለውጥ እየታየ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የዛሬ ሶስትና አራት አመታት ስፔሻሊቲ ቡና ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች የሚልኩት መጠንና የላኪዎቹም ብዛት እየጨመረ ነው። በፊት ስፔሻሊቲ ቡና አዘጋጅተው ይልኩ የነበሩት። አሁን ግን ከአስር በላይ ላኪዎች ስፔሻሊቲ ኮፊ እያዘጋጁ እየላኩ ናቸው፤ እነዚህ ላኪዎች አርሶ አደሩ ዘንድ ወርደው እየገዙና እያዘጋጁ ይልካሉ።
ለአርሶ አደሩ በጥራት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች መሰጠታቸው በስፔሻሊቲ ቡና ላይ እየታየ ላለው ለውጥ የራሳቸውን ሚና መጫወታቸውን አቶ ታጠቅ ጠቅሰው፣ የካፕ ኦፍ ኤክስለንስ ውድድር መጀመሩም እየተገኘ ላለው ለውጥ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ። ይህ ማለት በእዚህ አመት በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ እወዳደራለሁ ያለ አርሶ አደር ቡናውን በዚያ ደረጃ ያዘጋጃል ማለት ነው፤ አለፈም ወደቀም ቡናውን በዚያ ደረጃ ለማዘጋጃት ይሰራል ሲሉ ያብራራሉ።
የቀጥታ ግብይት መፈጠሩም የራሱን ሚና ተጫውቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ላኪው ከአቅራቢው ጋር ኮንትራት ሲገባ ደረጃ አንድና ሁለት ብሎ ከተስማማ አቅራቢው አርሶ አደሩን ወደ ማዘዝ ይመጣል፤ ቀዩን ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ቡና የሚውል ቡና ይገዛል ማለት ነው፣ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ መምጣት፣ የግብይት አማራጮች መስፋት፣ ገዢዎች የሚፈልጉት የቡና አይነት እየጨመረ መምጣት ተወደደም ተጠላ የጥራት ደረጃውን እያሳደግን፣ ከኮሜርሻል እየወጣን መጣን ማለት ሲሉ ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ስፔሻሊቲ አንድ ሁለት ሶስት ብለን ብቻ ሳይሆን ከሁለት አመት ወዲህ ደግሞ እየተለመዱ የመጡ የቡና አይነቶች አሉ። ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ የስፔሻሊቲ ቡና ተብለው የሚወሰዱት አነ ሀኒ ኮፊ፣ አናሮቢክና አሮቢክ ኮፊ ፕሮሰስና የመሳሰሉት ፊት ያልተለመዱ በሀገራችን የቡና ዝግጅት ስርአት ውስጥ ያልተካተቱ፣ ቢታወቁም ያልመድናቸውና ያልተካተቱ የቡና ዝግጅት ጥራቶች ናቸው። እነዚህን የቡና ጥራቶች አንዳንድ ላኪዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በመሆን እያዘጋጁ መምጣታቸውም እንዲሁ የስፔሻሊቲ ቡና አቅርቦትን እያሳደገው መጥቷል።
ቡናዎቹን ስፔሻሊቲ ከሚያሰኛቸው መካከል አንዱ ዝግጅታቸው ነው፣ ለምሳሌ ከዝግጅታቸው ውስጥ ቀይ ቀዩን ብቻ ወስዶ በሚገባ የበሰለውን ወስዶ በተሻለ የዝግጅት ሂደት እንዲያልፍ፣ በጸሀይ እንዲደርቅ ሲደረግ፣ በአግባቡ ሲጓጓዝ፣ አከመቻቸቱና የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ጥራትን ባገናዘበ መልኩ ሲሰሩ የቡናው ጥራት እያደገ ይመጣል። ወሳኙ ጉዳይ ያለው ዝግጅቱ ላይ ነው። ከመልቀም ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ጥራት ላይ መሰረት ያደረገ ስራ ተሰራ ማለት ወደ ስፔሻሊቲ ዝግጅት ውስጥ እንዲመጣ ተደረገ ማለት ነው።
ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል ቡና የታጠበ ሲሆን ይፈለጋል፤ አሁንም ብዙ ፈላጊ አለው። በተለይ የታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በብዛት ይፈለጋል ሲሉ ያብራራሉ። አሁን አሁን ደግሞ ቀይ ቀዩን ብቻ በመልቀምና በጸሀይ በማድረቅ የሚቀርብ ስፔሻሊቲ ቡና በጣም ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሀኒ ኮፊ ፣ አናሮቢክና የመሳሰሉት በስፔሻሊቲ ዝግጅት ውስጥ የመጡ ናቸው። እነዚህ እየተለመዱ መምጣታቸው ለስፔሻሊቲ ቡና እድገት የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ሲሉ ይገልጻሉ።
ቡናን ስፔሻሊቲ ስትለው ነገሮች የሚያያዙት ቀጥታ ከዝግጅት ጋር እንጂ ከቡና አይነት ጋር አይደለም የሚሉት አቶ ታጠቅ፣ ሲዳማ ስትል ሲዳማ ኮሜርሻልም ስፔሻሊቲም አለው ይላሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ቡና ጥራቱን ካልጠበቀ ወደ ኮሜርሻል፣ ጥራቱን ከጠበቀ ደግሞ ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ይሄዳል። ጉዳዩ ቀጥታ የሚገናኘው ከዝግጅት ጋር ነው። ከዘር መረጣ፣ ከተክሉ እንክብካቤ ከቡና አሰባሰብ፣ ከፕሮሰሲንግ ጋር የሚገናኝ ነው።
ኮሜርሻሉ እየቀነሰ ስፔሻሊቲ ቡና እየጨመረ ቢመጣም አሁንም አብዛኛው ወደ ውጭ የሚላከው ቡና ኮሜርሻል ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ የለውጡ ጉዞ ግን የቀስ በቀስ መሆኑን ነው የጠቆሙት። ኮሜርሻል ላይ እየሰራ ቆይቶ ባንዴ ወደ ስፔሻሊቲ መሸጋገር እንደማይቻልም ይገልጻሉ። መቶ በመቶ ስፔሻሊቲ ቡና ብታዘጋጅ፣ ለዚያ ገበያ የሚሆን ቡና ላታገኝ ትችላለህ ያሉት አቶ ታጠቅ፣ ስለዚህ በገበያ ላይ በሰራህ፣ እያስተዋወቅህና እየስለመድክ በሄድክ ቁጥር ከኮሜርሻል ወደ ስፔሻሊቲ የበለጠ እየገባህ መምጣት ትችላለህ ሲሉ ያብራራሉ።
ኮሎምቢያ በአብዛኛው ስፔሳሺሊቲ ቡና በመላክ ትታወቃለች፣ ወደውጭ ከምትልከው ቡና አብዛኛውም ስፔሻሊቲ ቡና ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ኮሎምቢያውያን ወደ እዚህ ለመምጣት የሚሄዱበትን መንገድ አስደንጋጭ እንደሆነም ይናገራሉ። እኛ እኮ ቡናችን ራሱ ገበያ እየተፈጠረ እንጂ እኛ እየሰራን አይደለም ነው የሚሉት። ለምሳሌ ኮሎምቢያውያን በእያንዳንዱ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገር ቡናቸውን የሚያስተዋወቁባቸውና የሚሸጡባቸው ሱቆች እንዳላቸውም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ታጠቅ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገሮች ከኤምባሲያችን ውጭ ምንም አይነት ሱቆች የሏትም። ኤምባሲውም ከሰራ ነው፤ ቢዝነስ ኦሬንትድ አይደለም። በእነዚህ ሀገሮች አንድም ሱቅ የላትም። እነሱ በኤዢያ ሀገሮችም ቡናቸውን የሚያስተዋውቁባቸውና የሚሸጡባቸው ሱቆች አሏቸው። ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ ነው ስፔሻሊቲ ቡናን በስፋት ለገበያ ማቅረብ የቻሉት።
ሀገርህ ተቀምጠህ፣ ለማስታወቂያ ምንም ገንዘብ ሳታወጣ እንዴት በዓለም ገበያ ከቡና ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለህ ሲሉም ይጠይቃሉ። አቶ ታጠቅ በሀገራችን ለቡና ፕሮሞሽን ምንም በጀት እንደሌለም ነው የጠቆሙት። በዚህ ዘመን አንድ ኩባንያ ምንም የማስተዋወቅ ስራ አልሰራም ሲባል መሸጥ አይችልም ወደሚል ደረጃ ይወስዳል ሲሉ አቶ ታጠቅ ይገልጻሉ። የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ቢኖርህም፣ እስካላስተዋወቅህ ድረስ ምርትህን ቀርቶ ሀገርህንም የማያውቁ አሉ ያሉት አቶ ታጠቅ፣ በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ በሰፊው መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዳይሬክተሩ በሀገሪቱ የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ተቋምም፤ የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ስትራቴጂም እንደሌለም ነው የጠቆሙት። ለእዚህም እያንዳንዱን ተቋም መመልከት ይቻላል። እንደ ሀገርም የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ለግብርና ምርታችንም ለኢንዱስትሪ ምርታችንም የለም ሲሉ ያመለክታሉ።
በ2014 ዓ.ም ላይ የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ሰነድ እየተዘጋጀ እንደነበረም አስታውሰው፣ ፕሮሞሽን ስትራቴጂው ባለፈው በጀት አመት እየተጠናቀቀ መሆኑን አውቃለሁ ይላሉ። አንደ ኮሎምቢያና ብራዚልና ቤትናም ሌሎች ሀገሮች ላይ ፕሮሞት የሚያደርጉ ኮፊ ሀውሶችና እደረጃጀቶች ባይኖሩንም በኢግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ የመሳተፍ፣ የተለያዩ የፕሮሞሽን ዘመቻዎችን የመጠቀም፣ ፕላትፎርሞችን የማዘጋጀት እቅዶች አሉን ብለዋል።
እነዚህም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ጠቅሰው፣ የፕሮሞሽን ስራ ከገበያ ባለድርሻዎች፣ ከፕሮሞሽን አካላት ጋር የሚሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ተቋሙ ብቻውን የሚሰራው አይደለም፤ በተለይ ከባለሀብት አደረጃጀት ማህበራት ጋር በቅንጅት የምንሰራቸው ይሆናሉ። የምንተውው አይሆንም። ቡና ላይ ፤እንደሚሰሩ ቡና አምራች ሀገሮች የተጠናከረ ስራ አይኖረንም እንጂ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015