የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቅርቡ ተመርቆ እየተጎበኘ ባለው በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ እየቀረበ ባለው አውደ ርእይ ላይ ስራዎቻቸውን ለእይታ ካቀረቡ በርካታ የመንግስትና የግል ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ነው። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ካሉ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱም ከዚህ አኳያ በርካታ ተግባሮችን እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ አውደ ርእዩ ላይ ተቋሙ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም የመንግስት እና የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይገኙበታል። ተማሪዎቹ በጉብኝታቸው ስለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ምንነት እና ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እየዋለባቸው ስለሚገኙ ዘርፎች በኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ገለጻ እየተደረገላቸው ነው። በዚህም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በጤና፣ በቋንቋ፣ ስማርት ሲቲ፣ ሮቦቲክስ እና ተያያዥ ዘርፎች እየሰራቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎች እንዲሁም ምርት እና አገልግሎቶችን እያስተዋወቀ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ ታዳጊዎች የተለያዩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተመልክተው ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ በማድረግ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው አውደ ርእይ ላይ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ሁነቶችን አዘጋጅቶ ማቅረቡን የዝግጅት ክፍላችን በስፍራው ተገኝቶ ለመመልከት ችሏል። ከእነዚህ መካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ መሠረት አድርገው በተቋሙ ከቀረቡ ሥርዓቶች መካከል የጡት ካንሰር ልየታ መተግበሪያ አንዱ ነው።
መተግበሪያው ሰዎች የጡት ካንሰር እንዳለባቸው ሲጠረጠር የሚታዘዘውን ማሞግራም (የጡት ኤክስ ሬይ) በቀላሉ በማንበብ የበሽታውን መኖር አለመኖር የሚጠቁም ነው። በዚህ ቴክኖሎጂ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሰውን ልጅ ዕውቀት ለማሽን ማስተማር ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህም ተግባር በአገራችን በውስን ቁጥር የሚገኙትን የዘርፉ ባለሙያዎች በፍትሃዊነት ለዜጎች ለማዳረስ ያስችላል። የጤና ዘርፉን ለማዘመን እና ለማሻሻል ተስፋ የተጣለበት ይህ ቴክኖሎጂ፣ በቀጣይ በስፋት ምርመራ ለማድረግ እና የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
ሌላው ተቋሙ በሙዚየሙ ያቀረበው ሁነት “አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማብቃት” በሚል መሪ ቃል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የተካሄደው ዓውደ ጥናት ነው። አውደ ጥናቱም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የአህጉሪቷን መፃኢ ዕድል የተቃና በማድረግ ረገድ ስለሚኖረው ሚና ተመክሮበታል። ሀያ አምስት የሚደርሱ ጥናታዊ ጽሁፎችም በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በዓውደ ጥናቱ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ለሳይንቲስቶች፣ ለተማሪዎች፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለምርምር እና እይታ ክፍት የተደረገው የሳይንስ ሙዚየም ከተከፈተ በኋላ ባሉት 21 ቀናት ብቻ 370 ሺ የሚሆኑ የአገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚዎች እንደጎበኙት መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ስፍራ የምርምር ውጤቶቻቸውን እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶችን ካቀረቡት መካከል ከላይ ያነሳነው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንት ኢንስቲቲዩት ይገኝበታል። በዚህም በበርካታ ሺዎች የሚቆጠር ህብረተሰብ የተቋሙን ምንነትና አጠቃላይ የምርምር ውጤቶች ለመመልከት እድሉን አግኝቷል።
በሳይንስ ሙዚዬሙ ጎብኚዎችን በማስተናገድና ገለጻ በማድረግ ላይ እንዳለች ያገኘናት ኬቲምን ተስፋዬ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሪሰርችና ዴቨሎፕመንት ቡድን አባል ነች። በተለይ በሮቦቶክና ኢንዱስትሪያል አውቶሜሽን ዲቪዥን ውስጥ በሚደረግ የምርምር ተግባር ውስጥ ከባልደረቦቿ ጋር በትብብር ትሰራለች። አርሷ እንደምትለው፤ ተቋሙ በሙዚዬሙ በርካታ ውጤታማ የምርምር ስራዎችን ይዞ ቀርቧል።
ኬቲም እና የቡድን ባልደረቦቿ በዲቪዥናቸው የሮቦ ሴኪውሪቲ ቴክኖሎጂን ነው ይዘው የቀረቡት። እንደ እርሷ ገለፃ፤ ይህ ተንቀሳቃሽ ቁጥጥርና ጥበቃን የሚያደርግ ሮቦ ሴኪውሪቲ አሁን በሙከራ ደረጃ የተሰራ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራና ምርት ሲገባ በተለያዩ መደብሮች እንዲሁም ህዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች፣ ህንፃዎችና ጥበቃ በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ሁሉ ውጤታማ ወንጀልን የመከላከል እና ቁጥጥር የማድረግ ተግባርን ማከናወን የሚችል ነው። ከዚህ ባሻገር ምርምሩና አጠቃላይ የቴክኖሎጂ ማበልፀግ ስራው እያደገ በሚመጣበት ወቅት ደግሞ የሮቦት ወታደር ሚናን ይዞ በመከላከያ ውስጥ የሚደረግ ተልእኮን እንደሚፈፅም ገልፃልናለች።
በዚህ ዲቪዥን ውስጥ ለጎብኚዎች ከቀረቡት የሮቦት ቴክኖሎጂዎች መካከል “ሰላም” የሚል ስያሜ ያላት ደግሞ የቱሪዝም ሴክተሩ ላይ ተጨማሪ የቴክኖሎጂ እሴት እንድትሆን ዲዛይን ተደርጋ እንደተሰራች ትናገራለች። መንግስት ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንት እንደሚደግፍ የምትናገረው የዲቪዥኑ ባለሙያ በቀጣይ ግዜያትም ተመሳሳይ የምርምርና የፈጠራ ክንውኖችን ተግባራዊ እንደሚሆኑ ትናገራለች። በግብርናው፣ በህክምናውና በሌሎች ወሳኝ የሚባሉ ዘርፎች ላይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና መሰል የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ገልፃልናለች።
“በሳይንስ ሙዚየም ውስጥ ህፃናት፣ ወጣቶችና በርካታ ሰዎች መጥተው እየጎበኙን ነው” የምትለው ኬቲም፤ ይህን መሰል እድል በመንግስት መፈጠሩ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ውጤታማ ስራዎችን እንድታከናውን እንደሚያግዛት ትናገራለች። በተለይ ህፃናት መሰል የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገቶችን እያዩና እየተማሩ በመጡ ቁጥር ትውልዱ በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ሆኖ እንደሚቀረፅ ትገልፃለች። ለትውልዱ መሰረት የሚሆን ስራዎችን ለመስራት አበረታች መሆኑን ትገልፃለች።
ወጣት ኤፍሬም አበበ ይባላል። በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ውስጥ የሶፍትዌር ዲቨሎፐር በመሆን ይሰራል። እርሱና የሙያ ባልደረቦቹ በሳይንስ ሙዚዬም ውስጥ “የፊንቴክ” ወይም በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚገኝ ቴክኖሎጂን ይዘው ቀርበው ለጎብኚዎች የማስተዋወቅ ስራን እየሰሩ ይገኛሉ።
“የፋይናንስ ቴክኖሎጂው ‘ማይክሮ ሎን’ ይባላል። ከዚህ ቀደም የቢዝነስ ሃሳብ ኖሯቸው የብድር አገልግሎት ያለ ማስያዣ ለማግኘት የሚቸገሩትን የስራ ፈጣሪዎች ችግር የሚያቃልል ነው” የሚለው ወጣት ኤፍሬም፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የተጠቃሚዎችን ሙሉ መረጃ በማስገባትና ከአበዳሪ ባንኮች ጋር በማቀናጀት፣ የተበዳሪውን ቀደምት የብድር ታሪክ በማጥናት፣ ያለውን ገቢና የመመለስ አቅም በማቀናጀት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀመር አማካኝነት ተበዳሪው ያለምንም መጉላላት እምነት አግኝቶ የስራ ማስኬጃውን እንዲያገኝ እንደሚያስችል ይናገራል። በዋናነት ይህ ቴክኖሎጂ ትክክለኛውን መረጃ ለአበዳሪ አካላት እንዲሰጥ እንደሚያስችል ይገልፃል።
“የቢዝነስ ወይም የስራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች የስራ ማስኬጂያ ለማግኘት ወደ ባንኩ መጥተው ብድር ይጠይቃሉ” የሚለው ወጣት ኤፍሬም፣ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የተሰራው ይህ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቱን በማጥናትና አዋጪነቱን በመለካት ተጠቃሚዎች ብድር ማግኘት እንዲችሉ ምክረ ሃሳብ እንደሚሰጥ ይናገራል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የሶፍትዌር ዲቨሎፐሩ ወጣት ኤፍሬም አንደሚለው፤ ‹‹ሰው ሰራሽ አስተውሎት” (አርቲፊሻል ኢንተለጀንት) እንደ ሰው ማስተዋል የሚችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ወይም ማሽን መተግበሪያዎችን የመፍጠር የሳይንስ እና የምህንድስና ዘርፍ ነው። የመጨረሻው ጥረት በዓለም ዙሪያም ሆነ በሰው ልጆች አኗኗር ላይ ያተኮሩ ችግሮችን ለመፍታት እና ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን መፍጠር ነው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ወይም በኮምፒውተር ፕሮግራም የሚደረጉ ማሽኖች ከመረጃ እንዲማሩ፣ ከአዳዲስ ግብዓቶች ጋር እንዲላመዱ እና የሰው መሰል ተግባሮችን እንዲያከናውኑም ያስችላል። ኢትዮጵያም በዘርፉ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችላትን ምርምሮች እያደረገች እንደሆነ ጠቅሶ፣ በሳይንስ ሙዚዬም ውስጥ የቀረቡትን ስራዎች ለእዚህ እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል።
“የማሽን ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራም የማሰብ እና የመማር ችሎታ ነው። የሰው ስራሽ አስተውሎት ጽንሰ ሀሳብ የተመሠረተው እንደ ሰዎች ማሰብ፣ መማር እና የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ችሎታ ያላቸውን ማሽኖችን በተለይም የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን በመገንባት ሀሳብ ላይ የተመሠረተ ነው” የሚለው ወጣት ኤፍሬም፣ ይህንን ሃሳብ የእነርሱ ዲቪዥን “የማይክሮ ሎን” ብድር ወደሚፈቅድ ቴክኖሎጂ በመቀየርና በማላመድ በዘርፉ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ምርምር ለማድረግ እንዳገዛቸው ይናገራል።
እንደ ወጣት ኤፍሬም ገለፃ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ “ፊንቴክ” ዘርፍ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ይገኛል። ይህን እድል ወጣቶች፣ ኢኖቬተሮችና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ የቢዝነስ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ለማስቻል የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የምርምር ስራዎችን በማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
ወጣት ኤፍሬም በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሲሰጥ “የሰው ልጆች የተለያዩ ተግባሮችን ማከናወን እና አብዛኛውን ጊዜ የሰውን የማሰብ ችሎታ የሚጠይቁ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን መስራት በዚህ ዘመን አስፈላጊ ነው” በማለት ከዚህ ቀደም በነበረው የተለምዶ አሰራር እንደ የእይታ ግንዛቤ፣ የንግግር ማወቂያ፣ የውሳኔ አሰጣጥ እና የቋንቋ ትርጓሜ ያሉ ነገሮች በመደበኛነት የሰውን የማሰብ ችሎታ የሚፈልጉ ሁሉም ነገሮች ነበሩ ይላል። አሁን ግን የኮምፒውተር ፕሮግራሞች እነዚህን ተግባራት ለመፍታት የማሰብ ችሎታቸውን እንደሚጠቀሙ ይገልፃል። እነርሱ የሚሰሩበት “የማይክሮ ሎን” ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂም የሰው ልጆችን ሚና በመተካት ፍትሃዊና ከአድሏዊ አሰራር የፀዳ እንዲሆን እንደሚያስችል ነው የሶፍትዌር ዲቨሎፒንግ ባለሙያው የሚያስረዳው።
እንደ መውጫ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚለው ቃል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1956 የተፈጠረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ፅንሰ ሃሳብ መሬት ላይ አውርዶ ተግባራዊ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ምርምር ማድረግ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታትን ነው ያስቆጠረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለማችን ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶች በተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካኝነት እየተወሳሰቡ እና እየተከማቹ በመጡ የኢንተርኔት መረጃዎች ክምችት፣ የላቁ ስልተ ቀመሮች እና ኮምፒውተሮች መሻሻሎች አማካኝነት እየዘመኑና ይበልጥ ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል።
ዓለም በቴክኖሎጂው በተለይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ዘርፍ እጅግ የረቀቀና የዘመነ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሉላዊነት የፈጠረው ትስስር ቴክኖሎጂ በፍጥነት እንዲያድግና ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የበራችን ደጃፍ የቀረቡን ያህል እንዲሰማን እያደረገ ይገኛል። ምድራችንን ይፈትኑ የነበሩ ውስብስብ ችግሮች አሁን በአስደናቂ የፈጠራ ውጤቶች መፍትሄ እያገኙ ነው።
አገራት የንግድ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች መሰል ትስስሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ (በይነ መረብ) ያደርጋሉ። ይህ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ከፍተኛ ወጪንና የተዛባ አሰራርን ከማስቀረቱም በላይ ደህንነትንና አስተማማኝነትን ማረጋገጥ አስችሏል። በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ምርምር በሰው ልጅ አቅም የማይታሰቡትን ሁሉ እንዲተገበሩ፣ ረቂቅና ሚስጥራዊ የሆኑ ትንግርት የሚመስሉትን እውን እንዲሆኑ ያስቻለ ነው።
ኢትዮጵያም በዚህ ሰፊ የቴክኖሎጂ ባህር ውስጥ መልህቋን መጣል እንድትችል ወጣቱ ትውልድ ራሱ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ምቹ አጋጣሚ እንዲፈጠርለት ይሻል። እንደ ሳይንስ ሙዚየም አይነት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ሌሎች ድጋፎች ደግሞ ሂደቱን በእጅጉ እንደሚያፋጥኑት ይታመናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015